በኢንዱስትሪ ማእከልነት ከሚታወቁት የአገሪቱ ከተሞች አንዷ የኮምቦልቻ ከተማ መሆኗ ይታወቃል። ከተማዋ በኢንዱስትሪ ከተማነቷ ፊትም ትታወቃለች፤ አሁንም በኢንዱስትሪ ማእከልነቷ ቀጥላለች።
በ1943 ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት የቀድሞዋ ‹‹ቢራሮ›› የአሁኗ ኮምቦልቻ ከተማ፣ ከ 1965 ዓ.ም ጀምሮ በማስተር ፕላን የምትመራ ዘመናዊ ከተማ ሆናለች። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሪጂኦፖሊታን ከተማ አስተዳደር መዋቅር እየተዳደረች የምትገኝ ሲሆን፣ በ14 የከተማ እና በስድስት የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረችም ናት። በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ያላትም ናት። በተለይ በውሃ አቅርቦት በኩል ስማቸው በበጎ ከሚነሱ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ ናት።
ኮምቦልቻ ለኑሮ ምቹ መሆኗ እንዳለ ሆኖ በእጅጉ የምትታወቀው ግን በኢንዱስትሪ መነኸሪያነቷ እና የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷ ነው። ከተማዋ የበርካታ አምራች ድርጅቶች መገኛ ናት። ከአዲስ አበባ በደሴ አርጎ ወደ ትግራይ የሚዘልቀው ዋና መንገድ ከሞቦልቻን ሰንጥቆ ነው የሚያልፈው። በከተማዋ የሚገኙት የደረቅ ወደብ (በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያ ስገኝ)፣ የአውሮፕላን ማረፊያና የኢንዱስትሪ ዞን እንዲሁም በከፊል የተጠናቀቀው የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሀራ ገበያ የባቡር ሃዲድ ኮምቦልቻን ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ካደረጉ ምክንያች መካከል ይጠቀሳሉ፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተማዋን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያስተሳስራትና የደረቅ ጭነት መተላለፊያ የሆነ አውራ ጎዳና መኖሩ ለኢንዱስትሪ መነኸሪያነቷ ትልቅ ሚና እንዳለው ይታወቃል።
ከተማዋ ለተለያዩ ትላልቅ ከተሞች ያላት ቅርበትም ሌላው ተፈላጊ የሚያደርጋት ነው። ለጅቡቲ ወደብ 440 ኪሎ ሜትር፣ ለአዲስ አበባ በ375 ኪሎ ሜትር፣ ለአሰብ ወደብ በ390 ኪሎ ሜትር፣ ለሰመራ ከተማ በ 161 ኪሎ ሜትር ለክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር ደግሞ በ505 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መገኘቷም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል።
በመልካም የኢንቨስትመንት መነቃቃትና ጉዞ ላይ የነበረችው ኮምቦልቻ፣ የሰሜኑ ጦርነት ለከፍተኛ ውድመት ዳርጓታል። የሰሜኑ ጦርነት በኮምቦልቻ ከተማ ከ 10 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት ማስከተሉን መረጃዎች ያመለክታሉ። በርካታ የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውድመቱ ሰለባ ሆነዋል። በአብዛኛው ንብረትነታቸው የኢንቨስተሮች የሆኑ ከ270 በላይ ኮንቴይሮች ከኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ተዘርፈዋል። ከገንዘብ በተጨማሪ ከተማዋ ከፍተኛ ማኅበራዊ ውድመትም ደርሶባታል።
ከዚህ የጦርነቱ ውድመት በማገገም የኮምቦልቻን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለማስቀጠል የከተማዋ አስተዳደር ከአማራ ክልል መንግሥትና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊታን ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ኃይሌ ስለከተማዋ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣ በተለይም ስላለፉት ስድስት ወራት የኢንቨስትመንት ዘርፍ አፈፃፀም፣ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ኢንቨስትመንት በኮምቦልቻ
በኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊታን ከተማ ከ 53 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 519 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 885 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ ናቸው። በማምረት ላይ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ግንባታ አጠናቀው በማሽን ተከላና መሰል ሂደቶች እንዲሁም በግንባታ እና በቅድመ ግንባታ ደረጃዎች ላይ የሚገኙም አሉ። በአምራች፣ በኮንስትራክሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝም እና በማኅበራዊ ዘርፎች ላይ የተሰማሩት የኮምቦልቻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች፣ ከስምንት ሺ700 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በ2015 በጀት አመት ባለፉት ስድስት ወራት ስድስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 46 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል። ፈቃድ የወሰዱት ፕሮጀክቶች ከ 17ሺ 990 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም የ 182 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ፍቃድ ማደስም ተችሏል።
የኮምቦልቻ የኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫዎች
የኮምቦልቻ ሪጂኦፖሊታን ከተማ ዋነኛ የኢንቨስትመንት የትኩረት ማዕከል የአምራች ዘርፍ ኢንቨስትመንት ነው። ከዚህም መካከል የጨርቃ ጨርቅ እና የምግብ ማቀነባበር ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው። ዘርፎቹ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው ከተማዋ መሰል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለመሳብና ለማስተናገድ ልዩ ትኩረት ትሰጣለች።
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎና ማበረታቻዎች
በኮምቦልቻ ከተማ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። ከአምራች ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል በውጭ ባለሀብቶች የተያዙት ሰባት ብቻ ናቸው።
የጦርነቱ ውድመትና የማገገሚያ ተግባራት
ኮምቦልቻና አካባቢው በሰሜኑ ጦርነት በእጅጉ እንደተጎዳ ይታወቃል። ጦርነቱ በኮምቦልቻ ከተማ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት አስከትሏል። በርካታ የአምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውድመቱ ሰለባ ሆነዋል። ጉዳት የደረሰባቸው አምራቾች ከዚህ ውድመት እንዲያገግሙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። በቅድሚያ ተቋማቱ የደረሰባቸውን ጉዳትና ችግሮቻቸውን ማጥናት አስፈላጊ በመሆኑ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ከክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመተባበር የተቋማቱን ጉዳት የማጥናትና ችግሮቻቸውን የመለየት ተግባሮች ተከናውነዋል። በተጨማሪም ከባንኮችና እርዳታ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ትስስር ፈጥረው የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረቶች ተደርገዋል። ባለሀብቶቹን ወደ ስራ እንዲመለሱ የሚያበረታቱ በርካታ የማነቃቂያ ሥልጠናዎችም ተሰጥተዋል።
የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን በመለየትና በተደጋጋሚ መድረክ በመፍጠር መግባባትና የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የመግባት፤ ነባር ኢንቨስተሮችን ዳግም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለይቶ የመመልመል እና ወደ ተግባር እንዲገቡ የማድረግ እንዲሁም ለአራት ጊዜያት ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ፓናሎችን በማካሄድ ለኢንቨስተሮችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት ተከናውነዋል።
ውድመት ደርሶባቸው ስራ ያቆሙ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲመለሱ ለማድረግና ለማበረታታት የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት መድረክ በመፍጠር ወደ ስራ እንዲመለሱ የሚያስችል ጥረት እየተደረገ ነው። ዘወትር ማክሰኞ የከተማዋ ከንቲባ የከተማዋን ኢንቨስትመንቶች በመጎብኘት የማበረታታት፣ ችግሮቻቸውን የመመልከትና የመፍታት ተግባራትን ያከናውናሉ። ነባር ባለሀብቶች ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን እንዲገነቡም ይበረታታሉ። ከዚህ በተጨማሪም የገጽ ለገፅ ፕሮሞሽን ስራዎችም ይከናወናሉ፤ ይህም ውጤታማ የሆኑ ዘርፎች ስራቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስራቸው እንዲጨምር ያስችላቸዋል፤ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ የገፅታ ግንባታ ስራ ለማከናወን ያግዛል።
ከወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበርም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባራት የሚሰጡ ሲሆን፣ አምራቾች አገልግሎቱን የሚያገኙት በቴክኒክ ክህሎት፣ በጥራትና ምርታማነት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በስራ ፈጠራ ማዕቀፎች ነው።
ከጦርነቱ ውድመት ለማገገም የተሰሩ ስራዎች ውጤቶችን አስገኝተዋል። ከ44 መካከለኛና ከፍተኛ አምራቾች መካከል 36 አምራቾች ወደ ስራ ተመልሰዋል። ከእነዚህ ተቋማት መካከል አስሩ በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ይገኛሉ፤ እነዚህ ድርጅቶች ቀደም ሲልም ጠንካራ አቅም የገነቡ ስለነበሩ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሊመለሱ ችለዋል። ሌሎቹ ወደ ስራ የተመለሱት ተቋማት እየሰሩ ያሉት ደግሞ ከ55 እስከ 60 በመቶ በሚሆነው አቅማቸው ነው። ስምንት ተቋማት ግን እስካሁን ወደ ስራ አልተመለሱም፤ወደ ስራ እንዲመለሱ የሚያስችላቸውን የማገገሚያ ብድርም አላገኙም።
የአገልግሎት አሰጣጥ ዝግጁነት
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችለውን የአሰራር ሥርዓት እየተገበረ ይገኛል። ለአብነት ያህል የከተማዋ ከንቲባ በየሳምንቱ ማክሰኞ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ጉዳዮችን ይመለክታሉ። በዕለቱ የኢንቨስትመንት ባለጉዳዮችንና ቅሬታዎችን ያስተናግዳሉ፤ የኢንቨስትመንት ተግባራትን ይጎበኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም የከተማዋ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ የመስክና የቢሮ አገልግሎቶችን በመዘርጋት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች
የኮምቦልቻን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለማስቀጠልና በጦርነቱ ባደረሰው ጉዳት የታጣውን ለማካካስ ከከተማዋ ቀጣይ የኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ የአምራች ዘርፉን ማጠናከር ነው። በተለይም ለግብርና ማቀነባበርና ለጨርቃ ጨርቅ ምርት ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል። እነዚህ ዘርፎች ብዙ የሥራ እድሎችን የሚፈጥሩ እና ለወጪ ንግድም ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ በመሆናቸው በዘርፎቹ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከ180 እስከ 200 ሄክታር መሬት እንዲዘጋጅ ይደረጋል። የክልሉ መንግሥት የኢንቨስትመንት መሰረተ ልማቶችን ያሟላል።
የኢንቨስትመንት መሰናክሎች
በኢንቨስትመንት መነኸሪያነቷ የምትታወቀው ኮምቦልቻ ከተማ በተለይም የሰሜኑ ጦርነት ባደረሰው ውድመት ምክንያት በኢንቨስትመንት ስራዋ ላይ እክል የሚፈጥሩ መሰናክሎች አሉባት። ከእነዚህም መካከል ክልሉ በጦርነቱ በመጎዳቱ ምክንያት ከሦስተኛ ወገን የፀዳ (ክልሉና ከተማዋ በራሳቸው አቅም) የካሳ ክፍያን እንዲሁም የመሬት፣ የመሰረተ ልማትና የፋይናንስ አቅርቦትን እውን በማድረግ ረገድ ያለው ክፍተት ተጠቃሽ ነው። የአምራች ዘርፉ ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ወደ ስራ እንዲመለስ የሚያስችለውን በቂ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ አለማግኘቱም በቀጣይ ጊዜያትም ተፅዕኖው እንዲቀጥል የሚያደርግ ጥል ሌላው መሰናክል ነው።
የፋይናንስ ተቋማትና የኢንቨስትመንት ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች ልዩ አሰራር በመከተል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መደገፍ ይኖርባቸዋል፤ መደበኛው አሰራር በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙና ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት በፍጥነት ወደ ስራ እንዲመለሱ የማድረግ አቅሙ የተገደበ በመሆኑ የተለየ አሰራር መከተልና መተግበር ያስፈልጋል። ከፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ጋር በተደረገ ምክክር ለ15 የአምራችና አገልግሎት ሰጪ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጓል። በየጊዜው የሚታዩ ለውጦች ቢኖሩም በርካታ አምራቾች አሁንም በቂ ብድርና እንደማሽን ያሉ ሌሎች ግብዓቶችን አላገኙም። በጦርነት ለወደሙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የተለየ የድጋፍና የአሰራር ሥርዓት በመንግሥት በኩል አለመነደፉና ማበረታቻ አለመዘርጋቱ በከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም