የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ከድርድር በኋላ ብዙ ጊዜ በመተማመን እጦት እና ቃል የተገባን ጉዳይ ባለመፈጸም ምክንያት ድርድሮች እንደሚበላሹ ከሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል። በዓለም ላይ 154 ድርድሮች የከሸፉት ከተስማሙ በኋላ ቃላቸውን መጠበቅ ባልቻሉ ወገኖች መሆኑን ጥናት እንደሚያሳይ አመልክተዋል።
እኛ ግን አንድ እርምጃ ሄደናል። ተወያይተናል፣ ተስማምተናል፣ ፈርመናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀጥሎ የሚጠበቅብን የገባነውን ቃል በታማኝነት በመፈጸም ሰላሙን ዘላቂ ማድረግ ነው ብለዋል። ሰላሙን ዘላቂ በማድረጉ በኩል ግን ፈታኝ ነገር አሊያም ችግር የለም ማለት እንዳልሆነ ያስረዱት ዶክተር ዐቢይ፣ የዓለም ልምምድም የሚያሳየው ችግር አለመኖሩን እንዳልሆነ አስረድተው፤ ችግር እንዳያጋጥም ግን አበክረን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
ይህን በፌዴራል መንግስትና በሕወሓት መካከል የተካሄደውን የሰላም ስምምነት ወደመሬት በማውረድ እያንዳንዱ ሕዝብ ከሰላሙ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው በሚል አዲስ ዘመን ላነሳው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንደገለጹት፤ ሰላም የውስጥ እርካታ ነው፤ ሰላም እረፍት ነው። ብዙዎች ሰላምን ከግጭት እና ከጦርነት ጋር በተቃራኒ ያለ ብቻ አድርገው ይስሉታል፤ ሰላም ግን ከአስተሳሰባችንም ከአመለካከታችንም ጋር የሚያያዝ ነው። የሰላም ትርጉም ብዙ ጊዜ ከውስጥ ሰላም ጋር የሚያያዝ ነው። የውጭ ሰላማችን በጣም ውስንነነት አለው። ለአብነትም የውጭ ሰላም ስንል ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሲሆን፣ ይህም የሚመነጨው ከውስጥ ሰላም ነው።
ስለዚህ ብዙ ጊዜ የውስጥ ሰላም ለውጪው ሰላም መሠረትም ወሳኝም ነው። የውስጥ ሰላም ሲጠናከር ለሀገርም ሆነ ከውጭ ጋር ላለን ግንኙነት ትልቁን ሚና ይጫወታል። የውስጥ ሰላም ጥንካሬያችንና ኃይላችንም ስለሚሆን የውጪው ጉዳይ ሰላም እንዲሆን ያደርጋል። በውስጣችን ያለው መተሳሰርም በጣም ከፍተኛ የሆነ ኃይል ይሰጣል። ስለዚህም የሰላም መሠረቱ የውስጥ እርካታ ብሎም የውስጥ አንድነት ነው። አንድነት ብዬ ስል አዕምሮ እና አካል ማለት ነው። ይህ የአዕምሮ እና የአካል መግባባት ሲኖር ውስጣዊ አንድነት ይኖራል ሲሉ አስረድተዋል።
ታዲያ ከሰሞኑን በደቡብ አፍሪካም ሆነ በኬንያ የተደረሰበት የሰላም ስምምነት እንዴት ዘላቂ ማድረግና ሕዝቡንም ከሰላሙ እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ለተባለው መሠረታዊ ጥያቄ ዶክተር ዮናስ፣ በመጀመሪያ በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደማይቻል ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚናገሩት ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም ለሰላሙ ዘብ መቆም አለበት። በተለይ ደግሞ ከማንም በላይ ሕዝቡ ከሰላሙ በተቃራኒ የቆሙ አካላትን በሰላማችን ላይ አትምጡብን ማለት ይጠበቅበታል። ይህን በብዙ ጥረት ያገኘነውን ሰላም ዳግም ማጣት አንፈልግም ሊሉም ይገባል። ከዚህ በፊት የተከሰተው ጥልና ግጭት አይደገም ማለትም ከሕዝቡ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በጠብና ግጭት ያተረፍነው ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት እልቂትን ብሎም የኢኮኖሚ ድቀትን እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት መተጣጣትን ነውና ከጦርነት አትራፊ የሆኑትን አካላት ከሰላማችንና ከሰላማዊ መንገዳችን ዘወር በሉ ማለት ተገቢ ነው።
ይህ የሰላም ስምምነት ወደመሬት ወርዶ ዘላቂ መሆን እንዲችል ዋናው የሕዝቡ ተነሳሽነት ነው ያሉት ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር ብሎም በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ሕዝብ፣ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ድርሻው ከፍ ያለ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ስለዚህም ይህ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ለጎን ለሰላሙ ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት። ይህ አንዱ ለሰላሙ ዘላቂነት ወሳኙ የምለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር ዮናስ ገለጻ፤ የሰላም ስምምነቱ ዘላቂ እንዲሆንና ሕዝቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ሁለተኛው ደግሞ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራውን በአግባቡ በማከናወን ላይ ይገኛል። ኮሚሽኑ በቀጣይ ወደትግራይም የሚጓዝ ይሆናል። ኮሚሽኑ የሚቀረው ነገር ቢኖር ስትራቴጂ ብቻ ነው። ዳግም ይህ ጦርነት እንዳይከሰት ምን እናድርግ? ይህንንስ ሰላም ከሕዝቡ ጋር በመሆን እንዴት ወደመሬት እናውርድ? ዳግም ይህ ጦርነት እንዳይከሰትስ ምን እናድርግ? ይህንን ሰላም እንዴት የእያንዳንዱ ሰው እንዲሆን እናድርግ? በሚለው ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር መመካከር ነው። ይህ ለሰላሙ ዘላቂነት ሌላው ተጠቃሹ ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በበኩላቸው፤ የማያልቅ ጦርነት ውሃ በወንፊት ነው። ዝም ብሎ እየተዋጉ መኖር አይቻልም። ውሃ በወንፊት ዘግኖ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ መውሰድ እንደማይቻለው በቀጣይነት በውጊያ አዙሪት ውስጥ የምንሽከረከር ከሆነ የምናስባቸውን ጉዳዮች ልናሳካ አንችልም ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ አንድን ነገር ለማስቀጠል ከፈለግን ሌላ ነገር መተው ይኖርብናል። ሰላምና ብልጽግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነትን ማቆም በእጅጉ ያስፈልጋል። ሁሉም እንደሚያውቀው እኛ የምንዋጋው ከአንድ ግንባር ጋር አይደለም። ለአንድ ሳምንት፣ ለአንድ ወር ቢሆን ችግር የለውም። እየቀጠለ ከሄደ ግን እንደ ሀገር እንደቃለን። ጦርነትን ማቆም ቀዳሚ ምርጫችን አድርገን የምንወስደው ለሰላማችንና ለብልጽግናችን ስንል ነው።
የሰላም መጥፎ፣ የጦርነት ጥሩ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰላም ሁሌም ጥሩ ነው፤ ጦርነት ሁሌም እያሸነፍክም ቢሆን መጥፎ ነው ብለዋል። ምክንያቱም በጦርነት ውስጥ ሰው መግደል አለ፤ በጦርነት ውስጥ የሚተኮሰው ዶላር ነው። ዶላር እየተተኮስና ሰው እየተገደለ የሚገኝ ጥቅምና ጥሩ ነገር የለም። ሁሌም ጦርነት መጥፎ ነገር ሲሆን ሰላም ደግሞ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያውያን ህልውና፣ ልዕልና እና አንድነት ላይ የሚገዳደር ነገር ሲፈጠር እና ያ ነገር በሰላም መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ መፋለም ግዴታ ነው ብለዋል።
ድርድርም፣ ንግግርም፣ ውይይትም ካለ ለኢትዮጵያ አንድነት፤ እድገት ብሎም ሰላም ብቻ ነው። ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነትና እድገት ድርድር እንኳን አፍሪካ ውስጥ ሌላም ቦታ ካለ እንሄዳለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ለሰላም ያለውን ጽኑ እምነት አሳውቀዋል። ለሀገር ጥቅም ሲባል መሄድ የማንፈልግባቸው ቦታዎችም ቢሆን እንኳ እንደሚሄዱ አመልክተዋል።
ሰላም እንዳይናጋ እና ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው ወደ አስገዳጁ ጦርነት ከመገባቱ ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበር ይታወሳል። በተለይም መንግሥት የአገር ሸማግሌዎችን፣ ታዋቂ ሰዎችን እና የሰላም እናቶችን ወደ ትግራይ ክልል በመላክ ሰላምን ለማስፈን የማይናቅ ሚና መጫወቱ የቅርብ ጊዜ ተውስታ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት፤ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ አምና ጦርነቱ ሰሜን ሸዋ ደርሶ እንኳ የአሸናፊነቱ ስሜት ከተፈጠረ በኋላ እስረኞች መፈታታቸውና የእስረኞቹ መፈታት ብዙዎችን ያስኮረፈ መሆኑ የሚታወስ ነው። እስረኞች የመፈታታቸው ጉዳይም ሰላም ማፅናት ከተቻለ ስለሚሻል በሚል እንደሆነም አይዘነጋም።
ዶክተር ዮናስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ እንደ አለመታደል ሆኖ እንጂ ገና ስንፈጠር በየትኛውም ሀገር ያለ ነጩም ሆነ ጥቁሩ ሰው በተፈጥሮ ሰላማዊ ነው። ከጊዜ ጋር ተያይዞ በመጣው ሒደት ሰው ወንድሙን ገድሎ በወንድሙ ደም ላይ መመላለስና ራሱን ከፍ ማድረግ እንዲሁም በወንድሙ ትከሻ ላይ ተንጠላጥሎ ወደስልጣን ማማ መፈናጠጥን ልምድ አድርጎ ይዞታል። በዚህም አካሄድ ከሰላም ሳይሆን ከጦርነት አትራፊ የሆኑ ሰዎችን እናገኛለን። የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎች አሉ፤ እነዚህ የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎች ማትረፍ የሚችሉት እኛ ስንባላ ነው። በተመሳሳይ ደግሞ ውጪ አገር ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ብሎም አፍሪካ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ከትርፋቸው አንጻር ብቻ የሚያዩ አሉ። እነርሱ የሚፈልጉት ምናልባትም ጦርነቱ የሚጠናከርበትን ሁኔታ ነው። የተገኘው ሰላም መሬት እንዲወርድ አይፈልጉም።
ምክንያቱም ከጦርነት ማትረፍ ስለሚችሉ ነው። ጦርነት ባለበት ቀጣና ሁሉ እነርሱ አትራፊነታቸውን እንጂ ለሰው ልጆች ሞት ምንም ያህል ርህራሔ የሌላቸው በመሆናቸው ነው። ከጦርነቱ የተነሳ ለሚደርሰው አካል መጉደልም ሆነ ከኢኮኖሚው መድቀቅ የተነሳ ለሚሰደደው ሕዝብ አዘኔታ የማያሳዩ ናቸው ይላሉ። እነዚህ አካላት የሚያስቀድሙት የእነርሱን አትራፊ መሆንና ምቾትን ነው። የእነርሱን ተደላድሎ መኖርን ብቻ ነው። ስለሌላው ስቃይም ሆነ መሰደድ በጭራሽ አይመለከተንም ብለው ራሳቸውን ያሳመኑ ናቸው ሲሉም ነው ዶክተር ዮናስ የሚናገሩት። ነገር ግን እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው የሕዝቡ ተነሳሽነት፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊታችን ጥረትና የመንግሥት ቁርጠኝነት እስካለ ድረስ የሰላም ስምምነቱ መሬት የሚወርድ ይሆናል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ ሰላምን የሚጠሉ የጦርነት ነጋዴዎች አሉ፤ ጦርነት የሚጠሉ የሰላም አምባሳደሮች አሉ። ግራ የሚያጋባው ሰላምም ጦርነትም የማይፈልጉት ላይ ነው። ሰላም ሲሆን ጦርነት ይላሉ። ጦርነት ሲሆን ሰላም ይላሉ። እነዚህ ግራ ያጋባሉ። ግራ የሚያጋባና መልስ ልሰጥበት የምቸገረው ጉዳይ ነው። ነገር ግን ውስጣዊ ሰላም የሌላቸው ሰዎች፤ ውስጣዊ እረፍት የሌላቸው ሰዎች በውጭ የሰላም አየር መተንፈስ ማየት አይችሉም። ውጫቸው የተናደ ነው። ከሁሉም ነገር ውስጥ ችግር መዘው ችግር ማየት ይፈልጋሉ። ለእኛ ግን ከዚህ ቀደም እንዳልነው፤ አሁንም እንደምንለው ሰላም በእጅጉ ያስፈልገናል። ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም፤ የሕግ መከበር ማለት ነው። የሕግና ሥርዓት መከበር ማለት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እኛ እንደ አገር ለመጽናትና ለመቀጠል በተቻለ መጠን ትዕግስተኞች፣ አስተዋዮች እና ሰላም ፈላጊዎች መሆናችን ጠቃሚ ይሆናል። ሁል ጊዜ ግጭትና ጦርነት ደግሞ ካልን ተመልሶ እርሱ ሊመጣ ይችላልና እንደሀገርም እንደ ሕዝብ ምንም እንኳን ጦርነት ፈላጊ ሰዎች የሉም ባይባልም ብዙዎቻችን ብናደርግ መልካም የሚሆነው ለሰላም መትጋት ነው፤ ለሰላም መሥራት፤ በምንችለው አቅም ልክ ሰላም እንዲረጋገጥ መጣር ቢሆን መልካም ይሆናል ብለዋል።
እርሳቸው ለፓርላማ አባላት እንደገለጹት፤ ለነገ ማንም ሰው ዋስትና ሊሰጥ አይችልም። እኛ ግን ዛሬም ነገም በተቻለ መጠን ለሰላም ታምነን መትጋት አለብን። ድርድሩም ሆነ ስምምነቱ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ፍሬያማ እንዲሁም ውጤታማ እንዲሆን መደገፍ ያስፈልጋል። ትግራይ ገብተን ያየነው ነገር ሕዝቡ በጣም ሰላም እንደሚፈልግ ነው። ውሃ፣ መብራት፣ ምግብ እንደሚፈልግ ነው መረዳት የቻልነው። ያስተዋልነው ነገር ቢኖር ከአማራ ወንድሞቹ፣ ከአፋር ወንድሞቹ ከኦሮሞ ወንድሞቹ ምንም ችግር እንደሌለበትም ነው። ይህን ብናስቀጥል መልካም ነው። በበኩሌ የምፈልገው ሰላም እንዲመጣ ነው፤ ደግሞም በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ፤ ሰላሙ እንዳይበላሽም በታማኝነት የምችለውን ሁሉ ጥረት ለማድረግ ነው የምፈልገው። እናንተም እንድትደግፉ የምፈልገው በዚያው መንፈስ ነው።
ዶክተር ዮናስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የሰላም ፍልስፍና እንዲሚለው ለሰላም መንገድ የለውም፤ ሰላም ራሱ መንገድ ነው። ስለዚህ ሰላም ራሱ መሄጃም መድረሻም መንገድም ነው። ስለዚህ ሰላም መሄጃም መድረሻም መንገድ ስለሆነ በጦርነት አሊያም በቅጣት ብቻ ሳይሆን በፍቅርም፤ በመነጋገርም ሰላምን ማምጣት ይቻላል ብሎ ማመን የግድ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ሰላሙ ወደመሬት እንዳይወርድ ሳይገባቸውና ሳያውቁ የሚተቹ አካላት ከዚህ አንጻር መረዳት ቢችሉ መልካም ነው።
ወደሰላም ስምምነቱ ከተመጣ በኋላ ግን ከጦርነቱ ያልተናነሱ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያን እንደሚጠብቋት መረዳቱ መልካም ነው ይላሉ። ከትጥቅ ማስፈታት ጀምሮ በጦርነት የቆየውን ኃይል ደግሞ እንዲታደስ ሁኔታዎችን እስከማመቻቸት ድረስ ሀገራችን ብዙ ልትሠራ ይገባል። ምክንያቱም ይላሉ ዶክተር ዮናስ፣ ለምሳሌ ከአንደኛው አካል የጦር መሣሪያ ይወሰድ እንጂ አሁንም በጦርነት የማመኑ ነገር ይኖራልና በዚያ ዙሪያ በመጀመሪያ መነጋገርና ማሳመን ተገቢ ነው ብለዋል። ምንም እንኳ በእጅ ላይ ምንም አይነት የጦር መሣሪያ ባይኖርም አሁንም ድረስ በጦርነትና በጦርነት ብቻ የማመኑ አመለካከት ስለሚኖር ያንን አመለካከት በመነጋገር ከወዲሁ መፍታት መቻሉ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም