ከዚህ በፊት በነበሩት ሳምንታት እንደገለጽነው ይህ የየካቲት ወር ታሪካዊ ክስተቶች የሚበዙበት ነው:: የካቲት 12 የሰማዕታት ጀግኖችን ተጋድሎ ዘክረናል:: በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ኢትዮጵያን ስመ ገናና ያደረጋት የዓድዋ ድል አለ:: ይህ ሁሉ የሆነው በኢትዮጵያውያን ጀግኖች መስዋዕትነት ነው::
ከእነዚህ ጀግኖች ውስጥ፤ ከ86 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 13 እና 16 ቀን 1929 ዓ.ም በጀግንነት ጦር ሲመሩና ሲዋጉ በባንዳዎችና በግፈኛው የጣሊያን ወራሪ መስዋዕት የሆኑትን ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድን እና ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪን እናስታውሳለን:: ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም የተሰው ሲሆን ራስ ደስታ ዳምጠውና ደጃዝማች በየነ መርዕድ ደግሞ የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም ተሰው:: በነገራችን ላይ ሁለቱ ጀግኖች(ራስ ደስታ ዳምጠው እና ደጃዝማች በየነ መርዕድ) የወቅቱን የኢትዮጵያ መሪ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ልጆች ነው ያገቡት::
ራስ ደስታ ዳምጠው የዓድዋው ሰማዕት የፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ ልጅ ናቸው:: የተወለዱት ከዓድዋ ጦርነት ሁለት ዓመት በፊት በ1886 ዓ.ም ነው:: ከታላቅ ወንድማቸው ልጅ አበበ ዳምጠው (በኋላ ሌተናል ጀኔራል) ጋር የቤተ መንግሥት ባለሟል ሆነው ቆይተዋል::
ልጅ ደስታ ዳምጠው በ1916 ዓ.ም በፊታውራሪ ማዕረግ የፈረስ ዘበኛ (የፈረሰኞች ኃላፊ/አለቃ) ሆነው ተሾሙ:: ልጅ ደስታ ዳምጠው እየተባሉ ከልጅ ኢያሱ ወገኖች ጋር በሜኢሶ በተደረገው ጦርነት፤ ፊታውራሪ ደስታ እየተባሉም ራስ ጉግሳን ሊወጋ ወደ በጌምድር ከዘመተው የማዕከላዊ መንግሥት ጦር ጋር ተሰልፈው ተዋግተዋል::
ኅዳር 7 ቀን 1917 ዓ.ም የልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን(አጼ ኃይለሥላሴ) ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅን በተክሊል አገቡ:: በዚህም መስፍንናቸውንና ከንጉሳዊው ቤተሰብ ጋር ያላቸውን ዝምድና አጠናከሩ:: ይህ የተክሊል ጋብቻ ስነ ስርዓት ታኅሳስ 4 ቀን 1917 ዓ.ም በታተመው አዕምሮ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል::
ራስ ደስታ በቅድሚያ በደጃዝማችነት ማዕረግ ከ1921 ዓ.ም ጀምሮ ከፋን ሲያስተዳድሩ ቆይተው በ1925 ዓ.ም ‹‹ራስ›› ተብለው ሲዳሞንና ቦረናን እንዲያስተዳድሩ ተሾሙ። ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የፋሽስትን ወረራ ለመመከት የክተት አዋጅ ካወጁ በኋላ የኢትዮጵያን ጦር በተለያዩ ግንባሮች እንዲመሩ ለጦር አበጋዞቻቸው ስምሪት ሰጡ::
በምስራቅ በኩል ወረራ የፈጸመውን ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒን ለመመከት ወደ ደቡብ ግንባር የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ቀኝ ደቡብ፣ መሐል ደቡብና ግራ ደቡብ በሚሉ ስያሜዎች በሶስት ምድቦች የተደራጀ ነበር። የቀኝ ደቡብ የጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ የወቅቱ የሐረርጌ እንደራሴ የነበሩት ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ነበሩ። የግራ ደቡብ ምድብ ዋና አዛዥ ደግሞ የወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና ገዢ ራስ ደስታ ዳምጠው ሲሆኑ፤ የወቅቱ የባሌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች በየነ መርዕድ ደግሞ የመሐል ደቡብ ጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ ነበሩ::
በሦስቱም ምድብ አዛዦች ስር ደግሞ ሌሎች የጦር አበጋዞች ሰራዊታቸውን ይዘው ተሰልፈው ነበር:: ከእነዚህም መካከል ደጃዝማች ሃብተሚካኤል ይናዱ፣ ደጃዝማች መኮንን እንዳልካቸው፣ ደጃዝማች አበበ ዳምጠው፣ ደጃዝማች አምደሚካኤል ሃብተሥላሴ እና ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት በደጃዝማች ነሲቡ ስር፤ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ ደጃዝማች መኮንን ወሰኔ፣ ደጃዝማች ደባይ ወልደ አማኑኤልና ፊታውራሪ ታደሰ ገነሜ ደግሞ በራስ ደስታ ዳምጠው ስር፤ እንዲሁም በጅሮንድ ፍቅረስላሴ ከተማ፣ ፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ወልደጊዮርጊስና ቀኛዝማች አስፋው ወልደጊዮርጊስ ደግሞ በመሐል ደቡብ ዋና አዛዡ በደጃዝማች በየነ መርዕድ ስር ተሰልፈው ነበር::
ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ‹‹የታሪክ ማስታወሻ›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ስለራስ ደስታ የጦር አሰላለፍና ፍፃሜያቸው እንዲህ ብለዋል::
‹‹ … ደስታ ዳምጠው ራስ ከተባሉ በኋላም በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በሲዳሞ በኩል ከነበሩት የጦር አዝማቾች መካከል ዋነኛው ነበሩ:: ራስ ደስታ ዳምጠው በታክቲክ ለመዋጋት አስበው በመደራጀት ላይ ሳሉ በግንባር ቀድሞ እንዲዋጋ የታዘዘው ጦር አለቃ የነበረው ፊታውራሪ ታደመ አንበሴ ከድቶ ከፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ጋር ስለተሰለፈ ራስ ደስታ ችግር አጋጥሟቸው ነበር:: በተጨማሪም በደቡብ በኩል የነበረው የጠላት ወረራ የበረታ ስለነበርም ከንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ሆነው ወደ ማይጨው እየዘመቱ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ከሰሜን ተመልሰው ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመጓዝ ራስ ደስታን እንዲረዱና ጠላትን እንዲመክቱ ተደረገ::
አብዛኛው የሲዳሞ ጦር የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ነበር:: ደጃዝማች ባልቻ ከሲዳሞ ከተነሱ በኋላ ጦሩ በደጃዝማች ባልቻ ጊዜ የለመደው ግብርና ሽልማት ቀርቶበት ያኮረፈ ነበር:: አዲስ የተሾሙት የሲዳሞ አገረ ገዢም የራሳቸውን አሽከሮች በማደራጀት ልምድ ያለውን ይህን ጦር ፊት በመንሳት ስላደኸዩት በወቅቱ ወራሪውን ለመመከት ጥሪ ሲደረግለት ትዕዛዝ ለመፈፀም ሲል ብቻ ዘመተ እንጂ አገሬን፣ ጌታዬን ብሎ ተባብሮ በየጦር ግንባሩ ሊጋፈጥና ሊዋጋ አልፈቀደም ነበር ይባላል::
የአዲሱ አገረ ገዢ ባለሟሎችም የጦር ልምድ አልነበራቸውምና ምንም እንኳ ሰልፉና አደረጃጀቱ ቢያምርም በጦር ግንባር በሚገባ ሊዋጋና ሊመክት አልቻለም:: ራስ ደስታ ዳምጠው በዚህ ቅር ቢሰኙም ከደጃዝማች ገብረማርያም ጋር ከተገናኙ በኋላ ግን እስከመጨረሻው ድረስ በጀግንነት ተዋግተዋል:: ደጃዝማች ገብረማርያም የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም በውጊያ ላይ ሳሉ ሲሞቱ ራስ ደስታ በጠላት ተያዙ…›› ብለዋል::
በሰሜንና በምስራቅ በኩል የማጥቃት ዘመቻ የከፈተው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ዋና ከተማው አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ መግባት ቢችልም በደቡብ በኩል የነበረው ጦር ግን ከነራስ ደስታ ዳምጠው እና ከነደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ በኩል በገጠመው የመከላከልና የማጥቃት ዘመቻ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መድረስ ስላልቻለ የግንባሩ ጦር አዛዥ ጀኔራል ጀሎዞ እና ዋናው የአስተዳደሩ ተወካይ ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ለራስ ደስታና ለደጃዝማች ገብረማርያም ልመና፣ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ የተቀላቀሉባቸው ደብዳቤዎችን ጽፈውላቸው ነበር::
ጥር 1 ቀን 1929 ዓ.ም ሻንቆ በተባለው ቦታ ላይ በተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያውያን በጠላት እግረኛ ጦር ላይ ከፍተኛ ድል ቢቀዳጁም የጠላት ጦር በአውሮፕላን የሚያዘንበውን ቦምብና መርዝ ግን መቋቋም አልተቻለም:: በመሆኑም አርቤጎናን በመልቀቅ ብዙ የወገን ጦር ወዳለበት ወደ ባሌ ግዛት ለመሄድ ተወሰነ:: ውጊያው በመንገድ ላይም አላባራም ነበር:: የወገን ጦር መንገድ የዘጋበትን የፋሺስት ጦር በመውጋት መንገድ እያስከፈተ ዘለቀ::
ጥር 20 ቀን 1929 ዓ.ም ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ ደጃዝማች በየነ መርዕድ፣ ደጃዝማች በዛብህ ስለሺ እና ፊታውራሪ ሽመልስ ሀብቴ ጦራቸውን ይዘው እነርሱም መድፍ ጠምደው ተሰለፉ:: በዚህ ተጋድሎ ኢትዮጵያውያን አካባቢው በጠላት እጅ እንዳይወድቅ ከማድረጋቸውም ባሻገር በጠላት ጦር ላይ ትልቅ ጉዳት ማድረስ ችለዋል::
ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› በሚለው መጽሐፉ እነራስ ደስታ ዳምጠው ከፋሺስት ጦር ጋር ስላደረጉት ፍልሚያ በጻፈበት ክፍል ‹‹ … በኢትዮጰያውያን በኩል በራስ ደስታ ዳምጠው አዝማችነት 40 ሺህ የሲዳሞና የባሌ ጦር፣ በደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል አዝማችነት 30 ሺህ የኦጋዴንና የሐረርጌ ጦር፣ በደጃዝማች አምደ ሚካኤል አዝማችነት 10 ሺህ የአርሲ ጦር በየቦታው በደቡብ አቅጣጫ ተሰልፎ ነበር:: በቤኒቶ ሙሶሊኒ ትዕዛዝ የሰሜኑ ጦር የመረብን ወንዝ ሲያቋርጥ የሩዶልፎ ግረዚያኒ ጦርም በዚያው ድንበር አልፎ ኦጋዴን ገባ:: በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም ቀላፎ፣ ገርለ ጉቢና ቆራሄ በፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች ተያዙ:: በኢትዮያውያን በኩል የራስ ደስታ ጦር ከነገሌ ጀምሮ ዶሎ ድረስ ያለውን ቦታ እንዲጠብቅ ስለታዘዘ 400 ኪሎ ሜትር ያህል በእግሩ ተጉዞ በወሰን አካባቢ እንዲደርስ ተደረገ:: ጦሩ በሚጓዝበት ጊዜ ለአውሮፕላን ጥቃት አመቺ ሆኖ በመገኘቱ በፋሺስት የጦር አውሮፕላን ቦምብ እየተደበደበ ነበር:: ከሞት የተረፈውም ከኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር ደርሶ ተሰለፈ …
… ይህን የኢትዮጵያን መንቀሳቀስ ያጠናው ማርሻል ባዶሊዮ በቴሌግራም ቁጥር 1897 ለግራዚያኒ መልዕክት አስተላለፈ:: መልዕክቱም ‹የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ዋና ኃይል ወደ እናንተ መጓዝ ጀምሯልና በእጅህ በሚገኘው ማንኛውም ዓይነት መሳሪያ በቦምብና በመርዝ ሁሉ መዋጋት አለብህ:: ከዚህ ኃይል በኋላ ሌላ የሚያጠቃህ ያለ አይመስለኝም:: እርግጠኛ ነኝና እንደእኔ ከሆነ ብታስብበት የሚከፋ አይመስለኝም› የሚል ነበር::
በኅዳር ወር ግራዚያኒ ዶሎ ገብቶ ጦሩን ሲያጠናክር ከርሞ ዝግጅቱን ከጨረሰ በኋላ ወደፊት በመግፋት ጥር 4 ቀን 1928 ዓ.ም የመጀመሪያው ታላቅ ውጊያ ገናሌ፣ ዶሪያ ላይ ተካሄደ:: በዚያም ቀን በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ በምድር በታንክና በዘመናዊ መሳሪያ የሚደረገው ውጊያ አንሶ በአውሮፕላን አንድ ሺህ 700 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቦምብና የመርዝ ጋዝ ተጣለበት::
የኢጣሊያ ጦር የጎድጓድ ውሃና ወንዝ ካለበት ቦታ እየመሸገ ስለተቀመጠ የኢትዮጵያን ሰራዊት ውሃ እንዳያገኝ አደረገው:: የኢትዮጵያ ሰራዊት ከወንዝም ሆነ ከጉድጓድ ውሃ ለመቅዳትና ለመጠጣት ሲጠጋ በየአካባቢው የመሸገው የኢጣሊያ ጦር በመትረየስ ይገድለዋል:: ግድያው ሰውን በመምረጥ ብቻ ሳይወሰን እንስሳትም ውሃ ሲጠጡ ይገደሉ ነበር:: ከላይ ከአየር ደግሞ አውሮፕላኖች በመመላለስ በመርዝ ጭስ ፈጁት … ››
በነራስ ደስታ ዳምጠው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት በእግረኛ ጦር ውጊያ ድሎችን ቢያስመዘግብም የፋሺስት ኢጣሊያ የጦር አውሮፕላኖች የሚያዘንቡበትን ቦምብና የመርዝ ጭስ መቋቋም እጅግ አስቸጋሪ ስለሆነበት አካባቢው በጠላት ጦር ቁጥጥር ስር ዋለ:: ራስ ደስታ ዳምጠውም በባንዳዎችና በፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ትብብር ተማርከው የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም ተገደሉ:: የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ አፅማቸው በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ‹‹ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል›› ለእርሳቸው መታሰቢያ የተሰየመ ነው።
ራስ ደስታ ከአርበኝነታቸው በተጨማሪ፣ የአውሮፓንና የአሜሪካን ዘመናዊነት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት መንገድ፣ የንፁህ ውሃ አገልግሎት፣ የህክምና፣ የትምህርት ወዘተ… ተቋማትን ለማስፋፋት የበኩላቸውን ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። የነጮችን ዘመናዊነት ለመቅሰም ፍላጎት ቢኖራቸውም ‹‹ነጮችን አያምኑም›› ይባል ነበር። ራስ ደስታ በ1923 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ተጉዘው እንደነበርና ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት ጋር ተገናኝተው እንደተመለሱም ታሪካቸው ያሳያል።
ደጃዝማች በየነ መርዕድ በሰሜን ሸዋ 1889 ዓ.ም እንደተወለዱ ይነገራል:: ደጃዝማች በየነ መርዕድ የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን ልጅ ልዕልት ሮማነወርቅ አግብተዋል::
ደጃዝማች በየነ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት በርካታ የጦር ተጋድሎዎችን አድርገው ለአገራቸው ተሰውተዋል::
ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ(አባ ንጠቅ) በ1866 ዓ.ም ምዕራብ ሸዋ፣ አገምጃ ውስጥ ልዩ ስሙ ሰርቦኦዳ ኮሎ በተባለ ቦታ ከአባታቸው አቶ ጋሪ ጎዳና እና ከእናታቸው ወይዘሮ ሌሎ ጉቴ 13ኛ ልጅ ሆነው ተወለዱ::
ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር የ22 ዓመት ወጣት የነበሩት ገብረማርያም ጋሪ ለንጉሰ ነገሥቱ የክተት አዋጅ ምላሽ በመስጠት ከበጅሮንድ ባልቻ ሰራዊት ጋር ዘመቱ:: የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጦርነቱ ሲጀመር ጎህ ሲቀድ ወደ ውጊያ የገባው የበጅሮንድ ባልቻ ጦር እጅግ ከባድ ውጊያ አደረገ:: ገብረማርያም አዝማቻቸው በጅሮንድ ባልቻ ጭምር እንዲቆስሉ ምክንያት ከሆነው ጦርነት ተርፈው የድሉ ተቋዳሽ መሆን ቻሉ:: እኚህ ለአገራቸው በክብር ለመሰዋት የተፈጠሩ ጀግና ከ40 ዓመት በኋላ በመጣው የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ግን በ63 ዓመታቸው መስዋዕት ሆኑ::
አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ‹‹ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት በስማቸው ተሰይሞላቸዋል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም