መንግስት ከአቅሙ በላይ በርካታ ፕሮጀችቶች የያዘ በመሆኑ በስራ ላይ ጫና የፈጠረ በመሆኑ ባለሃብቶች ፕሮጀክቶችን በማስተዳደርና በመገንባት ማሳተፍ ያስፈልጋል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ፡፡
ዶክተር እዮብ ይህን ያሉት የስኳር ኮርፖሬሽን ፕሮጀችቶችን ወደ ግል ይዞታነት የማዞር ስራን በተመለከተ አጠቀቃላይ ሁኔታን የሚያሳይ የመረጃ መጠይቅ (R.F.I) መዘጋጀቱን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው፡፡
መንግስት እነዚህን ፕሮጀክቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ስራ ሲያከናውን መቆየቱን የጠቀሱት ሚኒስቴር ዴኤታው አሁን ወደ ግል ይዞታነት የሚዘዋወሩት 13 ፕሮጀክቶች ሲሆኑ እነዚህ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ በስራ ላይ የቆዩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታ ላይ ያሉ ናቸው፡፡
እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ገለፃ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመረከብ ከተለያዩ አካላት ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን መንግስት አካሄዱን እያጠና ቆይቷል። በዚህም መሰረት የትኞቹ ፕሮጀክቶች፣ የባለሃብቶቹ አቅም? በምን ዓይነት አካሄድ? እንደነዚህነና የመሳሰሉትን ያካተተ 15 ያህል ነጥቦች የተዘረዘሩበት መረጃን ከሰኞ ጀምሮ በድረ-ገፅ አማካኝነት ለባለሃብቶች ይፋ እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የተገኙት የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዋዩ ሮባ በበኩላቸው የስኳር ኮርፖሬሽን ላይ የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ መደረጉ ከዋጋ አኳያ ለህብረተሰቡ ስጋት አይፈጥርም ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ለህብረተሰቡ ስጋት ሳይሆን የተሻለ እድል ፈጣሪ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ዋዩ አክለውም የተሻለ የፕሮጀክት አመራር ልምድ ያላቸው ባለሃብቶች ወደ ስራ እንዲሰማሩ ዕድል የሚፈጥር አሰራር በመሆኑ ተጨማሪ ምርት ያስገኛል፣ በዚህም የገበያ አማራጭን ያሰፋል፤ በተጨማሪም ይላሉ አቶ ዋዩ ይህ አሰራር የስራ ዕድል ለህብረተሰቡ የሚፈጥር ይሆናል።
በዳግማዊት ግርማ