የየካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በብዙ ታሪካዊ ክስተቶች የታጨቀ ነው። ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ያሉ የኢትዮጵያ ታሪኮች የተመዘገቡበት ነው። ወርሃ የካቲት ‹‹የጥቁሮች ታሪክ›› በመባልም የሚታወቅ ነው። የጥቁር ሕዝቦች የመብት ማስከበር ታሪኮች የሚነገሩበት ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው ይህን ወር ገናና የሚያደርገው የዓድዋ ታሪክ ነው። ስለዓድዋ ጊዜው ሲደርስ የምናወራ ይሆናል። ከዚያ በፊት የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያም የየካቲት ወር ሌላው መለያ ነው። የካቲት 26 የካራማራ የድል ታሪክም አለ።
ወደ አገር ውስጥ ጉዳዮች ብቻ ስንመጣ ደግሞ የካቲት 11 የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ምሥረታ ታሪክ አለ። በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ንጉሣዊ ሥርዓቱን ለመጣል የተቀጣጠለው የደርግ አብዮት የተጀመረውም በዚሁ በወርሃ የካቲት ነው።
ከእነዚህ የየካቲት ታሪካዊ ክስተቶች የወሩን ስም የያዘው ‹‹የየካቲት አብዮት›› የሚባለው ነው። ይህ አብዮት በወርሃ የካቲት ስለተቀጣጠለ በ1፣ በ2፣ በ3፣ ወይም በ20 ምናምን ተብሎ ሳይሆን የሚገለጽ በጥቅሉ የየካቲት አብዮት ተብሎ ነው የሚገለጽ።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ49 ዓመታት በፊት በወርሃ የካቲት 1966 ዓ.ም የነበረውን የየካቲት አብዮት እናስታውሳለን።
በወርሃ የካቲት 1966 ዓ.ም አዲስ አበባ በታክሲ አሽከርካሪዎች፣ በመምህራን፣ በሠራተኞች፣ በወጣቶች፣ በተማሪዎች፣ በወታደሮች በጥቅሉ በሕዝባዊ አብዮት ተናወጠች። መሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ መብት፣ የሃይማኖት እኩልነት፣ የብሔሮች እኩልነት፣ የሴቶች እኩልነት ከፍ ተደርገው ተጮኸላችሁ፣ ተዘመራላችሁ።
የካቲት 1966 ዓ.ም የፈነዳው እሳተ ገሞራ አድማሱን አስፍቶ ኢትዮጵያ ለዘመናት የተዳደረችበትን የዘውድና የአፄ ሥርዓት የገረሰሰበት ሕዝባዊ አብዮት ተወለደ።
የካቲት አዝሎት የነበረው ሕዝባዊ ተስፋ መጠነ ሰፊ ነበር። በረሃብ ዘወትር የሚጠቃው ሕዝብ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገበው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ፣ ጤናው እንዲሟላ፣ ትምህርት ያልደረሰው ወገን ትምህርት እንዲያገኝ፣ የነበረው የትምህርት ሥርዓትም የተሟላና ከምርትና ከዕድገት ጋር የተያያዘ እንዲሆን፣ ንጹህ ውሃ፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ተስፋና ምኞትን ተሸክሞ ነበር።
እነዚህ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ደግሞ የካቲት ፖለቲካዊ ተስፋም አንግቦ ነበር። ማን እቅዱን ያወጣል? ማን እቅዱን ይተቻል? ማን እቅዱን ያስፈጽማል? ማንስ ተፈጻሚነቱን ይከታተላል? ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ሁሉ የካቲት ተስፋዊ መልስ ሰጥቶ ነበር።
ሥልጣን የሕዝብ እንዲሆን፣ አገሪቱ በሕዝብ በተመረጡ ዜጎች እንድትተዳደርና ሕዝባዊ መንግሥት እንዲመሠረት፣ ዳኝነት ፍትሃዊ በሆነና ነፃ በሆነ መልኩ እንዲስፋፋ፣ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች፤ ማለትም በፖለቲካ ድርጅትም ሆነ በሠራተኛ ማኅበር የመደራጀት መብት እንዲከበር፣ በነፃነት የመጻፍ፣ የመወያየት … ወዘተ መብቶች ያለገደብ እንዲከበሩ የካቲት ተስፋውን ሰንቆ ነበር።
የካቲት 1966 ኢትዮጵያውን ለመለወጥ የትግል ችቦ የተለኮሰበት፤ አርሶ አደሮች ከባላባታዊ የጭሰኝነት ሕይወት ለመላቀቅ ያመጹበት፣ ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ የተጠየቀበት፣ መምህራን አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ «ሴክተር ሪቪው»ን የተቃወሙበትና በማህበራቸው ደህንነት የሞገቱበት፣ ታክሲ ነጂዎች በነዳጅ ጭማሪ ምክንያት ሥራ ያቆሙበት፣ ሙስሊሞች የሃይማኖት እኩልነት ብለው በአደባባይ ሰልፍ የወጡበት፣ ተማሪዎችና ተራማጅ ኃይሎች ‹‹መሬት ለአራሹ›› መፈክርን ከፍ አድርገው ሥር ነቀል ለውጥ የጠየቁበት ነበር።
የየካቲቱ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ወደ ወታደራዊ አብዮት ተሸጋገረ። በሦስት ወር ጉዞውም የንጉሱን 60 ሹማምንት ያለፍርድ ገድሎ በርካታ እርምጃዎችን ወሰደ። ንጉሱን ከስልጣን በማውረድ እራሱን ደርግ ብሎ በመሰየም ብቸኛው የኢትዮጵያ መንግስት ፈላጭ ቆራጭ ሆነ።
አማካሪዎቹም በዚሁ ሹም ሽር ከስልጣን ተካፋይነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ አማካሪነት ወረዱ። በዚህ ሁኔታ የመጣው ደርግ 17 ዓመት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር መጀመሪያ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› በኋላ ‹‹ሶሻሊስት ሪፑብሊክ›› እየፈጠረ ቢሄድም እየቆየ ግን እሱም በተራው ተቃዋሚዎች ተፈጠሩበት።
በዋና ተቃዋሚነት ኢሕአፓ በደርጉ ስርም እነ መኢሶን፣ ወዝ ሊግና ሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ የአብዮት ተውኔት መድረክ ላይ ያዋጣል ያሉትን የትግል ስልትና ዘዴ ቢከተሉም የደርግ መንግስት ወታደራዊ ባህሪው አይሎበት ሲጨፋጨፉ ቆይተዋል።
የደርግ መንግስት በተራው በስልጣን ዘመኑ የተነሱትን አበይት ጥያቄዎች ለመመለስ ከሰላም ውይይት ይልቅ ጦር ሰባቂ ጎራዴ ታጣቂ በመሆኑ ዘመኑን ሙሉ አገሪቱን ያላባራ ጦርነት ውስጥ ከተታት።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉት፤ ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት ደርግ ከያዘው ርዕዮት ጋር ለመተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ከማንም ያላነሰ ክህሎት አለኝ ለማለት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት ቀድሞ ከሚገኘው የግራ ክንፍ ኃይል ጋር ለመስተካከልና ብሎም ለማለፍ የነበረው ትግልና ጥረት ቀላል አልነበረም፤ ጥረቱም ተሳክቶ በሚያዝያ 1968 ዓ.ም ደርግ የመጨረሻውን ርዕዮተ ዓለማዊ እመርታ በማድረግ፣ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን በመመሪያነት አወጀ። በዚህ ድርጊቱም እየቀደመ ሲያስቸግረው ከነበረው የግራ ክንፍ የፖለቲካ ቡድን ጋር ተስተካከለ ማለት ይቻላል። ከዚያ የሚቀጥለው እርምጃ ራሱን የሰፊውንና የጭቁኑን ሕዝብ ትግል በግንባር ቀደምነት ለመምራት በታሪክ የታጨ ብቸኛ የፖለቲካ ኃይል አድርጎ ማየቱ ነው።
ይህን አስደናቂ የደርግ የርዕዮተ ዓለም ጉዞ ካሰመረለት አንዱ፤ የግራ ክንፉ ተከፋፍሎ ወደ አብዮቱ መድረክ መውጣት ነው። በተለይም ከሀገር ውጭ የሚገኘው የተማሪው ንቅናቄ አካል አብዮቱ ሲፈነዳ በሁለት አክራሪ ጎራዎች ተሰልፎ ነበር። ኋላ ገሀድ እንደ ወጣው እነዚህ ሁለት ጎራዎች የኢሕአፓና የመኢሶን ድርጅቶች ተከታዮች ነበሩ። እነዚህ ሁለት አንጋፋ የግራ ክንፍ ኅቡዕ ድርጅቶች በተማሪ ድርጅቶች ሽፋን ደጋፊዎቻቸውን ማብዛትና ማጠናከር ተያይዘው ነበር። በአብዮቱ ዋዜማ ሁለቱ ጎራዎች በዓለም አቀፉ የተማሪዎች ድርጅት አወቃቀር ላይ ሳንጃ ቀረሽ ክርክር እያደረጉ ነበር። የኢሕአፓ ወገኖች በአዲስ መልክ የተዋቀረውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን ሲደግፉ፣ የመኢሶን ተከታዮች ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር የነበረው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር እንዲቀጥል ይሟገቱ ነበር።
በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ያለው ደርግ ‹‹ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ›› ዘመቻውን በተለያዩ ዘርፎች ማጧጧፍ ቀጥሏል።
እንዲህ እንዲህ እያሉ ነጭና ቀይ ሽብር የሚባሉ የሽብር ድርጊቶች ተፈጥረው የደርግን ታሪክ የጦርነት ታሪክ አደረጉት። በመጨረሻም ደርግ በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይና አጋሮቹ በመሰረቱት ኢህአዴግ ተወግዶ መሪው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሀገር ተወሰዱ። እነሆ የየካቲት አብዮትም የዚያ ታሪክ አካል ሆነ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም