በስፔን በተካሄደው አገራዊ ምርጫ «የስፔን የሠራተኞች ሶሻሊስት ፓርቲ» (Spanish Socialist Workers’ Party – PSOE) በመባል የሚታወቀውና ገዢው የጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፓርቲ የፖለቲካ ቡድን አብላጫውን (30 በመቶ) ድምፅ በማግኘት አሸንፏል።ፓርቲው ከአገሪቱ ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል 123ቱን ሲያገኝ፤ «ፒፕልስ ፓርቲ» (People’s Party – PP) በመባል የሚታወቀው የሶሻሊስቱ ፓርቲ ታሪካዊ ተቀናቃኝ 66፣ «ሲቲዝንስ ፓርቲ» (Citizens Party) 57፣ «ቮክስ» (Vox) የሚባለውና ቀኝ አክራሪ እንደሆነ የሚነገርለት ፓርቲ ደግሞ 24 መቀመጫዎችን አግኝተዋል።ይሁን እንጂ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ ባለማግኘቱ ከሌሎች የፖለቲካ ማኅበራት ጋር ጥምረት ለመፍጠር መገደዱ አይቀርም ተብሏል።
ከምርጫው ውጤት ይፋ መሆን በኋላ በማድሪድ ከተማ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ «መጪውን ጊዜ ብሩህ የማድረግ አቅም ያለው ሃሳብ አሸንፏል» ብለዋል።በጥቂት ቀናት ውስጥም ጥምር መንግሥት መመስረት ስለሚቻልበት ሁኔታ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እንደሚወያዩም ተናግረዋል።ደጋፊዎቻቸውም የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ስም እየጠሩ በመንቀፍ መጪው ጊዜ ከፓርቲያቸው ጋር ብሩህ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የ«ፒፕልስ ፓርቲ» ሊቀ-መንበር ፓብሎ ካሳዶ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው የተቃውሞውን ጎራ እየመራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።«ሲቲዝንስ ፓርቲ» እና «ቮክስ» የተባሉት የፖለቲካ ቡድኖች በምርጫው ያልተጠበቀ ድምፅ ማግኘታቸው የቀኝ አክራሪነት (Far-Right) ፖለቲካ በስፔን ውስጥ እግሩን እየተከለ እንደሆነ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
ባርሴሎና ውስጥ በሚገኘው በፖምፔው ፋብራ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ሳንቲያጎ ዛባላ፤ ስፔን በቀኝ አክራሪ ፖለቲከኞች እጅ ልትወድቅ እንደምትችል ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ።እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ባለፉት ዓመታት በስፔን ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ውስጥ በተከሰቱ ምስቅልቅሎች ምክንያት መሰረት እያገኘ የመጣው «ቮክስ» ፓርቲ ተቀባይነቱ እያደገ ስለመጣ አገሪቱ በቀጣዮቹ ዓመታት በዚህ ፓርቲና አጋሮቹ እጅ ላይ ልትወድቅ ትችላለች።
ፓርቲው ሥራ አጥነት፤ የዋጋ ንረት፤ የስደተኞች መበርከትና ሌሎች ችግሮች የፈጠሩትን ቀውስ በመጠቀም ጽንፈኛ ብሄርተኝነትን እያስፋፋ ይገኛል።ይባስ ብሎም የቀድሞውን አምባገነን መሪ ጀኔራል ፍራንኮን እንደ ትግል ምልክት መጠቀሙና የአምባገነኑን ሰው ሥራዎች ማድነቁ ስፔንንና አውሮፓን በእጅጉ አስገርሟል።
ፓርቲው እንደሌሎቹ የቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ሁሉ ጽንፍ የወጡ ፖሊሲዎችን ይከተላል።ከእርሱ በተቃራኒ የቆሙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝንና ደጋፊዎቻቸውን «የስፔን ጠላቶች» በማለት ፈርጇቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ አወዛጋቢ በሆነው የካታላን ግዛት የመገንጠል ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም እንዳላቸው ይነገራል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓርብ ባርሴሎና ከተማ ውስጥ ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ «በካታላን ጉዳይ ላይ ሕዝበ ውሳኔም ሆነ መገንጠል / ነፃነት የሚባል ነገር አይኖርም» በማለት እቅጩን ተናግረዋል።
ጌራርዶ ሮድሪጌዝ የተባለ የ42 ዓመት ስፔናዊ ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ በካታላን ላይ ያላቸው አቋም ድምፁን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ እንዲሰጥ እንዳደረገው ተናግሯል።«ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ የካታላንን የመገንጠል ጥያቄ እንደማይቀበሉና ሕዝበ ውሳኔም ሆነ ነፃነት የሚባል ነገር እንደማይኖር መናገራቸው እንዳምናቸው አድርጎኛል» ይላል።
ከዚህ በተጨማሪም ቀኝ አክራሪ ነው የሚባለው የ«ቮክስ» ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ለቀድሞው የስፔን አምባገነን መሪ ለጀኔራል ፍራንኮ ያላቸው አድናቆት እንደሚያበሳጨው ይናገራል።«በአምባገነኖች ታሪክ ከሚኮሩ ሰዎች ጋር አብሮ የመስራትና የመተባበር ፍላጎት ስለሌለኝ ምርጫዬ የጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፓርቲ ነው» በማለት ያስረዳል።
የአሸናፊው የስፔን የሠራተኞች ሶሻሊስት ፓርቲ ሊቀ-መንበርና የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የማድሪድ ተወላጅ የሕግ ባለሙያ ናቸው።ስልጣን ከያዙበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ አሽቆልቁሎ የነበረው የስፔን የሰራተኞች ሶሻሊስት ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነቱ እንዲጨምር አስችለውታል።በበርካታ ጉዳዮች ላይ መሐል ላይ ያለ አቋም አላቸው።የስደተኞችን ጉዳይ፤ የአውሮፓ ኅብረትንና ምጣኔ ሀብትን በሚመለከትም ያላቸው አቋም ወደ መሐል ያዘነበለ ነው።
በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይም ሊበራል እንደሆኑ የሚነገርላቸው የ47 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፤ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻንና የሴቶችን ውርጃ የመፈጸም መብት ይደግፋሉም ይባላል።ባለፈው ዓመት በስፔን ያለውን ዝቅተኛ የክፍያ ጣሪያ በ22 መቶ ለማሳደግ ሃሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ያቀረቡት በጀት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
ያም አለ ይህ፤ የአውሮፓዊቷ አገር ስፔን ዜጎች ለሚደግፏቸው ቡድኖች የሰጡት ድምጽ አንዱን ፓርቲ ለብቻው መንግሥት ለመመስረት ስላላስቻለው ጥምር መንግሥት ለመመስረት የጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝን ፓርቲና የሌሎች ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ድርድር በጉጉት ይጠባበቃሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በአንተነህ ቸሬ