በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይም በብዙ ተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ችግር የሚታይበት በመሆኑ ይህ የመልካም አስተዳደር ችግር ዜጎችን ሲፈትን ይስተዋላል፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ ቢሆን በሚል በተለያየ ጊዜ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ተሞክሯል፡፡ ዛሬም ድረስ ግን ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ ችግሩ ደግሞ በአዲስ አበባ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ዘላቂ መፍትሔው ምንድነው? በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ገበየው ሊካሳ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተገልጋይ እርካታ ያለፉት ወራት አፈፃፀም ምን ይመስላል?
ዶክተር ገበየው፡- የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዘመናዊ ለማድረግና የኅብረተሰቡንም እርካታ ያረጋገጠ እንዲሆን ብዙ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ተቋሙ ብዙ ተግዳሮቶች የነበሩበት ነው፡፡ ከ2002 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ የግብዓት እጥረት የነበረበት ከመሆኑ በተጨማሪ የቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይም ዘገምተኛ በመሆኑ የደንበኞች ቅሬታ ምንጭ ሆኖ ከርሟል፡፡ ይህንን ለመለወጥ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በተለይ የኃይል መቆራረጥና የገንዘብ አሰባሰብ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለአብነት ያህል የኃይል መቆራረጥን ከመቀነስ አኳያ የስትራቴጂክ እቅድ ተቀርፆ በአራት ምዕራፍ አዲስ አበባ ውስጥ የማከፋፈያ መስመሮች ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራ ተከናውኗል፡፡
ሁለቱ ምዕራፍ እስከ 2014 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ተጠናቋል፡፡ ይህም 10 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡ እነዚህ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ሲገቡ የደንበኞች ቅሬታ እየቀነሰ፣ የኃይል መቆራረጡም እየተሻሻለ ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል የክፍያ አማራጮችን ከማስፋት አኳያ ቴክኖሎጂን ስለተጠቀምን ደንበኛ በደረሰበት ቦታ መክፈል ይችላል። ከዚህ ቀደም ከአንደኛው የሀገሪቱ ክፍል ሆኖ በባንክ ክፍያ መፈጸም የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ይህ ተችሏል፡፡ በእርግጥ በታሰበው ልክ ባይሆንም የደንበኞች እርካታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡
እኛ የደንበኞችን እርካታ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በየስድስት ወሩ ግምገማ እናካሂዳለን፡፡ በዓመት አንዴ ደግሞ በውጭ አካል ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን እናሠራለን፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮውን ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ በሦስተኛ ወገን ባስጠናነው ጥናት ተቋሙ አፈፃፀሙ 61 በመቶ ላይ ነው፡፡ አምና 58 ከመቶ ነበርን፤ አሁን ሦስተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት ደግሞ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ግማሽ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ የኃይል መቆራረጡ ይቀንሳል፡፡ ከዚህም የተነሳ የደንበኞች እርካታ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥናቱ ያላችሁበትን ደረጃ አመላክቷችኋል ?
ዶክተር ገበየው፡- በእኛም ሆነ በውጭ የተጠናው ጥናት ብዙ እንደሚቀረን አመላክቶናል፡፡ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብንም አስተውለናል፡፡ ከለየናቸው ክፍተቶች አንደኛው አስቀድሜ የጠቀስኩት የኃይል መቆራረጥ ነው፡፡ ሌላው ከ2002 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ የሆነ የግብዓት እጥረት ነበረ፡፡ በዚህ ምክንያት ከፍለው የሚጠባበቁ ብዙ ደንበኞች ነበሩ፤ አሁን ግን እየጨረስን ነው፡፡ እነዚህን በሙሉ እያጠናቀቅን ስንመጣ የደንበኞቻችን እርካታ ይሻሻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግምገማችሁ በዋናነት ችግር ነው ብላችሁ የለያችሁት ዘርፍ የትኛው ነው?
ዶክተር ገበየው፡- እንደጠቀስኩት አንዱ የቅሬታ ምንጭ የኃይል መቆራረጥ ነው፡፡ ይህን መሠረታዊ በሆነ ደረጃ ለመፍታት አስቀድሜ እንደጠቀስኩት በአራት ምዕራፍ የተከፋፈለ የሪሃቢሊቴሽን (Rehabilitation) ፕሮጀክት አለ፡፡ ነባራዊ ሁኔታው ሲታይ ኔትወርኩ በጣም ያረጀ ነው፡፡ ይህን ለመቀየር ስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፎ እየተሠራ ነው፡፡ የሁለቱ ምዕራፍ ፕሮጀክት ተጠናቋል፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ በ2016 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ አራተኛው ምዕራፍ ደግሞ አሁን ተጀምሯል፡፡
የግዥ አማካሪ ቅጥር እየተካሄደ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በዓለም ባንክ የገንዘብ ወጪ የተሸፈነ ነው። ፕሮጀክቱ በ2017 ዓ.ም ሲጠናቀቅ አሁን የሚታየው የኃይል መቆራረጥ ይቀንሳል፡፡ በአራተኛው ምዕራፍ ሁለት ሺህ የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችን አቅም የማሳደግ ሥራ ይሠራል፡፡ ያሉን አስር ሺህ ናቸው፤ በዚህ ሂደት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራርን በመጠቀም በተለያየ መንገድ ይሠሩ የነበሩ በአንድ የቁጥጥር ጣቢያ ውስጥ ይገባሉ። ኃይል ሲቋረጥ በቀላሉ ማወቅ ስለሚቻል በኃይል መቆራረጡ ላይ የሚታይ ለውጥ ይመጣል፡፡ ከወቅታዊ የአየር ሁኔታ ጋር የነበረው የኃይል መቆራረጥን አሁን በምንችለው ደረጃ በቅድመ መከላከል ጥገና እና በመልሶ ግንባታ የምንሠራቸው አሉ፡፡ ነገር ግን በመሠረታዊነት ችግሩን ለመፍታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ የግድ ይላቸዋል፡፡
ሁለተኛው የገንዘብ አሰባሰብ ላይ ክፍያ በዛብኝ፤ ንባብ በትክክል አይወሰድም፤ የተሳሳተ ቢል ነው፤ የሚሉ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ይህን ለመፍታት ብዙ መንገድ ሄደናል፡፡ እኔ ወደዚህ የኃላፊነት ስፍራ የመጣሁት በ2012 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ያኔ የነበረው ትልቁ ቅሬታ ሰልፍ ነው፡፡ አሁን ግን በዓመት በዓል ወቅቶች ከሚያጋጥመው ውጭ አንድም ሰልፍ የለም፡፡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የቆጣሪ ንባብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን አድርገናል። የቆጣሪ አንባቢ ቆጣሪው ያለበት ቤት የግድ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ ችግሩ እየተቀረፈ ነው፡፡
ሌላው የለየነው ችግር አዲስ ከፍለው የሚጠባበቁ ደንበኞች ጉዳይን ናቸው፤ ከ2002 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት እጥረት ነበር። ይህም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ከውጭ ይገባ የነበረ ሁሉም እቃ አሁን ሀገር ውስጥ ይመረታል፡፡ ስለዚህ ከፍለው ያልተስተናገዱትን ደንበኞች ቁጥር እያቃለልን በመሆኑ የቀሩት ከስድስት ሺህ የማይበልጡ ደንበኞች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ደንበኞች ሂሳብ በጣም እንደሚጋነን የሚጠቅሱ ሲሆን፣ እኛም የተጠቀሙበት ስለመሆኑ ሁኔታውን በግልጽ በማሳየት እናሳምናቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡- የምታሳምኗቸው በምን አግባብ ነው?
ዶክተር ገበየው፡- ባለፉት ዓመታት ሲከፍሉ የነበረው ከአጠቃቀማቸው አኳያ ሲነጻጸር ትንሽ ብር ነው፡፡ በመሆኑም እኛ በጊዜ ያለማስከፈላችን እንጂ የተጋነነ አለመሆኑን እናሳምናቸዋለን፡፡ ከዚያም በክፍያ ሂደቱ ጫና እንዳይፈጠርባቸው እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ ጊዜ እንሰጣቸዋለን፡፡ የቢል ስህተት ካለ ደግሞ ይታረማል፡፡ ድሮ ከታተመ አይታረምም ነበረ፤ አሁን ቢል ላይ ስህተት ካለ በአገልግሎት መስጫ ማዕከል ላይ እርምት ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ይህን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ አድርገናል ማለት አንችልም፡፡ አሁንም እየሠራንበት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቆጣሪ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ያለው ፍትሐዊ አሠራር ምን ይመስላል? አገልግሎቱን በወጥነት አትሰጡም፤ ቆጣሪ ቀድመው ተመዝግበው የሚጠባበቁ እያሉ ከኋላ መጥተው ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች አሉ ይባላል፤ ለምን?
ዶክተር ገበየው፡- ይህ የሚፈጠርበት ሁኔታ አለ፤ አልፎ አልፎ አንደኛው ደንበኛ አራት ምሰሶ ይፈልጋል ወይም ትራንስፎርመር ይፈልጋል፡፡ ሌላው ደግሞ ከምሰሶ ብቻ በሽቦ የሚገባለት ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንድ ትራንስፎርመር የሚጠብቅ ሰፈር አለ፤ ግን የከፈለው የዛሬ ዓመት ነው፡፡ ምንም ተጨማሪ ነገር ሳያስፈልገው ቆጣሪ ማግኘት የሚችል ሰው ደግሞ ይመጣል፡፡ ለዚህ መስጠት እየቻልን የደንበኛ ቅሬታ ይፈጥራል በሚል መቆም ስለሌለብን እናስተናግዳለን፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ግለሰቦች አሉ።
ከውጭ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚሠሩ፣ በውጭ ላኪነት የተሠማሩ፣ የውሃ ተቋማት እንዲሁም የጤና ተቋማት በአሠራሩ መሠረት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ሲስተም ላይ እናውቃቸዋለን። መቼ እንደተመዘገቡ፣መቼ እንደገባላቸው ለኦዲት በሚያመች ሁኔታ እያየንና እነዚህን ችግሮች በአሠራር እየገመገምን ብሎም እየፈታን እየሄድን ነው፡፡ ተመሳሳይ ምሰሶ ከፍሎ እየተጠባበቀ ለአንዱ ቅድሚያ የሚሰጥበት አሠራር ካለ እርምጃ እንወስዳለን፡፡
ሠራተኞች ይህንን አይነት ችግር ፈጠሩ ማለት የፈጠሩት ችግር የሚታይ ስለሆነ መደበቅ አይችሉም፡፡ የሚያየው ቴክኖሎጂ ነው። ስለዚህ ማንም ምንም አድርጎ መደበቅ አይችልም፡፡ ቢል አይወጣለትም፤ ቆጣሪ አይነበብም፤ ስለሆነም ይያዛል፡፡ ይህ ስህተት የመፈጠሩ አጋጣሚ ጠባብ ነው፡፡ ሌላው ሲሪ ፌዝ ቆጣሪ በቅርብ የጀመርነው አገልግሎት ነው፡፡ ሲንግል ፌዝ አመልካቾች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡
ስሪ ፌዝ አመልካች እያለ ማለት ነው፤ እና ትላልቅ ኬብሎች የሚጠብቁ ደንበኞች ይቆያሉ ወይም ገዝተው እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ ሌላው ከውጭ የሚገቡ ኬብሎች አሉ፤ ስለዚህ ማስተናገድ የምንችለውን ደንበኛ ይዘን ቁጭ ብለናል፤ ደንበኞች እኛ ዘንድ ከፍለዋል፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ይህ አይነቱ ጥያቄ ግን ከአንድ ወር ወይም ከ15 ቀን በኋላ ጥያቄ አይሆንም፡፡ ደንበኞች ደግሞ ገዝተው እንዲያቀርቡ ይደረጋሉ፤ ለዚህ ፍቃደኛ የሆነ ወይም የቻለ ሰው ያመጣና ይስተናገዳል፤ ያላመጣ ደግሞ የኛን አቅርቦት ይጠብቃል፡፡ እንዲያውም ትልቁ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ደንበኞች ገዝተው ከቀረቡ ቀድመው ለእኛ የከፈሉት ገንዘብ ይመለስላቸዋል፡፡
ከጋራ የመኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ አሁን የሚለጠፈው ቆጣሪ ሌላው መሠረተ ልማት ከኋላ ስላልተሟላ ቅድሚያ ያለውን ዕቃ ለመሥራት ነው እንጂ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ አሁን አንደኛው ተለጥፎ ሌላው የሚቀረው በተለያየ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የሚሠራው አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሳይሆን ኮንትራክተር ነው፡፡ ይህንን ሥራ አዳዲሶቹ ኮንዶሚኒየሞች ጋር ያለው ሁኔታ ይህ ነው፡፡
የጨረስናቸው ደግሞ አሉ፤ ቱሪስት፣ እህል ንግድ፣ ኢምፔሪያል፣ መሪ ሎቄ፣ ቦሌ አያት አንድ እና ሁለት፣ አስኮ እንዲሁም ባሻ ወልዴ ቆጣሪም ሆነ ትራንስፎርመርም ተከላ ሙሉ በሙሉ ጨርሰናል። አንዳንድ ቦታ ደግሞ የተወሰነ ቆጣሪ ተለጥፏል፤ ነገር ግን ትራንስፎርመሩን ስላላስቀመጥን ቅድሚያ አንሰጥም። ከዛ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በአንድ ወር ከአስራ አምስት ሺህ እስከ ሃያ ሺህ ደንበኛ ማገናኘት እንችላለን። ነገር ግን አንድ ቆጣሪ ለማገናኘት አስራ አራት አይነት ዕቃ ይፈልጋል፡፡ አንድ ዕቃ ከመሐል ሲጎድል ሥራው ይቆማል፡፡ እነዚህን እና መሰል ችግሮች ለመፍታት እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት ሰጥታችሁ የፍጆታ ገቢ በተገቢው መንገድ ትሰበስባላችሁ?
ዶክተር ገበየው፡- በድምሩ በአራቱም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻችን ስር የሚተዳደሩ አዲስ አበባ ላይ አንድ ሺህ የሚሆኑ የመንገድ መብራት ቆጣሪዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ቆጣሪዎች በወቅቱ ቢል አንብበን ለማንኛውም ደንበኛ እንደምናነበው ሂሳብ መሰብሰብ መቻል አለብን፡፡ ይህን ደግሞ የሚከፍለው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ነው፡፡ የመንገድ መብራት የመብራት ኃይል ንብረት አይደለም፤ የትኛውም ሀገር ላይ የሚያስተዳድረው የከተማ ማዘጋጃ ቤት ነው። ሌላው ዓለም ላይ እኛም ዘንድ የከተማ አስተዳደሩ የሚያስተዳድረው ክፍል አለ፡፡ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ያለውን እያስተዳደረ ያለው የከተማ አስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን ነው፡፡ ለዚህ የኃይል ፍጆታ በየወሩ እንደማንኛውም ደንበኛ መክፈል አለበት፡፡ እኛም አንብበን የቆጠረባቸውን መላክ አለብን፡፡
የመንገድ መብራት ላይ የተፈጠረው ችግር በ2012 ዓ.ም ERP SYSTEM ተግባራዊ ሲደረግ ዳታ ከአሮጌው ሲስተም ወደ አዲሱ ሲስተም መሸጋገር ነበረበት። በዚህ መሐል የተንጠባጠቡ ደንበኞች አሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የመንገድ መብራት አንዱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሳይከፍሉ ቆዩ፤ ይህ በመሆኑ ምክንያት ሂሳባቸው ተጠራቀመ፡፡ ያለባቸውን ሂሳብ ባሳወቅናቸው ጊዜ በጀት አጣን አሉ፡፡ 2015 ዓ.ም ላይ እንከፍላለን በሚል ጉዳዩ አደረ፡፡ አሁን 2015 ዓ.ም ላይ ደግሞ ሲመጡ በጀታችን አነሰ አሉ፡፡ እስካሁን ተንከባሎ የመጣ፤ ሰባ ሚሊዮን ብር ዕዳ አለባቸው፡፡ እነርሱ የነበራቸው ደግሞ ሃያ ሚሊዮን ብር ነው፡፡ እርሱን ጥቅምት ላይ ከፍለዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ምን ያህል ዕዳ አለባቸው?
ዶክተር ገበየው፡– አሁን አርባ ስምንት ሚሊዮን ብር ዕዳ አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናንተ ለምን መሰብሰብ አልቻላችሁም?
ዶክተር ገበየው፡– መጀመሪያ አካባቢ የዳታ ለውጥ ጉዳይ ተፈጠረ፤ እኛ 2014 ዓ.ም ላይ ደግሞ የዳታ migration ሥራ ጨርሰን ሂሳብ ስናሳውቃቸው በዚህ ልክ አልተዘጋጀንም አሉ፡፡ እናንተ ያመጣችሁት የተንከባለለ ሂሳብ ነውና በሚቀጥለው በጀት ዓመት እንክፈል በሚል የቆየ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ተቋማት የመብራት ፍጆታ ክፍያ በወቅቱ አይከፍሉም፤ እናንተም በተገቢው መልኩ አትሰበስቡም፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ዶክተር ገበየው፡- ይህ እውነት አይደለም፤ እኛ እንዲያውም እየተቸገርን ያለነው በሀገር ውስጥ የመንግሥት ተቋማት ነው፡፡ ይህም የሚስተዋለው ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የጤና ተቋማት ላይ ነው፡፡ ደንበኛ ባይከፍል እንቆርጣለን፤ ቆርጠን በሕግ ከሰን ገንዘብ እናስከፍላለን፤በመንገድ መብራት ላይ ይህን ማድረግ አልቻልንም፡፡ የእኛም ጥፋት አለበት፤ አንዳንድ ተቋማት ደግሞ ጭራሽ ቢሯቸው አካባቢ አያስጠጉንም፡፡ በዚህ ችግር ያለባቸው ተቋማት አሉ፤ ይህ መስተካከል አለበት፤ በዚህ ሂደት መከላከያን ላመሰግን እወዳለሁ፤ አንዳንድ ተቋማት ተከታትለው እራሳቸው ይከፍላሉ፡፡ የተወሰኑት ላይ ደግሞ ችግር አለ እንጂ በውጭ ተቋማት ላይ ችግር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመብራት መቆራረጥ ዛሬም ችግር ሆኖ ዘልቋል፤ ከተለመደው ምላሽ ውጭ ዘላቂ መፍትሔ ምንድን ነው?
ዶክተር ገበየው፡– የተለመደ መልስ አንሰጥም፤ ለሕዝብ የኃይል መቆራረጡን ከመነሻው ለማስረዳት ያህል የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ደካማ ነበር፡፡ 1990ዎቹ ላይ የነበረን 400 ሜጋዋት ኃይል ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ሠርቷል፡፡ ከየትኛውም ሴክተር በበለጠ ሀብት የፈሰሰው ኤሌክትሪክ ላይ ነው፤ በዚህም አሁን አምስት ሺህ ሜጋዋት አለ፤ ዛሬ ከሁለት ዓመት በኋላ አስር ሺህ ሜጋዋት ይደርሳል፡፡ ከእኛ ተርፎ ለጎረቤት ሀገራት ሊሆን የሚችል ኃይል አለ፡፡
በዚያው ልክ በማከፋፈያ ከተሞች አካባቢ ያለው የማከፋፈያ ኔትዎርክ አልተሠራም፡፡ ምክንያቱም ቅድሚያ ለኃይል ግንባታ በመሰጠቱ ነው፡፡ ወደ ከተሞች አካባቢ ደግሞ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተጠናከረ ሁኔታ እየሠራን ነው። በአዲስ አበባ ሁለት ምዕራፍ ፕሮጀክት ተጠናቋል። በአጠቃላይ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ፣አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ እንዲሁም አስር ሽህ አምስት መቶ የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮች አሉ፡፡
እነዚህ ያረጁ ናቸው፤ ሌላ ነገር ብናወራ ጥቅም ስለሌለው ወይም ደግሞ ይህን ኔትዎርክ በሙሉ በአንድ እና በሁለት ዓመት በማሻሻል እናጠናቅቅ ቢባል የማይቻል ስለሆነ ከእውነት ውጭ እንሆናለን፡፡ ፋይናንስ ከማግኘት ጋር ሆነ መሬት ላይ ከመተግበር ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የሠራናቸው የማሻሻያ ሥራዎች ቢኖሩም፤ በባቡር ዝርጋታ ምክንያት ቀደም ሲል የተዘረጉ መስመሮች ተበጣጥሰዋልና ከአሮጌ ኔትወርክ የጀመርነው ለዚህ ነው፡፡
አንደኛ በኃይል ግንባታ ላይ ቅድሚያ ስለተሰጠ፣ ሁለተኛ ከ2003 እስካ 2011 ድረስ በሜቴክ ምክንያት የዕቃ አቅርቦት እጥረት በመኖሩ የነበረው ቃል በቃል ያረጀ ኔትወርክ ነው፡፡ 2011 ዓ.ም ላይ ይህን ሁለት ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ፣ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ እንዲሁም አስር ሽህ አምስት መቶ የማከፋፈያ ትራንፎርመሮችን ስትራቴጂ በመቅረፅ በአራት ምዕራፎች ተደራሽ ለማድረግ ፕሮጀክት ተነደፈ፡፡
የመጀመሪያው ፕሮጀክት የስምንቱ ከተሞች ፕሮጀክት ይባላል፡፡ 2011 ዓ.ም ላይ ተጀምሮ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀው በ2013 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የክልል ዋና ዋና ከተሞችንና አዲስ አበባን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ ሥራ የተሻሻሉት አዲስ አበባ ላይ 40 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ፣ 412 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፣ 82 የማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችና 15 switching station ናቸው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ በ2012 ዓ.ም ተጀምሮ 2014 ዓ.ም ላይ ተጠናቀቀ። በዚህ ደግሞ በዋናነት የተሰራው 725 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ ቮልቴጅ፣ 400 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፣ 400 አጋዥ የማከፋፈያ ትራንፎርመርና 73 switching station ነው፡፡
ሁለተኛው ፕሮጀክት የተሠራው በቻይና መንግሥት ድጋፍ ሲሆን፣ እሱም ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ወጪ ተደርጎ የተጀመረው ባለፈው በጀት ዓመት ነው፡፡ በዚህ የበጀት ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም በኮሮና እና በሌላም ምክንያት ሳይጠናቀቅ ቆይቷል። በዚህ ሥራ ደግሞ 733 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ፣ 400 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ ቮልቴጅ፣ 258 አጋዥ የማከፋፈያ ትራንፎርሜሮች፣ ሰብ እስቴሽኖችና የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ጨምሮ አሁን እየተሠራ ነው፡፡ ይህም በ2016 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡
የዚህ ስትራቴጂክ ዕቅድ አራተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ 600 ኪሎ ሜትር መካከለኛ ቮልቴጅ፣ ቀሪውን በሙሉ ማለት ነው፣ 2000 የማከፋፈያ ትራንፎርመሮች ያሉት በ2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡ የአማካሪ ቅጥርና የጫረታ ሂደት ተጀምሯል፡፡ እየተሠራ ያለው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ የመስመር ዝርጋታው በመሬት ስር ይካሄደል፤ የሚሠራው ኮንክሪት ምሰሶ ነው፡፡ የምንጠቀመው ሽፍን ሽቦ ነው፡፡ ይህ የኃይል መቆራረጡን ይቀርፋል፡፡ በዚህ በተዋቀረ ፌዝ አሮጌውን ኔትዎርክ ለመቀየር እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መብራት በአንድ አካባቢ መንገድ ከፍሎ ይጠፋል፤ ይህ ለምንድነው የሚፈጠረው?
ዶክተር ገበየው፡- ይህ የሚሆነው አንደኛው ትራንስፎርመር አገልግሎት የሚሰጠው ለተወሰነ ደንበኛ ነው፡፡ እሱ ላይ ችግር ሲፈጠር ሰፈሩ መብራት ያጣል። እስኪጠገን ድረስ በዛ መስመር ብልሽት ካለ መስመሩ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ ሌላው ግን ያገኛል፡፡ እና በዚህ ምክንያት በኔትወርኩ ነባራዊ ሁኔታ የሚፈጠር ነው። በአካል ሄደን አይተናል፡፡ ማሻሻያ ያደረግንባቸው መስመሮች በሰሞኑ የአየር ሁኔታ እንኳ አልተጎዱም፤ እና በዚህ ስትራክቸርድ በሆነ ፌዝ እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ሥንሰራ ችግሮች ያገጥሙናል፡፡ የከተማው ማስተር ፕላን አሁን እየተተገበረ ነው፤ እነዚህን ኔትዎርኮች አንሱ የሚል ይመጣል፤ እርሱን እናነሳለን፤ ይህ ችግር ነው። በመሠረተ ልማት የሚቆራረጡ ደግሞ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እንጂ ብዙ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ይሁንና በብዙ ምክንያት በአንድ ምሽት ችግሩን መቅረፍ ደግሞ አንችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ዘላቂ መፍትሔው ምንድነው?
ዶክተር ገበየው፡– ዘላቂ መፍትሔው 2017 ዓ.ም ላይ በሚጠናቀቀው ፕሮጀክት የሚገኝ ነው፡፡ ሰሞኑን የተከሰተው የኃይል መቆራረጥ ደግሞ ባልተጠበቀ የአየር ሁኔታ የመጣ ነው፡፡ ሁለተኛውና ትልቁ ችግር አራቱንም ምዕራፍ ሥንሰራ አሮጌውን መስመር በአንድ መንገድ ላይ ትተን በሌላው አይደለም የምንሠራው፡፡ ኮሪደር የለም፤ ከተማ ውስጥ እያጠፋን ነው ሌላውን የምንሠራው በዚህ ምክንያት ኮንክሪት ተክለን እስኪደርቅ እንጠብቃለን፣ እንሱሌተር እናሥራለን ያኔም ይጠፋል እና ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈፀም ሲባል የሚጠፋው ኤሌክትሪክ ነው የሚበዛው በእቅድ ላይ የተመሠረተ የኃይል መቆራረጥ ነው ያለው፤ ይሄ ሲኖር ደግሞ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ለኅብረተሰቡ እናሳውቃለን፤ ትልቁ ለኃይል መቆራረጡ ምክንያት በእራሳችን የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በብዛት ከኅብረተሰቡ የሚነሳው ጥያቄ ከሌሎች የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመናበብ ያለመሥራት ችግር ነው፤ አንዱ የሠራውን ሌላው ያፈርሳል በሚል እርስ በእርስ መወቃቀስም አለ፤ ከዚህ አኳያ የቅንጅት አሠራራችሁ ምን ይመስላል?
ዶክተር ገበየው፡- አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ማስተር ፕላን አለ፤ በጣም አሮጌ ሰፈሮች እንደገና ፈርሰው የሚሠሩ አሉ፡፡ መሠረተ ልማት ገና እየተስፋፋ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ደግሞ ቴሌ፤ ውሃና መብራት ይኖራል፡፡ ይህ ካልተቀናጀ ሊመራ አይችልም፡፡ ከአዲሱ የመንግሥት ሪፎርም በፊት ከ2006 እና 2007 ዓ.ም ጀምሮ አዳዲስ በሚሠሩ መንገዶች ላይ በሙሉ ነበር። አሁን ቅንጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ የመሠረተ ልማት ቅንጅት የሚባል ተቋም አለ፤ በዚህ መልኩ በተሠራው ሥራ ለውጥ ታይቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግሩ ግን አሁንም እንዳለ ነው፤ አልተቀረፈም፤ ለምን?
ዶክተር ገበየው፡- አዎ! በዋናነት ያለው ሁለት ችግር ነው፡፡ የቅንጅት ችግር አይደለም፤ ለምሳሌ ለቡ ማሳለጫ አሁን ደግሞ ኢምፔሪያል ሲሠራ የእኛ መስመር ተቆርጦ ተነስቷል፡፡ ይህ ደግሞ ብንቀናጅም ሆነ ባንቀናጅም የግድ መሆን ያለበት ነው፡፡ እኛ ያንን መስመር የዘረጋነው 2000 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ነው፤ ከገርጂ ማከፋፈያ ወደ ቦሌ ያለው ማሳለጫ ይመጣል የሚል ነገር አልነበረም፡፡ አሁን መጣ፤ ሽቦውን ወይም መስመሩን ማንሳት ግዴታ ነው፡፡ ማንሳት ደግሞ አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም አንደኛው የቦታ ነው። ኮርደሩ እዛው ላይ ነው፡፡
መንገዱን ሲጨርሱ ያንን ሠርተውልን ያልፋሉ፡፡ እዛ ውስጥ መልሰን በሌላ ሽቦ እንቀብራለን፡፡ ሁለተኛው የጊዜ ችግር ነው፤ እነዚህ ሽቦዎች የተሠሩት በሀገር ውስጥ አይደለም፤ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ቅንጅት በመጥፋቱ የመጣ አይደለም፡፡ ይህም በዚህ ተቋም ገፅታ ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡
ሌላው በዚህ የቅንጅት አሠራር ውስጥ ያልተቀረፉ ተቋማት አሉ፤ ሁሉን በዚህ ውስጥ ማካተት አይቻልም። መሠረታዊ የሆኑ የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ናቸው ያሉት፡፡ በዚህ ያልተቀረፉ አጥርና መሰል ሥራዎችን በሚሠሩ ተቋማት ደግሞ የሚፈጠሩ ችግሮች እና ጉድለቶች አሉ፡፡ በመሠረታዊነት መሻሻል የሚገባው ነገር ቢኖረውም ችግሩ እየተፈጠረ ያለው የግድ በሆኑ ጉዳዮች ነው፡፡
አሁን በጣም ፈታኝ የሆነብን ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ መስመሮችን እናነሳለን፤ ለአዲስ አበባ መንገዶች ፕሮጀክት ሥራና በመሬት ውስጥ ሲሆን ደግሞ ከባድ ነው፡፡ በጣም ከባድ ፈተና የሆነብን ይህንን ማንሳት ነው፡፡ ስለዚህ በዕቅድ ወቅት ለዚህ ትልቅ ትኩረት ቢሰጥ የተሻለ ነው፡፡ በዕቅድ ደረጃ የማቀድ አይነት ጉድለቶች ግን አሉ ብለን ለመሥራት ግን አቅም እያጠረን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ የሠራተኛ ሥነ ምግባር ምን ይመስላል?
ዶክተር ገበየው፡- እዚህ መሥሪያ ቤት የገባሁት 1995 ዓ.ም ነው፡፡ በሥነ ምግባር ጥሩ የሆነ ተቋም ነው የነበረው፤ ያኔ የነበረው እሴት እኔ ዘንድ ቀርቷል። እኔ የዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅም ነበርኩ፡፡ 1998 ዓ.ም አካባቢ የሥራ የተቋም ፍቅር እንጂ የሥነ ምግባር ችግር አልነበረም፡፡ በመሠረታዊነት ችግሮች መፈጠር የጀመረው በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት 2002 እና 2003 ዓ.ም ነው፤ ከውጭ የሚገባውን ምርት እንዲተካ ታስቦ ሜቴክ ተቋቋመ፡፡ ግን በወቅቱ በማኔጅመንት ችግርና በተለያዩ ምክንያቶች እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ዕቃ በተገቢው አልቀረበልንም፡፡
አሁን ይህ እጥረት የሥነ ምግባር ችግር ፈጥሯል የሚል ግምገማ አለን። የሚመጣው የተወሰነ እቃ ነው፡፡ እዛ ላይ ብዙ የመሽቀዳደም ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ አንድ ምክንያት ይሆናል፤ አሁን ይህንን በመሠረታዊነት የምንፈታበት ሥርዓት ተዘርግቷል። ደንበኛ እና ሠራተኛ እንዳይገናኝ ደግሞ እየሠራን ነው፡፡ በሲስተም ደንበኛ ቤቱ ቁጭ ብሎ አገልግሎት የሚያገኝበት ሁኔታ የሚፈጥር ሥርዓት እየተዘረጋ ነው። ይህ ሁሉ በመሠረታዊነት ችግሩን ለመፍታት፡፡
ሌላው በአራቱ ቅርንጫፎች ስር በሚገኙ በሠላሳ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የሥነ ምግባር ክበባት ተቋቁመዋል። የሚመሩት ጥሩ ሥነ ምግባር ባላቸው ሠራተኞች ነው። በዚህ ሂደት በተሠራው ሥራ ለውጦች አሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ግን ችግሩ አልተቀረፈም፡፡ ይሄንን ሁሉ አልፈው በሚያጠፉት ላይ ምሕረት የሌለው የዲሲፕሊን ቅጣት ይወሰዳል፡፡ በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት አንድ መቶ ዘጠኝ ሠራተኞችና አመራሮች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ተወስዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 15 ሠራተኞችና ኃላፊዎች ላይ ስንብት፣ 38 ሠራተኞች ላይ እስከ አራት ወር የደመወዝ ቅጣት፣ 16 ኃላፊዎች ላይ ደግሞ ከኃላፊነት መነሳት፣ 14ቱ ላይ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 26 ሠራተኞች ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተቋሙን ወደ ዘመናዊ ተቋም ለመለወጥ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ላነሳናቸው ጥያቄዎች ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ገበየው ሊካሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2015