እኛ ኢትዮጵያውያን ወዲህ በቂ ውሃ፣ ወዲያ ደግሞ ሰፊ መሬት አለን። ይህን ሁሉ ወሳኝ ሀብት ይዘን ክፉኛ የተጣባን ድህነት እጣ ፈንታችን እስኪመስለን ድረስ ድህነቱን ይዘነው መዝለቃችን የሚያስገርም፣ የሚያሳፍርም ነው። ከዚህም አልፎ ከተለያዩ ለጋሽ አገራትና የተራድኦ ድርጅቶች ረድኤት እንዲደረግልን መጠበቁን የመብት ያህል መቁጠራችን የሚያሳፍር የረጅም ጊዜ መገለጫችን ሆኖ ቆይቷል፤ እንደ አለመታደል ሆኖም በዚህ አመለካከት ጥቂት የማይባሉ አስርት ዓመታትን አሳልፈናል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት መንግስት አንዳንድ ግዙፍ ተግባራትን ለመስራት መንደርደር ሲጀመር፤ ሊተገበሩ የማይችሉ ስራዎች ናቸው በሚል ብዙዎች ውጥኖቹን እንደቅዠት መቁጠራቸው ይታወሳል። በአንጻሩ አንዳንዶች ደግሞ ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎች ይፋ በሚደረጉበት ጊዜ ግርምት እንዳጫረባቸው በተለያየ አጋጣሚ ገልጸዋል።
በእርግጥ እነዚህ አካላት እነዚህ እቅዶችና ግቦች አግራሞት ቢያጭሩባቸውም፣ አሊያም እቅዶቹንና ግቦቹን እንደ ቅዥት ቢቆጥሯቸውም ላይፈረድባቸው ይችላል። ለዚህ ምክንያቴ ደግሞ አንድ ሰው በመጀመሪያ አገሩ ያላትን ሀብትና የመንግስትን ቁርጠኛነትና አቅም ጠንቅቆ ማወቅ አለመቻሉ ላይ ይሆናል። እነዚህ እቅዶችና ግቦች እንዴት ሊሳኩ እንደሚችሉ ለመረዳት ለጉዳዩ ቅርብ መሆንና የበኩልን ሚና መጫወትንም ይጠይቃል።
ይህ የውስጥ ጉዳያችን እንደተጠበቀ ሆኖ እኛ ያለንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅመን የተለያዩ የእህል አይነቶችን ማምረት የማንችል ተደርጎ በውጪው ዓለም ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ሲነገረን መቆየቱም ሌላው ጉዳይ ነው። ሁሌም ቢሆን ከጉያቸው ስር እንዳንወጣ የሚፈልጉ አገራትም ሆኑ ተቋማት ከሚሰፍሩልን ስንዴ ውጭ ሌላ እንዳያምረንና እንዳናይ ለአይናችንን ታይቶ በሚጠፋ እርዳታ ሲከልሉን ቆይተዋል።
ይሁንና ግብን ስኬታማ ማድረግ ይቻላል በሚል እሳቤ ወደስራ የገባው መንግስት፣ በተለይ በስንዴው ልማት ስኬታማ ተግባር አከናውኗል። የሰላም እጦት፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎችና ሌሎችም ተግዳሮቶች ፈተና ሆነውበትም እቅዱን መፈጸም እንደሚችል ማሳየት ችሏል፤ በአገሪቱ ላይ ተፈጥሮ በነበረ ጫና ለግብርና ልማቱ የሚያስፈልገውን ማዳበሪያ ገዝቶ ማቅረብ ስጋት እንደነበር አይዘነጋም። ኢትዮጵያ ግን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የግብርና ልማቷን በተለይም የስንዴ ልማቷን ጠላትንም ወዳጅንም በሚያስደምም መልኩ አሳክታለች። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያስጀመሩት ስንዴን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ጅማሮ ለእዚህ ሌላው ሕያው ምስክር ነው።
ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ ታደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ጥቂት በማይበሉ አካላት ዘንድ እንደ ቅዠት ተቆጥሮም ነበር፤ አንዳንዶችም እንቅስቃሴውን ‹‹ትለብሰው የላት…›› ሲሉ ለማጣጣልም ሞክረዋል። ጥቂት የማይባሉ ጉዳዩ ያልገባቸው አካላትም እንደተለመደው ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ማስገባቷን እንድትቀጥል፣ ሌሎችም ቢሆኑ ‹‹ራስ ሳይጠና…›› በማለት ከመስራት አሊያም ለሚሰራው ስራ እውቅና ከመስጠት ይልቅ ማላገጥን መርጠውም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረብ በጀመረበት እለት ‹‹ያለምነውን በተግባር የምናሳይ እንጂ የምንቃዥ አይደለንም›› ማለታቸውን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል። ጉዳዩን ከቅዠት የቆጠሩት ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረ እለት ምን ብለው ይሆን?
ግራም ነፈሰ ቀኝ ወይም ደግሞ ተወደደም ተጠላ ሁሉም አይኑ እያየ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ውል በማሰር አገሪቱ የአላጋጮችን አፍ ማሰር ችላለች። ይህ ደግሞ እንዲሁ በዋዛ የመጣ ስኬት አይደለም። ለዚህ እቅድ መሳካት በፈጻሚውም ሆነ በአስፈጻሚው ዘንድ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። በአንድ ጀምበር ታቅዶ በአንድ ጀምበር የተተገበረ ስራ አይደለም።
ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ሲታቀድ አስቀድሞ ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን መናገር ከንቱ ድካም ይሆንብኛል። ምክንያቱም አገራችን ለስንዴ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት በአገር ደረጃ ስንዴ በመስኖ በአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በስፋት ለማምረት እንቅስቃሴው መግባት በራሱ ምን ያህል አድካሚ ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች አይሆንምና ነው።
አሁን ኢትዮጵያ በዘርፉ የያዘችው እቅድ ውጤታማ ስለመሆኑ በአደባባይ ታይቷል። መንግሥት የስንዴ ምርቱን ከሚገዙ አገራት ጋር እየተነጋገረ ስለመሆኑም ተነግሯል። እስካሁንም ጎረቤታችን ከሆኑት ሱዳን እና ኬንያ ጋር እንዲሁም ሌሎች ስድስት ገዢ አገራት ጋር ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ የሶስት ሚሊዮን ኩንታል ውል መፈረሙን መንግስት አስታውቋል። የረድኤትና ሌሎች የአገር ውስጥ ድርጅቶችም ከውጭ የሚገዙትን ስንዴ በአገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት በመፈረም ላይ እንደሆነም እየተገለጸ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ሒደት ነው።
መንግስት ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሲነሳ በቂ ጥናት አድርጓል፤ የስንዴ ምርት ምን ያህል እንደሆነና የአገራችን የምግብ ፍጆታም ደግሞ ታይቷል። ከዚህም አንጻር ከአገራችን ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ስንዴ እንደሚኖር ተረጋግጧል።
ብዙዎች ‹‹ሊሳካ አይችልም›› ሲሉ ያሟረቱበት የስንዴ ልማት እውን ተደርጓል፤ አገራዊ የስንዴ ፍጆታን ከመሸፈን አልፎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ ተሳክቷል። እነዚህ በስንዴ ልማቱ የተሳለቁ ሁሉ ጆሯቸው እየሰማ፣ አይናቸው እያየ፤ ወገንና ወዳጅ የሆኑቱ ደግሞ ደስ እያላቸው በያዝነው ዓመት አጋማሽ ላይ ስንዴን ወደ ውጭ የመላክ ስራ በይፋ ተጀምሯል። የስንዴ ምርት ወደ ውጭ የመላክ ጅማሬውም በምርታማነቷ ከምትታወቀው ኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ተደርጓል።
የስንዴ ምርትን በውጭ ምንዛሬ እየገዙ ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና ስንዴ አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ መካከል እጅግ በጣም ሰፊ ልዩነት አለ፤ ስንዴ ማስገባት ለተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ሊውል የሚችልን የውጭ ምንዛሬ ለስንዴ ግዥ ማዋልን ይጠይቃል፤ ይህ ብቻም ሳይሆን የስንዴ ምርት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ተረጂነትንም ሊያመለክት ይችላል። ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ወገብን አስሮ መስራት የሚያስከብር መሆኑን ከማሳየት ባሻገር ይነስም ይብዛ የውጭ ምንዛሬን ያስገኛል። ከዚህ ጎን ለጎን በስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረብ ላይ ሲጠራጠሩ የነበሩ የዋሆችን አተያይ በመቀየር በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ደጋፊ እንዲሆኑ ማድረግም ያስችላል።
ብዙዎች እንደዋዛ ያዩት ሕልም እውን ሆኗል፤ ይህ ደግሞ ጅማሬ ነው፤ ስራው በስንዴ መላክ ብቻ አይገደብም። መንግስት የያዘው ውጥን ትልቅ ነው። ውጥኑንም አክብሮ ለውጤታማነት ሳያሰልስ ጥሯል። ይህ የአሁኑ ስኬት መንደርደሪያው ሲሆን፣ በቀጣይ በስፋት እንደሚሰራ እምነቱ አለኝ።
የትኛውም አገር የትኛውንም አይነት ምርት ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ ተርፎት አሊያም በአገር ውስጥ ከበቂ በላይ ምርት በመኖሩ እንዳልሆነ ከአንባቢዎች የተሰወረ ምስጢር እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። በእኛም አገር የሆነው ይኸው ነው። የስንዴ ፍላጎታችንን በራስ አቅም ለማሟላት መጣር አንድ ነገር ሲሆን፣ ከራሳችን አልፈን በስፋት ማምረት የምንችልበት ጊዜም ሩቅ አለመሆኑን የተደረገው ጥረትና የተገኘው ስኬት አመላክቶናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ በተጀመረበት መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት ‹‹ባሌ ላይ ያየነው ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ሂደት ለኢትዮጵያ ማድረግ ከሚገባን ትንሹ ስኬት ነው›› ቢሉም ጅማሮው ታላቅ ስኬት ነው። ‹‹አይቻልም፤ አይሳካም›› ባሉት ዘንድ ደግሞ ቅዠት ያሉት እውን መሆኑን ያመላከተ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አግራሞትንም ያጫረ ነው። በእርግጥም ቅዠት የተባለው ሕልም እውነት ሆኗል። ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያውያኑን አስደስቷል፤ አኩርቷልም። ለዓለምም የኢትዮጵያን ተናግሮ ፈጻሚነት ማሳየት አስችሏል።
ወጋሶ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም