የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሁለቱን ሀገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነትታቸውን ከማጠናከር ባለፈ ስለ ኮርያ ስርጥ ጉዳይ ለመምከር በትናንትናው ዕለት በሩስያ ምሥራቃዊት ከተማ ቭላዲቮስቶክ አቅራቢያ በሚገኝ ረስኪ በተባለ ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ።
ከወራት በፊት በቬትናም ዋና ከተማ ሀኖይ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር ያደረጉት ውይይት መክሸፉን ተከትሎ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ወደ ሩሲያ ያቀኑት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም “ጉብኝቴ ውጤታማ እና ጠቃሚም ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ለሩስያ የቴሌቪዥን ጣቢያ የተናገሩ ሲሆን፤ የሰሜን ኮርያና የሩስያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ስለ ኮርያ ሰርጥ ጉዳይ ለመወያየት እቅድ እንደያዙም ኪም ተናግረዋል።
ረጅም የወዳጅነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ሀገሮች መካከል አሁን ላይ ይህን ውይይት ማድረጋቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማዳበር፣ የተረጋጋ እና ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር በጣም ጠቃሚ መሆኑን ኪም አክለው ተናግረዋል። የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገሮች የቀድመ የወዳጅነት ታሪክ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው በኮሪያ ስርጥ ያለውን አለመረጋጋት ለመፍታት ማገዝ እንደሚፈልጉ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች በሩሲያ የሚደርጉት ውይይት በሰሜንና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለውን አለመግባባት ታሪካዊ መንስኤውንና ችግሩን በመረዳት በቀጠናው ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ነው ብለዋል። በመሆኑም በቀጠናው ያሉት ችግሮችንና አዎንታዊ ጉዳዮችን በማወቅ አሁን ላይ በቀጠናው የተጀመረውን የሰላም አየርእስከ ወዲያኛው እንዲነፍስ ሩሲያ የበኩሏን ድጋፍ እንድታደርግ የሚያግዝ መሆኑን ፑቲን ተናግረዋል።
ነገርግን የሩስያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ የኮርያ ስርጥ የኒውክሌር ጉዳይን በተመለከተ አሁን ላይ ውጤታማ ሊሆን የሚችል ዓለም አቀፍ ጥረት እምብዛም አለመኖሩን ተናግረዋል። ለአብነትም እአአ በ2003 ተጀምሮ የነበረው የሰሜን ኮርያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሩስያና አሜሪካ መካከል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶች አመርቂ ውጤት እንዳላመጡ ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። አሁን ላይ በሁለቱ ኮሪያ መካከል ያለውን ነፃ የኒኩሊየር የጦር ሰፈር ለመፍጠር የሚያስችል ጥረት ዓለም ላይ እየተደረገ አይደለም ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ይህ ሁኔታ ባለበት ሁለቱ መሪዎች መገናኘታቸው ባሉት ችግሮች ላይ በመወያየት በቀጠናው ያለውን ችግር ለመቅረፍና ከኒኩሊየር የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ በር ከፋች ግንኙነት ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከወራት በፊት በቬትናም ዋና ከተማ ሀኖይ ያደረጉት ውይይት ፍሬ ስላላፈራ ሰሜን ኮርያ እንደ ሩስያ ያሉ ወዳጆች ከጎኗ ማሰለፍ ግድ ይላታል ብለዋል።
ስለዚህ የሰሜን ኮሪያው መሪ ወደ ሩሲያ ማቅናታቸው ሰሜን ኮርያ በምጣኔ ሀብት ረገድም ብቸኛ አጋሯ አሜሪካ እንዳልሆነች ለማሳየት ስለምትፈልግ ነው ብለዋል። በሁለቱ መሪዎች ውይይትም የሰሜን ኮሪያው መሪ ሀገራቸው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ የተጣለባት ማእቀብ እንዲቀነስላቸው ድጋፍ ሊጠይቁ ይችላሉ ብለዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ከኪም ጋር ለመገናኘት በጉጉት ሲጠብቁ የነበር መሆኑን ቢቢሲ በድረገጹ ያስነበበ ሲሆን፤ ሩስያ በኮርያ ስርጥ ጉዳይ ቀንደኛ ተዋናይ መሆን ትፈልጋለችም ብሏል። እንዲሁም እንደ አሜሪካና ቻይና ሁሉ ሩስያም የሰሜን ኮርያ የኒውክሌር ክምችት እንቅልፍ ከሚነሳት ሀገሮች መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2011
ሶሎሞን በየነ