አዲስ አበባ፡- ሴቭ ዘ ችልድረን ኢትዮጵያ ከዩ ኤስ ኤድ ጋር በመተባበር 9 ሚሊዮን ብር በመመደብ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ እየሰራ መሆኑ ተነገረ፡፡
በኢትዮጵያ አንድ መቶኛ ዓመቱን እያከበረ ያለው ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ከሚሰራቸው ሥራዎች በተጨማሪ በህጻናት ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የስቆጣ ቃል ኪዳን ክፍል ሲኒየር ማኔጀር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ እንዳሉት፣ መቀንጨርን ለማጥፋት ‹‹የፖሊሲ ሰነዶቻችን በተለይም ውሃ ላይ ያሉ ነገሮች ስለ ሚልኒውትረሽን ምንም የሚሉት ነገር አልነበረም፡፡ አሁን ግን በሰቆጣ ስምምነት ላይ «ወሽ» እንዲገባ ተደርጓል፤›› ይላሉ፡፡
የቀነጨረ ዕድገትን ለመቀነስ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ማድረግ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህም ሥርዓተ ምግብን ለማስተካከል በሚሠራበት ማኅበረሰብ ላይ እንደ ወሽ ያሉ ፕሮግራሞች የውሃ አቅርቦት፣ የመፀዳጃ ቤት መኖር፣ የግልና የአካባቢ ንፅሕና አጠባበቅ ሥራዎችን መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡
የሴቭ ዘችልድረን የግሮስ ኒውትሬሽን ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ መሰረት አሰግድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የስርዓተ ምግብን ለመቅረፍ በህጻናት የአመጋገብ ስርዓት ማሻሻያ ላይ በጋራ ቢሰሩ ሊያመጡ የሚችሉትን ውጤት በማጥናት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡
በሥርዓተ ምግብ ችግር ዙሪያ እ.ኤ.አ. በ2016 በተሠራ አንድ ጥናት፣ በኢትዮጵያ 67 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች ዕድገት እንዲቀጭጭ ሆኗል፡ ፡ በጥናቱ መሠረት፣ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች በሆኑ ሕፃናት የመቀንጨር ችግር በስፋት የሚታየው በአማራ ክልል ነው፡፡በክልሉ የመቀንጨር ችግር 46.3 በመቶ ሲሆን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 42.7 በመቶ፣ በአፋር ክልል 41.1 በመቶ ችግሩ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡በዚህ ረገድ የተሻሉ የተባሉት አዲስ አበባ 14.6በመቶና ጋምቤላ ክልል 23.5 በመቶ መሆኑን ከጥናቱ መረዳት ተችሏል፡፡
ይህንን አገራዊ ችግር በ2022ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን፣ይህን እውን ለማድረግም ለሕፃናቱ ዕድገት ትልቁን ድርሻ በሚይዙት በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ ብዙ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ይህም ማለት ሕፃኑ (ኗ) ከተረገዘ ወይም ከተረገዘችበት ጊዜ እስከ ሁለት ዓመቱ (ቷ) ድረስ ባሉት ቀናት የሚደረግ እንክብካቤ ነው፡፡ ይህም የሆነው በሕፃናት አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ላይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ትልቁን ሚና ስለሚጫወቱ ነው፡፡ የሰቆጣ ስምምነትም ይህንን ዕውን ለማድረግ የተጀመረ ፕሮግራም ነው፡፡
በአገሪቱ ለጤና ጠቃሚ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን የሚመገቡ፣ ከስድስት እስከ 23 ወራት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናት ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
አብርሃም ተወልደ