ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ደግሞ ከዛሬ 109 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም የተከሰተው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሕልፈተ ሕይወት ነው።
መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፤ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አምስት ዓመት ከአራት ወር በሕመም ላይ ከቆዩ በኋላ ታኅሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም በዕለተ አርብ አረፉ።
አቤቶ ኢያሱ በዚህ ሌሊት በአዲስ አበባ ፍልውሐ በመታጠቢያ ቤታቸው አድረው ነበርና የንጉሠ ነገሥቱን ሞት ሲሰሙ ወደ ቤታቸው መጥተው ተቀመጡ።
የንጉሠ ነገሥቱ አጼ ምኒልክ ሞት እንደተሰማ ሕዝብ ይሸበራል ተብሎ ስለተሰጋ የሞታቸው ዜና እንዳይነገር በጥብቅ ተከለከለ። በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለቅሶ ጀምረው የነበሩትንም ወዲያውኑ አስቆሟቸው።
አቤቶ ኢያሱ የንጉሠ ነገሥቱ ሞት እንዳይሰማና እንዳይገለጥ በማለት የሐዘን ምልክት ሳያሳዩ ቀሩ። እንዲያውም በማግስቱ ቅዳሜ ወደ ጃንሜዳ ሄደው በፈረስ ተቀምጠው ከአሽከሮቻቸው ጋር ጉግስ ሲጫወቱ ዋሉ። ይህም ሐዘን እንደሌለ ለማስመሰል የታቀደ ዘዴ ነበር።
የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሞት በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ሁሉ ሳይገለጽ ተደብቆ ኖረ። ሆኖም ወሬው መሰማቱና መታወቁ አልቀረም። የምንጃር ገበሬ በጤፍ ውቂያ ጊዜ እንዲህ ብሎ እንደገጠመ በታሪክ ተቀምጧል።
እምዬ ምኒልክ ገንዘብ ስጠኝ ብዬ አላስቸግርህም
አምና ነበር እንጂ ዘንድሮ የለህም
ከዚህ በኋላም አጼ ምኒልክ በሕይወት አሉ እየተባለና እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ድረስ ሁለት ዓመት ከአሥር ወር ተደበቀ። ንጉሠ መንግሥቱ ሥራም በስማቸው ይካሄድ ነበር። አጼ ምኒልክ የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም ስለሆነ በሞቱበት ጊዜ ዕድሜያቸው ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ከአራት ወር ነበር።
የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ ደግሞ የሚከተለውን ይነግረናል።
‹‹…ምኒልክም ቢሆን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል አመለካከት አልነበረውም። ሌሎች ግፊቶች ባይታጡም በ1900 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያቋቋመበት አንዱ ምክንያት ለመንግሥት ድርጅታዊ መሰረትና ቀጣይነት ለመስጠት ከነበረው ፍላጎት ይመስላል። ››
ከምኒልክ ሕልፈተ ሕይወት በፊት ስለነበረው ሁኔታም የታሪክ መጽሐፉ ይህን ይነግረናል። የንጉሠ ነገሥቱ በሞትና ሕይወት መካከል ተንጠልጥሎ መቆየት የኢያሱን የፖለቲካ እድልም እንዲሁ በእንጥልጥል እንዲቀር አደረገው፡
በ1905 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በኢያሱና በግቢ ዘበኞች መካከል የተፈጠረው ግጭት መንሥኤም ይኸው የኢያሱ ትዕግሥት ማጣት ይመስላል። ከምኒልክ ሌላ ጌታ የማያውቁት ዘበኞች ቀደም ሲል ራስ አባተን ግቢ አናስገባም እንዳሉ ሁሉ አሁንም ኢያሱ፤ ምኒልክን ወደ አንኰበር ለማስወሰድ ሐሳብ አለው ማለትን ሰምተው እኛ ሳንሞት ንጉሣችን ከግቢ አይወጡም ብለው በኢያሱ ላይ በሩን ዘጉበት።
ኢያሱም ግቢውን ከቦ ዘበኞቹ ከውጭ ምንም ስንቅ እንዳያገኙ አደረገ። አምስት ሰዓት የቆየ ተኩስም ተከፍቶ አሥራ ሰባት ያህል ሰዎች ሞቱ።
ይህ ሽኩቻ ቀጥሎ ነው እንግዲህ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ መሞትና ከልጅ እያሱ መተካት በኋላ የሰገሌ ጦርነት የተከሰተው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ታህሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም