ስለንባብና መጻሕፍት ጠልቀው የተረዱ ሰዎች ሲናገሩ «ማንበብ አእምሮን ወደ ሥራ የሚያሰማራ ተግባር ነው» ይላሉ። አልፎም «መጻሕፍትም ሆኑ ንባብ ለአእምሮ ምን ያደርግለታል?» የተባለ እንደሆነ ለሰውነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምን ይጠቅማል ብሎ እንደመጠየቅ ነው የሚሉ አሉ። አእምሮ በተለያዩ ሃሳቦች፣ እይታዎችና አመለካከቶች ይዳብራል፤ ይጠነክራል። በዚህም ባለአእምሮው አዲስ መንገድ ማግኘት ይችላል፤ አሁን ላይ በተደጋጋሚ እንደሚባለውም «ምክንያ ታዊ» ይሆናል።
እንግዲህ አካል እንዲበረታ ሆድ ምግብ ያስፈልገው እንጂ ምግብ የሚያበስለውና የሚያቀርበው፤ የሚያጎርሰውም እጅ ነው። ልክ እንደዛው ሁሉ ለአእምሮ ብስለትና ስፋት፤ አስፈላጊ የሆነውን መጽሐፍ በማቅረብና በማንበብ በኩልም የሰው ተነሳሽነት አስፈላጊ ነው። እንጂ ያልቀመሰውን ነገር አእምሮ «አምጡልኝ» ብሎ አይጠይቅም፤ የተሻለና የበለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ ግን ግብዓት እንደሚያስፈልገው ይታወ ቃል።
ይህን ግብዓት ለማሟላት፣ ምክንያታዊ ትውልድ እንዲፈጠር ለማገዝና አእምሮው የዳበረ ትውልድ ለማፍራት በአገራችን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ እናያለን። እንቅስቃሴዎቹ በቂ ናቸው ወይ? በምንስ መንገድ ቢሠራ ነው አንባቢ ዜጋን በሚፈለገው ልክ ማፍራት የሚቻለው? የሚሉ ጥያቄዎች ይቆዩን። ነገር ግን ጊዜና ዘመን አዳዲስ ነገሮችን ሲያመጣብን፤ መፍትሄውን ከያለበት እንፈልጋለንና፤ የንባብ ነገርም አሁን ላይ በስፋት እየተነሳ ይገኛል።
በተለይም በአገራችን አሁን ላይ «አልተማረም» ከሚባለው ነገር ግን ገራገር ልብና ቀና አስተሳሰብ ከታደለው ማኅበረሰብ ይልቅ፤ «ተምሯል» የተባለው ችግር ፈጣሪ ሆኖ ይታያል። ይሄኔ አንባቢ ብንሆን ኖሮ ይህ ችግር አይፈጠርም ነበርና፤ የተማረውን ሰው የንባብ ነገር ሳይቀር እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ይህም ብቻ ሳይሆን መጻፍና ማንበብ የሚችል ሰው ከቀደመው ጊዜ ይልቅ አሁን ላይ በብዛት ያለ ቢሆንም፤ መጻሕፍት ጋር ያለው የትውልድ ቅርበት በዛ ደረጃ አለመሆኑም የሚያጠያይቅ ነው።
ወዲህ እንመለስ፤ በአገራችን እየተደረጉ ካሉና ንባብን ከሚመለከቱ ሥራዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ
በየጊዜው የሚያካሂደው የንባብ ሳምንት ንቅናቄ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይህም በመዲናይቱ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ክልል ከተሞች የሚከናወን ሲሆን፤ ብዙውን ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በየክልል ከተሞቹ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ነው።
ካለፈው ሳምንት ቀደም ብሎ ለዚሁ ተመሳሳይ የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር ጅማ ከተማ ተገኝተን ነበር። ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ከጅማ ከተማ መስተዳድር እና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተዘጋጅቷል። በጅማ ባለአራት አንበሳ አደባባይ አካባቢ በተጣለ ነጭ ድንኳን ስር ለአንድ ሳምንት በቆየው በዚሁ ዝግጅት ላይ፤ መጽሐፍት አቅራቢዎች፣ አንጋፋ ደራስያን፣ የመገናኛ ብዙሃንና ከጅማ ከተማ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ተገኝተዋል። ነዋሪውም መጻሕፍትን ለመሸመት በአውደ ርዕዩ ታድሟል።
ስለ ጅማ ከተማ አንድ ነገር ልበል። ጅማ «ከተማም እድሜው ሲጨምር እንደሰው ይደክማል እንዴ?» ታስብላለች። ምንም እንኳ ዋና ከተማ ከሆነችው አዲስ አበባ በእድሜ የምትልቅ ቢሆንም፤ በር የተዘጋባትና የተዘነጋች ትመስላለች። ወደከተማዋ መግቢያ መንገድ ሳይቀር ሳይጠገን ለዓመታት እንደቆየ ከብዙ ጊዜ በኋላ ወደዛው ያቀኑ ሰዎች ይናገራሉ። ዘመናዊነት ወደ አገራችን የገባበት በር ናት እስኪያሰኝ ድረስ የአባ ጅፋር ታሪክና ሥራ ብዙ እውነትን የሚነግረን ሆኖ ሳለ፤ ጅማ ለስሟ ቡና ቀርቶላት በመሠረተ ልማት ወደ ኋላ ቀርታ መታየቷ እጅግ የሚያሳዝን ነው።
ይህ ይቆየንና ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ። የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሐፍት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይኵኖአምላክ መዝገቡ አሁን ላይ ስለንባብ መወያየት ዋነኛ ቁም ነገር የሆነበት ጊዜ ላይ መደረሱን ያነሳሉ። እንዳሉትም ንባብ የመጻሕፍት ብቻ አይደለም፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ያነባል። በዚህም ንባብ «ሕይወት በዚህች ምድር ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም?» ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል፤ ይመራመራል።
ይህስ የህዋና የሥነ ፍጥረት ነገር የሚጠልቅና የሚርቅ ሲሆን፤ የሰው ልጅ ራሱንና የራሱንም ተፈጥሮ፤ በውስጡ ስለሚሠሩትና ስለሚሠሩለት ህሳዋሳቱም ያነባል። ይሁንና አቶ ይኵኖአምላክ እንደሚሉት፤ እነዚህን የተፈጥሮ ነገሮች የማንበቡ ሥራ ለየባለሙያው የተተወ ነው። እናም ስለንባብ ሲነሳ ዓለማችንን አሁን ላይ እያሳሰበ ያለው «የሰው ልጅ እርስ በእርሱ ተባብሮ መኖርን መቀጠል ይችላል ወይስ አይችልም።» የሚለው ሆኗል። ይህም ደግሞ ከመጻህፍት ንባብ ጋር የተያያዘ ነው።
ቀጥለው እንዳሉት፤ አሁን ላይ ሁለት ዓይነት ንባብ አለ። ቀዳሚው የገጽ ንባብ ነው። አቶ ይኵኖአምላክ የገጽ ንባበ ያሉት በማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚደረገውን ንባብ ነው። አንድ ሰው በማኅበራዊ ድረ ገጽ ያለውን ጽሑፍና አንባቢ አይቶ፤ «በቃ! ትውልዱ’ኮ አንባቢ ሆኗል።» ሊል ይችላል። ነገር ግን፤ ይህኛው የገጽ ንባብ አካሄዱም ሆነ ፍጻሜው መረጃን ማቀበል ነው እንጂ እውቀት መስጠት አይደለም።
አሁን ላይ የሰው ልጅ ተንቀሳቃሽ ስልኩን አውጥቶ በሚከፍትበት ቅጽበት፤ መረጃ ከአንዱ የዓለም ጥግ ሌላው ይሸጋገራል። ይህም መረጃ የማቀበል ነጻነትን እንዲሁም ኃላፊነትን ለሁሉም ሰው እኩል የሰጠ ሥርዓት ነው ሊባል የሚቻል ነው። ያም ብቻ አይደለም፤ ማኅበራዊ ድረ ገጽ አባላቱን ሁሉ «ጋዜጠኛ» ስላደረገ፤ የመረጃ ሽሚያ እዛም እዚህም ተፈጥሯል። ይህንንም ተከትሎ የሽሚያ ገበያው የተመቸው አዲስ ወሬ ፈጥሮ እንካችሁ ሲል ይታያል።
የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይኵኖአምላክ «ይህ ዓለማችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥሏታል።» ይላሉ። ታዲያ ለዚህ ነው ከገጽ ንባብ በተቃራኒ የመጻህፍት ንባብን ማዳበር አስፈላጊ የሚሆነው ብለውም ያነሳሉ። ይህም የንባብ ዓይነት እውቀትን ሊሰጡ የሚችሉ መጻሕፍት የሚነበቡበት ነው።
በዚህ መሰረት የመጻሕፍት ንባብ ሲዳብርና ሲጠነክር፤ የመረጃ ሽሚያ ቀርቶ የእውቀት ሽሚያ ይፈጠራል ማለት ነው። እንግዲህ የአገራችን ሰው «የተማረ ይግደለኝ!» እንዲል፤ ስለ እውቀት የሚደረግ ሽሚያ የሚያስማማና በምክንያት የሚያግባባ እንጂ፤ በሀሰትና ባላገናዘቡት ነፋስ ባመጣው ወሬ የሚያጣላ እንደማይሆን እናምናለን።
እናም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛገብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ እንደመሆኑ በአገራችን ካሉ የተለያዩ ተቋማት ጋር ይህን የእውቀት ሽሚያ ለመፍጠርና ንባብን ለማስፋፋት እየሠራ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ይናገራሉ። ያም ከመረጃ ሽሚያና ከሚያስከትለው አደጋ እንድንተርፍ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ሊበረታ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በብሔራዊው ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ንባብ ላይ እየሠራው ያለው ንቅናቄ ይህን ለውጥ ማምጣት የሚችለው በየክልል ከተሞች በሚያደርጋቸው ጉዞዎች ብቻ እንደማይሆን ግልጽ ነው። በተለይም የከተማ መስተዳደሮችና አመራሮች፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ይህን ኃላፊነት ወስደው መልካሙን ነገር ተቀብሎና ተከትሎ በማድረግ እንዲተባበሩ ይጠበቃል። ኤጀንሲው ይዞላቸው የሄደውን መርሃ ግብር በማስተባበርና በማዘግ ብቻ ሳይሆን፤ ለአገርም ስለእውቀት ቀናዒ የሆነና የሚሻማ ትውልድን ለማፍራት ለወጣቱ አእምሮው መጽህፍትን መመገብና ለዛም ቋሚ ሥራን እንዲሠሩ ይጠበቃል።
እዚህ ላይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጽጌ ከተማ በበኩላቸው፤ ለንባብ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ንባብን ባህል ማድረግ አልተቻለም ብለዋል። እንጂ የታሪክና የጥበብ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ እንደታሪኳ ከሆነ የንባብ ባህል የዳበረባት ልትሆን በተገባ ነበር። አሁንም ቢሆን ግን ችግሩን ለመፍታት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች፣ የባህል ቢሮዎች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የግል እንዲሁም የመንግሥት ተቋማትና ሁሉም መተባበርና መረባረብ እንዳለባቸው ምክትል ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።
ምክንያታዊ ዜጋን ከመፍጠር በተጓዳኝ፤ በተለይ በተለያዩና አላስፈላጊ ሱሶች እየተጠመደ ያለውን ወጣት የንባብን ባህልና ክህሎት ማዳበር ለነገ ብለው የሚያሳድሩት አይደለም። ዶክተር ጽጌ እንዳሉት፤ የጅማ ዩኒቨርሲቲ በጅማ ከተማ ንባብ ላይ በሚገባ ለመሥራት ከሚመለከታቸው ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል።
እናብቃ! በጅማ ከተማ ለአንድ ሳምንት በቆየው የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር ኪነጥበባዊ ምሽት በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የውይይትና የምክክር እንዲሁም የልምድ ልውውጥ መድረኮችም ተከናውነዋል። ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ እንደ እግር ዱካ ሥራው ባረፈባቸውና ልምድ ባካፈለባቸው ከተሞች፤ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በገቡት ቃል መሠረት ፍሬ አፍርተውና ሠርተው እንደሚገኙ ተስፋ እናደርጋለን። ለአገሩ የሚያስብ ዛፍ ሲተክል ለዛሬ ብሎ ሳይሆን ለነገም ነውና፤ ነገ በሚታየው ውጤት ደግሞ ሁሉም የሚመዘን ይሆናል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2011
በሊድያ ተስፋዬ