«ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ» በቅርቡ ባወጣው ዓመታዊ የፕሬስ ነጻነት የአገራት ደረጃ ኢትዮጵያ ዓምና ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110ኛ ደረጃን ይዛለች ብሏል፡፡
አትዮጵያ ደረጃዋን ለማሻሻል የበቃችው የታሰሩ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን በመልቀቋ፤ የታገዱ ድረ- ገጾችን በመክፈቷና አፋኝ አዋጆችን ለማሻሻል በመንቀሳቀሷ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ከያዝነው ሳምንት አጋማሽ አንስቶም የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ ኢትዮጵያ በሚዲያ ዘርፍ እያደረገች ባለችው ለውጥ ዙሪያ ምክክር ተካሂዷል፡፡ ወቅቱን በማስመልከት ከለውጡ በኋላ በተወሰዱ እርምጃዎች የተገኘውን ነጻነት ሚዲያዎች እንዴት እየተገለገሉበት ነው ስንል የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮችን ጠይቀናል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሚዲያዎች አሰራር ላይ የተወሰኑ አውንታዊ ነገሮች አሉ:: ነገር ግን አሁንም ቢሆን በመንግሥት ሚዲያዎች በኩል የመንግሥት ካልሆኑ ሌሎች ስብሰባዎችን ሽፋን አለመስጠት ይስተዋላል ብለዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ ዝም ብሎ ቆይቶ መንግሥት ችግሩን እያቃለልኩ ነው ብሎ የሚናገረውን መጨረሻ ላይ ማስተላለፍ አሁንም አለ›› የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ገና በትኩስነቱ ያለ መዘገብ እና ዘገምተኝነት እንደሚስተዋል ይናገራሉ፡፡
የመንግሥት ፍላጎቶችን አልፎ ያለመሄድ ችግር መኖሩን አመልክተው፤ በውድድሩ እየተሸነፉ መሆኑን እና በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ባህል ተሻገረው ተነሳሽነት ኖሯቸው ሰፊ ጉዳዮችን ሲዘግቡና ሲዳስሱ አይታይም ብለዋል፡፡
‹‹የግሉ ሚዲያ በ1997 ዓ.ም ከሞተ በኋላ አሁን ደግሞ በጣም እያንሰራራ ነው›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ ምን ያህል በኃላፊነት ይንቀሳቀሳሉ የሚለው ሁሉንም እንደሚያጠያይቅ ይገልፃሉ፡፡
ፕሮፌሰር መረራ ሲያብራሩ፤ የግል ሚዲያዎች ነጻነትን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ውስንነት ይታይባ ቸዋል። የተወሰኑት አንዳንድ የፖለቲካ አቅጣጫዎችን ይዘው ያራግባሉ፡፡ አልፈው ተርፈው ወሰን ጥሰው ችግር ሊፈጥሩ በሚችሉበት ደረጃ የፖለቲካ አቋሞችን የራምዳሉ፡፡
ለገበያ ብለው አንዳንድ ነገሮችን ከሚገባው በላይ የማራገብ ሁኔታዎች ይታያል፡፡ ምናልባትም የህዝቦችን ግንኙነት ሊጎዳ በሚችል መንገድ ውስጥ ሲገቡ ሁሉ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይ ትንተና እያሉ የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች ውሎ አድሮ ህዝቡን አቅጣጫ የማሳት ሁኔታ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸውም ይናገራሉ፡፡
ፕሮፌሰር መረራ በቀጣይ በሁለቱም ወገን ካሉት ሚዲያዎች ምን እንደሚጠበቅ ሲገልጹ «በአጠቃላይ የመንግሥት ሚዲያዎች ላይ የተነሳሽነትና በድፍረት የመንቀሳቀስ ችግር የግል ሚዲያዎች ላይ ደግም ኃላፊነት የመሸከም ችግርና የጥንቃቄ ጉድለት እያየሁባቸው ነው። የመንግሥት ወይም መንግሥት ነክ የሆኑት ሚዲያዎች በተለያየ መንገድ በህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
እንደ ድሮ መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ ማራገብ ሳይሆን ችግሮችንም ሌሎች ነገሮችንም ተነሳሽነት ኖሯቸው ተንቀሳቅሰው የመዘገብ ህዝቡን የማሳወቅ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል። በተወሰነ ደረጃ ለውጡን በሥራ ላይ በመተርጎም ማጣጣም መቻል አለባቸው፡፡ የመንግሥት ክልሎችን አልፈው የህዝብ ጥቅሞችን በተመለከተ እየተንቀሳቀሱ መዘገብና ችግሮች ሲኖሩም ለህዝብ መንገር አለባቸው።መንግሥት ተኝቶ እስኪነሳ እስኪነግርና እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ዝም ማለት የለባቸውም ብለዋል፡፡
‹‹ የግል ሚዲያዎችም አጉል የፖለቲካ ትንተና ውስጥ እየገቡ ምናልባትም ህዝቡን ወደ የማይፈለግ መንገድ በመምራት ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ለገበያ ብቻ ብለው መስራት የለባቸውም» ብለዋል፡፡
የመጫወቻ ሜዳውን በዋናነት የሚወስነው መንግሥት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በአጠቃላይ የህዝብ መብትና ነጻነት እንዲከበር ለማድረግ ጋዜጠኞች ኃላፊነት ኖሯቸው እንዲንቀሳቀሱ «መንግሥት ስለሚከ ፍለንና ስለሚያስተዳድረን መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ በመዘገብ መቀጠል አለብን» ለሚሉት፤ ተነሳሽነት ኖሯችሁ መንቀሳቀስና መዳፈር አለባችሁ ብሎ መንግሥት መመሪያ መስጠት አለበት፡ ፡ ለግል ሚዲያዎችም በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ በቂ መልዕክት ማስተላለፍ መቻል አለበት፡፡ ከማሳሰብ በተጨማሪ ስልጠናም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
የአትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ከአንድ ዓመት በፊት ሚዲያዎችና ባለሙያዎች የገዢው መንግሥትና ድርጅት አይንና አፍ ሆነው በእነሱ ሳንባ የሚተነፍሱ ነበሩ፡፡ መታገል የሚፈልጉ ግለሰቦችና ባለሙያዎች ቢኖሩም እንደ ተቋም መታገል ባለመፈለጋቸው ሙሉ ለሙሉ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ባሳለፍነው አንድ ዓመት ግን ይህ ስዕል ተቀይሯል፡፡ ይህ በቃላት ብቻ ሳይሆን በሕግም በደምብም እየተረጋገጠ ነው ይላሉ፡፡
መንግሥት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው የሚሉት ፖለቲካኛው፤ አሁን በዘርፉ ላሉት ችግሮች ምንጮቹ ራሳቸው ሚዲያዎቹ ናቸው፡፡ ሚዲያዎች ራሳቸውን በሙያው ክህሎት አዳብረው ህዝብንና ተፎካካሪ ፓርቲ ዎችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት በቅንነት ማገልገል የሚያስችል አቋም ላይ ያሉ አይመ ስለኝም ይላሉ፡፡ አሁንም ቢሆን የቀድሞ መንፈስ ከሚዲያ ተቋማት ጓዙን ጠቅልሎ አልወጣም ካሉ በኋላ፤ የአመለካከት ለውጥና የዴሞክራሲያዜሽን ሪፎርሚስት መሆን ገና ይቀራቸዋል፡፡ ከውጪ የሚነገረውም የሚታየውም ይሄው ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም «ኳሱ በሚዲያ ተቋማትና በባለሙያዎች እንጂ በመንግሥት እጅ ያለ አይመስለኝም፣ ሜዳውም ፈረሱም ያው ተብሏል፡፡ ነገር ግን በአዋጁና ኤዲቶሪያል ፖሊሲው መሰረት ህዝብን እንደ ህዝብ ተቋሞችንም በእኩልነት ዓይን አይተው ያለአድሎ ይሰራሉ ? በቂና ትክክለኛ መረጃዎች ያስተላልፋሉ ? የሚሉት ጥያቄ ዎች እስካሁን አልተፈቱም፡፡ ገና ዳርዳር እየተባለ እንጂ የሚጠበቀው ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ጊዜው አጭር ቢሆንም ፍላጎቱ ካለ ይቻላል።» ብለዋል፡፡
እንደአቶ ተሻለ ገለጻ፤ ሚዲያዎች የሙያ ብቃታቸውን በማሳደግና ወቅታዊ በመሆን ህዝብንና አገርን አንድ የማድረግ ጥላቻንና ቁርሾን፣ ቂምንና በቀልን የማስወገድ ተልዕኮ በመያዝ እየሰሩ አይደለም፡፡ የዘውግና የዜግነት ጥያቄዎች ህዝብን እንደገና በሌላ ይዘትና ደረጃ እየከፋፈሉ ባሉበት በዚህ ወቅት ሚዲያዎች በብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም ዙሪያ ለሚሰሩ ሥራዎችና ለውጡን ለማስቀጠል ለሚደረጉ ጥረቶች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ቀን ከሌሊት በመስራት ከተራማጅ መንግሥትና ለውጡን ከሚፈልጉ ብዙኃን ዜጎች ጎን መቆም አልቻሉም ይላሉ፡፡
ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አፍራሽ ነገር በርክቷል በአገር ውስጥ ያንን የሚመክት የፕሬስ ኃይል ጎልቶ የህብረተሰቡን ልብ መማረክና ማስረቅ አልቻለም የሚሉት አቶ ተሻለ፤ ይህ ባለመሆኑ አሁን እንድ ተራ አፍራሽ የማህበራዊ ድረ ገጽ ጽሑፍ እየበጠበጠ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ እየተሰራ ያለው ሰፊ ጊዜ ወስዶ የሚመለከታቸውን አካላት አቅርቦ አነጋግሮ የመልስ ምት በመምታት ህዝቡን ማትረፍ በሚያስችል መንገድ እየተሰራ አይደለም፤ አካሄዱ ሁሉ ‹‹የፈሪ ዱላ›› ዓይነት ነው ብለዋል፡፡
ወደ ፊት ምን እንደሚጠበቅ ሲገልጹም «ሚዲያዎች ራሳቸውን መለወጥ አለባ ቸው፡፡ ራስህን ችለህ ሂድ ከተባሉ ፈራ ተባ ሳይል በአደረጃጀት፣ በባለሙያና በራዕይ መንግሥትንም ህዝብንም ለመ ምራት የሚያበቃ ቁመና ላይ መድረስ መቻል አለባ ቸው። የህዝቡን ፍላጎት፣ ጥያቄዎችና ችግሮች በተለያዩ መንገዶች ፈልፍለው እያወጡ ከነመፍትሄዎቻቸው በማቅረብ ግንባር ቀደም መሪዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል» ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በየትናየት ፈሩ