የኢትዮጵያ እርቀሰላም ኮሚሽን በቀጣይ ሶስት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰው በግጭቶች መሰረታዊ መንስዔዎች ላይ እንደሚሆን ዛሬ ሚያዚያ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው ኮሚሽኑ ችግሮችን ከምንጫቸው ለማድረቅ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው በእሳት ማጥፋት ተግባር ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስልትን ነው።መግለጫው አያይዞም ኮሚሽኑ እስካሁን ዘላቂ ሰላምና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ ዕርቅ ለማምጣት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመለየት ጀምሮ ለኮሚሽኑ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አመልክቷል።
እውነትና ፍትህ ላይ የተመሰረተ ዕርቅ ለማካሄድ እንዲሁም ብሄራዊ አንድነት ወዳላት ኢትዮጵያ ለማምራት የምናደረገው ጉዞ በመከባበር፣ በመደማመጥና በመተማመን ላይ እንዲሆን መንግስትን ጨምሮ የበርካታ አካላት ድርሻ ጉልህ ነው ብሏል መግለጫው።
በመሆኑም ሁሉም አካላት ለኮሚሽኑ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው በመግለጫው ተገልጿል። በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ በመሆኑ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃን ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ከመሰናዘር ይልቅ ለመነጋገር፣ ከመፎካከር ይልቅ ለመተባበር፣ ከመጣላት ይልቅ ለመግባባት፣ ከመወቃቀስ ይልቅ ለመተጋገዝ ቅድሚያ በመስጠት መስራት እንደሚገባቸው ኮሚሽኑ አሳስቧል።
የኮሚሽኑን ተግባር ለመደገፍ ከውጭም ሆነ ከውስጥ እየተደረገ ያለው ጥረት የሚመሰገን እንደሆነም ኮሚሽኑ በመግለጫው በማጠቃለያ ላይ አመልክቷል።
ተ.ተ