አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም የሌማት ትሩፋትን ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት ማድረግ አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ፡፡
በደቡብ ክልል የወተት፣ የዶሮ፣ የስጋና የማር ምርት ማሻሻያ ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ተካሂዷል፡፡
በሌማት ትሩፋት ክልሉን በቅርበት እንዲደግፉ የተመረጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በመድረኩ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ፤ በአርባ ምንጭ ከተማ የተጀመረው ሀገራዊ መርሐ ግብር በተለያዩ አካባቢዎች በማስተዋወቅ ተግባራዊ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
አክለውም ‘’የሌማት ትሩፋት’’ ትርጉም ቤቱ ሙሉ ይሁን ማለት እንደሆነ አንስተው ፥ ይህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ አይደለም በባህላዊ ምርቃቱ ያውቀዋልም ነው ያሉት ።
በተመጣጠነ ምግብ ጤናው የተጠበቀ ትውልድን ማፍራት ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፥ በአካባቢው ያለውን ፀጋ በመጠቀም የሌማት ትሩፋትን እውን ለማድረግ መረባረብ አለብንም ነው ያሉት፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ የተደረገው የ ’ሌማት ትሩፋት’ መርሐ-ግብር በምግብ ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ክብርን ከማረጋገጥ ጋር ቁርኝት አለው ተብሏል ።
በመድረኩ የ ’ሌማት ትሩፋት’ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትዋናን እንድታረጋግጥ ማስቻል፤ በተለይም ስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ቅንጦት ሳይሆን ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተጨማሪ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ፣የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው እንዲሁም የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር