ማታ ሊሆን ትንሽ ሲቀረው..አስራ ሁለት ግድም ላይ ከቤት ወጣሁ ሳሮንን ላገኝ:: ሳሮን ከብዙ የእንገናኝ ውትወታ በኋላ ቃሏን የሰጠችኝ የመጀመሪያዋ ሴት ነች:: ደሞ እኮ አታምርም..ቆንጆ ሆና ብታለፋኝ አይቆጨኝም ነበር:: አስቀያሚ ናት..የሌለ:: በአስቀያሚ ሴት ደጅ ስጸና ሳሮን የመጀመሪያዬ ናት:: አስቀያሚ ከሆነች ምኗን ወደድከው ካላችሁኝ አንዲህ እላችኋለው..ሳሮን የትኛዋም ሴት የሌላት ሁለት ነገሮች አሏት..ኩራትና ንቀት:: እና እጆቿ በጣም ነው የሚያምሩኝ..እግሮቿ እንደ ቤተመቅደስ ሜንጦላይት ጸዐዳ ናቸው:: በተለይ ጉርድ ቀሚስ አድርጋ ስትመጣ (ባትመጣ ነው የሚሻለኝ) የምሆነውን አላውቅም::
አቤት ስትንቀኝ! እንደ ሰው እኮ አትቆጥረኝም:: አጠገቧ ስቆም ወይም ደግሞ ላገኛት ሰፈሯ ስሄድ ወይም ደግሞ ደውዬ ሳወራት የማታደርገኝ የለም:: አንድ ቀን ምን አለችኝ መሰላችሁ ‹በማልመጥንህ በእኔ ጊዜህን ከምታጠፋ ለምን ብጤህን አትፈልግም? አለችኝ:: ምክር ይሆን ራሮት ምን እንደሆነ ዛሬም ድረስ አልደረስኩበትም:: ብቻ ከእሷ ውስጥ ጥሩ ነገር እንደማይወጣ ስለማወቅ ንቀት ነው ስል በሙሉ ደምጽ ተቀብዬዋለው:: አዎ ንቀት ነው..ከንቀት ውጪ ምንም ሊሆን አይችልም:: ስትናገረኝ እንዴት እየሆነች እንደሆነ አስታውሰዋለው:: ራሮት ቢሆን ኖሮ በዛ ቅላጼ፣ በዛ ምጽድቅና፣ በዛ ኩፈሳ፣ በዛ የፊት እንቅስቃሴ አትናገርም ነበር:: ምን እንደነካው እንጨት እንደሚባለው ፊቴን ተጸይፋው..እንድሄድላት በመጋበዝ አይነት ነበር ያናገረችኝ:: ይቺን ሴት ነው ያፈቀርኳት::
እንደፈለገች መሆኛዋ ነኝ..:: ያልተሰደብኩት ስድብ፣ ያልተገላመጥኩት ግልምጫ የለም:: ፍቅሬን ተጠቅማ የቻለችውን ያክል ከፍና ዝቅ አድርጋኛለች:: ራሴን ግልጽ ባደረግ ብዙ የተሰደበ ተብዬ ኒሻን እንደማገኝ አልጠራጠርም:: ግን የፍቅር ስድቦች አያሙም..አይሰሙም:: ምናልባት ወደፊት ታሪኬን ስገልጽ በነዛ ስድቦች እታመም ይሆናል ለጊዜው ግን መልካም ሁኔታ ላይ ነኝ:: እዚህ ምድር ላይ በሚያፈቅረው ሰው እንደ እኔ የተናቀ እንደ ሳሮንም ሰው የናቀ አለ አልልም:: የንቀትን ጥግ፣ የውርደትን አጽናፍ አይቼዋለው:: ግን በንቀቷ ፊቴ ተቀይሞ፣ ቀልቶና ተሸማቆ አያውቅም:: ብዙ ጊዜ ሰው ባለበት ቦታ ላይ ለዛውም ድምጽዋን ከፍ አድርጋ በሚያዋርድ ክፉ ዋል ተናግራኝ ታውቃለች በነጋታው ግን አጠገቧ ነን..ለሌላ ውርደት:: ይቺን ሴት ነው ያፈቀርኳት::
ራሴ ግራ ተጋብቼ ጓደኞቼንም ግራ አጋብቻለው:: በሳሮን ፍቅር ፈምሻለው..የማያውቀኝ የለም:: እሷም በእኔ በመወደዷ እንደ እኔ ታዋቂ ሆናለች:: ሰፈር ውስጥ የማይጠቋቆምባት የለም.. በእኔ ስም ነው የምትጠራው:: ናሆም ያበደላት ሴት እየተባለች በሄደችበት ሁሉ ይወራላታል:: ከሰፈሯ ራቅ ካለች ደግሞ ‹ያ ቆንጆው ልጅ ያፈቀራት ሴት ናት አይደል?..ታድላ ትባላለች:: እኔ አንድም ቀን እንደ እሷ ታድሎ ተብዬ አላውቅም:: ሰው የሚጠቋቆምብኝ ሞኝነቴን ሊነግሩኝና እንዳው ይሄን የመሰለ ልጅ ምን አስነክታው ነው? ለማለት ነው::
ከፍቅሯ የተረፈኝ ጅላጅልነትና ከንፈር የሚመጠጥለት መሆን ነው:: ይገርመኛል ፍቅር..ይገርመኛል የሰው ልጅ:: ሰው ለመታደል የግድ የምትወደውን መውደድ አለበት? ለመታደል የግድ ቆንጆ ሴት ማፍቀር አለብኝ? ሳሮን እኮ በእኔ ልብ ውስጥ የቆንጆዎች ቆንጆ፣ የውቦች ውብ ናት..ለምን ታድለህ አይሉኝም? ስል እበሳጫለው:: ፍቅር እውነት ሆኖ ሳለ በራሳችን የፍርድ ሚዛን ባልዋለበት እናውለዋለን:: የእኔን ቁንጅናና የሳሮንን ፉንጋነት ሰማይና ምድር አድርገው ምን ብታስነካው ነው አሉ? በፍቅር ለመውደቅ ምን መነካት ይጠይቃል..?
ሳሮን አፍቅሬ ሳዘባንናት ተፈቅራ አሸማቀቀችኝ:: በዛች ኩራተኛ ነፍስ ፊት ቆሜ ግን አሁንም ፍቅር መልኩ አልጠፋኝም:: ፍቅርን ነውር የምናደርገው እኛ የሰው ልጆች ነን:: ፍቅር ነውር ሆኖ አያውቅም..ዛሬም እንደ ትላንቱ አዲስ ነው..የእየሱስን ስም ይዞ የሚኖር:: መርጠን ስለምናፈቅርና ተመርጠን መፈቀር ስለምንፈልግ ግን ነውር እናደርገዋለን:: ግፍ ነው ብለን መርጠን ከጣልነው እውነት ጀርባ ያለውን ጸጋ ስለማናውቅ እንደ አኔና እንደ ሳሮን አይነት የፍቅር ታሪክ ስንሰማ አፋችንን ለፍርድ እናሞጠሙጣለን::
በአለም ጥግ የአፍቃሪን ያክል ፍቅርን የተረዳ የለም:: ነፍስ ስታፈቅርና ስትፈቀር ሁለት አይነት ናት:: ስናፈቅር ፍቅርን ነን..:: እውነትን ጥበብን፣ ማስተዋልን ድንቁርናንም እየተለማመድን ነው:: ስንፈቀር ግን ደንቆሮ ብቻ ነን:: ብዙ ጊዜ የማይገባን አንዳንድ ጊዜ የሚገባን:: ስናፈቅር እንደ እየሱስ ባለማዕረግ ነን…በህይወታችን መቼም እንዴትም የማይጎበኘን የሆነ አዲስነት እየተዋሃደን ነው:: ስንፈቀር ከጽድቅ ይልቅ ለስህተት የተጋለጥን ነን…እየሄድን የማንደርስበት ብዙ ነገር አለን:: እኔና ሳሮን፣ እኔና ታዛቢው፣ እኔና አሽሟጣጩ ፣ እኔና ወጪ ወራጁ፣ እኔና መንገደኛው፣ እኔና ሳሮንን ለምን አፈቀርካት የሚሉኝ፣ እኔና በሳሮን ፍቅር እንደ እብድ የሚያዩኝ፣ እኔና ሳሮን ምን አስነክታው ነው የሚሉ፣ እኔና የሚስቁብኝ፣ እኔና በማፍቀሬ የሚዘባበቱ፣ እኔና በሳሮን ፍቅር ሞኝ የሚሉኝ፣ እኔና የሚቀልዱብኝ ሁለት አይነት ነን..የገባንና ያልገባን::
አለም ሁሉ በአንድ ድምጽ በማፍቀሬ ቢስቅብኝ ሳሮንን ከመከተል አልቆምም:: ለፍቅር የማይሆን ብዙ ነገር እያላት ነው የምከተላት:: የትም ቦታ አይቼው ያልማረከኝ ኩራትና ማንአለብኝነት አላት:: በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ወደ እሷ እሄዳለው:: ከሰባት ወር ስድብና ንቀት በኋላ ዛሬ ልታገኘኝ ፍቃዷን ሰጥታኛለች::
አትኖርም እያልኩ እየሰጋሁ ካለችኝ ቦታ ደረስኩ:: ለሁልጊዜ በሚገርመኝ ሁኔታ ባለችኝ ሰዐት ላይ እየጠበቀችኝ አገኘኋት:: እንዴት ደስ እንዳለኝ አትጠይቁኝ…ጉንጭዋን ስመኘው እጄን ሰላም አለችኝ:: ጣቶቿ ነኩኝ..:: በህልሜ በሚመጡ እጆቿ ተጨበጥኩ:: በቆምኩበት አንድ ጸሎት ጸለይኩኝ በእንዛ እጆች ለዘላለም ለመዳበስ፣ ለዘላለም ለመነካት፣ ለዘላለም ለመጨበጥ:: እጆቿ ይለሰልሳሉ..እንደ መልኳ አይጎረብጡም::
ወንበር ስቤ አጠገቧ ልቀመጥ አይኔን ስቀይስ ሁለት ወንዶች ስሟን እያቆላመጡ ከበስተኋላዬ ሲመጡ ሰማሁ:: ገና እኮ አልተቀመጥኩም፣ ገና እኮ መቀመጫየ ወንበር አልነካም..ገና እኮ በመምጣቷ ተደስቼ አላበቃሁም..በሁለት ወንዶች ተጨበጠች:: ተጨብጣ ብታበቃ ጥሩ ነበር ሰባት አመት ስመኘው ያላገኘሁትን ጉንጩዋን ሳሙት..አንገቷን ተጠመጠሙበት::
‹አቤት የሰው ፍቅር› አልኩ በሆዴ::
የሚሄደው የሚመጣው እጅ ይነሳታል፣ ይስቅላታል..ይጠመጠምባታል:: ማንም እየተነሳ በሚጨብጠው እጇ ቀናሁ:: አጠገቧ ሆኜ ሰባት ወንድ ጉንጩዋን ስመው..
‹ስንቱን ነው የምታውቀው? ሆቴላቸው ነው እንዴ የቀጠረችኝ? ስል አሰብኩ::
የረሳችኝ መሰለኝ..‹በቃ አፍቃሪ መቀለጃ ሆኖ ቀረ? አልኩ ደግሜ::
ወደ እኔ ዞረች..
‹እና ይሄውልህ..እእእ..
‹ይቅርታ ማነበረ ስምህ?
ስሜ ጠፋባት..ሰባት ወር የተከተላትን ወንድ ስም:: ነፍሴ ተቀየመቻት..ከሰባት ወር በኋላ ላመል ቅያሜ ወደ ውስጤ ሰረገ..
‹ናሆም..› ስል መለስኩላት
‹ይሄውልህ ናሆም..እዚህ የጠራውህ ..› አለች ሆቴሉ ውስጥ ወዳሉት ወንዶች እየጠቆመች ‹በነዚህ ሁሉ ወንዶች የተከበብኩ እንደሆንኩ እንድታውቅ ነው:: በአንተ መፈቀሬን ሳስብ ራሱ ይደብረኛል..እንድታፈቅረኝ አልፈልግም› ብላኝ ትታኝ ወጣች::
ልጋብዛት..ብዙ ብር ተበድሬ ነበር..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2015