አዲስ አበባ፡- የመሬት ወረራ እንዳልቆመና በስፋትም እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ፡፡ መንግሥት የመሬት ወረራን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ችግሩ መቆም እንዳልቻለ የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 9 ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት ከበደ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎችና ከመሀል ከተማ በመምጣት በህገ ወጥ መንገድ መሬት በመውረር ግንባታ የሚያካሂዱ አካላት አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የቦሌ ክፍለ ከተማ ከአርሶ አደር መሬት ጋር ኩታ ገጠም ስለሆነ ለህገ ወጥ ወረራ የተጋለጠ ነው፡፡ እንዲሁም ወረዳው ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ህገ ወጥ ግንባታዎች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡
ህገ ወጥ የመሬት ወረራን በተመለከተ የመንግሥት አቋም ይታወቃል ያሉት አቶ ጉልላት ከበደ ወረዳችንም አይደራደርም ከክፍለ ከተማ ጋር በመቀናጀት በመሬት ወረራ ዙሪያ ምህረት የለሽ እርምጃዎች እየወሰድን ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ጉልላት ገለፃ ፤ ወረዳው ለመሬት ወረራ የተጋለጠ ቢሆንም ተቆጣጥሮ ግንባታዎችን ከማስቆምና በዚህ ዙሪያ ተሳትፈው የተገኙ አካላትን ለሕግ ከማቅረብ አንፃር ውጤታማ ሥራዎችን ሰርተናል በወረዳው ምክር ቤትም ተረጋግጧል፡፡
እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ ወደ 155ሺ ካሬ ሜትር የሚሆን መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስገባት ችለናል፡፡ መሬት የጋራ ሀብት ነው ያሉት ኃላፊው ያለንን ውስን ሀብት በጋራና በፍትሃዊ መንገድ መጠቀም እንድንችል ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ግንባታዎች ሲገነቡ ጥቆማ እንዲያደርጉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅ መንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍፁም ኢቲቻ፤ የመሬት ወረራ በብዙ ወረዳዎች በስፋት ይስተዋላል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ግንባታ መገንባትና መሬት መውረር በህግ እንደሚያስጠይቅ ለህብረተሰቡ በየጊዜው ግንዛቤ እናስጨብጣለን፡፡ በእኛ በኩልም ንብረት እንዳይወድምና ግጭቶች እንዳይነሱ ግንባታ ከመገንባቱ በፊት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ከቁጥጥር አልፈው የተገነቡትንም ግብረኃይል በመላክ እንዲፈርሱ በማድረግ ላይ ነን፡፡ እንዲሁም አስተማሪ የሚባሉ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው፡፡ ህገወጥ ግንባታዎችና የመሬት ወረራዎች ሲስተዋሉ ክፍለ ከተማው እየሰራ አይደለም ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም ትናንት ግንባታ እንዳይገነባ ያስቆምንበት ቦታ ዛሬ ተገንብቶበት ሊያድር ስለሚችል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
ሞገስ ፀጋዬ