
ሮናልዲንሆን ከሌሎች ብራዚላውያን ተጫዋቾች ልቆ ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ። ይሄም በብሄራዊ ቡድን ውስጥ በሁሉም የእድሜ ክለል ላይ የሚደረጉ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፉ ነበር። በ1997 የፊፋ በግብፅ ባካሄደው ከ17 አመት በታች የዓለም ዋንጫ፣ በ1999 የደቡብ አሜሪካ ወጣቶች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም በዚያው ዓመት በተመሳሳይ ናይጄሪያ ውስጥ በተሰናዳው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተካፋይ ሆኗል። በዚህም የሚከተሉትን ስኬቶች አግኝቷል።
ሮናልዲንሆ በብራዚል ብሄራዊ ቡድን በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች የጫወተ ሲሆን በ1999 ኮፓ አሜሪካን ውድድር ላይ ላቲቪያን 3ለ0 በሆነ ውጤት ብራዚል ስታሸንፍ የመጀመሪያውን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። በዚያው አመት በተመሳሳይ ወር ላይ በተካሄደው የፊፋ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ በተደረጉት እያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ከዋንጫ ጨዋታው በስተቀር ለብሄራዊ ቡድኑ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዋንጫ ጨዋታው ላይ ብራዚል በሜክሲኮ የ4ለ3 ሽንፈት ደርሶባት ዋንጫውን ማግኘት ባትችልም ኮንፌዴሬሽን ካፕ ጎቾ የ«ጎልደን ግሎብ» የምርጥ ተጫዋችነት ሽልማት እና የወርቅ ጫማን በግሉ አሳክቷል። በ2000 ላይ ደግሞ ሲድኒ ላይ በተካሄደው ኦሎምፒክ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመጓዝ ተጫውቷል። በቅድመ ኦሎምፒክ ውድድሮች ላይም በሰባት ጨዋታዎች 9 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
ጎቾ በዓለም ዋንጫ ታሪኩ ከብራዚል ጋር የማይረሳ ትዝታን ያስተናገደው በኮሪያና ጃፓን አስተናጋጅነት በ2002 ዓ.ም ነው። በዚህ ውድድር ላይ በስሙ ሁለት ግቦች እና በርካታ ለግብ የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ችሏል። በተለይ በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ከእንግሊዝ ጋር የተገናኘችውን ብራዚል ጨዋታውን በድል እንድትወጣ ያስቻላትን አስደናቂ ቅጣት ምት አስቆጥሯል። በተለይ ጎሏን ልዩ የሚያደርጋት ከ40 ሜትር ርቀት ላይ የተቆጠረች እና ዴቨድ ሴማንን በእጅጉ የፈተነች በመሆኗ ነበር። በ2005 ሮናልዲንሆ የብራዚል ብሄራዊ ቡድንን
በአንበልነት እየመራ የፊፋ ኮንፌደሬሽን ካፕን አንስቷል። በተለይ በውድድሩ በሜክሲኳዊው ኩቲሞክ ብላንኮ የተያዘውን የ9 ጎል ክብረ ወሰን መጋራት ችሏል። በ1999 አሜሪካን ካፕ እንዲሁም በ1997 በፊፋ 17 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮን ዋንጫን አንስቷል።
በዋናው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በ97 ጨዋታዎች ተሰልፎ ያስመዘገባቸው 33 ጎሎች ናቸው። ከ1996 ጀምሮ በብራዚል ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በ6 ጨዋታዎች 2 ግብ አስቆጥሯል። ከ1999 ጀምሮ በብራዚል 20 ብሄራዊ ቡድን በ5 ጨዋታዎች 3 ጎሎችን፤ ከ1999 እስከ 2008 በብራዚል 23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በ27 ጨዋታዎች 18 ጎሎች፤ ከ1999 እስከ 2013 በብራዚል ብሄራዊ ቡድን በ97 ጨዋታዎች 33 ጎሎች አስመዝግቧል።
2006 ለጎቾ ጥሩ ጊዜ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ አንድ ነው። የዓለም ዋንጫ። እርሱን፣ አድሪያኖን እና ካካን የያዘው ብሄራዊ ቡድን ዋንጫውን ያነሳል የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን በግልባጩ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ። ስምንት ውስጥ ቢደርሱም በፈረንሳይ የ1ለ0 ሽንፈት ስለገጠማቸው ከውድድሩ ውጪ ለመሆን ተገደዱ። ጎቾ በዚህ ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አቋሙ ወርዶ ነበር። ዓለምን ያስደነቀው ምርጥ ተጫዋች በዚያን ዓመት ለአገሩ ሊደርስላት አልቻለም። በዚህ የተናደዱት ደጋፊዎችም 7 ነጥብ 5 ሜትር የሚደርሰውን ለክብሩ የተተከለለት ሀውልት ጥቃት አድርሰውበት ነበር።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በዳግም ከበደ