‹‹ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች አገር ናት›› የሚለው አገላለጽ በጣም ስለተደጋገመ ምናልባትም አሰልቺ ይመስል ይሆናል። ምናልባትም ለአንዳንዶች ራሳችንን ለማካበድ የምንጠቀመው ወይም የተለመደ ተረት ተረት ይመስላቸው ይሆናል። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን ለማሳየት ግን የሳይንስ ጥናትም ሆነ የፈላስፋ ጥቅስ መጥቀስ አያስፈልገውም። በየወቅቱ በዓለም መገናኛ ብዙኃን የምናየውና የምንሰማው ሀቅ ነው። የውጭ አገራትን የማየት ዕድል ያገኙ ደግሞ በዓይናቸው ያዩት ነው።
የሥልጣኔ ማማ ላይ ያሉ አገራት በከፍተኛ ሙቀት ወይም በከፍተኛ ብርድ ይጠቃሉ፤ በአየር ንብረት ምክንያት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያልፋል። በቅርቡ እንኳን በአሜሪካና የአውሮፓ አገራት ውስጥ ያየነው ይህንኑ ነው። ተሽከርካሪዎች ሥራ እስከማቆም የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ለዚያውም እነዚህ የበለጸጉ አገራት አለ የሚባለውን የሙቀትም ሆነ የቅዝቃዜ መከላከያ የሚጠቀሙ ናቸው።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የ13 ወር የፀሐይ ፀጋ ያላት አገር ናት። አልፎ አልፎ ሙቀትና ቅዝቃዜ ቢኖርም የሰው ሕይወት የሚቀጥፍና ተሽከርካሪን ሥራ የሚያስቆም ግን የለንም። በዚህ አየር ንብረት ምክንያት ብዙ አይነት የዕፅዋትና አዝርዕት አይነቶች አሉን። በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የእንስሳት አይነቶች አሉን። አስገራሚ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቦታዎች አሉን። ታዲያ ይህን ድንቅ ተፈጥሮ፣ ውብ ባህልና ትውፊት ለዓለም የምናስተዋውቀው መቼ ነው?
ምንም እንኳን አገርን ለማስተዋወቅ የጊዜ ገደብ ባይኖረውም የታኅሣሥና ጥር ወራት ግን የበለጠ ምቹ ናቸው። ምክንያቱም የገና እና የጥምቀት በዓላት አሉን። ሁለቱም የዓለም ሕዝብ የሚመለከታቸው ናቸው። ገና የዓለም ሀብት በሆነው ላልይበላ ይከበራል። ጥምቀት ደግሞ አከባበሩ ራሱ የዓለም ሀብት ሆኗል።
እነዚህ በዓላት የሚከበሩት ከሚከበሩበት ቀን ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት እና የሚከበሩበት ቀን ካለፈም በኋላ ነው። ለምሳሌ ለገና የመጡ የውጭ አገራት እንግዶች የመጡት ቀደም ብለው ነው። አሁንም ይኖራሉ። የፊታችን ጥር 11 ለሚከበረው የጥምቀት በዓልም እንግዶች ከወዲሁ መግባት ይጀምራሉ።
የዘንድሮውን በዓላት ደግሞ ለየት የሚያደርጋቸው የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሲያስፈራሩበት የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እልባት አግኝቶ ሰላም በሰፈነ ማግስት መሆኑ ነው። እግረ መንገዳቸውንም ‹‹ይህን የመሰለ ሰላም ያለበት አገር ነው እንዴ ጦርነት ነበረበት የተባለ!›› ብለው እንዲገረሙ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ሁነቱም ይሄንኑ ያደርጋል።
ምክንያቱም አገራችንን የምናስተዋውቃት በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው። ምናልባት ብዙዎቻችን ለውጭ ዜጎች አገርን ማስተዋወቅ የአስጎብኚዎች ሚና ብቻ ይመስለናል። ሆኖም በአገሩ ጉዳይ ማንም አስጎብኚ ነው። ለውጭ አገራት ዜጎች ተገቢውን መረጃ መስጠት የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
ይህን ለማለት የተገደድኩበት ምክንያት በብዙ ቦታዎች የምታዘበው ነገር ስላለ ነው። ባረፍንበት ቦታ፣ በገባንበት ካፌ፣ በምንጓዝበት ተሽከርካሪ ውስጥ እንዲሁም በዓላቱ በሚከበሩባቸው ቦታዎች ላይ የውጭ ዜጎችን እናያለን። ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ለእነዚህ የውጭ ዜጎች ያላቸው አቀባበልና መረጃ አሰጣጥ ልክ አይደለም።
እርግጥ ነው የቋንቋ ገደብ ይኖራል፤ ችግሩ ግን የቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአመለካከትም ጭምር መሆኑ ነው። አንዳንዱ ልክ እንደ ኩራት በማየት ለነጭ አልለማመጥም አይነት ምልክት ያሳያል። ሆኖም እንግዳን መንከባከብ ፍርሃት ወይም ባርነት ሳይሆን ትህትና ነው። አዎ! በቅኝ ያልተገዛን፣ ወራሪን አሳፍረን የመለስን፣ የራሳችን ማንነት ያለን ነን። ይህን የምናሳየው ግን እንግዳ ሆኖ በመጣ አካል ላይ አይደለም።
እዚህ ላይ ባለፈው ዓመት የተከሰተ የአንድ ግለሰብ ገጠመኝ ልጥቀስ። ግለሰቡ ከአንዲት ሴት ጋር ካፌ ውስጥ ቁጭ ብሏል። ወደ መታጠቢያ ክፍል እንደሄደ አራት የውጭ ዜጎች ወደ ካፌው መጡ። ካፌው ውስጥ ያሉ ቦታዎች ተይዘው አራት ሰው መያዝ የሚችል ያለው እኚህ ሴትና ወንድ የተቀመጡበት ቦታ ብቻ ነው።
የካፌው ባለቤት ይሁን ሥራ አስኪያጅ በትህትና ወደ ልጅቷ ሄዶ ‹‹እናንተ ሁለት ስለሆናችሁ እዚያች ጋ ብትቀመጡ›› ብሎ ነገራት። ልጅቷም ተነስታ ሁለት ሰው ብቻ ወደሚይዘው ወንበር ሄደች። ልጁ ከመታጠቢያ ክፍል ሲመለስ ቦታ ቀይራለች። ‹‹ምነው?›› ሲላት የሆነውን ነገረችው። በፊት የተቀመጡበት ቦታ ላይ የውጭ ዜጎችን ሲያይ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ። እንደ ዓድዋ ያሉ የታሪክ ድሎችን መዘርዘር ጀመረ። ‹‹ኧረ ባክህ ይሄ ከእርሱ ጋር አይገናኝም!›› ቢባል ሊሰማ አልቻለም። በመጨረሻም ካፌውን ለቆ ሄደ።
እስኪ ይህን ነገር በቅንነት እንየው! እንግዶቹ አራት ናቸው፤ እነዚህኞቹ ደግሞ ሁለት ናቸው። ታዲያ ቦታ ቢቀይሯቸው ምን ችግር አለው? በዚያ ላይ የውጭ ዜጎች አይደሉም ተነሱልን ያሉት፤ የካፌው ባለቤት ነው በትህትና የጠየቃቸው። በትህትና መጠየቁን ደግሞ ያዙኝ ልቀቁኝ ያለው ልጅ ራሱ አምኗል።
እንዲህ አይነት ስሜቶችን እንደ አገር ፍቅር አላያቸውም! እንዲያውም አገርን እንዴት ማስተዋወቅ እንዳለብን አለማወቃችንን ነው የሚያሳየው። አዎ! አገርን ለማስተዋወቅ ባሪያ እና አጎብዳጅ መሆን የለብንም፣ ለፈረንጅ መስገድ የለብንም፤ ዳሩ ግን አግባብ ባልሆነ ሁኔታ መፎከር ደግሞ ኋላቀርነትን እንጂ ሥልጣኔን ወይም ኩሩነትን አያሳይም።
አገርን ማስተዋወቅ ምርትና አገልግሎትን እንደማስተዋወቅ ነው። የሰዎች አዕምሮ ውስጥ መሥራት ነው። ማስተዋወቅ ደግሞ አወንታዊ ጎኖችን ለይቶ ማጉላት ማለት ነው። በለጸጉ በሚባሉ አገራትም እያየነው ያለነው ይህንኑ ነው። በፊልሞቻቸውና በባህላቸው ውስጣችን ገብተዋል። በፊልሞቿና ባህሏ የምንወዳት ሕንድ የድሃ ድሃ የሚባሉ ሕዝቦች ያሉባት ናት። በየዘጋቢ ፊልሞች እንደምናየው እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የችግር ኑሮ የሚኖሩ ዜጎችም አሏት፤ ዳሩ ግን በሰራችው ራስን የማስተዋወቅ ሥራ ህንድ የምትታወቀው በዚህ አይደለም።
የዓለም ልዕለ ኃያል የምትባለው አሜሪካ የመማሪያ ክፍል ውስጥ የጦር መሳሪያ የሚያዝባት ናት። በዚህ ሳምንት እንኳን አንድ የስድስት ዓመት ሕጻን መምህሩን በሽጉጥ አቁስሏል። ይህ በተደጋጋሚ የሚሰማ ሃቅ ነው። እንዲያውም የቀድሞ ፕሬዚዳንቷ ዶናልድ ትራምፕ መምህራኑን አስታጥቃለሁ ሲሉ ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አሜሪካ የምትታወቀው የሥልጣኔ ጣሪያ በመሆኗ ነው።
እንዲህ ተፈጥሮ አድሎን፣ ሰው ሰራሽ ችግሮቻችን ግን ኋላቀር አድርገውናል። ስለዚህ ከእነዚህ ችግሮች እንላቀቅ። አገራችንን በበጎ እናስተዋውቅ። ለዚህ ደግሞ እንደ ገና፣ ጥምቀትና መስቀል የመሳሰሉ በዓላት ምቹ ናቸው። አገርን ማስተዋወቅ ሲባል ግን የግድ እነዚህን ቀናት ብቻ መጠበቅ አይደለም። ቀደም ሲል እንዳልኩት በየትኛውም አጋጣሚ ለምናገኛቸው እንግዶች ተገቢውን መረጃ መስጠት ነው።
በዚህ ረገድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ አንድ ልብ ያልኩት ነገር አለ። የውጭ ዜጋ የሆኑ መምህራን ገና ወደ ክፍል የገቡ ቀን የመጀመሪያ ሥራቸው ስለአገራቸው መናገር ነው። የአገራቸው ምርት የሆኑ ነገሮችን ከቦርሳ እያወጡ ይሰጡናል። በተለይም የአውሮፓ አገራትና የህንድ ዜጎች ይህን ነገር በሚገባ ይጠቀሙታል። እናም እኛ ኢትዮጵያውያን ቦታ እና ጊዜ ሳይገድበን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ አገራችንን እናስተዋውቅ!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015