መረጃ ለማግኘት መስማት የተሳናቸው ማህበር ስደርስ ማህበሩን የምትመራው እንስት አቀላጥፋ ትናገራለች። እኔም በጸሐፊዋ አማካኝነት እንድገባ ተፈቅዶልኝ እርሷ ዘንድ ስደርስ ጥያቄዎቼን ማቅረብ ጀመርኩ። ግን እኔና እርሷ ለካ እየተደማመጥን አልነበረም። ከዚያም «አስተርጓሚዬ ትምጣ አትድከሚ እኔ አልሰማሽም» አለችኝ። ለጊዜው ብዙ አላመንኳትም።
ምክንያቱም በከንፈሮቼ እንቅስቃሴዎች ጥቂት ምላሾችን ስትሰጠኝ ነበርና። በከንፈር እንቅስቃሴ መረጃዎችን መቀበሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጥበብ ነው።። አስተርጓሚዋ መጣች። የማቀርበው ጥያቄ በምልክት ቋንቋ ምላሽ ለምትሰጠው ሥራ አስኪያጅ ይነገራት ጀመር። አሁንም ቢሆን ምላሿ በድምጽ ነበር ሃሳቧን ያስረዳችኝ።
ወይዘሪት ትዕግስት አለማየሁ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናት። የራሷን ህይወት አብነት በማድረግ ነው መስማት የተሳናቸውን ሰዎችን ችግር የምትናገረው። «እኔ መስማት የተሳነኝ በቅርብ ጊዜ ነው። መናገር ደግሞ በሚገባ እችላለሁ። ይህ መሆኑ ደግሞ ብዙዎችን ያስኮርፋቸዋል። መስማት እየቻልኩ የማልመልስላቸው ይመስላቸዋል። ለማስመሰልም የምጠቀም የሚመስላቸው አሉ። በዚህም ብዙዎች ኩራተኛ፣ ሰው ትንቃለች፣ ከማን በልጣ ነው ወዘተ ይሉኛል። ይህ የሆነው ደግሞ የውስጥ ህመሜን ባለመረዳታቸው እንደሆነ አስባለሁ። በመሆኑም ብዙም አልከፋባቸውም» ትላለች።
የዓይን እይታና መናገር ብቻ ብዙዎችን ያሳስታል የምትለው ትዕግስት፤ይህም መስማት የተሳናቸውን ትኩረት እንዳያገኙ ሆኗል። አሁን ባለው ሁኔታ ብንመለከት እንኳን አገሪቱ ውስጥ ያሉት መስማት የተሳናቸው ልጆች የምልክት ቋንቋ ከመማር አንጻር ዕድሉ አልተሰጣቸውም። በጤና፣ በሥራ ዕድል፣ በትምህርት፣ በፖለቲካው ተሳትፎና በሌሎች ጉዳዮችም ቢሆን እምብዛም አይታዩም። ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው ነው ህይወታቸውን የሚመሩት።
በአገር ደረጃ ያልተማረ ኃይል ቢፈለግ የመጀመሪያ ደረጃውን የሚይዙት መስማት የተሳናቸው ለመሆናቸው ከእኔ በላይ ምስክር አይኖርም» ትላለች። ለሥራም ሆነ ለተለያዩ ስብሰባዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲገናኙ የከንፈር እንቅስቃሴን በመመልከት ብቻ እንደሚግባቡና ልምዱ የሌላቸው ደግሞ ምንም መረጃ ሳይዙ ይመጣሉ ትላለች።
መስማት የተሳነው ይህ ያስፈልገዋል ተብሎ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አልተደረገም። በአገር ደረጃ እንኳን 27 ቅርንጫፎችን ከፍቶ ማህበሩ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፤ ከሚሰጠው በጀት አንጻር የሚጠበቅበትን ሥራ እያከናወነ እንዳልሆነ ታስረዳለች። ይህ መሆኑም መስማት የተሳናቸው ካሉባቸው ችግሮች መላቀቅ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
መስማት የተሳናቸው በብዙ ነገር ተጎጅነታቸው እያየለ ነው የምትለው ትዕግስት፤ ከሰሞኑ የገጠማትን አንድ ጉዳይ ለአብነት ትጠቅሳለች። ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ዕድሉን ያገኘ አንድ ወጣት ወደእርሷ መፍትሄ ፍለጋ መጥቶ ነበር። ይህንንም ዕድል ያገኘው በበርካታ ፈተና ውስጥ አልፎ ነው። ሆኖም ከመምህራንም ሆነ ከተማሪዎች ጋር ለመግባባት የሚችልበት ሁኔታ በዩኒቨርሲቲው የለም።
ማንም በምልክት ቋንቋ አያናግረውም። ስለዚህም ትምህርቱን ለማቋረጥ መገደዱን ነገራት። እርሷም ከአቅሟ በላይ በመሆኑ ማድረግ የምትችለው ነገር ባለመኖሩ ለቀጣይ የቻለችውን እንደምታደርግለት ቃል በመግባት እንደሸኘችው ገልጻለች።
እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጿ፤ ባደጉት አገራት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከጽዳትና ጥበቃ ጀምሮ የምልክት ቋንቋ ተምረው ግልጋሎት ይሰጣሉ። ይህ ተሞክሮም በአገራችን መጥቶ በአዲስ አበባ ሆሳዕና መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል። ነገር ግን በሚሊዮን ለሚቆጠር መስማት የተሳናቸው አንድ ትምህርት ቤት በቂ አይደለም። ስለዚህ መንግሥት እይታውን ወደ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማድረግ ይኖርበታል።
ብዙዎች አካል ጉዳተኝነትን ከአካል መጉደል ጋር ብቻ ያያይዙታል። ትኩረት ለአካል ጉዳተኞችም ሲባል መጀመሪያ የሚታወሰው አይነስውር፣ እጅና እግሩን ያጣ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ መስማት የተሳነውን ትኩረት እንዳገኙ አድርጓቸዋል። በዚህም አብዛኛው በአገሪቱ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው የትምህርት ዕድል እንዳያገኙ ሆነዋል።
ዕድሉ ገጥሟቸው መማር የቻሉትም ቢሆኑ የሥራ ዕድል የላቸውም። ከነበሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት ወጥተው ዩኒቨርሲቲ ሲገቡም መስማት ከሚችለው እኩል እንዲማሩ ይገደዳሉ። ይህንን አስመልክቶ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ «አካል ጉዳተኞችን እንደ ሁለገብ የልማት ጉዳይ በመቁጠር አካል ጉዳትን በመከላከልና አካል ጉዳተኞች የትምህርት፣ የሙያ ሥልጠናና የተሀድሶ አገልግሎት የእኩል ዕድል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል» ተብሏል። ግን ከወሬ ያለፈ እንዳልሆነ የመረጃውን አሰራር ብቻ ማየት ይበቃል ይላሉ።
እናስ ምን ይሁን? ከተባለ አሁንም በአስተርጓሚዋ አማካኝነት ሃሳቧን ያጋራችኝ መንበረ መኮንን እንዲህ ትላለች። «የምልክት ቋንቋ መማር ለሁሉም ቋንቋ በቀላሉ መልስ መስጠት ነው። ይሁንና የመስማት የተሳናቸው መግባቢያ ተደርጎ ስለሚወሰድ ለሁለቱም አካላት ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል። በስመ አካል ጉዳተኛም ማንም ትኩረት ሰጥቶት ሲሰራበት አይታይም። ይህ ደግሞ በይበልጥ ተጎጂውን መስማት የተሳነው አድርጎታል»
መስማት የተሳናቸው በሚሄዱበት ሁሉ እንደተቸገሩ ነው። ሱቅ ለመግዛት ማስተርጎም፣ ለመማር ማስተርጎም፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘትም ማስተርጎም ይጠበቅባ ቸዋል። መረጃ የማግኘት ነጻነታቸውም በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ላይ በእጅጉ ችግር ያለበት ነው። በጣም ትልልቅ መርሐግብሮችን አዘጋጅቶ የምልክት ቋንቋ አለመጠቀምም የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ ሠራተኛ ለሆነ መስማት የተሳነው ተስፋ አስቆራጭ ነው። ምክንያቱም ያለ ድምጽ መረጃ ማግኘት አይቻልም ትላለች።
እንደ መንበረ ማብራሪያ፤ በማህበረሰቡ አመለካከት መስማት የተሳነው ህመምተኛ ነው። ስለዚህም ከቤት እንዲወጣ እንኳን ዕድሉ አይሰጠውም። እናም ሁሌም በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲኖር እየተደረገ ነውና ትኩረትን ይሻል።
በተለይ መንግሥት ልዩ ትኩረት ካልሰጠው በስተቀር ማንም አይደርስለትምና የምልክት ቋንቋን ከህጻንነት ጀምሮ በሥርዓተ ትምህርት አካቶ ማስተማር ቢችል በጥቂቱም ቢሆን አሁን በጉዳቱ ውስጥ የሚኖሩ ህጻናትን መታደግ ይቻላል። መምህራንና ብዙዎች መማር ከቻሉም እንዲሁ መስማት የተሳነው መፍትሄ ያገኛልና ይታሰብበት ትላለች።
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው