አዲስ አበባ ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተቋራጮች ከሚያስገነባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የአያት ኮንዶሚንየም -አራብሳ ኮንዶሚንየም መግቢያ የመንገድ ፕሮጀክት በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት ፕሮጀክቱ መጓተቱ ተነገረ ፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ በ2011 በጀት ዓመት ተሰርቶ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም አራብሳ ኮንዶሚኒየም መግቢያ አካባቢ የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ባለመፍረሳቸው ለመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ መጓተት መንስኤ ሆኗል፡፡
የወሰን ማስከበር ሥራው የዘገየው ባለንብረቶቹ ከከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን የካሳና የምትክ ቦታ እስከሚረከቡ ድረስ ቢሆንም መንገዱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 30 ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቱን ግንባታ ሰናን ኮንስትራክሽን እያከናወነው የሚገኝ ሲሆን የግንባታ ቁጥጥሩንና የማማከር ሥራውን ደግሞ ቤዛ አማካሪ ድርጅት እየሰራው ይገኛል፡፡
የፕሮጀክቱ አፈፃፀም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ 60 በመቶ ተከናውኗል፡፡ ለዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የከተማ አስተዳደሩ ከ208 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦለታል፡፡
መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለአራብሳ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡ ፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአያት ወደ ቦሌ አራብሳ እና ሌሎች አካባቢዎች ለመጓዝ አቋራጭ መንገድ በመሆን ከማገልገሉም በላይ የከተማዋን የመንገድ ሽፋን በማሳደግ የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
በወሰን አለመከበር ምክንያት የሚዘገዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ለብክነት ከመዳረጋቸውም በላይ ለትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን አስተላልፏል::
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
አብርሃም ተወልደ