ሰፈራችን ውስጥ ለቤታችን የቀረበ አንድ አጥቢያ አለ። ጠዋት አይሉ ማታ ቄሱ በማይክራፎኑ ውስጥ ለዛ ሁሉ ለተሰበሰበ መዕምን ‹መታዘዝ ከሰነፍ መስዋዕት ይበልጣል› ሲሉ እሰማለው። በቅስናቸው ውስጥ የያዙት አንድ ቃል እሱ ይመስል ተኝቼ በነቃሁ ቁጥር የምሰማው ይሄኑኑ ቃል ነው። አያቴ ግን ትወዳቸዋለች። ያን የቄሱን የስብከትም ሆነ የቡራኬ ድምጽ በቤቷ ውስጥ ኮሽ ሳይልባት ትንፋሻን ውጣ ነው የምታደምጠው። እኔ ግን ‹እይ እኚህ ደግሞ ከመታዘዝ ውጪ ሌላ ቃል አያውቁም እንዴ? ስል በውስጤ አርጎመጉምባቸዋለው።
ከአያቴ አጠገብ ስለማልጠፋ በግድም ቢሆን የቄሱን ስብከት መስማት ግድ ነበረብኝ። እየቆየሁ ስመጣ ቄሱ ይናፍቁኝ ጀመር። ሳላውቃቸው አፈቀርኳቸው። አያቴ በእርጅና ምክንያት ሰውነቷ ስለማይታዘዝላት ብዙም ቤተክርስቲያን አትሄድም..ከእሷ ውጪ ይዞኝ የሚሄድ ስለሌለ ያፈቀርኩትን የቄሱን መልክ ሳላየው ሰነበትኩ።
ከቄሱ ሰምቼ ይሆን እንጃ መታዘዝ ለመድኩ። በተለይ ለአያቴ ሲሆን ሌላ ነኝ። ገና ስሜን ልትጠራ..ም..ስትል በርሬ አጠገቧነኝ። በልጅነቴ ለአያቴ ከታዘዝኳቸው ትዕዛዞች ውስጥ ሚዛን የሚደፉት ‹ሂድ..ና› የሚሉ ትዕዛዞች ናቸው። አያቴ ‹ሂድ› እና ‹ና› ሳትለኝ ቀርታ አታውቅም። ነፍሴ ከአያቴ ትዕዛዝ እፎይ የምትለው ማለዳ በቄሱ ስብከት ስትጠመድ ነው።
‹ምዕራፍ..አንተ ምዕራፍ? ትለኛለች ዝግ ባለ ድምጽዋ ወደ መምጫዬ እያስተዋለች።
‹አቤት! እላለው..በሆነ ነገር ተጠምጄ እንደ እስከዛሬዬ በርሬ ፊቷ ሳልቆም።
‹ና ወዲህ ምን እዛ ሆነህ አቤት ትለኛለህ? ስትል በትንሹ ቆጣ ትለኛለች።
የምሰፋውን የጨርቅ ኳስ እንደታቀፍኩ ወደ አያቴ እጠጋለው። ምን ልትለኝ ይሆን ብዬ አላውቅም..አያቴ ጠርታኝ ምን እንደምትለኝ አውቀዋለው። አራት ነገሮችን ነው የምታዘኝ..የመጀመሪያው እጅህን ሳትነክር የሚጠጣ ውሀ አምጣልኝ ነው። ቀጥሎ የተቀደደ ሸማዬን እጥፍበት
መርፌና ክር አምጣልኝ ነው። ሶስተኛው ራዲዮኑን ላመል ቀነስ አድርገው ስብከቱን ልስማበት ነው። የመጨረሻው እስኪ እማሆይ ቤት ሂድና እምነት ይዘህልኝ ና ነው። አያቴ ከነዚህ ከአራቱ ውጪ ለምንም ነገር አትፈልገኝም።
አያቴ ትገርመኛለች..በቀን ውስጥ ከነዚህ ከአራቱ አንዱን ሳታዘኝ ቀርታ አታውቅም። እጅህን ሳትነክር ውሀ አምጣልኝ ሳትለኝ አዛኝ አታውቅም። በጣም የሚገርመው ደግሞ እጄን ሳልነክር ውሀ ወስጄላት አለማወቄ ነው። ተሰፍቶ ያላለቀ ኳሴን በግራ ጎኔ ብብቴ ውስጥ ወሽቄ በቀኜ እጄን ሳልነክር ለአያቴ ውሀ ለመቅዳት እምክራለሁ። እጄን ላለመንከር የምጠነቀቀውን ጥንቃቄ ለምንም ተጠንቅቄው አላውቅም። ግን እነክረዋለው..ሶስት ጣቶቼ ውሀው ውስጥ እየተንቦራጨቁ ‹እንደተነከሩ› የቀዳሁትን ውሀ ለአያቴ አቀብላታለሁ። ‹አይ ያንተ ነገር..እጅህን አትንከር እያልኩህ? ብላኝ ውሀውን ትቀበለኛለች። የውሀውን ግማሽ ወደ መሬት ካፈሰሰች በኋላ ትጠጣዋለች። የጠጣችበትን ብርጭቆም ይሁን ንኬል እንድቀበላት አዛኝ አታውቅም። አጠገቧ የሆነ ቦታ ታስቀምጠዋለች..ስታስቀምጠው ሳይንከባለል ቀርቶ አያውቅም። ከተንከባለለበት የማነሳው እኔ ነኝ..
አያቴ ትገርመኛለች..ሁሌ እንደሰፋች ነው። እየቀደደች የምትሰፋ ይመስል ሁሌ መርፌና ክር አምጠልኝ እንዳለችኝ ነው። ቤቱ ውስጥ ቀዳዳ ልብስ እንዳለ አላውቅም። አያቴን ግን ሁሌ ስትሰፋ ነው የማያት። እጇ ከመርፌና ክር ጾሙን አድሮ አይቼ አላውቅም። አንዳንዴ የምትሰፋው ስታጣ ይመስለኛል ‹የተቀደደ ጥብቆ የለህም? ካለህ አምጣ ማለፊያ አድርጌ ልጣፍልህ› ትለኛለች የምትሰፋው ስታጣና እጇ ጾሙን ማደሩን ስታውቅ። የለኝም እላታለሁ የምሰፋው ኳስ ላይ በማቀርቀር። የምሰፋውንም ኳስ አምጣ ልስፋልህ አለማለቷ ተመስጌን የምልበት ነገር ነው። ዘር ከልጓም ይስባል እንደሚባለው በእሷ ወጥቼ ይመስለኛል እኔም ሰፊ ሆኜ የቀረሁት። ኳስ ሳልሰፋ የኖርኩበት የልጅነት እድሜ የለኝም። እኔ አያቴን እላለው እንጂ አያቴም እኔን የምትታዘበኝ ይመስለኛል። አንድም ቀን ኳስ ሳልታቀፍ ፊቷ ቆሜ አላውቅም። አትናገረው እንጂ ‹እንዳው መቼ ይሆን ኳስህን ሰፍተህ የምትጨርሰው? የምትለኝ ይመስለኛል።
አያቴ ትገርመኛለች..ሁሌ ማለዳ ሲሆን በቄሱ ስብከት እንደተወሰደች ነው። ቀስ ብሎ የሚያወራው ራዲዮ እንቅፋት ሆኖባት ‹ራዲዮኑን ላመል ቀነስ አድርገው ስብከቱን ልስማበት› ትለኛለች። አንዳንዴ አመል ሆኖባት የተዘጋውን ራዲዮ ሁሉ እንድቀንሰው ታዘኛለች። ሳቄን አፍኜ ‹ራዲዮኑ እኮ ተዘግቷል..› እላታለሁ።
‹ታዲያ ምንድነው የሚጮኸው? ስትል መልሳ እኔኑ ትጠይቀኛለች። የሚጮህ ነገር መኖርን ለማድመጥ ጆሮዬን እቀስራለሁ። ምንም አይሰማኝም። ‹ምንም እኮ የለም› እላታለሁ። ባለማመን ወደ ቄሱ ስብከት ትመለሳለች።
ከአያቴ ትዕዛዞች ውስጥ አራተኛውን አሎደውም። እማሆይ ቤት ከምትልከኝ ሰማይ ወድቆብኝ ቢጨፈልቀኝ ይቀለኛል። ገና ፊቷ ስቆም ምናለ እማሆይ ቤት ሂድ ባላለችኝ እያልኩ ነው። እማሆይ መቃብር ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ከሰማሁ በኋላ መፍራት ጀምሬአለው። በፊት እማሆይ ቤት ስላክ እየፈነጠዝኩ ነበር የምሄደው። እሳቸውም ስለሚወዱኝ ፊቴን ሀምሳ ቦታ ይስሙኛል። ስራ ሲኖራቸው፣ ማህበር ቤት ሲሄዱ፣ ቅዳሴ ሲገቡ ና ቤቴን ጠብቅልኝ ብለው ያስልኩብኛል። እኔም እየፈነጠዝኩ ወደ ቤታቸው እሄዳለሁ። አንድ ቀን አንድ ገበዝ ወደ እማሆይ ቤት ሰተት ብለው ገብተው ‹ይሄ መቃብር ቤት እድሳት ያስፈልገዋል..ቀለሙ ደብዝዟል› ሲሉ ሰማሁ። ስላልገባኝ ምንም አላልኩም።
‹እንዴት ያለ ጥሩ ሰው መሰለህ..ሞት ቀደመው እንጂ› ሲሉ ትክዝ አሉ።
‹ማነው እሱ? አልኩ ስለሞት ሲወራ በማይወድ አንደበት።
‹አታውቀውም። ይሄ የእሱ መቃብር ነው› ሲሉ የቆምኩበትን ወለል በመቋሚያቸው እየተቆሙ አሳዩኝ። ነፍሴ በልቤ ውስጥ ፍርስ ስትል ታወቀኝ። ከእማሆይ ቤት የሮጥኩ ቤት የደረስኩት ላብ በላብ ሆኜ ነበር። አያቴ የትንፋሼን መቆራረጥ እያየች ‹ምን ሆነህ ነው የምታለከልከው አለችኝ። አልነገርኳትም..‹አይ ውሻ አባሮኝ ነው ስል ዋሸኋት። ከዛ ከቀን በኋላ እማሆይንና ቤታቸውን ሽሽት ጀመርኩ። አያቴ ከእማሆይ ቤት ውጪ የትም ትላከኝ በደስታ ነው የምቀበላት። ከፍራቴ የተነሳ ያኔ መቃብር ቤት መሆኑን ሳልሰማ በፊት የምሆነውን መሆን እያሰብኩ መደንገጥ ሁሉ ጀምሬ ነበር። ለካ መቃብር ቤት ነበር ለብቻዬ የዋልኩት። ለካ ከአስከሬን ጋር ነበር የእማሆይን ቤት ስጠብቅ የኖርኩት እያልኩ በፍርሀት ስርድ ነበር።
‹ምን ልታዘኝ ይሆን? እያልኩ አያቴ ፊት ቆምኩ። እማሆይ ጋ ባላለችኝ። እንጦሮጦስም ይሁን እወርዳለው ብቻ እዛ መቃብር ቤት ሄደህ ና ባላለችኝ እያልኩ እያሰብኩ ፊቷ ቆምኩ።
‹እማሆይ ቤት..› ብላ ሳትጨርስ..
‹እኔ እዛ ቤት መሄድ አልፈልግም› አልኳት።
‹ለምንድነው የማትሄደው?
ዝም አልኩኝ
‹ሂድና..የአርሴማን ጸበል ይዘህልኝ ና› አለችኝ።
ከአያቴ ፊት ሳልሸሽ ቆየሁ። በዝምታዬ ውስጥ የቄሱ ስብከት አስተጋባ። መታዘዝ ከሰነፍ መስዋዕት ይበልጣል የሚለው። ከአያቴ ፊት ሸሸሁ..ሩቅእስክደርስ ድረስ ወዴት እንደምሄድ አላውቅም ነበር። የአያቴን ትዕዛዝ ልፈጽም አቅም አጣሁ። እማሆይ ሞት ሆነው ታዩኝ። ሀመሳ ጊዜ የተሳመ ፊቴ በሞት የተሳመ መሰለኝ።
በዛው ብር ብዬ ወደ አያቴ አልመለስ ይሆን? ወይስ እማሆይ የሉም ብዬ ከመንገድ ልመለስ? መልስ አጣሁ..። ተጨንቄ እያለ ከእኩዮቼ መካከል ደፋር የሚባለውን ሰይፉን መንገድ አገኘሁት። ‹ኳስ አጫውትሀለው እማሆይ ቤት እንሂድ›..አልኩት።
‹ካጫወትከኝ አብሬህ እሄዳለው› አለኝ
‹አጫውትሀለው› አልኩት። አላመነኝም። ‹እስኪ ማልልኝ? ሲል መዳፉን ዘረጋልኝ።
መዳፉ ላይ የመስቀል ቅርጽ ሰርቼ ማልኩለት።
አመነኝ…
ተከተለኝ..
ሞትን የገደልኩት መሰለኝ።
መከራዬን አጋርቼው ወደ እማሆይ ቤት ሄድን..
‹ደሞ መታዘዝ ከሰነፍ መስዋዕት ይበልጣል..›አልኩት።
‹ከቄሱ ሰምተህ ነው?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 /2015