በልደት ስሙ ጁሊያን ፖል ሆውኪንስ በመባል የሚታወቀው አውስትራሊያዊው የኮምፒዩተር ፕሮግራመር፣ ጋዜጠኛና የታዋቂው የመረጃ ግልፅነት አቀንቃኝ ድረ ገጽ መስራች “ጁሊያን አሳንጄ” በሚለው ስሙ ነው ዓለም ሁሉ የሚያውቀው። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 ዊኪሊክስን ከመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በዋነኝነት ራሷን እንደ ዴሞክራሲ ዘብ የምትቆጥረውን ኃያሏን አሜሪካን ጨምሮ የመንግሥታትንና ፖለቲከኞቻቸውን ገመና የሚያጋልጡ ጥብቅ ምስጢራዊ መረጃዎችን በማውጣት ይታወቃል።
የ47 ዓመቱ አውስትራሊያዊ ባለፉት ከአስር በላይ ዓመታት አቻ እስኪታጣለት ድረስ ዝናው በዓለም ላይ ናኝቶ ቆይቷል። ደጋፊዎቹ “ዓለም አቀፍ የመረጃ ጀግና” በሚል ያሞካሹታል። በተቃራኒው ጎራ ያሉት በተለይም አሜሪካና አጋሮቿ “ብሔራዊ ጠላታችን” ነው ይሉታል። ከዚህም አልፈው ካገኙት ሊያስሩትና ሊቀጡት ይፈልጋሉ። በዚህም ሰውየው በአወዛጋቢነትም ዝናን አትርፏል።
ባለፈው ሚያዝያ ሁለት ቀን 2011 ዓ.ም ለጁሊያን አሳንጄ ወዳጆች “መርዶ” ለጠላቶቹ ደግሞ “የምስራች” ዜና ተምቷል። ምክንያቱም አሳንጄ በጥገኝነት ከሚኖርበት በለንደን የኤኳዶር ኤምባሲ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሏል። ሆኖም አወዛጋቢው ሰው አሁንም በአወዛጋቢነቱ ቀጥሏል።
ለመሆኑ ጁሊያን አሳንጄ ማን ነው?፣ “አወዛጋቢው ሰው” ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? እንዴትስ በዚህ ደረጃ የዓለም መነጋገሪያ ለመሆን በቃ? በእርግጥ አሳንጄ “ጠላት” ወይስ “ዓለም አቀፍ የመረጃ ጀግና?” የዛሬው የዓለም አቀፍ ጉዳያችን እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በጥልቀት የሚዳስስ ይሆናል።
የግል ሕይወት
ጁሊያን አሳንጄ የተወለደው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሐምሌ ሦስት ቀን 1971 ታውንስቪል ከተማ ክዊንስላንድ ግዛት አውስትራሊያ ውስጥ ነው። እናቱ ክርስቲያን አን ሆውኪንስ አርቲስት አባቱ ደግሞ ፀረ ጦርነት አክቲቪስትና ግንበኛ ነው። ጁሊያን ተረግዞ እያለ እናትና አባቱ በፍቺ ተለያዩ።
አንድ ዓመት ሲሞላው እናቱ የፊልም ተዋናዩን ሪቻርድ ብሬት አሳንጄን አገባች። የእንጀራ አባቱን እንደ አባት እያዬ ያደገው ሕፃኑ ጁሊያን ሆውኪንስም መጠሪያ ስሙም ጁሊያን አሳንጄ እንዲሆን በመምረጡ ሲወለድ የተሰየመለት ጁሊያን ሆውኪንስ ቀርቶ ጁሊያን አሳንጄ በሚለው ጸና።
ሆኖም ስምንት ዓመት ሲሞላው እናቱ ከብሬት አሳንጄ ጋር ተፋታች። ከዚያም እናቱ ሌላ ባል አግብታ በሃሚልተን ቤተሰብ ውስጥ መኖር የጀመረች ሲሆን ጁሊያን እንደ ዘላን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ የሕፃንነት
ዘመኑን ለማሳለፍ ተገድዷል። በዚህም ጁሊያን አስራ ስድስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ የአውስትራሊያ ከተሞች እየተዘዋወረ ኖሯል።
ከዚህ በኋላ በሜልቦርን ከእናቱ ጋር መኖር የጀመረው ጁሊያን ጉልማንጋርና ኒው ሳውዝ ዌልስን ጨምሮ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን ተከታትሏል። ሁለተኛና ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በሴንትራል ክዊንስና በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ ፕሮግራሚንግ፣ ሂሳብና ፊዚክስ ቢያጠናም ዲግሪውን መጨረስ አልቻለም።
ጁሊያን አሳንጄ በወጣትነት ዘመኑ ካገባት ቴሬሳ የተባለች የልጅነት ፍቅረኛው ዳንኤል አሳንጄ የተባለ ልጅ የወለደ ሲሆን ዳንኤል በአሁኑ ሰዓት የሶፍትዌር ኢንጅነር ነው። ጁሊያን አሳንጄ የዳንኤልን እናት ከፈታ በኋላም ፈረንሳይ ውስጥ ሁለተኛ ልጅ እንዳለውና በሚሰራው ሥራ ምክንያት ልጁና ሚስቱ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው መሆኑን በአንድ ወቅት ለፕሬዚዳንት ፍራንሷ ሆላንድ በጻፈው ደብዳቤ መግለጹን የዊኪ ፒዲያ መረጃ ያመለክታል።
የኮምፒዩተር ጠለፋ ሀሁ
አሳንጄ የኮምፒዩተር ጠለፋ ሥራን “ሀ” ብሎ የጀመረው “ሜንዳክስ” በሚል ስም በፈረንጆቹ 1987 ነው። በወቅቱ እርሱና “ትራክስ” እና “ፕራይም ሰስፔክት” በሚል መጠሪያ በተመሳሳይ ሥራ ከተሰማሩ ሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን “ኢንተርናሽናል ሳብቨርሲቭስ” የሚል መጠሪያ ያለው የመረጃ ጠላፊዎች ቡድን አቋቁሞ ነበር። ጁሊያን አሳንጄ በወጣትነቱ በሴንትራል ክዊንስና በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲዎች የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ መማሩ ልቡ ለተሸነፈለት የመረጃ ጠለፋ ሥራ ሳያግዘው አልቀረም።
አሳንጄ “ኢንተርናሽናል ሳብቨርሲቭስ” የመረጃ ጠላፊዎች ቡድን ውስጥ በነበረበት ወቅት በ1989 በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ላይ ደርሶ ለነበረው የመረጃ ጥቃት እጁ አለበት በሚል ተጠርጥሮ የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ የሰጠው ማረጋገጫ የለም።
በመስከረም 1991 ደግሞ አሳንጄ ሜልቦርን የሚገኘውን ግዙፉን የካናዳ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ የኖርቴልን ዋና የመረጃ ክፍል ጠልፏል በሚል በአውስትራሊያ ፌዴራል ፖሊስ ስልኩ ተጠልፎ ለሦስት ዓመታት ሲመረመር ከቆየ በኋላ በ1994 በሰላሳ አንድ የመረጃ ጠለፋና ተያያዥ ወንጀሎች ክስ መስርቶበታል።
እስከ ታኅሣሥ 1996 ለሁለት ዓመታት ምርመራ ሲደርግበት ከቆየ በኋላ ከሰላሳ አንዱ ክስ በሃያ አምስቱ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል። በመጨረሻም የመረጃ ጠለፋ ወንጀሉ የተፈጸመው ከውጭ ጠላት ጋር በቅጥረኝነት በመተባበርና በሀገር ላይ ክህደት ለመፈጸም ታስቦ የተፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ባለመገኘቱና በልጅነት ዘመኑ ያሳለፈው ውጣ ውረድ በአሳንጄ ሕይወት ላይ የፈጠረው መልካም ያልሆነ ተፅዕኖ ግምት ውስጥ ገብቶ ቅጣቱ ቀልሎለት 2ሺ 100 ዶላር ካሳ ከፍሎ ከእስር እንዲለቀቅ ተደርጓል።
አሳንጄ፣ ዊኪሊክስና አሜሪካ
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2006 ጁሊያን አሳንጄ ትልልቅ ምስጢራዊ መረጃዎች ባለቤታቸው ሊቆጣጠራቸው በማይችልበት መንገድ የመረጃ መረብ ላይ ለመልቀቅ የሚያስችል ዊኪሊክስ የተባለ ድረገጽ መሠረተ። ከዚያም በዓለም ዙሪያ የሚፈጸሙ ትልልቅ መንግሥታዊ ወንጀሎችንና ሙስናዎችን እያጋለጠ የባለሥልጣኖችንና የፖለቲከኞችን ድብቅ ሴራና ገመና ይፋ ማውጣቱን ተያያዘው።
ዊኪሊክስ ባለፉት ከአስር በላይ ዓመታት በመንግሥታት፣ በፖለቲከኞችና በንግድ ኮርፖሬሽኖች አማካኝነት በዓለም ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ሸፍጦችንና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን የሚያሳዩ አስር ሚሊዮን ጥብቅ ምስጢራዊ መረጃዎችን አውጥቷል። ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው መረጃ ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ከመላው ዓለም በስደት ሄደው በውስጧ ለሚኖሩ የሌላ አገር ዜጎች ሁሉ በምትሰጠው ነፃነትና የኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት “የተስፋዋ ምድርና የዴሞክራሲ ተምሳሌት” እየተባለች የምትሞካሸውን ልዕለ ኃያሏን አገር አሜሪካን የሚመለከት ነው።
አሳንጄ በከፍተኛ ጥበቃ በጥብቅ ምስጢር ይዛው የምትኖረውን ከባባድ አስደንጋጭ ገመና በማጋለጥ የአሜሪካን ቅድስና አፈር ድሜ ማብላት የጀመረው ዊኪሊክስ ከተመሰረተ ገና በዓመቱ ነው። በ2007 በጓንታናሞ እስር ቤት የአሜሪካ ፖሊስ በታራሚዎች ላይ የሚፈፅመውን ዘግናኝ ድርጊት አስመልክቶ ዊኪሊክስ ያጋለጠው መረጃ መላውን ዓለም አነጋገረ። ከሦስት ዓመታት በኋላ በ2010 ደግሞ ሌላ ዓለምን ጉድ ያሰኘ አሜሪካን የተመለከተ መረጃ ወጣ።
ይህም በኢራቅ ጦርነት ወቅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 የአሜሪካ ጦር በባግዳድ ጎዳና በሁለት ጋዜጠኞችና በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ በሄሊኮፕተር የፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚያሳይ ነበር። የአሜሪካ ጦር የፈጸመውን ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት በቪዲዮ ሲመለከት ዓለም ሁሉ አዘነ፤ አሜሪካም አርቃ ቀብራው የነበረችው ገመናዋ ገሃድ ሲወጣ ሃፍረተ ሥራዋ ተገለጠ፤ የስመ መልካሟ አገር ሌላኛው ማንነት ተገልጾ ታዬ።
በዚህ ብቻ አላበቃም። በኢራቅ ጦርነት ወቅት የአሜሪካ መንግሥት የፈጸመውን ወንጀል የሚያሳዩ አራት መቶ ሺ፣ በአፍጋኒስታኑ ጦርነት የተፈጸመውን ወንጀል የሚመለከቱ ደግሞ ዘጠኝ መቶ ሺ ጥብቅ የአሜሪካ መንግሥት ወታደራዊ መረጃዎችን በጁሊያን አሳንጄ ፊታውራሪነት የሚመራው የዊኪሊክስ ድረ ገጽ አከታትሎ አወጣ።
ከዚህም በአሻገር አሜሪካ በደህንነት መስሪያ ቤቷ አማካኝነት ሁሉንም የዓለም አገራት እንደምትሰልል የሚያሳዩ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ጥብቅ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ምስጢራዊ መረጃዎችን ይፋ በማውጣት የአሜሪካን መንግሥት እርቃኑን አስቀረው። እናም አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅሜን የሚመለከቱ ውድ መረጃዎቼ በጠላቶቼ እንዲታወቁ አድርጓል በሚል የመረጃ ነፃነት ታጋዩን ጁሊያን አሳንጄን በይፋ በጠላትነት ፈርጃ ታሳድደው ጀመር።
በ“ጠላትነት” ወይስ በ“አርበኝነት”
ባለነጭ ጸጉሩ አውስትራሊያዊ ጁሊያን አሳንጄ ድረ ገጹን ዊኪሊክስ በ2006 ከመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከቻይና እስከ አፍሪካ መካከለኛው ምሥራቅ በሁሉም የዓለም ሀገራት የመንግሥታትንና የፖለቲከኞችን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ሴራ በማጋለጥ ይታወቃል። በዚህም በደጋፊዎቹ ዘንድ በተለይም የመረጃ ነፃነት እንዲኖር ባደረገው የላቀ አስተዋፅኦ እንደ “የጀግኖች ተምሳሌት” ተደርጎ ይወሰዳል።
በሌላኛው ጎራ በዋነኝነት በአሜሪካና በአጋሮቿ ዘንድ ደግሞ ብሔራዊ ደህንነታችን ስጋት ላይ የጣለ በሚል ተደጋጋሚ ክስና ወቀሳ ይቀርብበታል። እነ አሜሪካና ምዕራባውያን ከዚህም አልፈው ጁሊያን አሳንጄን ለመያዝና ለማሰር ብርቱ ክትትል ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ባለፈው ሐሙስ ለንደን ውስጥ በቁጥጥር ስር አውለውታል።
ቀንደኛ ጠላቱ አሜሪካም ብሪታኒያ አሳልፋ እንድትሰጣት በይፋ ጠይቃለች። ተላልፎ ይሰጥ ወይስ አይሰጥ የሚለው ጉዳይም በስድሳ ቀናት ውስጥ እልባት የሚያገኝ ይሆናል። የትውልድ ሀገሩ አውስትራሊያ በዊክሊክስ አማካኝነት ለሚሰራው ሥራ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በወንጀል ቢጠይቁት ኃላፊነቱን እንደማትወስድለት መግለጿን ተከትሎ አሳንጄ ከ2012 ጀምሮ የአኳዶር መንግሥት ጥገኝነት ፈቅዶለት ለንደን ውስጥ በኤኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ይኖር ነበር።
በ2010 በስዊድን ሴት ደፍረሃል በሚል በስዊድን መንግሥት ክስ ተመስርቶበት በኋላ የተሰረዘለት ጁሊያን አሳንጄ ወደ ለንደን ሸሽቶ በዚያ ሁለት ዓመታት ከቆየ በኋላ ብሪታኒያ ለስዊድን አሳልፋ ትሰጠኛለች በሚል ስጋት በዚያው እንዳለ የኤኳደርን መንግሥት ጥገኝነት ጠይቆ በተፈቀደለት መሠረት ባለፈው ሚያዝያ 2 ቀን በለንደን ፖሊስ እስከተያዘበት ድረስ በለንደን የኤኳዶር ኤምባሲ እየኖረ ነበር።
እናም አወዛጋቢው ሰው በአንድ ወቅት በጥገኝነት ለተወሰነ ጊዜያት የኖረባት ሩስያ “የአሳንጄ መያዝ ተገቢ አይደለም” በማለት የአሳንጄን መያዝ የተቃወመች ሲሆን ከሕጋዊ ባልደረቦቹም ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበ ይገኛል። አሜሪካ በበኩሏ አሳንጄ ተላልፎ እንዲሰጣት ጠይቃለች። የዊኪሊክስ ሕጋዊ ቡድን በበኩሉ “ለንደን አሳንጄን አሳልፋ የምትሰጥ ከሆነ በዴሞክራሲ ታሪክ ጥቁር መዝገብን ጥሎ የሚያልፍ አሳዛኝ ቀን ይሆናል” ሲል ድርጊቱን አውግዟል።
“አሳንጄ እውነተኛ መረጃዎችን ለዓለም ሕዝብ ሰጠ እንጂ የማንንም ስም በሃሰት አላጠፋም ወንጀለኛም አይደለም፤ ሊያዝም አይገባም” ብሏል ቡድኑ። እናም አወዛጋቢው ሰው በመረጃ ነፃነት አርበኝነትና በወንጀለኛነት መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሞ ዓለምን ከሁለት ጎራ ከፍሎ ዛሬም በአወዛጋቢነቱ ቀጥሏል።
የዓለም መገናኛ ብዙኃንም ከቢቢሲ እስከ ሊ ሞንዴ፣ ከሲኤንኤን እስከ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከዘጋርዲያን እስከ ኒው ዮርክ ታይምስ ትኩረታቸውን አሳንጄ ላይ አድርገዋል። የመገናኛ ብዙኃኑ የዛሬ ዜናዎች የነገ ታሪኮች ናቸውና አወዛጋቢውን ሰው ለሚመጣው ትውልድ ምን ብለው ያስተዋውቁት ይሆን? “ጀግና” ወይስ “ጠላት”? “አርበኛ” ወይስ “አሸባሪ”?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በይበል ካሳ