ድንበር የለሹ የሪፖርተሮች ቡድን የዘንድሮውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ የዓለም አገራት የሚገኙበትን ደረጃ የሚጠቁም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። ቡድኑ የዓለም አገራትን የፕሬስ ነጻነት ደረጃን በለካበት መመዘኛው ፖለቲከኞች ለጋዜጠኞች ያላቸው ጥላቻ እያሻቀበ መምጣቱንና ጥላቻው እየተባባሰ መጥቶ ወደ ጥቃት እየተቀየረ መሆኑን አመላክቷል።
180 በሚሆኑ አገራት ጋዜጠኝነት ያለበትን ሁኔታ በመገምገም በድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን የተዘጋጀው የ2019 የዓለም አገራት የፕሬስ ነጻነት መለኪያ፤ «በብዙ አገራት ፖለቲከኞች ለጋዜጠኞች ያላቸው ጥላቻ እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ በጋዜጠኞች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል» ይላል። ይህም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ ፍርሃትን ፈጥሯል፤ በራሱ በጋዜጠኝነት መጻኢ ዕድል ላይም ስጋት ደቅኗል።
የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ዋና ጸሐፊ ክርስቶፊ ዲሎይር፤ «ጋዜጠኞችን እንደ ኦሪት ፍየል በመጠቀም ፖለቲካው በግልጽም ይሁን በስውር ከሚፈጽመው ሃጢአት ለማምለጥ መስተጋብሩ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዲያጋድል ማድረግ ለዴሞክራሲ ትልቅ አደጋ ነው» በማለት ነው የሁኔታውን አደገኛነት የገለጹት።
በዘንድሮው የ2019 የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ጠቋሚ ዝርዝር አውሮጳዊቷ የስካንዲንቪያን አገር ኖርዌይ ለሦስተኛ ጊዜ የአንደኝነቱን ደረጃ ተቆናጣለች። ሌላኛዋ የሰሜን አውሮፓ አገር ፊንላንድ ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል ሆላንድን አስለቅቃ የሁለተኛነትን ደረጃ ይዛለች። ሆላንድ በበኩሏ ካለፈው ዓመት ሁለት ደረጃዎችን ተንሸራታ አራተኛ ሆናለች። ምክንያቱም ሆላንድ የተቀናበረ ወንጀልን ለህዝብ ይፋ ያደረጉ ሁለት ሪፖርተሮቿን በቋሚነት በፖሊስ ጥበቃ ስር እንዲሆኑ አድርጋ ስለነበር ነው።
እንደዚሁ የስካንዲንቪያኗ ስዊድን በሳይበር አማካኝነት በዜጎቿ ላይ የምታደርገው ዛቻና ማስፈራሪያ እየጨመረ በመምጣቱ ካለፈው ዓመት ደረጃዋ በአንድ ቀንሳ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ከአፍሪካ አርባ ደረጃዎችን ያሻሻለችው ኢትዮጵያና ሰላሳ ደረጃዎችን ያሻሻለችው ጋምቢያ ከፍተኛ ዕድገትን በማሳየት አድናቆትን ተችረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ ወደ 110ኛ ከፍ ብላለች። ጋምቢያም እንደዚሁ ከ120ኛ ወደ 62ኛ ደረጃ መጥታለች። ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ለጥቃት የሚጋለጡባትና የሚታሰሩባት ላቲናዊቷ ፈርኦናዊት አገር ቬንዙዌላ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት የ148ኛ ደረጃ አምስት ደረጃዎችን ወደ ታች «አሻሽላ» 153ኛ ደረጃ ላይ አርፋለች።
ምስራቃዊቷ ልዕለ ኃያል አገር ሩስያ በበኩሏ ነጻውን ፕሬስ ለማሽመድመድ አፋኝ ህጎችን ትጠቅማለች እንዲሁም ያለ በቂ መረጃ ጋዜጠኞችን ታስራለች በሚል ከነበረችበት በአንድ ነጥብ ወደ ታች ወርዳ ከ148ኛ ወደ 149ኛ ደረጃ መጥታለች።
በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ግርጌ የሚገኙት የፕሬስ ነጻነት ሰነፍ ተማሪዎችና የአፈናና የአምባገነንነት ጎበዞች ደግሞ እርስ በርስ ቦታ ከመቀያየራቸው በቀር ዛሬም እንደ ወትሮው የኋልዮሽ አንደኝነታቸውን አስጠብቀዋል። በዚህም በህዝብ ብዛቷ አንደኛ በሃብቷ ደግሞ ከዓለም ሁለተኛ የሆነችው ታላቋ ቻይና ከነበረችበት አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ በ177ኛ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በፈጠረችው ሰላም አንድ ደረጃን ወደ ላይ ያሻሻለችው ጎረቤት ኤርትራ በ178ኛ፣ ሰሜን ኮሪያ አንድ ደረጃ በማሻሻል በ179ኛ እንደ ቅደም ተከተላቸው አራተኛ፣ ሦስተኛና ሁለተኛ በመሆን የኋለኛውን ደረጃ ተቆጣጥረዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጠዋል።
ከነበረችበት ሁለት ደረጃዎችን ዝቅ ብላ አንድ መቶ ሰማንያ አገሮች 180ኛ በመውጣት በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ ሆና ወራጅ ቀጠናዎች የተሰባሰቡበትን የፕሬስ ነጻነት አፈና ቡድን በአንደኝነት የምትመራው ደግሞ ሚጢጢዋ የመካከለኛው እስያ አንባገነን አገር ቱርክሚንስታን ነች። ሂዩማን ራይትስ ወች ይችን አገር «ለዘመናት እጅግ ጨቋኝ ሆነው ከዘለቁ የዓለማችን አገሮች መካከል አንዷ ሆና የቀጠለች አገር» በማለት ይገልጻታል። ይህም ቱርክሚንስታን በፕሬስ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው «ነጻነት አይኑርብሽ» ተብላ የተረገመች ናት ብለን እንድናስብ ሳያስገድደን አይቀርም።
የፕሬስ ነጻነትን በሚመለከት ለአገራት የተሰጠው ደረጃ ስድስት ዋና ዋና መመዘኛዎችን መሰረት ያደረገ ነው። እነዚህም የሚዲያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን በእኩልነት የማስተናገድ አቅምና የብዝሃነት ደረጃ፣ ገለልተኝነት፣ ሚዲያዎች የሚገኙበት ሁኔታ ምቹ መሆን፣ አለመሆንና በዚህም ለግለ ሳንሱር የሚያስገድድ ሁኔታ መኖር አለመኖር፣ ሊያሰሩ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎች መኖር፣ ግልጸኝነት እንዲሁም መረጃዎችን ለመሰብሰብና ዜናዎችን ለማዘጋጀት የሚያግዝ ደረጃውን የጠበቀ መሰረተ ልማት መኖርን የሚመለከቱ ናቸው።
መቶ ሰማንያዎቹም አገራት በእነዚህ መመዘኛዎች መሰረት ተለክተው ጋዜጠኝነት ያለበት ሁኔታ «ጥሩ»፣ «አጥጋቢ»፣ «ችግር ውስጥ ያለ»፣ «አስቸጋሪ» እና «በጣም አስቸጋሪ» በሚል በአጠቃላይ በስድስት ምድብ ተከፍለዋል። ከመቶ ሰማንያው አገር ጋዜጠኝነት በመልካም ሁኔታ ውስጥ የሚገኝባቸው 24 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።
ይህም ሃያ ስድስት በመቶ የሚሆኑት አገራት ከጥሩም አልፈው «በጣም ጥሩ» ሁኔታ ውስጥ ከነበሩበት ካለፈው ዓመት አሃዝ ጋር ሲነጻጸር ጋዜጠኝነት በከፋ ሁኔታ መገኘቱን የሚያመላክት ነው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያቱ ከዚህ ቀደም በፕሬስ ነጻነት ይዞታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኙ በነበሩና ለጋዜጠኞች ምቹ ይባሉ በነበሩ አገራት ሳይቀር በጋዜጠኞች ላይ የፖለቲከኞች ጥላቻ እያየለ መምጣቱ ነው።
አሜሪካ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። በአሜሪካ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ፕሬዚዳንት ትራምፕን ጨምሮ የጋዜጠኞች ጥላቻ ጨምሮ ተስተውሏል። ባለፈው ዓመት በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2018 ላይ አንድ ግለሰብ በአናፖሊስ ሜሪላንድ ወደ ካፒታል ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ውስጥ ገብቶ ሦስት ጋዜጠኞችንና አንድ ሌላ የዝግጅት ክፍሉ ሠራተኛን በጥይት ደብድቦ መግደሉ በአሜሪካ እያደገ ለመጣው የጋዜጠኞች ጥላቻ ዓይነተኛ መገለጫ ነው።
ግለሰቡ ጋዜጠኞቹን ከመግደሉ ቀደም ብሎ በተደጋጋሚ ለጋዜጠኞች የነበረውን ጥላቻ ሲገልጽ እንደነበርም ተረጋግጧል። እናም አሁን አሜሪካ በርካታ ጋዜጠኞቿ ለደህንነታቸው ሲሉ የጋዜጠኝነት ሙያቸውን እየለቀቁ ወደ ሌላ የግል ሥራ የሚገቡባትና በሙያው ላይ ያሉትም ቢሆን በተደጋጋሚ ጥቃትና ለሞት አደጋ የሚጋለጡባት አገር ሆናለች። ጋዜጠኝነት በአሜሪካ በታሪኩ አስከፊውን ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በመሆኑም አገሪቱ ባለፈው ዓመት ከነበራት ደረጃ ሦስት ደረጃዎችን ወደታች ተንሸራታ 48ኛ ደረጃ ላይ አርፋለች። የፕሬስ ነጻነት ገጽታውም «መልካም» ከሚለው ወጥቶ «ችግር ውስጥ» ገብቷል።
ይህም ብቻ አይደለም እድሜ ለ«አይደንቄዎቹ» አምባገነን ጎረቤቶቿ ለእነ ብራዚል፣ ቬንዙዌላና ኒካራጓ አሜሪካ የምትገኝበት አጠቃላዩ «የአሜሪካ» ቀጠናም በዘንድሮው ፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ጋዜጠኝነት «እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ» የሚገኝበት አካባቢ ተብሎ ተመዝግቧል። ምክንያቱም አካባቢው ባለፈው ዓመት ብቻ በጥቂቱ አስር ጋዜጠኞች የተገደሉባትና «የዓለም ቁጥር አንድ ሚዲያ ገዳይ አገር» የምትባለው ሜክሲኮን ጨምሮ በብዛት ጋዜጠኞችን የሚያስሩና የሚገድሉ አገሮች የሚገኙበት በመሆኑ ነው።
እንደዚሁ ከዚህ ቀደም በፕሬስ ነጻነት ገጽታቸው ጥሩ ስም የነበራቸው የአውሮፓ ህብረትና የባልካን አገራትም የሚዲያ ነጻነት በእጅጉ አሽቆልቁሎ መገኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል። ከዚህም ባሻገር አካባቢው ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ቀጥሎ በዚህ ዓመት የፕሬስ ነጻነት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠበት ክልል ሆኖ መገኘቱ በእርግጥም የጋዜጠኝነት ሙያ ምን ያህል ችግር ውስጥ ለመሆኑ ማሳያ ነው።
«በጋዜጠኝነት ላይ ለተፈጠረው ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው በፖለቲከኞች ቀስቃሽነት በጋዜጠኞች ላይ አላግባብ የተፈጠረው ጥላቻ ነው» የሚለው የዘንድሮው የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ጥናታዊ ሪፖርት፤ ችግሩ ስር ሰድዶ የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ከመሆኑ በፊት አፋጣኝ መላ መዘየድ የሚያሻው መሆኑን ጠቁሟል።
«ስለሆነም በጋዜጠኝነትና በጋዜጠኞች ላይ የተፈጠረውን የፍርሃት አዙሪት እዚህ ላይ እንዲቆም ማድረግ የነጻነትን ዋጋ የሚያውቅ ሁሉ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊፈጽመው የሚገባ ተግባር ሊሆን ይገባል» በማለት ያሳስባሉ። እናም የፕሬስ ነጻነት አፍንጫ ሲመታ ዴሞክራሲም ዓይኑ ስለሚታመም ነጻነትን ማየት አይቻልምና ይኼኛው የፖለቲከኞች የቃየል መንገድ የበለጠ አደገኛ በመሆኑ እኛም እንደ አገር የጀመርነውን አዎንታዊ ለውጥ አጠናክረን በመቀጠል የዓለማችንን ችግር ለመፍታት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በይበል ካሳ