የአሜሪካ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሮድ ሮዝንስቴይን የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸው ተዘግቧል።ከሁለት ዓመታት በፊት ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች የተባለውን ጉዳይ እንዲያጣሩ ልዩ መርማሪ ሮበርት ሙለርን የሾሙት ሮዘንስቴይን፤ የሥልጣን መልቀቂያቸውን ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር የምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የሥልጣን መልቀቂያ ማመልከቻ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ መድረሱን አረጋግጠዋል።በደብዳቤው እንደተገለጸው፤ ሮዝንስቴይን ከ10 ቀናት በኋላ ስልጣናቸውን ይለቅቃሉ።ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በስልጣን መልቀቂያ ማመልከቻቸው ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሰጧቸው ዕድል አመስግነዋል።
ሮዝንስቴይን በአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት ውስጥ ለ30 ዓመታት ያህል እንዳገለገሉና በቆይታቸውም ስኬታማ ተግባራት እንዳከናወኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ተናግረዋል።
በእርግጥ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቅቁ የሚጠበቅ ነበር።ሮዝንስቴይን ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ያሰቡት ከአንድ ወር ቀደም ብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ልዩ መርማሪው ሮበርት ሙለር የምርመራ ውጤታቸውን አጠናቅቀው እስከሚያስረክቡ ድረስ ጥቂት ሳምንታትን በኃላፊነት ላይ ለመቆየት ተገድደዋል።
ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ስለመግባቷ ጉዳይ በልዩ መርማሪ ሲካሄድ የቆየው ምርመራ ውጤት ባለፈው ወር ይፋ መሆኑና በምርመራውም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩስያ ባለስልጣናትና ድርጅቶች ጋር ንክኪ እንደነበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለመገኘቱ ይፋ መድረጉ የሚታወስ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም፤ ልዩ መርማሪው ሮበርት ሙለር ምርመራውን በሚያካሂዱበት ወቅት የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ፍትሕን ለማዛባት ጫና ስለማድረጉ የሚያመለክት በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሮድ ሮዝንስቴይን ፕሬዚዳንቱ የሕግ ጥሰት ፈፅመዋል ብለው እንደማያምኑ ገልጸው ነበር።
የልዩ መርማሪው ሪፖርት የፕሬዚዳንት ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ከሩስያ ባለስልጣናትና ተቋማት ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ማስረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ቢያመለክትም ፕሬዚዳንቱ ሙሉ በሙሉ ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ? ወይስ አይሆኑም? የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም ድረስ አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል።
የልዩ መርማሪው የምርመራ ሪፖርት ይፋ በሆነበት ወቅት በርካታ አንጋፋ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የልዩ መርማሪው ሙሉ ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠይቀዋል።ከዚህ በተጨማሪም፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ጉዳዩን በያዙበት መንገድ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸውም ተናግረው ነበር።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በአንተነህ ቸሬ