ማንም ሰው በአንድ ግለሰብ ይህን ያህል የጦር መሳሪያ ተከማችቶ ይገኛል ብሎ ሊገምት አይችልም:: ይህ በጣም አነጋጋሪ የሚሆነው ደግሞ በጣም ሰላማዊ በሆነ አካባቢ መገኘቱ ነው:: ሌላው አጃዒብ የሚያስብለው ደግሞ ግለሰብ ከሚታጠቀው የጦር መሳሪያ ውጭ የቡድን መሳሪያ በግለሰብ ቤት መገኘቱም ጭምር ነው:: ጉዳዩ በምዕራብ አርሲ ዞን ቆሬ ወረዳ ፍርድ ቤት ጀምሮ የተሰጠው ውሳኔ ብዙዎችን ቅር አሰኘ:: በ50 ብር ቅጣት ብቻ ሊታለፍ የነበረው ጉዳይ ከረር ብሎ እስከ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብሎም ክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ::
ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡትን ውሳኔ መቀበል ያልፈቀዱት የወንጀል ተጠርጣሪ ጉዳዩን ይዘው ወደ ፌደራል ፍርድ ቤት አመሩ:: የመጨረሻ መዳረሻቸውም ሰበር ሰሚ ችሎት ሲሆን፤ ውሳኔ ሃሳብ ለማስቀየር ያለመ ነበር:: ይህን የክርክር ሂደትና ውጤት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሣኔዎች ቅፅ አስራ አምስት ላይ የወንጀል ድርጊት ሆነው የሰበር ውሳኔ ከተሰጣቸው መካከል ውሳኔዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሶ ለመማሪያ እና ብይን ሰጪዎችም ይጠቀም ዘንድ በመፅፍ መልክ አሳትሞታል::
የሰነድ መለያ ቁጥር 93173 ሲሆን፤ ታኅሳስ 17 ቀን 2006 ዓ.ም ሰበር የመጨረሻውን ውሳኔ ይሰጣል:: ዳኞች ከፍርድ መንበር ላይ ተቀምጠዋል:: አመልካቾች አቶ ተዋበ እስጢፋኖስ እና ወይዘሮ አበራሽ አስራት ሲሆኑ፤ ተጠሪው የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ህግ በችሎቱ ዘንድ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስማት ተገኝተዋል::
የክርክሩ መነሻ
ለዚህ ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁን የሰበር ተጠሪ ከሳሽነት የተጀመረው በምዕራብ አርሲ ዞን ቆሬ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን፤ የአሁን አመልካቾች እንደ ቅደም ተከተላቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾች ነበሩ:: ክሱም ተከሳሾች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(3) እና 481(1) (ሀ) የተመለከተውን በመተላለፍ በክሱ የተዘረዘሩትን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችንና ጥይቶችን በቤታቸው አከማችተው በፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ ቤታቸው በፖሊስ ሲፈተሽ የጦር መሳሪያዎቹና ጥይቶቹ ስለተገኙ ተከሰዋል የሚል ነው::
ተከሳሾች ምን አሉ?
አንደኛ ተከሳሽም በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል በክሱ ከተጠቀሱት ጦር መሳሪያዎች መካከል በተወሰኑት ላይ ፍቃድ አለኝ ባይ ናቸው:: ከቤቴም የተገኘ ቦንብ ባለመኖሩ የፈጸምኩት ወንጀል የለም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም ሲሉ ተከራከሩ:: ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ የእምነት ክህደት ቃል ስለመስጠታቸው የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያመላክት ሆኖ አልተገኘም:: የወረዳው ፍርድ ቤትም አንደኛ ተከሳሽ ፈቃድ አለኝ ያሉዋቸውን የጦር መሳሪያዎች በተመለከተ ፍቃድ የተሰጠበትን ማስረጃ እንዲያቀርቡ በማዘዙ የሁለት ቺኮዝ፣ የክላሽንኮፕ፣ የኡዝ እና ካርቤን መሳሪያዎች ፍቃድ የተሠጠባቸውን ማስረጃዎች በማቅረብ በፍርድ ቤት መዝገብ ሰፈረ::
ነገር ግን ኤፍ1-1 የሆነ ቦንብና በክሱ ተዘርዝረው ፍቃድ የሌላቸውን የጦር መሳሪያዎች በተመለከተም የከሳሽ ምስክሮችን ቃል ከሰማ በኋላ በሰጠው ውሳኔ የብርብራ ትዕዛዝ ተሰጠ:: ትዕዛዙ የአንደኛ ተከሳሽ እና ሼህ አህመድ ሐጂ አህመድ የተባሉት ግለሰብ ቤቶች እንዲበረበሩ የሚል ነበር:: የሚበረበሩ የጦር መሳሪያዎች ዓይነት በዝርዝር በፍርድ ቤት ብርበራ ትዕዛዝ ካለመገለጹም ሌላ ብርበራው የተካሄደው አንደኛ ተከሳሽ በሌሉበት ቤታቸው ተሰብሮ በመሆኑ ብርበራው የተካሔደው ህጋዊ አካሄዱን ጠብቆ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው::
ይሁን እንጂ ተከሳሾች ይህን ያህል የጦር መሳሪያ በቤት ውስጥ ማስቀመጣቸው ተገቢ ባለመሆኑ ሊማሩበትና የአካባቢውም ሌሎች ሰዎች ትምህርት ይሆናቸው ዘንድ እንዲሁም ብርበራው የህጉን ሥርዓት ተከትሎ ያልተካሔደ ነበር:: ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ክስ የቀረበባቸውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 481(1)(ሀ) በመቀየር በወንጀል ህግ አንቀጽ 809 ጥፋተኞች በመሆናቸው እያንዳንዳቸው 50 ብር ይቀጡ ሲል ይወስናል:: ይህ ጉዳዩን አቅልሎ ማየትና ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ግን በዚህ አልተቋጨም:: ነገሩ ጦዘ፤ ወደ ሌላ ምዕራፍ ሊሸጋገር ችሎት ሊሰየምለት ግድ ሆነ::
ከሳሽም በወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማቅረባቸው ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ወገን ካከራከራቸው በኋላ በሰጠው ውሳኔ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፖሊስ የመልስ ሰጪዎችን ቤት ሲፈተሸ የጦር መሳሪያዎቹ መገኘታቸው የተረጋገጠ መሆኑን ያመለክታል::
የሥር ፍርድ ቤት
የሥር ፍርድ ቤትም የይግባኝ ባይ ምስክሮችን ከሰማ በኋላ የመልስ ሰጪዎችን ማስረጃዎች መስማት ሲገባው መልስ ሰጪዎቹ ያቀረቡትን መቃወሚያ መነሻ በማድረግ የጦር መሳሪያዎቹን ፍቃድ እንዲያቀርቡ በማድረግ በቀረበው ማስረጃ ላይ ይግባኝ ባይ አስተያየት ሳይሰጥበት ከመዝገቡ ጋር ማያያዙ ተገቢነት የለውም የሚል ነው:: እንዲሁም መልስ ሰጪዎቹ እንዲከላከሉ ብይን ሳይሰጥ ያለአግባብ ክስ የቀረበባቸውን የወንጀል ህግ ድንጋጌ በመቀየር ቀላል ቅጣት የወሰነው መልስ ሰጪዎችንና መሰሎቻቸውን የማያስተምር እንዲሁም የሕዝቡን መረጋጋት የማያረጋግጥ ጉድለት ያለበት ውሳኔ ነው:: በመሆኑ የይግባኝ ባይ ምስክሮች የመልስ ሰጪዎች ቤት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲፈተሽ ቦንብ እና ኡዝ መትርየስ የተባሉት በግል የማይያዙና ፈቃድ የማይሰጥባቸው የጦር መሳሪያዎች የተገኙ ስለመሆናቸው በማረጋገጣቸው ክስ በቀረበባቸው የወንጀል ህግ ድንጋጌ ስር ጥፋተኞች ሊሆኑ ይገባል ሲል በዚሁ ድንጋጌ እያንዳንዳቸው በሁለት ዓመት እስራትና በብር 3000 እንዲቀጡ ወሰነ::
ተከሳሾችም ደግሞ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ቅሬታቸውን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 195(1) መሰረት የሰረዘባቸው ሲሆን፤ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ወገኖች ካከራከራቸው በኋላ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትዕዛዝ ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም ሲል የሰበር አቤቱታቸውን ውድቅ በማድረጉ ለችሎት አቤቱታቸውን አቀረቡ::
አመልካቾች በአቤቱታቸውም የጠቀሱት ቅሬታ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ሰበር ሰሚ ችሎት ያስተላለፉብን የጥፋተኛነት እና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ሊሻር ይገባል የሚል ነው:: ተጠሪው በበኩሉ በሰጠው መልስ አመልካቾች የጦር መሳሪያዎቹን በቤታቸው አከማችተው የተገኙት
ለንግድ ዓላማ ስለሆነ፤ ክስ በቀረበባቸው ወንጀል ህግ አንቀጽ ጥፋተኞች ናቸው በሚል የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው የሚነቀፍበት ምክንያት ባለመኖሩ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የለም ሲል የሰበር አቤቱታቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል:: አመልካቾችም ተጠሪው ላቀረበው መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራከሩ::
የጠነከረው ምርመራ
በምርመራው መሰረት አመልካቾች የፈጸሙት ወንጀል በወንጀል ህግ 481(1)(ሀ) የሚሸፈን ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ ለመምርመር ተገደደ:: በዚህም የአመልካቾች ቤት በፍርድ ቤት በተሰጠ የብርበራ ትዕዛዝ በፖሊስ ሲፈተሽ ቦንብ እና ኡዝ መትርየስ የተባሉት በግለሰብ ደረጃ የማይያዙና ፈቃድ የማይሰጥባቸው የጦር መሳሪያዎች የተገኙ ስለመሆናቸው የተጠሪ ምስክሮች ለሥር ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ካስረዱት የተረጋገጠ ፍሬ ነገር በመሆኑ ይህን የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር ይህ ችሎትም የሚቀበለው ነው::
በምርመራው መሰረት ‹‹ይህንኑ የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር ይዘን ክስ ወደቀረበበት የወንጀል ህግ አንቀጽ 481(1)(ሀ) ስንመለስ፤ ማንም ሰው መንግስት አደጋ ላይ ስለመጣል በተወሰኑት ድንጋጌዎች ከተመለከተው ውጭ ፈቃድ ሳይኖረው ወይም ህግን ተቃራኒ በሆነ መንገድ ማናቸውንም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች፣ ፈንጂዎች፣ ወይም ጥይቶች በመነገድ ዓላማ የሰራ፣ ከውጭ አገር ያስመጣ፣ ወደ ወጭ አገር የላከ፣ ያጓጓዘ፣ የገዛ፣ የተቀበለ፣ ያስቀመጠ፣ ያከማቸ፣ የደበቀ፣ ለሽያጭ ያቀረበ ወይም እንዲዘዋወሩ ያደረገ ወይም ያከፋፈለ እንደሆነ በዚሁ ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ሆኖ ይቀጣል›› ይላል::
አመልካቾችም በብርበራ ከቤታቸው የተያዙትን የጦር መሳሪያዎች ውስጥ ፈቃድ የላቸውም የተባሉትን የጦር መሳሪያዎች በቤታቸው ውስጥ ያከማቹት ለንግድ በሚል እንደሆነ የተጠሪ ማስረጃዎች ስለማስረዳታቸው የሥር ወረዳ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚያመላክት ሆኖ አልተገኘም:: በአዋጁ አንቀጽ 481(1)(ሀ) በተነገረው መሰረት አንድን ሰው በዚህ ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ነው ለማሰኘት ግለሰቡ መሳሪያዎቹን ያከማቸው ወይም በድንጋጌው ከተዘረዘሩት ድርጊቶች አንዱን ወይም ከአንድ በላይ የሆኑትን ድርጊቶች የፈጸመው በመሳሪያዎቹ ለመነገድ በሚል እንደሆነ ከሳሽ ሊያስረዳ ይገባል::
ምክንያቱም የወንጀል ህግ አንቀጽ 481(1)(ሀ) በጠቅላላው ለአንቀጽ 481 ከተሰጠው ርዕስ ወይም ስያሜ ጋር በማያያዝ ሊተረጎም የሚገባ በመሆኑ ነው:: በመሆኑም አመልካቾቹ የፈጸሙት ወንጀል በወንጀል ህግ አንቀጽ 481(1)(ሀ) ስር የሚሸፈን ሆኖ አላገኘነውም ይላል:: ይልቁንም ችሎቱ እንደሚገነዘበው አመልካቾች ፈቃድ የሌላቸውን የጦር መሳሪያዎችንና ጥይቶችን በቤታቸው አከማችተው የመገኘታቸው ሁኔታ የአገሪቱ የወንጀል ህግ አንቀጽ 808(ሀ) የጦር መሳሪያዎችንና ጥይቶችን ስለመቆጣጠር የተደነገገውን የሚጥስ ሆኖ ስለሚገኝ በዚሁ በተጠቀሰው ድንጋጌ ስር የጥፋኝነትና ቅጣት ውሳኔ ሊተላለፍባቸው የሚገባ ነው:: ይህ ሆኖ ሳለ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልካቾችን በወንጀል ህግ አንቀጽ 481(1)(ሀ) ጥፋተኞች ናቸው ሲሉ በዚሁ ድንጋጌ የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፉባቸው በዚሁ ድንጋጌ ስር ጥፋተኞች ሊሆኑ የሚያስችሉት ህጋዊ ፍሬ ነገሮች ስለመኖራቸው ተጠሪው ባላስረዳበት ሁኔታ ስለሆነ ውሳኔው በከፊል መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል ሲል ነበር ሰበር ቀጣዩን ውሳኔ ያስተላለፈው::
ውሳኔ
የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 12859 በቀን 04/12/2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠውን ውሳኔ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመለያ ቁጥር 119417 በቀን 10/05/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመለያ ቁጥር 146183 በቀን 13/12/2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 195(2) (ለ)(2) መሰረት አሻሻለ፡፡
አመልካቾችም እያንዳንዳቸው በሁለት ዓመት እስራትና በ3000 ብር እንዲቀጡ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡትን የውሳኔ ክፍል ተሻረ፡፡ አመልካቾች ጥፋተኞች ናቸው ሊባል የሚገባው በወንጀል ህግ አንቀጽ 32(3) እና አንቀጽ 481(1)(ሀ) ስር ሳይሆን በወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 808(ሀ) ስር ነው በማለት በመወሰን በዚሁ ድንጋጌ እጃቸው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ በ3 (ሦስት) ወር እስራት ሊቀጡ ይገባል የሚል ውሳኔ ተላለፈ፡፡
ሆኖም አመልካቾቹ በዚሁ ወንጀል የታሰሩበት ጊዜ ከ3 ወር በላይ መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከሰጠበት ቀን አንጻር ስለተረዱ በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ በዕለቱ ከሚገኙበት ማረሚያ ቤት እንዲለቀቁ ትእዛዝ ተሰጠ፡፡ ለሚገኙበት ማረሚያ ቤት ይጻፍ ተባለ፡፡
ፈቃድ የሌላቸውን የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች መንግስት እንዲወርሳቸው የሥር ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው የውሳኔ ክፍልና ይህንኑ የውሳኔ ክፍል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ሰበር ሰሚ ችሎት በማጽናት የሰጡት የውሣኔ ክፍል አልተሻረም፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015