በጎ ሥራ በመስጠትና መቀበል ስሌት ባይለካም መታየትና ለሌሎች ምሳሌ መሆን ግን አለበት።ምክንያቱም አድራጊዎቹ ይበረታታሉ፤ ድጋፉን የሚያገኙ ሰዎችም ይበራከታሉ።እናም ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ በአገር ደረጃ በተከበረው የበጎ ፈቃደኞች ቀን ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመሆን ይህንን አድርጓል።በጎ አድራጊ ድርጅቶችና እናቶችን ከፍ ብለው እንዲታዩ ምስጋና እና ዕውቅና ሰጥቷል።ይህንን ምስጋና እና እውቅና ከአገኙት መካከል ሁለት እናቶችን ለዛሬ ይዘን ቀርበናል።
እናት እናኑ ሁሴን አንዷ ናቸው። እናኑ በሙያቸው መምህር ሲሆኑ፤ ከረጅም ጊዜ አገልግሎት በኋላ በጡረታ ቢገለሉም ቤታቸው አልተቀመጡም። ልክ ጡረታ እንደወጡ የጎልማሳ ማሰልጠኛ ጣቢያ ውስጥ ገቡ።የተሸሉ ስለነበሩም ቦታው ላይ የመምራት ኃላፊነቱን ተረከቡ።‹‹ጀርመኖች በጎልማሳ ትምህርት ነው ያደጉት›› የሚሉት እናኑ፤ ጊዜያቸውን አስተምሮ ማንበብ፤ መፃፍ፤ ቁጥር ማስላት እንዲችሉ ማድረግ ላይ ብዙ ለፍተዋል።በዚህ ተግባራቸው ደግሞ እጅግ ደስተኛ ናቸው።ቀሪው የሕይወት ዘመናቸውን በመልካምነት ማሳለፍ የፈለጉትም በዚህና ቀደም ብለው ከጓደኞቻቸው ጋር ጎልማሶችን ያበቁበት የነበረውን አገልግሎት ነው።እናም ዛሬም ይህንኑ ጉዳይ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሆነዋል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1997 መካኒሳ አካባቢ ቢሮ በመከራየት ‹‹ዳንፌ›› የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት የመሰረቱት እናኑ፤ በመሰረቱት ድርጅት አማካኝነት በተለያዩ ምክንያቶች የማንበብ፤ ማስላትና ቁጥር መፃፍ ያልቻሉ ጎልማሶችን፤ ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ያላገኙና ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የሆኑ ህፃናትን እየሰበሰቡ ማብቃታቸውን ተያያዙት።
ህፃናትን ‹‹ስፒድ እስኩል›› በተሰኘ አቀራረብ በአንድ ዓመት አራተኛ ክፍል ያደርሳሉ። በዚህ አሰራራቸውም የ15 ዓመቱ ልጅ አራተኛ ክፍል ለመድረስ ሁለትና ሦስት ዓመት መቆየት አይጠበቅበትም።አክለውም እንደሚሉት፤ በአንድ ዓመት ውስጥ አራተኛ ክፍል እንዲደርስ በማድረግ ከ6ሺህ በላይ ህፃናትን ማብቃት ችለዋል። ያበቋቸው በቀላሉ ሳይሆን ከሰኞ እስከ አርብ ሙሉ ቀን ቅዳሜ ግማሽ ቀን በድምሩ 1 ሺህ 442 ሰዓት ለፍተውባቸው ነው።
ይህ የትምህርት አሰጣጥ ወይም አቀራረብ ዘዴ በመቐለና በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተጠንቶ ውጤታማነቱ መረጋገጡን የሚያወሱት እናኑ፤ ዘዴው በመንግስትም ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በሌላ የማስተማርያ መንገድ በርካታ ጎልማሶችን ማብቃታቸውንም ያስረዳሉ። በተለይ ትኩረት ሰጥተው ካበቋቸው ጎልማሶች መካከል ስድስት ሺህ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ሴቶች ይገኙበታል።
እናኑ እንዲህ ዓይነቱን ሰናይ ተግባር የሚያከናውኑት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወስነው ብቻ አይደለም። በኦሮሚያ፤ በቤንሻንጉል፤ በአማራ ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ ጭምር ነው። ይሄን በጎ ተግባራቸውን የተመለከቱና በግብረ ሰናይ ተግባር ላይ የሚሰሩ አንዳንድ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ድርጅቶች ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያግዟቸዋል።
እናኑ ከዚህ ሥራቸው ባሻገር አገር በቀሉ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባደረገላቸው የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ በተለያየ ምክንያት ትምህርት ቤታቸው ለወደመባቸው ታች ዘሪም እንዲሁም ዘሪም ድባ ባህር ለተሰኙ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መቀመጫ ወንበር፤ ጠረጴዛ እንዲሁም ደብተርና እስኪሪብቶ ለግሰዋል።
እናኑ ሴቶች በኢኮኖሚ እንዲበቁ በማድረጉ ረገድም ትልቅ ጥረት ያደርጋሉ። በቅርቡ ብቻ ከዩኤን ዲፒ ጋር በሚሰሩት ሥራ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ ለሚኖሩ 180 ሴቶች የንብ ቀፎ ገዝተው በመስጠት በንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ አድርገዋል። በተጨማሪም በጦርነት ለተፈናቀሉ 2 ሺህ 778 ሴቶች በበግ፤ በዶሮ እንዲሁም በእርሻ ሥራ እንዲሰማሩ ለማስቻል በጎች፤ ዶሮዎችና ምርጥ ዘር ገዝተው ሰጥተዋል።
ሌላው እናኑ ያደረጉት ነገር በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይም በሰፊው ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፤ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሴቶች በአየር መዛባት አማካኝነት ከሚከሰት አደጋ አካባቢያቸውን እንዲከላከሉ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ትምህርት ይሰጣሉ።ሻገር ብለውም በአካባቢያቸው ችግኞች እንዲተክሉ ያደርጋሉ። በተለይ አዳማ ላይ በዚህ ተግባራቸው ጎልተው የወጡ ናቸውና ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል።ይህና መሰል ሥራቸው ደግሞ የበጎ ፈቃደኞች ቀን ሲከበር ዕውቅናና ምስጋና አስችሯቸዋል።
ሌላዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመድረኩ ዕውቅናና ምስጋና የተቸራቸው እናት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በቀለ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው ሀዋሳ ሲሆን፤ በዚሁ ከተማ የሚገኘውና የዛሬ 17 ዓመት የተመሰረተው ‹‹የቤተ ሳይዳ ›› በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እኝህ እናት እንደሚናገሩት፤ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ነው። ወደ ሀዋሳ የመጡት በትዳር ሲሆን፤ በበጎ ተግባር ለመሰማራት ምክንያት የሆኗቸው በዚህ አጋጣሚ ሀዋሳ ከተማ ላይ ያይዋቸው ጎዳና የወጡ ልጆች ናቸው።
የእነዚህ ልጆች የኑሮ ሁኔታ ያየው ውስጣቸው ለከተማዋ እንግዳ ነሽ ሳይል በሰውነታቸው የአቅማቸውን እንዲያደርጉ አስገደዳቸው። በሁለት ጎዳና የወጡ ህፃናትም ተግባሩን ጀመሩት። በጎ ተግባራቸው እየሰፋ ሲመጣም አንዳንድ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ይረዷቸው ጀመሩ። በ1999 ከክልሉ ፍትህ ቢሮ ፈቃድ ወሰዱ። ከዚህ ጀምሮም እስከ 2002 ዓ∙ም ያለማንም ድጋፍ ሀዋሳ ከተማ ካሉ ጥቂት ግለሰቦች ጋር የጎዳና ህፃናት እንዲማሩና መሰረታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟላ አደረጉ።
“ጎዳና የወጡ ልጆች ቀርቤ እንዳያኋቸው ፍቅር ነው የሚፈልጉት” የሚሉት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ለጎዳና የተጋለጡትን ልጆች በተለይ እሁድ እሁድ እሳቸው ጋር እየመጡ የስነ ምግባር ትምህርት እንዲማሩና የቤተሰብ ፍቅር እንዲኖራቸው ያደርጉ ነበር።ሰርክ ቁርስም ያበሏቸዋል።የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ለሚቆሙ የጎዳና ልጆች የንፅህና መጠበቂያና አልባሳት የሚገዙላቸው በጎ ሰዎችን ፈልገው እንዲሟላላቸውም ያደርጋሉ።በዚህ ደግሞ ፈጣሪ በጎዎችን እንዳበዛላቸው ይናገራሉ።
ሰዎቹ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጉላቸውም ነበር። እስከ 2014ዓ.ም 22 ጎዳና የወጡ ሕፃናትን በመመገብና ጥሩ ስነ ምግባር እንዲኖራቸው በማድረግ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችለዋል። ሆኖም ልጆቹን እዚህ ደረጃ ለማድረስ ብዙ ችግር ገጥሟቸዋል። አንዱ ለሚሰጠው ገንዘብ ደረሰኝ መጠየቅ ነው። ልክም ነበር። ምክያቱም በጎነትን ያጠለሸው ብዙ አጋጣሚዎች ስላሉ።ስለዚህም ይህንን ችግር ለመፍታት ሕጋዊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ወደ ፈቃድ ማውጣት ገቡ።
በነበረው አሰራራቸው ብዙ ሰዎችን መድረስ አልቻሉም። በዚህም ሌሎች የሚደግፏቸው ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ለመሄድ ወሰኑ። ከክልሉ ኤጄንሲ ፈቃድ አገኙና ከግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ ጋር ሕብረት ፈጠሩ። ከነሱም ትንንሽ ድጋፎችን አገኙ። ከዚህ በኋላ ፕሮጀክት እየቀረፁ ለተለያዩ ኤምባሲዎች በማቅረብ ብዙ ሴቶችን፤ ህፃናትን መድረሱን ተያዙት።ሆኖም ለድርጅታቸው ቤተ ሳይዳ ብዙ አስተዳደራዊ ወጪ የሚሰጡ ድርጅቶችን ማግኘቱ ቀላል አልነበረም። ትንንሽ ድጋፎችን ወድያው ወደ ተጠቃሚው ስለሚዛወሩ ከስራ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ከኪሳቸው ገንዘብ ማውጣት ያስፈልጋቸው ነበር። እሳቸውም ጥቂት ደሞዝ የሚከፍላቸው ድርጅት ያገኙ ከ2014 ጀምሮ ነው። አሁን ላይ ብዙ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይ ሀዋሳ ከተማ ላይ ብዙ ሰርተዋል።
ወጣቶችን እያደራጁ የፀጉር ሙያ፤ የልብስ ስፌት ዕቃዎችን በመስጠት እንዲሁም ሴቶችን በማደራጀት በግና ፍየል ዶሮ ወደ ማርባት ሥራ እንዲገቡ አድርገዋል። ቀድሞ ይደግፏቸው የነበሩት 20 ህፃናትን ጨምሮ ሌሎቹ በባጃጅ ማሽከርከር፣ በፀጉር ሥራና በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው እራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውን እየደገፉ ናቸው። በቅርቡም ከሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ባለስልጣን ድጋፍ በማግኘት በአማራ ክልል አጣዬ ከተማ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ላይ ለ200 ሴቶች የምግብ፤ ለ100 ታዳጊ ልጆች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
ወይዘሮ አለምፀሐይ 30 ሴቶችን በማደራጀት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ አሰማርተዋል። በቀጣይ ወደ ወላይታ በመዝለቅ በጎ ሥራዎቻቸውን ለማከናወን በዝግጅት ላይ ናቸው።አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ላይ ቢሮ ከፍተው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ለእነዚህ እናቶች ዕውቅናና ምስጋና የቸረው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ እንደሚሉት፤ ተግባራቸው የሚበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ነው። በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ ሁሉም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል።እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ አርዓያ ናቸው።በተለይም በተግባሩ ሴቶች የቤተሰብ መሰረት እንደመሆናቸው በስፋት መሳተፋቸው ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል።
ወይዘሮ ሙና አክለውም በአሁኑ ወቅት በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ሳቢያ በርካታ ወገኖች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። አብዛኞቹም ሴቶችና ህፃናት ናቸው። እናም እነዚህን በጎ ፈቃደኛ ድርጅቶች እንዳደረጉት ሁሉ ሌላውም ማድረግ ይኖርበታል። ሁሉም ሰው የሰብዓዊነት ግዴታ አለበትና በቻለው ሁሉ መደገፍ ይገበዋል።እንዲህ አይነት ተግባር የሚከውኑ አካላትም መበረታታት አለባቸው። ምክንያቱም የሁሉም ዜጎች የመስኩ ተሳትፎ ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የጎላ ድርሻ አለው።
ድጋፎች መደረግ ያለባቸው በበዓል ወይም በክረምት ብቻ ሳይሆን ሰርክ እንደዜጋ መሆን አለበት የሚሉት ወይዘሮ ሙና፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከቅን ልቦና በመነጨ እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣ አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር፣ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን በማጎልበት ወገኖቹን ሊያግዝ ይገባል። ከገጠማቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊታደጋቸው ያስፈልጋልም ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላም ይህንን ለማስፋት እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎችን አንስተዋል።አንዱ ተሳትፎውን የበለጠ ያጎለብታል የተባለለት ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ነው።በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። የሴቶች በጎፈቃድ ተሳትፎ መሰረታዊ መሆኑን በሚገባ ያስረዳል።ስለሆነም ወደተግባራዊነቱ ሲገባበት ብዙ መፍትሄን እንደአገር እንደሚያመላክት ነው የጠቀሱት።
በስከዛሬው የበጎ ተግባር ላይ ብዛት ያላቸው ወጣት ወንዶች ናቸው የሚሳተፉበት። የሴቶች ተሳትፎ በጣም አነስተኛ ነው። ወደ አደባባይ ወጥተው በስፋት ሲሰሩም አይታዩም። ከዚህ አንፃር ሴቶች ወደፊት መጥተው በጎ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ይህ አዋጅ እጅግ ጠቃሚ ነው።ምክንያቱም ሴቶች ተሳትፏቸውን አሳደጉ ማለት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ቤተሰባቸውን ይዘው እንዲወጡ ያደርጋል።ለዚህ ደግሞ ማህበረሰቡ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። በስፋት ወጥተው እንዲሳተፍ መደገፍ ይኖርበታል።
የበጎ ፈቃድ ሥራ የበለጠ ባህል እንዲሆንና እንዲለመድ በማድረግ ረገድ ሰርተው አርአያ ሆነው የወጡ ሴቶችን ማጉላትና ማሳየት ያስፈልጋል።ለዚህም አሁን የወጣው ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ ፤ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ አጋዥ ነው።በዚህም ማንንም ሳይለይ ሁሉም እንደዜጋ የሚሳተፍበት ይሆናልም ይላሉ አቶ ፋሲካው።እኛም ሴቶች በበጎ ፈቃድ ያላቸው ተሳትፎ ይጎልብት ፤ተጠቃሚነታቸውም ይስፋ በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊትውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም