ዓይናችን ጥሩ ነገር ሲመለከት መቼም አይተን አሊያም ሰምተን በሰጠነው ክብደት መጠን አግራሞትን ሳይጭርብን አያልፍም። ለየትና ወጣ ያሉ ነገሮችንም በክፉም ሆነ በደግ በየማህበራዊ ሚዲያዎች መቀባበላችንም እየተለመደ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማህበራዊ ሚዲያዎችን ያጨናነቀ አንድ ጉዳይ እንደነበር ምናልባት አንዳንዶቻችን እናስታውሰው ይሆናል። አንዳንድ የፋሽንና የስነ-ውበት አፍቃሪያን ብቻ ሳይሆኑ የግል እና የመንግስት ትላልቅ የሚዲያ ተቋማት ጭምር ርዕሳቸው አድርገውት ሰንብቷል። ጉዳዩ ደግሞ አንዲት ቆንጆ ኢትዮጵያዊት ወጣት በባህል ልብሷ ፎቶ ተነስታ በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ በአንድ ፎቶግራፏ ምክንያት ነበር። መነጋገሪያ የነበረችውም የ20 አመቷ ወጣት ቅድስት ብርሃን ስትሆን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪና የአዊ ማህበረሰብ ነዋሪም ናት። የአገው ፈረሰኞች አመታዊ በዓልና ፌስቲቫል በማህበረሰቡ ዘንድ በድምቀት እንደሚከበር የሚታወቅ ሲሆን፣ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃችው ወጣትም በዚሁ በዓል ላይ ተገኝታ በተነሳችው ፎቶግራፍ ነበር። ለመሆኑ ይህን ያህል አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ ምንድነው?
ነገሩ እንዲህ ነው፣ የአገው ማህበረሰብ የፈረስ ትርኢት በድምቀት እየተከበረ በነበረበት ዝግጅት ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ባሻገር የውጭ ሀገር ቱሪስቶች፣ አርቲስቶች፣ ባለስልጣናትና ተጋባዥ የነበሩ እንግዶች ሁሉም ቻግኒ ከተማ ላይ ተገኝተው በዓሉን ታድመዋል። ቅድስት ብርሃንም እንደማንኛውም የማህበረሰቡ አባል የአዊ የባህል ልብስ በመልበስ ከጸጉሯ ጀምሮ ፍጹም ባህላዊ የሆነ ውበትን ተላብሳ ነበር የታደመችው። የለበሰችው ልብስ ከተፈጥሮ ውበቷ ጋር ሲደመር የተለየ ድባብ ዘርቶባት ለዓይን የምትስብ ማራኪ ልጃገረድ ሆና እንድትታይ አድርጓታል። እሷም ልብሱን፣ ልብሱም እሷን አደመቃት። ይህን የተመለከተ አንድ ፎቶ አንሺም ፎቶዋን በካሜራው አስቀርቶ በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጨው። አንዳንዶች በልጅቷ ቁንጅና፣ ሌሎች ደግሞ በለበሰችው የባህል ልብስ እየተደመሙ በአድናቆት ተቀባበሉት።
ቅድስት ብርሃን ስለሁኔታው ስታብራራ እንዲህ ትላለች። “በሕይወቴ ማሳካት ከምፈልጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ ይህንን የማህበረሰቤን የባህል ልብስ ከሀገራችን አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተወዳጅ እንዲሆን ማድረግ ነው። የተፈጠረው አጋጣሚ ግን ፍጹም ያልጠበቁት ነበር። የአገው የፈረስ ውድድር በሚካሄድበት እለት እኔም ከውዝዋዜ ቡድን አባላቱ ጋር እየተወዛወዝኩ ነበር። አንድ ፎቶ አንሺ መጣና ከመሃል እጄን ይዞኝ ወጣ። ፎቶ ላንሳሽም አለኝ። በወቅቱ ብቻዬን አልነሳም ስላልኩት ከጓደኛዬ ጋር ሊያነሳኝ ተስማማሁ። የማውቀውም አንድ ላይ እንዳነሳን ነበር። ለካስ እሱ ብቻዬን ነጥሎ እያነሳኝ ነበር። ወደቤት ከተመለስኩ በኋላ ወንድሜ ጠራኝና ኧረ ፎቶሽ የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል ሲል አሳየኝ። ፎቶ መነሳቴን እንኳን እረስቼው ስለነበረ በጣም ነበር የደነገጥኩት። ኋላ ላይ የሚያገኙኝ ሰዎች አድናቆትና እየደወሉ የሚያበረታቱኝ ሰዎች እየተበራከቱ መጡ። እኔም በጣም ደስ አለኝ። ህልሜን እውን ለማድረግም ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥርልኝ ጅማሮ እንደሆነም እየተሰማኝ መጣ።”
ወጣቷ ቅድስት፣ አሁን ላይ የአዊ ማህበረሰብን ቱባ የሆኑ የአልባሳትና ባህላዊ ፋሽኖችን እየለበሰች ከማስተዋወቋ በተጨማሪ የማህበረሰቡን ልዩ ልዩ የሆኑ የጸጉር አሰራሮችን በመሰራት በማህበራዊ ሚዲያዎች ታስተዋውቃለች። ወጣቷ ከዚህ ልዩ አጋጣሚ በኋላ በርካታ እድሎች ተፈጥረውላታል። አንዳንድ ትልልቅ ተቋማትም ምርታቸውን እንድታስተዋውቅላቸው እየጎተጎቷት ይገኛሉ። እስካሁን ለሰራችው ስራ የአዊ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የማህበረሰቡ አምባሳደር አድርጎ ሰይሟታል። የተሰጣትን የአምባሳደርነት ማዕረግ ለቀጣይ ስራዎቿ የሞራል ስንቅ በማድረግም የአዊን ማህበረሰብ ባህል ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያን ያልተነኩ የባህል እሴቶችን በማንጸባረቅ ተግታ እንድትሰራም የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቱ በአደራ መልክ አስረክቧታል። በምታደርጋቸው የተለዩ እንቅስቃሴዎችና ባህሏን በመጠበቅ የማህበረሰቧን ገጽታ በመገንባት፣ አጉልታ ለማውጣት ከምትሰራቸው ስራዎች አንጻር የተሰጣት የአዊ ማህበረሰብ የአምባሳደርነት ማዕረግ በትክክልም የሚገባት መሆኑን በርካቶች ያምናሉ።
ቅድስት የአምባሳዳርነት ማዕረግ በተሰጣት እለት አንዲት ጋዜጠኛ እንዲህ ስትል ጠይቃት ነበር “የባህላዊው ፋሽን ተከታይ እንደመሆንሽ፣ ዘመናዊ አልባሳትን ትጠቀሚያለሽ? ወይንስ ሁሌም በባህል አልባሳት ብቻ ነው የምትታይው?” ቅድስት ለዚህ ጥያቄ የሰጠችው ምላሽ፤ “የባህል አልባሳት የክብር ልብስ እንደመሆናቸው የምለብሰውም በተለያዩ ክብረ በዓላት፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሚኖርበት ወቅት ነው። ዘወትር የባህል ልብስ ለመልበስ የማያመቹ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ስራ እየሰራሁ ጭምር በየእለቱ ብለብሰው እየለመድኩት እመጣና የልብሱን ክብር የምቀንስበት ይመስለኛል። ውድ ነገሮች ያለቦታቸው ሲገኙ ይረክሳሉ። በጣም ለምንወደው ነገር ደግሞ እንክብካቤያችንም የዛኑ ያህል ነው፣ በጣም እንጠነቀቅለታለሁ። ስለዚህ በሌላ ጊዜ ዘመናዊ አልባሳትን እጠቀማለሁ። ትልቁ ነገር ግን ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ አልባሳቱን ለማስተዋወቅ እጥራለሁ።” የሚል ነበር።
ወጣቷ የኢትዮጵያን የባህል አልባሳት በዘመናዊው ዓለም ተፈላጊ እንዲሆኑና ከሀገር ወጥተው ዓለም አቀፍ ተመራጭነትን እንዲያገኙ የመስራት ህልም እንዳላት ትገልጻለች። የዘመናዊ ፋሽን ኢንዱስትሪው ገና በሁለት እግሩ መቆም ባልቻለባት በሀገራችን ኢትዮጵያ አሁናዊ የፋሽን ምሶሶዋ ባህላዊውና የቆየው የፋሽን ስርዓቷ ነው። ከእነዚህም ባህላዊ የፋሽን ስርዓቶች መካከል ነጥረው መውጣት የቻሉትም እነዚሁ ባህላዊ አልባሳት ናቸው። ወደ ዘመናዊው ዓለም በሚደረገው ሽግግርም የእነዚህ ፋሽኖች ስርዓት በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳያመራ ትልቅ ጥንቃቄን ይሻል። በየጊዜው ስለዚህ ጉዳይ አብዝተን የምናወራውም ለዚህ ነው። ወደሚቀጥለው ስርዓት ከመሸጋገራችን በፊት አስቀድመን አሁን ያሉንን ነገሮች በሚገባ ማወቅና ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት እንደ ቅድስት ያሉ የሀገራቸውን ባህል ለማስተዋወቅ ተግተው የሚሰሩ ብርቱ ተምሳሌቶች በየአቅጣጫው ብቅ ማለት ጀምረዋልና ስራቸውን በመደገፍ እውቅና ልንሰጣቸው ይገባል። በመጨረሻም፨ ለባህል አምባሳደሯ እንዲሁም ያን የመሰለ የፎቶ ምስል በካሜራው በማስቀረት ትልቅ የባህል አሻራ ማሳረፍ ለቻለው ወጣት ያለንን አድናቆት መግለፅም ያስፈልጋል። ማህበራዊ ሚዲያዎቻችን እሴቶቻችንን አውጥቶ ለዓለም ለማሳየት ምቹና መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩ ናቸውና፣ በተቻለን አቅም ሁሉ ለዚሁ አላማ እንጠቀማቸው ለማለት እንወዳለን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም