ባሳለፈነው የፈረንጆቹ ዓመት በሴራሊዮን በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ለ10 ዓመታት ሀገሪቱን የመሩትን ኧርነስት ባይ ኮሮማንን የስልጣን ዘመን በመቋጨት በምትካቸው የተፎካካሪ ፓርቲው መሪው ጁሊየስ ማዳን አምጥቷል። በምርጫው 51 ነጥብ 8 በመቶ ድምጽ በማግኘት ያሸነፉት ማዳ ቢዮም ወደ ፕሬዚዳንትነት ስልጣን ከመጡ ከቀናት በፊት አንድ ዓመት አስቆጥረዋል።
በ1990ዎቹ አሰቃቂ የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን የተነጠቀችው ሴራሊዮን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ አላት። በወጪ ንግድ ገቢ ላይ ኢኮኖሚዋን የመሰረተችው ሴራሊዮን ከአፍሪካ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት በቀደምትነት ትጠቀሳለች።ምንም እንኳን በማዕድን ሃብት የበለፀገች ብትሆንም፣ ሙሰኞች ከደሃ አገራት ተርታ እንድትሆን አድርገዋታል።
ጂሊዬስ ማዳ ቢዮ በፈረንጆቹ 1994 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ይዘው የነበረ ሲሆን፤ 1996 በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣናቸውን አስረክበዋል። ከዚህ በኋላም ወደ አሜሪካ በማቅናት በፖለቲካ ጥገኝነት ኑሯቸውን በመምራት ትምህርታቸውን በመከታተል ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል።እ.ኤ.አ በ2005 ወደ አገራቸው በመመለስም ላለፉት ዓመታት በፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ባሳለፍነው ዓመትም ሴራሊዮንን ለመምራት ኃላፊነት በተረከቡበት በፈጸሙት ቃለመሃላ ፤የደቀቀው የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ አዳዲስና ጠንካራ ፖሊሲዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።በተለይ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በገቡት ቃል መሰረትም ‹‹አገሪቱን በዝብዘዋል፤ የመንግሥትና የህዝብ ንብረትን ያለ አግባብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል» የተባሉ ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር በማዋል ቃላቸውን በተግባር ለማሳየት ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም።የፀረ ሙስና ዘመቻውም ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የቀድሞ አመራሮችን ሳይቀር አዳርሷል።ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶር ፎህናናንና የማዕድን ሚኒስትር ማንሳራይ ሚንካይሉን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችንና ባለሃብቶችን ተጠያቂ እስከማድረግ የደረሰ ነው።አንዳንዶችንም ከመንግሥት ኃላፊነት አሰናብቷል።
በዚህ የአገሪቱ የፀረ ሙስና ዘመቻ የአፍሪካው ኒውስ ዘጋቢ አብዱር ራህማን አልፋ ሻባን የአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ከቀናት በፊት ይዞት በወጣ ዘገባ እንዳመለከተውም፤ አገሪቱ እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2018 ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ተመዝብሯል። ምርመራውም የአገሪቱን ብሄራዊ ቴሌኮም ጨምሮ በአሥራ አንድ የመንግሥት ተቋማት የተካሄደ ነው።
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው አንድ ዓመት የስልጣን ቆይታቸውም ያከናወኗቸው ተግባራትም በበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ፖለቲከኞችና ተቋማት ዘንድ አድናቆትን አትርፏል።በተለይ በሙስናና ሙሰኞች ሰንሰለት የታሰረችውን አገር ለማስፈታት ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን ከሁሉ በላይ አስወድሷቸዋል።አገሪቱን ከኢኮኖሚ ድቀት በማላቀቅ ወደ ተስፋ ጎዳና በማመላከት ረገድም ተስፋ ሰጪ ተግባራትን መፈፀማቸው ታምኖበታል።
የኒው አፍሪካን መጽሄትም በበኩሉ ስልጣናቸውን በከፍተኛ ውሳኔና ራዕይ የጀመሩት ፕሬዚዳንቱ፤ሙስናን ከመዋጋት አንስቶ አዳዲስና ጠንካራ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ይፋ እስከማድረግ የደረሰ ተግባር በመፈፀም የፈለጉትን ለውጥ መመልከት መጀመራቸውን አትቷል።
ፕሬዚዳንቱ ከመጽሄቱ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስም፤በኢኮኖሚ ድቀት የተንኮታኮተች ፣በከፍተኛ ሙስናና ሙሰኞች የምትበዘበዝ አገር መረከባቸውን ጠቅሰው፣ይህም የፈለጉትን ለውጥ ለማምጣት በሁሉም መስክ ከአዲስ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፤ የሚፈልጉትን ለውጥ ለማስመዝገብም እየተጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሴራሊዮን ቴሌግራፍ ጸሐፊው አብዱል ረሺድ ቶማስም እንደሚያትተው፤ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት በአገሪቱ የነበረው ቅጥ ያጣ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደርና ብልሹ አሰራር ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ንና የዓለም ባንክን ሳይቀር በእጅጉ አስከፍቷል፤ብልሹ አሰራሩ ማናቸውንም ዓይነት ድጋፍ እስከ መከልከልና ፕሮጀክቶችን እስከ መሰረዝ ተሻግሮም ታይቷል።
ይህ በሆነበት ፕሬዚዳንቱ ባለፈው አንድ ዓመት የስልጣን ቆይታቸው የተቋማቱን ጥያቄና ፍላጎት እንዲሁም የሚያስቀምጡትን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ብዙ ስለመድከማቸው የተመላከተ ሲሆን፤ በተለይ የኢኮኖሚ አስተዳደሩን ለማሻሻል የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ግዙፎቹን የገንዘብ ተቋማት የማሳመኑ አቅም እየፈጠረ ስለመሆኑም ተብራርቷል።
ፕሬዚዳንቱ፤ከመጽሄቱ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ይዘው ወደ አገሪቱ እንዳይመጡ ከሚያደርጉት ዋነኛ እንቅፋቶች መካከል ሙስና አንዱ ነው፤በሚያስገርም ሁኔታ ከዓለማችን ሙስና የተንሰራፋባቸው አገራት በግንባር ቀደምትነት የሀገሪቱ ስም ይነሳል።
‹‹በዚህ መልኩ እየተጠቀስን እድገት ማስመዝገብ ይከብደናል››ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በሙሉ ቁርጠኝነት ሙስናንና ሙሰኞችን መፋለም መጀመሩን ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ሙስና በአንድ ጀንበር የማይጸዳ እና የሴራሊዮን ብቻም ሳይሆን የዓለም ራስ ምታት ነው።መንግሥታቸውም የፀረ ሙስና ዘመቻውን በመጀመር በርካታ ተግባሮችን አከናውኗል።
‹‹ሙስናን መፋለም ብቻ ሳይሆን የተዘረፈ ገንዘብን በማስመለስና ሙሰኞችን ፍርድ ቤት በማቅረብ ረገድ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ውጤታማ እየሆንን እንገኛለን›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣እስካሁንም የቀድሞው ፓርቲ አመራሮች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወደ መንግሥት ካዝና እንዲመለስ መደረጉን ይጠቅሳሉ።ሴራሊዮን አሁን ሙስናን በመፋለም ለአፍሪካውያን ምሳሌ መሆኗን ይጠቅሳሉ፤መንግሥታቸውን ይህን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ሁሉ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየው ሙስና ባለሃብቶችን ከኢንቨስትመንት ከማስተጓጎልና ለአገሪቱ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ማስገደዱን የሚስማማበት የሴራሊዮን ቴሌግራፍ ፀሐፊው አንዱል ረሺድ ቶማስም፣ አሁን የፕሬዚዳንቱና የፓርቲያቸው ጠንካራ የገንዘብ አስተዳደርና የሙስና ፍልሚያ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ይጠቅሳል።ፕሬዚዳንቱ በዓለም አቀፉ ደረጃ የአገሪቱን ስም ያጎደፈውን ይህን ድርጊት በማስቆም ስሟን ለማደስ የአጋር ተቋማትን እምነት ለማግኘት ብዙ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይገልጻሉ፤በዚህም ከሞላ ጎደል ስኬታማ እየሆኑ መምጣቸውን ተናግሯል።
ሰውየው ከኢኮኖሚ ለውጦች ባሻገር በተለይ በአገሪቱ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሄዱበት ርቀት የብዙዎች አድናቆት ተችሮታል።በተለይ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ከዓመት ዓመት እየጨመረ ፈጻሚዎች በአንፃሩ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ የሚቀሩበት ነው።በአገሪቱ ለጾታዊ ጥቃቶች የሚጣለው ከፍተኛው ቅጣት የ15 ዓመት እስር ሲሆን፤ጥቂቶች ብቻ መቀጣታቸውን ነው የተጠቆመው።
ይህን ያስተዋሉት ፕሬዚዳንቱ፣ «ሴቶችን በተለይም ሕጻናትን የሚደፍሩ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል›› ማለታቸውን ተከትሎ ለውጦች ስለመታየታቸውም ተመስክሯል።
ከዚህ በተፃራሪ ፕሬዚዳንቱ በአንድ ዓመት የስልጣን ቆይታቸው ለአገራቸው ከኢንቨስትመንትም ሆነ ከእርዳታ ሰጪ ተቋማት ይህን ያህል የሚባል አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ማምጣት አልቻሉም ሲሉ መውቀሳቸውም ታውቋል።
የአፍሪካን አርጊውመንት ዘጋቢው ካርስ ቡርጂን፤የሴራሊዮን ህዝብ ፓርቲ የቀድሞ የመንግሥት ኃላፊዎችን፤አምባሳደሮችና የባንክ ኃላፊዎች ለእስር መዳረጉን ጠቅሶ፣አንዳንዶችንም ከመንግሥት ኃላፊነት ማሰናበቱን ይገልጻል።በተለይ በቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የተመዘበረውን ገንዘብ በማስመለስ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ፈር አለመያዛቸውን አትቷል።
ከዚህ ባሻገር በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረቶችና መጠነኛ የሚባሉ ግጭቶችም እየታዩ ይገኛሉ ያለው ፀሐፊው፤ እነዚህ ክስተቶች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ እንዳልሆኑም ይናገራል።ችግሮቹ እ.ኤ.አ 2013 እስከ 2014 ከነበረው በመጠን ከፍ ያሉ መሆናቸውን አመላክቷል።
ባለፈው አንድ ዓመት የስልጣን ቆይታቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሻሻልና ሙስናን በመታገል ረገድ የመገናኛ ቡዙሃንን፣ የፖለቲከኞችን፣የተለያዩ የተቋማትንና የህዝብን ይሁንታ ያገኙት ፕሬዚዳንት ጂሊዬስ ማዳ ቢዮ፣ ከኒው አፍሪካን መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታም ሳይውል ሳያድር የህግ የበላይነትን ማስከበር ቀዳሚ አጀንዳቸው ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2011
በታምራት ተስፋዬ