የፋሽን መሰረታዊውና ዋናው ጉዳይ ዲዛይኑ ነው። ዲዛይን በፋሽን ሙያ ውስጥ ትልቁን ስፋራ ይይዛል። አንድ ቤት ለመሥራት ቅድሚያ ዲዛይን እንደሚያስፈልገው ሁሉ በፋሽንም ሙያ ተመሳሳይ ነው። ዲዛይኑ የሚዘጋጀው ደግሞ በባለሙያው ነው። በዛሬው የፋሽን አምዳችንም ስለ ዲዛይን ሙያ ምንነትና በፋሽን ውስጥ ስላለው ሚና ለመቃኘት ወደናል።
ዲዛይነር እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ ለረጅም ዓመታት በዲዛይነርነት ሙያ ላይ ሰርተዋል። እርሳቸው የዲዛይኒንግ ሙያ ከሀሳብ የሚመነጭ የፈጠራ ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ። የዲዛይኒንግ ሙያ በአእምሮ ያለ ነገር በንድፍ አስቀምጦ ወደ ተግባር መለወጥ መሆኑንም ያስረዳሉ። ሙያው ምንም ነገር ከሌላ ሳይቀዳ በሀሳብ ያለን ፈጠራ በወረቀት በማስፈር፣ በምን አይነት ጨርቅ ወይም እቃ ይሰራል? እንዴት ተግባር ላይ ቢቀመጥ የሚገፈለገውን ቅርፅና ውበት ሊይዝ ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በተግባር ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ያብራራሉ።
“ዲዛይነር ያየውን ነገር ሁሉ ወደ ልብስ መቀየር ይችላል። ዲዛይነርነት ሙያ በሀሳብ ያለን ወደ ተግባር መለወጥ ቢሆንም፣ በተፈጥሮ የሚሰጠው ተሰጥኦ እንዳለ ሆኖ በትምህርትም ሊዳብር ይችላል” የሚሉት ባለሙያዋ፤ ከዚህ መነሻ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ግንባታ ከሚፈለጉ አውታር ዘርፎች መካከል አንዱ የፋሽን ዲዛይን መሆኑን ይናገራሉ።
ሙያው በአገር ደረጃ ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ይገልፃሉ። የዲዛይነርነት ሙያ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የሚሰጠው ቦታ “ልብስን መስፋት” በሚለው እይታ ብቻ እንደሚታሰብ አስረድተው፤ ተሰጥኦን የሚጠይቅ የፈጠራ ሙያ መሆኑ ይዘነጋ እንደነበር ይናገራሉ።
“የዲዛይኒንግ ሙያ በኢትዮጵያ አሁን ጅምር የሚባል ነው የሚሉት ዲዛይነር እጅጋየሁ፤ ቀደም ካሉት ዓመታት አንጻር ሲታይ በሀሳብ ደረጃ የተሻለ ግንዛቤ አግኝቶ በህብተረሰቡ ዘንድ እየታወቀ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ። አሁን ያለበት ደረጃ ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም ገና ብዙ እንደሚቀረውና ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን እንደሚጠይቅ ያመለክታሉ።
ቀደም ሲል በሙያ በትምህርትና በስልጠና የተደገፈ አልነበረም የሚሉት ዲዛይነሯ፤ ከአስር ዓመት ወዲህ ግን የፋሽን ዲዛይኖች እየሰፉ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችም የፋሽን የትምህርት ክፍሎችን እያቋቋሙ እንደሚገኙ ይገልጻሉ። በሙያ በትምህርትና በስልጠና ቢደገፍ አምራች ኃይል ማፍራት እንደሚቻልም ይጠቁማሉ።
ዛሬ የኒውዮርክን ኢኮኖሚ አብዛኛውን ድርሻ የሚያንቀሳቀሰው ሞተር የፋሽን ኢንዱስትሪው መሆኑን በምሳሌነት ያነሳሉ። በኢትዮጵያም በትኩረት ቢሰራበት እንደ ቡና፣ ወርቅና መሰል ወደ ውጪ የሚላኩ ገቢ አምጪ ምርቶች እንደሚሆን እምነታቸውን ይገልፃሉ።
ልብስና ፋሽንን መከተል የማይቀር መሠረታዊ ፍላጎት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራበት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የአገር ገጽታን መገንባት እንደሚችልም ዲዛይነሯ ይጠቁማሉ። የፋሽን ዲዛይን አብዛኛው የሚሰራው በአገር ምርት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሆኑን አንስተው፤ ቱባ ባህሉን ከማስተዋወቅ አንጸር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
‹‹ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ባካበትኩት ልምድ የዓለም ሰዎች የኛን የፋሽን ዲዛይን ሥራ በእጅጉ ያደንቁታል›› የሚሉት ዲዛይነር እጅጋየሁ፤ የኢትዮጵያ ልብሶች ምንም እንኳን በፋብሪካ የሚሰሩ ቢሆኑም በተፈጥሮ ከሚገኙ ነገሮች መሥራታቸው ከጤና አኳያ እንዲመረጡ ያደርጋቸዋል ነው የሚሉት።
ልብሳችን መገለጫችን ነው የሚሉት ዲዛይነሯ፤ የፋሽን ዲዛይኑ በሁሉም ረገድ ድጋፍ ቢደረግለት ያለን ተሰጥኦና ሀብት አውጥተን የምናሳይበት ነው ይላሉ። ይህም ሥራ ላይ ያልዋሉ የፈጠራ ሥራዎችን ሥራ ላይ ውለው ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ዲዛይነር እጅጋየሁ እንደሚሉት፤ አሁን የፋሽን ዲዛይን ማህበር የተቋቋመ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል በአንዳንድ ቦታዎች መሳተፍ እየተቻለ ነው። ኢንተርፕራይዞች ማህበሩን ለመደገፍ ፍቃደኞች ናቸው። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም ግን እስከምን ድረስ የሚለው መታሰብ ይኖርበታል።
ዲዛይነሯ ማምረቻ ቦታዎች መስጠት፣ መሳሪያዎች ከልማት ባንክ በሚደረግ ድጋፍ በትንሽ ክፍያ ማግኘት እየተቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሚሰራበት ግብአት እንደሚያስፈልግ አልሸሸጉም። ድጋፍ መደረጉ ካልቀረ ምርቱን ማንኛውም ሰው በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ መጠቀም የሚችልበት መሆን እንዳለበት ነው የሚናገሩት።
“አሁን ላይ ድርና ማግ የሚያመርቱ ፋብሪካዎቻችን እየሰሩ አይደለም። ድርና ማግ በውድ ዋጋ ከውጭ ነው የሚመጣው” የሚሉት ዲዛይነር እጅጋየሁ፤ በዚህ አይነት ሁኔታ ተወዳድሮ ማሸነፍ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ያስገነዝባሉ። ዲዛይነሯ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተገኝተው ልምድ ቀስመዋል። ‹‹ሌላው አገር ላይ በእጅ የሚሰሩ ከሽመና ጀምሮ ያሉ እቃዎች በጣም ርካሽ በመሆናቸው ልብስ በጥራት ተመርቶ ህብረተሰቡ ለብሶት አምሮበት ይሄዳል። በኢትዮጵያ ሁሉ ነገር እያለን ለምን የሚል ቁጭት አሳድሮብኛል›› ይላሉ።
በተለይ በእደ-ጥበብ ውጤቶች ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝቡት ዲዛይነር እጅጋየሁ፤ የእደ-ጥበብ ውጤቶች ስንል በቆዳ፣ በሽመና፣ በቅርጻቅርጽ፣ በእጅ የሚሰሩ፣ ቤት ውስጥ ከሚሰሩ ሙያዎች ሁሉንም እንደሚያካትት ያብራራሉ። እነዚህን ሙያዎች ማሳደግ እንደሚያስፈልግ እንደ አንድ ባለሙያ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
ሙያው ውስጣዊ ተሰጦኦ ያስፈልገዋል የሚሉት ዲዛይነሯ፣ ከትምህርት ተቋማት የሚወጡ ልጆች የተሰጣቸው ትምህርት በቂ እንዳልሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየታየ መሆኑን ነው የሚመሰክሩት። አንድን ልብስ ዲዛይን አድርጎ ለማውጣት ብዙ ሂደቶችን ማለፍ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ አሁን ያሉ የሙያው ተማሪዎች ግን ለሙያው ውስጣዊ ፍቅር የሌላቸው ቶሎ የሚሰለቹ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ያላቸው ስታንዳርድ ግን በቂ አለመሆኑንም ይገልጻሉ። ስለሆነም ከዚህ የሚወጡ ተማሪዎች ውጤታማ ሲሆኑ እንደማይታዩም ጠቅሰው፣ ለዚህም ትምህርት ቤቶች ስርአተ ትምህርቱን መፈተሽ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።
ሙያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ እንዲሆን ካስፈለገም ዲዛይን ሙያ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም የሚማረው ሳይሆን ልዩ ተሰጦ ያላቸውን ተማሪዎች በመምረጥ በኩል ውጤታማ መሥራትን ይጠይቃል ይላሉ። ውጤት ብቻ ሳይሆን ክህሎት ላላቸው ቅድሚያ መስጠት ቢቻል ጥሩ እንደሆነ የጠቆሙት ዲዛይነሯ፤ ሙያው ያላቸው ባለሙያዎች ተምረው በዘርፉ ከወጡ፣ ሥራው ከተሰራ ሙያውን የማናሳድግበት ምንም ምክንያት የለም ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም