ሥራ ውሎ ለመግባትና ህይወትን ቀና በሆነ መንገድ ለመምራት ያስችል ዘንድ ትራንስፖርት ቁልፍ መሣሪያ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን እንዲሁም በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ለመኖር አስፈላጊ ነው። በተለይም ደግሞ እንደ አዲስ አበባ ላሉ ከተሞች የተሻለ የትራንስፖርት ዘዴ መኖር ከአስፈላጊነቱ በላይ የህልውና ጥያቄ ነው።
ለዚህም አንዱ ማሳያ የሆነው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራነስፖርት አገልግሎት አሁን ላይ የህዝቡ ቀዳሚ ተመራጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። እኛም የዚህን ትራንስፖርት አገልግሎት በተገልጋዮች እይታ ምን እንደሚመስል በተለያዩ የባቡር መዳረሻ ጣቢያዎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት እንደሚከተለው አሰናድተን ለአንባቢያን አቀረብን።
ወይዘሮ በድባብ ወልደማርያም ይባላሉ፣ ያገኘናቸው ለገሐር በሚገኘው የባቡር ጣቢያ ወደ መኖሪያ ቀያቸው ልደታ ለመሄድ ከሳሪስም ሆነ ከሀያት የሚመጣውን ባቡር በመጠባበቅ ላይ እያሉ ነው። ዕድሜያቸው የገፋ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ በመሰለፍ ታክሲም ሆነ አውቶብሶችን ለመጠበቅ አቅም እንደሌላቸው ፊተ ገፃቸው ይናገራል። ይህን ችግራቸውን ያቀለለውን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት እንዳቃለለላቸው ከሚናገሩት በላይ ከገፅታቸው የሚነበበው ስሜት ይናገራል። የትራንስፖርት አገልግሎቱን መጠቀም የጀመሩት ልክ ባቡሩ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጊዜ አንስተው ነው። የሥራ ቦታቸው ጎሮ አካባቢ መሆናቸውን የሚናገሩት ወይዘሮዋ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን ይችሉ ዘንድ በሰዓቱ መግባትና መውጣትን ይመኛሉ። እናም ምኞታቸውን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ሁነኛ የትራንስፖርት አማራጫቸው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሆኖ አግኝተውታል። ለምን ቢሉ በሰዓቱ በመድረሱና ለፈለጉት አላማ ጊዜያቸውን ለመጠቀማቸው የባቡር አገልግሎቱ ወደር የማይገኝለት ነው።
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በህብረተሰቡ ተመራጭ እንደሆነ ስታዲየም የባቡር ጣቢያ ላይ ወደ ሳሪስ ለመሄድ ባቡሩን በመጠባበቅ ላይ እያሉ አግኝተን ካነጋገርናቸው መካከል አቶ ዳኛቸው ገለታ አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የባቡር ትራንስፖርትን በብዛት እንደሚጠቀሙ ነግረውናል። ምክንያቱም የባቡሩ ተደራሽነት በጣም ፈጣንና መስመሩም ልክ እንደተሸከርካሪዎች ስለማይዘጋጋና ክፍያውም ተመጣጣኝ መሆኑን ወደውት ይገለገላሉ። ይህም በፈለኩት ጊዜና ሰዓት ወደፈለጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራቸውንና ማህበራዊ እንቅስቃሴአቸውን ለማከናወን አስችሏቸዋል።
በሌላ በኩል ስታዲየም የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ስትጠባበቅ ያገኘናት ወጣት ማርታ አበበ በበኩሏ፤ ይህን የትራንስፖርት አገልግሎት እንድመርጠው ያደረገኝ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መቻሉ ነው። ምክንያቱም ሌሎች የትራንስፖርት አይነቶች ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ስላለና ታክሲም ሆነ አውቶብሶች በቀላሉ ስለማይገኙ ለረጅም ጊዜ በሰልፍ መጠበቅ እጅግ አሰልች ነው። ስለሆነም ባቡሩ ይህን ችግር በመቅረፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችል በመሆኑ ከሁሉም ልዩ ያደርገዋል። ወጣቷ እንዳለችው አገልግሎቱን ስትጠቀም የታዘበችው የቴክኒክ ችግር ካላጋጠመው በስተቀር ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ ነው። ለወደፊትም ከዚህ አጠናክሮ ከቀጠለ የበለጠ ተወዳጅ እንደሚሆን ተስፋቸውን ሰንቀዋል።
ወጣት ጉተማ ገመዳ ኗሪነታቸው አዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ ነው ካላቸው የሥራ ባህሪ አንፃር በሁሉቱም ምዕራፎች አገልግሎቱን ይጠቀማሉ። እናም እርሳቸው የቀላል ባቡር ትራነስፖርቱን የመረጡበት ዋናው ምክንያት በተመጣጣኝ ክፍያ ወደፈለጉት ቦታ ለመድረስ በቶሎ እንዲደርሱ ስላስቻላቸው ነው። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ፈልገውና ወዳው የሚጠቀሙት የትራንስፖርት አማራጭ ነው። ቀላል ባቡሩ የህዝቡ አይን መሆኑን የሚያመላክተው ደግሞ ማሳፈር ከሚችለው አቅም በላይ በመያዝ አገልግሎቱን እየሰጠ በመገኘቱ ነው። ለህዝቡም ሆነ ለቀላል ባቡሩ አገልግሎት ምቹ እንዲሆን ማድረግም የሁሉም ተሳትፎ መኖር አለበት። በተለይ ጧትና ማታ ተጠቃሚው በጣም ስለሚበዛ ወደባቡሩ ለመግባት ከፍተኛ የሆነ የመገፋፋት ሁኔታ ይታያል። ይህ ደግሞ በተለይ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ እድሚያቸው የገፉ ሰዎች ለጉዳት ይዳረጋሉ። ስለሆነም ህብረተሰቡ ይህንን በመገንዘብ ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት ተረጋግቶ አገልግሎቱን መጠቀም መቻል ያስፈልጋል። ከመገፋፋት ይልቅ ቀጣዩን ባቡር መጠበቅም አንዱ አማራጭ ነው ምክንያቱም ለጤንነትና ለደህንነትም መልካም ነው። በተለይ ተሳፋሪ በሚበዛበት ወቅትም ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ባቡሮች ቶሎ ቶሎ የሚደርሱበትን መንገድ ቢመቻች መልካም ነው ብለዋል።
አቶ ደመላሽ አጋፋሪ ጉርድ ሾላ አንድ የባቡር ጣቢያ አገልግሎቱን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ አግኝተናቸዋል። በብዛት የሚጠቀሙት የቃሊቲ ቢሆንም በሥራ ምክንያት የሃያቱን መስመር ሲጠቀሙ አግኝተን አናግረናቸዋል። አሁን እዚህ የተገኘሁት ከዚህ ጉርድ ሾላ ወደ ባምቢስ ለመሄድ ነው። እሳቸውም ስለባቡሩ አገልግሎት ተመራጭነቱ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም የሚመሰክረው ሀቅ ነው። አገልግሎቱን እንድጠቀም ያደረገኝ አንዱ የሰዓት አጠቃቀም ነው። ጧት ጧት አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ አለ። ይህ በመሆኑ ምክንያትም ሰዎች የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴቸውን ለማከናወን እንከን ሲፈጥር ይታያል። እናም ለዚህ ዋናው የመፍትሔ አካል ሆኖ ያለው የቀላል ባቡሩ አገልግሎት ነው። አቶ ደመላሽ እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባቡሩ ተደራሽነት እየተሻሻለ መጥቷል። በዚህም ምክንያት የህብረተሰቡ የአገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ታዝበዋል። ምክንያቱም ይላሉ ጊዜ ለሰው ልጅ ሁሉም ነገሩ ነው። ስለሆነም የቀላል ባቡሩ አገልግሎት ከምንም እና ከማንም በላይ የህዝቡን ህይወት ለማቅናት አንዱ ቁልፍ አማራጭ ነው። ታዲያ ይህ ተተኪ የሌለውን የትራንስፖርት አማራጭ በባለቤትነት ስሜት መጠቀም የሁሉም ድርሻ ነው።
እነዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም በቀላል ባቡሩም ሆነ በአገልግሎት ተጠቃሚው ማህበረስብ ዘንድ ያዩትን ክፍተት እንዲሻሻል የሰጡትን ሀሳብ በሚከተለው መንገድ አስፍረነዋል። ባቡሩ ተበላሸ ማለት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው በጣም የተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰት በሚታይባት አዲስ አበባ ትራንስፖርት በቀላሉ ማግኘት ፈተና ይሆናል። ሌሎች የተሸከርካሪ ትራንስፖርት አማራጮችን ለማግኘት የሥራ ሰዓትን ተሰልፎ መጠበቅ አሰልች ከመሆኑም ባሻገር ሥራን በሚፈለገው ደረጃ ለማከናወን አያስችልም። አሁን አሁን የባቡር አገልግሎት መስጠት አቆመ ማለት ሊከሰት የሚችለውን ቀድሞ ማሰብ በቂ ነው። ስለሆነም ይህን በመገንዘብ የሚመለከታቸው አካላት ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እንዲኖር ማስቻል ይጠበቅባቸዋል። ብልሽት በሚከሰትበት ወቅትም በቶሎ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎቱን መስጠት እንዲችል ቢደረግ፤ አገልግሎቱን የሚጠቀመው ህብረተሰብ ሳይጉላሉ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። የቴክኒክ ችግር በሚከሰትበትም ወቅት ተገቢ የሆነ መረጃ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማድረግ ተገቢ ነው።
ጧትና ማታ ከቀኑ በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ህብረተሰብ አገልግሎቱን ስለሚጠቀም ከፍተኛ መጨናነቅ ስላለ ባቡሮች ቶሎ ቶሎ እንዲደርሱ ቢደረግ መልካም ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህብረተሰብ ባቡሩን ስለሚጠቀም ይጨናነቃል። ከመጨናነቁ የተነሳም ስርቆት እንዲስፋፋ በር ከፋች ነው። ምክንያቱም ሁሉም የወጣበትን አላማ አሳክቶ ወደቤቱ ለመመለስ ሲል ሀሳቡን ሁሉ ከወጣበት አላማ ላይ ስለሚያደርግ ለስርቆት የተዘጋጁ ሰዎች በቀላሉ የቦርሳ፣ ስልክ፣ ገንዘብና መሰል ንብረቶችን ይነጥቃሉ። ቀላል ባቡሩም የተሳፋሪዎችን ቁጥር ያጣጣመ አገልግሎት ቢሰጥ ችግሩን በመቅረፍ ከዚህ በላይ ተወዳጅ እንዲሆን ስለሚያስችለው ጥብቅ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት ቢዘረጋ ጥሩ ነው። አልፎ አልፎም የሚከሰቱ መዘግየቶችን አርሞ አገልግሎቱን ቢሰጥ መልካም ይሆናል ሲሉ አስተያየታቸውንና ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
ስለሆነም ይህን ቁልፍ የሆነ የትራንስፖርት ዘርፍ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የግል ተቋማትና ህዝቡ በጋራ በመሆን በባለቤትነት ስሜት በመያዝ መገልገል ቢቻል መልካም ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሞገስ ተስፋ