ወቅታዊውን የኑሮ ውድነት በማስመልከት ሃሳቤን በጥያቄ ልጀመር። ለእናንተ ኢትዮጵያዊነት ምንድነው? በዚህ ታላቅ ጥያቄና መልስ ውስጥ ራሳችሁን አስቀምጣችሁ ተከተሉኝ:: ሀገር የታማኝ ልቦች ነጸብራቅ ናት:: ብዙ እውቀት ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ማስተዋል ሊኖረን ይችላል እንደ ሀገርና ሰው ጥበብና እውቀት ግን አላውቅም:: ከትላንት እስከዛሬ በዚህ እውነት ውስጥ የኖርን ህዝቦች ነን:: ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ እኔን የሚገርመኝ እናንተንም የሚገርማችሁ አንድ የጋራ እውነት አለን። እርሱም ተካፍሎ የመብላት ባህላችን መሆኑ ነው:: ይሄ እኔና ሌላውን ዓለም የሚያስደንቀን ጥልቅ..ምጥቅ እሴታችን ነው:: በዚህ ባህላችን ብቻ ከዓለም እና ከታሪኳ ልዩዎች ነን:: ዓለም እኔነትን ባስቀደመበት..ብቻ መብላትን እንደ ስልጣኔና እንደ ዘመናዊነት በያዘበት ዘመን ላይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን በጋራ በመቆም፣ በጋራ በመብላት የማንነጣጠል ህዝቦች መሆናችንን ስናሳይ ኖረናል..እያሳየንም እንገኛለን::
ይህ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሌለ የሚያኮራና የሚያስደንቅ ኢትዮጵያዊ መልክ ነው:: ይህ ለሰው ልጅ ክብር የሰጠ አንድነትን ያስቀደመ የስልጣኔ አሻራ ነው:: ይህ የእኛ ብቻ የሆነ የድንቅ ስርዓት ውጤት ነው:: ሁሌም እንደምለው ስልጣኔ ራስን ከመውደድና የራስን እውነት ከመቀበል የሚጀምር ነው:: ሁሌም እንደምለው ዘመናዊነት ከራስ እውነት ተነስቶ ወደ ሌሎች የሚተላለፍ የአስተሳሰብ ውጤት ነው:: እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቀደምት ስልጡን ህዝቦች ስለመሆናችን በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ይሄ ሁሉ ባይሆን እንኳን አብሮ መብላታችን፣አብሮ መቆማችን በደስታና በሀዘናችን ጊዜ መረዳዳታችን ቀዳሚነታችንን ከማሳየቱም በላይ የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች እንደሆንን አንዱ አመላካች እውነታ ነው::
እኔ በግሌ እንደ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄና መልስ አላውቅም..እርግጠኛ ነኝ እናንተም አታውቁም:: ብዙ እውቀት፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ማስተዋል ሊኖረን ይችላል እንደ ሀገርና ሰው..እንደ ታሪክና ባህል እንደ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጥበብና ማስተዋል ግን የለንም..አይኖረንምም:: እንግዲህ ይቺን ነው ኢትዮጵያ የምላችሁ:: ይሄን ነው ኢትዮጵያዊነት የምላችሁ:: ይሄን ነው ሀገርና ታማኝ ልቦች ስል የማወጋችሁ:: ከነገርኳችሁ በላይ የምታውቁት ሀቅ አለ? ከሀገርና ሰው በላይ ምን ጥበብ ምን ልቀት አላችሁ? ከዚህ እውነት በመነሳት የሰሞኑን ከኢትዮጵያ ባህልና አብሮነት ያፈነገጠውን ሰሞነኛ እውነት ላውጋችሁ:: የሰሞኑ የኑሮ ውድነት ያላማረረው ማነው? እርግጠኛ ነኝ ሁላችሁም ተማራችኋል:: ከመማረርም ባለፈ የብዙዎቻችንን ህልውና እየተፈተነ ነው። ለዚህ ደግሞ እኔም እናንተም ምስክሮች ነን:: ይሄ እንዴት ሆነ? በማን ሆነ? ለምን ሆነ? ብለን ስንጠይቅ መልሱን እናገኘዋለን::
ኢትዮጵያዊነት ተካፍሎ መብላት ነው:: ኢትዮጵያዊነት የታማኝ ልቦች አብራክ ነው:: በዚህ እውነት ውስጥ ተወልደንና አድገን ነገር ግን በደጋግ ልቦች መሀል በበቀሉ የክፋት ልቦች የድሮ ጸዐዳ መልካችንን እያጣን ነው:: ክፋትንና እኔነትን በለመዱ..ሌብነትንና ስግብግብነትን በተማሩ አንዳንድ ነጋዴዎች የጥንት ፍቅራችንን እየተነጠቅን ነው:: ራስ ተኮር የሆኑ ወጪት ሰባሪዎች ሆን ብለው የኑሮ ውድነትን በመፍጠር በህዝቡ ላይ ግፍና በደልን እየሰሩ ነው.. በተለይ ድሀው ማህበረሰብ በእነዚህ ውሸታምና አጭበርባሪ ነጋዴዎች ለስቃይ መዳረጉ ጎልቶ እየታየ ነው።
አላማቸውን ህዝብ ከማገልገል ይልቅ ያልተገባ ትርፍና ጥቅም ለማግኘት በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የታሪፍ ጭማሬ በማድረግ ጊዜውን ፈታኝ አድርገውታል:: ምርት በመደበቅ፣ በማሸሽና ሌሎች ማጭበርበሪያ መንገዶችን በመጠቀም ከመንግስት እውቅና ውጭ በሆነ አሰራር ራሳቸውን ሲጠቅሙና ድሀ ህዝብ ሲበዘብዙ ማየት አዲስ ነገር አይደለም:: ወቅታዊውን የሀገራችን ችግር እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሀብት በማጋበስና የኑሮ ውድነትን በመፍጠር መንግስትና ህዝብን ሆድና ጀርባ ለማድረግ እየሰሩ ያሉ የክፋ ልቦች እዚም እዛም ተሰግስገው ይገኛሉ:: የነዚህ ግለሰቦች ስውር አላማ የታወቀ ነው..በአንድ ላይ ሆነን እኚህን ህገ ወጦች በማጋለጥና ለህግ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ማስተካከል የሁላችንም ሀላፊነት ነው::
ለዘመናት አብሯቸው የኖረን ህዝብ በማገዝና በመደገፍ በዚህ ክፉ ቀን ላይ ውለታውን እንደመመለስ ዞሮ ጨካኝ መሆን ውለታ ከመብላት ባለፈ ነውረኛ ድርጊት ነው:: አብረው የማይኖሩ ይመስል..ይሄ ክፉ ቀን የማያልፍ ይመስል እንዲህ አይነት ያልተገባ ግፍ መስራት ተገቢ ሊሆን አይችልም። ይሄ ጊዜ ያልፋል..ሁላችንም የምንናፍቀው አዲስ ቀን ይፈጠራል፣ በዚህ የንጋት ዋዜማ ላይ እንደ አባቶቻችን ስርዓት እርስ በርስ መተጋገዝ እንጂ ሆድና ጀርባ መሆን የለብንም:: ይህ የኢትዮጵያዊነት መልክ አይደለም:: በዚህ ስርዓት ውስጥ አልመጣንም:: ይሄን የጭካኔ ተግባር አናውቀውም:: ስርአታችን አብሮ መብላት፣ አብሮ መጠጣት ነው:: ስርዓታችን ተካፍሎ መብላት ነው… ያለው ለሌለው መስጠት ነው::
ነውር የምናውቅ ህዝቦች እኮ ነን…ነውራችን የት ሄደ? ድሀን እንደማስጨነቅ..ከድሀ ላይ እንደመውሰድ እኮ ግፍና ነውር…ሀጢያትና በደል የለም:: የሰሞኑ የነጋዴዎቻችን ሁኔታ ከዚህ የዘለለ አይደለም:: ለድሀ እየሰጡ እንጂ ከድሀ እየነጠቁ ማደግና መበልጸግ በምድርም በሰማይም ያስጠይቃል። እድገት ያለው በመስጠትና በቸርነት ውስጥ ነው:: ሀብትና በረከት የሚመጣው ለድሀ ቸርነትን በማድረግ እንጂ ድሀን በማስጨነቅ አይደለም:: አካሄዳችሁን አስተካክሉ…ስራችሁ በእውነትና በእውቀት ህዝብን ማዕከል ያደረገ ይሁን:: እኛ ስንሰጥና ስናካፍል እንጂ ስንዘርፍና ስናታልል አልኖርንም:: እኛ በጋራ በመብላት በጋራ በመኖር እንጂ በውሸትና በማጭበርበር ራሳችንን ብቻ ስንጠቅም አልኖርንም:: እኛ የሌላውን ጎደሎ በመሙላት ተያይዘን የመጣን ህዝቦች ነን ይሄን ኢትዮጵያዊ እውነት አትሳቱ::
ኢትዮጵያዊነት የሚደበዝዝበት ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደምቆ የሚወጣበት ቀን ይመጣል። እንተጋገዝ…ይሄን ክፉ ጊዜ በመተሳሰብ ማለፍ እንጂ ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት የምናልፈው አይደለም:: ከእውነታችሁ አትውጡ…ከስርዓታችሁ አትሽሹ…አዲሱ ትውልድ ከእናንተ የሚማረው ብዙ ነገር አለና እባካችሁ መልካምነትን ተማሩ:: ለድሀ ወገናችሁ የምትቆሙበት…አለኝታነታችሁን የምታሳዩበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ናችሁ:: ርህራሄን የምትማሩበት፣ መልካምነትን የምትሹበት ሰሞን ላይ ናችሁ። በዚህ የጭንቅ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ርህራሄአችሁ ያስፈልጋል:: በጥቂት ራስ ወዳዶች መልካችን እየወየበ ነው፣ በጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች አንድነታችን እየተሸረሸረ ነው:: ወደቀደመ አንድነታችን፣ወደ ቀደመ ፍቅራችን እንመለስ ዘንድ ከእኔነት መውጣት ግድ ይለናል:: ያለዛ ኢትዮጵያ ታዝንባችኋለች…ያለዛ ለተዋችሁት ስርዓት በልጆቻችሁ በኩል ዋጋ ትከፍላላችሁ:: ይሄ ኢትዮጵያን ለማሻገር ለእኔና ለእናንተ ትክክለኛው ጊዜ ነው::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 6/ 2015 ዓ.ም