ሰኞ ዞራ በመጣች ቁጥር ስማረርባትና ስጠላት ነው የኖርኩት። እንዲያውም ከዓመቱ ሰኞዎች ሁሉ የምወዳት የዛሬዋን ሰኞ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። መቼም «ምን ተገኘ?» ብሎ ጠያቂ አይጠፋምና ልመልስ፤ የዛሬዋን ሰኞ ከሌሎች ዘመዶቿ ይልቅ የምወዳት በበዓል ማግስት ስለምትመጣ ነው። ያው ከእንቅልፌ ስነቃ ጀምሮ እንደ ሌላው ጊዜ ሳይጫጫነኝ በደስታ መንፈስ እንዳለሁ ነኝ። የምከውነው ስለሌለኝም ሲያሻኝ መተኛት አሊያም ለበዓል ከተሰናዳው እየበሉና እየጠጡ መዋል ወይም ደግሞ ጎረቤትና ወዳጆችን በመጠየቅ አሳልፋለሁ። መቼም ሁሉ ቀን አንድ አይደለምና የዛሬ ዓመቷ ሰኞ ግን ከደስተኝነት ይልቅ ንዴትን በንዴት ላይ እንደ ድንጋይ ካብ ደራርባብኝ ነበር ያለፈችው።
ትናንት ብዙም ደስተኛ ሳልሆን በስጋት መዋሌን ለሰውም አላዋየሁም ነበር። ለሰው ያላወጋሁት ደግሞ እንዳለፈው ፋሲካ ዶሮው ከመገዛቱ አንስቶ ተሰርቶም አንዳች እክል ይደርስበት ይሆናል የሚል ስጋቴን ነው። ያደለው እንደቀልድ ቆጥሮ ይስቅብኝ ይሆናል፤ ለእኔ ግን ሰቀቀኑ ነበር ያመዘነብኝ። ምክንያቱም ዶሮ የምገዛው በዓመት አንድ ጊዜ ፋሲካን አስታክኬ ነዋ! ፋሲካ አንድም ከዶሮ ጋር የተያያዘ ሃይማኖታዊ እንድምታ ስላለው፤ ሁለትም ለሁለት ወራት አደብ የምትገዛውን ሚስቴን ለማስገደፍ ነው። እንጂማ ለትንሿ ዶሮ ሲባል የሚወጣውን ያንን ሁሉ ወጪ ማን ይችለዋል? ከቤት ከጠፋ ያለፈው ቅዳሜ ዓመት የሞላውን ዶሮ ልገዛ ከገበያ የወጣሁት በዚህ ምክንያት ነበር።
እንደ ሸማች ግርግሩን ተቀላቅዬ ገበያውን ስዞር የታዘብኩት ግን የማልገዛው መብዛቱን ነበር። ከዶሮ ተራው ደርሼ መጠያየቅ ከመጀመሬ፤ ነጋዴዎቹ እንደ ፌስታልአንጠልጥለው ለሚያወዛውዟቸው ዶሮዎች እንደ ቀልድ የሚጠሩትን ዋጋ ስሰማ የሒሳብ ችሎታየንም ኪሴንም ተጠራጥሬ ነበር። ዶሮ ከእነ ቅመማ ቅመሙ አንድያውን ከበግ ሊስተካከል ምን ቀረው ጎበዝ? በርካሽ ዋጋ ለማግኘት ወዲያ ወዲህ ስል ቆይቼ ከብጤዎቹ ተለይቶ ብቻውን የቆመ ኮስሟና ዶሮ ላይ ዓይኔ አረፈ። ክንፎቹ እንደሌሎቹ ግርማ ሞገስ የላቸውም፤ እንዲያውም ተቆጥተውት እጁን የፊጥኝ ያጣመረ ብላቴና ይመስላል። የተያዘለትን ቀጠሮ የተሳለለትን ቢላዋ ጠርጥሮ በሃሳብ የነጎደ ይመስልም ምልከታው ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ነበር።
ጠጋ ካልኩት በኋላ እኔም እንደሱ በሀሳብ ነጎድኩ በአንድ ወገን ይሄ አንድ ሀሙስ የቀረው ዶሮ እቤት ሳይደርስ እጄ ላይ ቅርት ቢል ምን ሊውጠኝ ነው? በሚል በሌላ ወገን የደሀ አምላክ ረድቶኝ ከነነፍሱ ቤት ቢደርስ እንኳ በነጋ በጠባ ነገር በደላላ የምትፈልገው ጭቅጭቅ የሚቀናት ባለቤቴን ፈራሁ። ሌሎቹን ዶሮዎች ተመለከትኳቸው፤ የኮስሟናውን እጥፍ ይሆናሉ። ግን ምን ያደርጋል ምርጫው የኔ ሳይሆን የኪሴ ነው። እናማ ቀልቤ ባይወደውም ከዚያም በላይ የሚከተለው ጣጣ ቢያሰጋኝም ዋጋውን ስለወደድኩለት ብቻ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ገዛሁት። ወደ ቤቴ ስወስደውማ ዶሮ ሳይሆን ላባ የያዝኩ ያህል እንደቀለለኝ ነበር። ስደርስም ጥሬ በትኜለት ከቤቴ በራፍ እንደ ወጉ እግሩን አስሬ ገባሁ። ምን ዋጋ አለው አመሻሹ ላይ የገባበት ጠፋ እንጂ፤ እኔ የባለቤቴ ቁጣ ሲያሳስበኝ ለካስ ያልታሰበ ሌላ እዳም አለ። ደግሞ እኮ በጨዋ ደንብ ፈትቶት የሄደ ይመስል የታሰረበት ገመድ እዚያው ነበር። መጀመሪያም ሃሳብ የገባው የመሰለኝ ዶሮ የማምለጫ መንገዱን ሲፈልግ እንደነበር የገባኝ ቆይቶ ነው። እንዲያው በሞኝነቴ በስጨት ብዬም ነበር።
በበዓል ዋዜማ የጠፋ ዶሮን መፈለግ የቂል ተግባር ቢሆንም አማራጭ ሰላልነበረኝ ባትሪ ይዤ ስሽከረከር አመሸሁ፤ ግን እንኳን ዶሮውን ላባውን ሳላገኝ ቀረሁ። ቢፈለግ ሰፈሩ ቢታሰስ የገባበት ጠፋ ዋዜማውም በንዴት፤ በዓሉም በውሸት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ በሚለው እየተባለ አለፈ። ባለቤቴም ያለ ወትሮዋ ነገር ሳትቆሰቁስ እያፅናናችኝ እንዳያልፉት የለም በውሸት ዶሮ አለፈ። በንጋታውም(የዛሬ ዓመት መሆኑ ነው) ያ ጉረኛ ከስራ ወሬው የቀደመ ጎረቤቴ፤ «… ዶሮ ጠፋብህ ሲሉ ሰማሁ፤ ፋሲካ የመካፈል በዓል ነውና ከእኔ ጋር ብናሳልፍ ፍቃዴ ነው። ካሻህ በዶሮ ካልሆነም በቅርጫ ስጋ ጾምህን ትፈታለህና እንድትመጣ» የሚል መልዕክት በልጆች ሰደደልኝ።
እስኪ አሁን ማን ይሙት ሲመጻደቅብኝ እንጂ የመጨረሻው ንግግር በዚህ መልኩ መተላለፍ ነበረበት? ይሄ ሰውዬ በእድር ስብሰባና ለቅሶ ቤት እየተገኘ ጉራውን መቸርቸር የዘወትር ተግባሩ ነው። በጥላ ቢስ ሰውነቱ ካፖርቱን ለብሶ እጁን ወደ ኋላ በማጣመር ወዲያ ወዲህ ማለቱ ከጠፋው ዶሮ ጋር ተመሳሰለብኝ። ንዴቴን ውጬ ጠሪ አካባሪ ነው ብዬ ከቤቱ ስሄድም እንደ ፈራሁት ከነጉራው ነበር የተቀበለኝ። ኧረ እንዲያውም የሽሙጥ አስተያየቱን ሳስተውል ከዶሮው ጋር ተመሳጥረው ይህንን ተንኮል እየሰሩ የሚሳለቁብኝ መስሎኝ ነበር።
ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ የቀረበልኝን ዶሮ መብላት ቀጠልኩ፤ ግና ሁለት ከመጉረሴ ባለቤቱ ከፍተኛ የሙያ ክፍተት እንዳለባት ለመረዳት ቻልኩ። ይህን ዶሮ ባለቤቴ ብታገኘው እንዴት ልትከሽነው እንደምትችል ሳስብ ደስታ ቢጤ ተሰማኝ፤ ምክንያቱም የኔ ባለቤት ከእርሱ ባለቤት በሙያ ትበልጣለቻ። ህሊናዬ ግን፤ ሙያ ብቻውን ምን ይፈይድ፤ እንዳንተ ዓይነት ፈዛዛ ሳለ ይለኝ ነበር። እውነት ነው፤ አልኩ ለራሴ። ሰው እንዴት በስንት ልፋት ያመጣው ነገር እንደ ቀልድ ያመልጠዋል? ለነገሩ ይሄ የእኔ ብቻ ችግር አይደለም፤ የኢትዮጵያውያን መለያ ባህሪ ከሆነ ሰነባብቷል። ይኸው በስንት ጥረትና መስዋዕትነት ያመጣውን ሰላምና እንድነት በመተባበር ገመድ ማጥበቅ ተስኖን ስንውተፈተፍ አምልጦን ከሌሎች እየቀላወጥንም አይደል? ይህ በዓል የምህረት ሆኖ ሳለ ይቅር አለመባባሉ እኛን አይወክልምና ልቦና ይስጠን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
ብርሃን ፈይሳ