ዛሬ ላይ ለመድረስ በሴትነቷ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች። ሆኖም የገጠሟትን ፈተናዎች በራሷ ጥረት ታግላ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚያስተምሩ ምሁራን መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች።
ስሟ ዶክተር ትርሲት ሳህለድንግል ይባላል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪ፣ በሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና በቅርቡ በዚሁ የትምህርት መስክ የፒኤች ዲ ዲግሪ ባለቤት ሆናለች። ላለፉት ጥቂት አመታትም ስትማርና ስታስተምር ቆይታለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ እያለች በእርሷም ሆነ ሌሎች ከእርሷ ጋር ሲማሩ በነበሩ ሴት ተማሪዎች ላይ በተለያየ መልኩ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስ እንደነበር ታስታውሳለች። በጊዜው በሴት ተማሪዎች ላይ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት የማድረጉ ተግባር ደካማ እንደነበረም ትገልፃለች። በሴቶችና ወንዶች መካከል የፆታ እኩልነት እንደሌለም ታስረዳለች።
ዩኒቨርሲቲዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉና የማህበረሰቡ ነፀብራቅ በመሆናቸው በነዚህ ተቋማት የፆታ እኩልነት አለመኖር አዲስ እንዳልሆነም ነው ዶክተር ትርሲት የምትናገረው። ይህ ችግር እንዲሚቀጥልና ከዚህም በላይ ገፍቶ ሊሄድ እንደሚችልም ትጠቁማለች።
መጀመሪያ አካባቢ በምንም አይነት መልኩ የሴቶች የፆታ እኩልነት ጥያቄ የማይመለስ እንደነበር፤ ነገር ግን አሁን በተደረጉ ትግሎች እየተሻሻሉ የመጡ ነገሮች እንዳሉ ትገልፃለች። እርሷ አሁን የደረሰችበት ደረጃም ለዚህ አንዱ ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ትጠቅሳለች።
በተለይ ሴቶች መማራቸውና የትምህርት ደረጃቸው እየጨመረ መምጣቱ የትግሉ ውጤት መሆኑንም ታስባለች። ነገር ግን አሁንም ችግሩ ቀጥሎ በዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በሌሎች ተቋማት ውስጥ እንዳለ ነው የምትገልጸው። ይህም በተለያየ መንገድ ሊገለፅ እንደሚችልም ትጠቁማለች።
‹‹ለሴቶች ምቹ ሁኔታ የለም የምትለው›› ዶክተር ትርሲት እርሷ ከአስር ዓመት በፊት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስትቀጠር በምን መልኩ ማስተማርና ከዩኒቨርሲቲው ሁኔታ ጋር አብራ መሄድ እንዳለባት አንድም የነገራት ሰው እንዳልነበር ታስታውሳለች። ከሌሎች የዩኒቨርሲቲው ወንድ መምህራን ጋር የነበራት ግንኙነትም የከረረ በመሆኑ ይህ ለሷ ከባድ ውጣውረድ እንደነበረም ነው የምታስታውሰው።
ተማሪዎቿ በሆነ አጋጣሚ ስልኳን አግኝተው እየደወሉ የመጀንጀን ነገሮች እንደነበሩም ትገልፃለች። እርሷ ያለፈችበትን ሁኔታ ላለመድገም ከተማሪዎች ጋር እንደ ጓደኛ የመሆን መርህ የነበራት ቢሆንም በተለይ የተማሪዎች ውጤት ሲደርስ የነበረውን ውጣ ውረድ መቋቋም አቅቷት እንደበረም ነው የምትገልጸው። አልፈው የሚመጡ ሰዎች እንዳጋጣሟትም ትናገራለች።
እንደውም በአንድ ወቅት አንዱ ተማሪዋ ታክሲ ውስጥ ስትገባ አይቷት ተክትሎ ገብቶ በግድ የፍቅር ጥያቄ እንዳቀረበላት ታስታውሳለች። እነዚህንና መሰል የፆታ ትንኮሳዎች ከወንድ ተማሪዎቿ ሲገጥሟት እንደነበርም ገልፃ፤ እንዲህ አይነቱ ችግር ሲገጥም ችግሩን እንዴት ማለፍ እንዳለባት የሚያሳዩ ከእርሷ የበለጠ ልምድ ያላቸው መምህራን እንዳልነበሩም ታመለክታለች።
ዶክተር ትርሲት እንደምትናገረው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተለይ ከሴት መምህራን ጋር አብሮ መስራት፣ መደጋገፍና ሴቶች ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መከላከልና ቢደርስባቸው እንኳን የገጠማቸውን ችግሮች እንዴት ማለፍ እንደሚችሉ ሀሳብ ማቀበል ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል።
የአካዳሚው አካባቢ ሁሌም ማንበብና ውጥረት የሚታይበት እንደመሆኑና ብዙ ነገር እንደመፈለጉ ለዚህ የግድ መተጋገዝ የሚጠይቅ ቢሆንም ይህ ነገር ግን በብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እምብዛም አይታይም። በጀማሪና ልምድ ባላቸው መምህራን መካከልም ሰፊ ክፍተት እንዳለ ሁኔታዎች ያሳያሉ። ተነጋግሮ ችግሮችን የመፍታትና የመረዳዳት ባህሉም ዝቅተኛ ነው።
እንደ ዶክተር ትርሲት ገለፃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን የፆታ እኩልነት ከፍተት ለመሙላት ከሁሉ በፊት ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል። መገፋፋት ባለ ቁጥር በርካታ ነገሮች ሊጎሉ ስለሚችሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ልጆች ጭንቅላት የሚሰራባቸው በመሆኑ መልካም ስብእና ግንባታ ላይ ብዙ ሊሰራ ይገባል።
ይህ በሆነ ቁጥር ሰዎች ሌላውን እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ጥሩ የመግባባት ክህሎት ማዳበርም ያስፈልጋል። ሁሌም አምባገነን መሆንና ሁሌም እውቀቱ መምህራኑ ጋር ብቻ እንዳለ መቁጠርም አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ ሌሎችንም መስማት ተገቢ መሆኑን መረዳት ይገባል። የሁለትዮሽ እውቀት መጋራትም ያስፈልጋል።
ብዙ ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከላይ ወደታች ናቸው። ሌላው ምንም አያቅም ብለው ነው የሚነሱት። የትኛውንም ሴክተር መምራት ይፈልጋሉ። ይህ ግን መሆን የለበትም። ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸው ከማህበረሰቡና ከሌሎች ሴክተሮች መማር አለባቸው። አሁን እየተወራ ላለው የትምህርት ጥራት መጓደልና ውድቀት ብሎም የማህበረሰብ ክስረት ዩኒቨርሲቲዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። አሁን ላይ ለተፈጠሩ ቀወሶችም በጎ ባልሆነ መልኩ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ከዚህ አንፃር ይህን ክፍተት መቀበል ለማስተካከል ጠቃሚ ይሆናል። በተለይ ለወደፊት የተሻለ ነገር ለማምጣት ፖሊሲን ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ጭንቅላትን ጭምር መቀየር ያስፈልጋል። መልካም ስብእና ግንባታና መደጋገፍ ላይም መስራት ይገባል።
ከዚህ በፊት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሴቶች መብታቸውና ግዴታቸው ምን እንደሆነና ፆታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ብሎም በሴትነታቸው ችግሮች ሲያጋጥሟቸው የት መሄድ እንዳለባቸው የተለያዩ ኔትዎርኮች ነበሩ። ሆኖም ይህ ኔትዎርክ በመላላቱ ምክንያት መምህራን ከሚያደርጓቸው መጠነኛ ጥረቶች ውጭ ስርዓቱን የተከተለ ስራ እየተሰራ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱን ችሎ የተቋቋመ ቢሮም የለም።
ከዚህ አንፃር በርካታ ክፍተቶች በመኖራቸው በብዙ ሊሰራ ይገባል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ አመራሮች ችግሩን ወርደው ማየት ይጠበቅባቸዋል። ጉዳዩን ፖለቲካዊ መልክ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ በፀዳ መልኩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ ነው።
ዶክተር ሰውዓለም ፀጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰርና በስርዓተ ፆታና ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ዳይሬክተር ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሶስት ዋና ዋና ዘርፎች ስራቸውን ይሰራሉ። እነዚህም ማስተማር፣ መመራመርና ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት ናቸው።
ከዚህ አኳያ በሶስቱም ምሶሶዎች በማስተማር የፆታ ጥናት በሚል ትምህርቱ ሊሰጥ ይችላል። በምርምር ደግሞ የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ያደርጋሉ። በማህበራዊ አገልግሎትም ከሲቪል ሰርቪስ ድርጅቶችና ከማህበረሰቡ ጋር የማስተማር፣ የአድቮኬሲና ሚዲያውን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራሉ።
የፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥ አንፃርም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናቸው ጉልህ ነው። ነገር ግን ተቋማቱ ሚናቸውን በሚፈለገው ልክ ባለመወጣታቸው የፆታ እኩልነትን በሚገባ ማረጋገጥ አልተቻለም። ይህ ሲባል ግን ደግሞ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በተቋማቱ በኩል ምንም አልተሰራም ማለት አይደለም።
ዶክተር ሰውዓለም እንደሚያብራሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናቸውን በሚገባ በመወጣት የፆታ እኩልነትን እንዲያረጋግጡ ሚዲያውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። ስርዓተ ፆታ ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮችን መስራትም ይጠበቅባቸዋል። በተለይ የፆታ ጉዳይ ሁሉንም የትምህርት መስኮች የሚነካ በመሆኑ ተቋማቱ የስርዓተ ፆታ ጉዳይን ከነዚህ የትምህርት መስኮች ጋር አዛምደው ጥናትና ምርምሮችን መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ተቋማቱ ያጠኗቸውን ጥናቶች ደግሞ ሼልፍ ላይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ማሳተምና ማሰራጨት፣ በሚዲያ ማቅረብ፣ ሀገር እንዲያውቀውና ህዝብ እንዲማርበት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ደግሞ ሞዴል ሆነው በሚዲያ ሲቀርቡ በየቤቱ ያሉ ታዳጊ ሴቶች ይነሳሳሉ። በሂደት የሴቶች እኩልነት ሲረጋገጥና የበለጠ እየተዋወቀ ሲሄድ ሀገር ታድጋለች። ሀገር እንድታድግ ደግሞ ተባብሮ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ስርዓተ ፆታ ፖሊሲ እ.ኤ.አ በ2015 ወጥቷል። በመቀጠልም ተከልሷል። የትገባራ መመሪያም ተዘጋጅቶለታል። ፖሊሲውን ተከትሎ ቀደም ሲል ከነበረው ሁኔታ አንፃር አሁን ላይ ብዙ መሻሻሎች ይታያሉ። ለአብነትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ሴት ምክትል ፕሬዝዳንቶች አሉ። ቀደም ሲል ሴት ዳይሬክተሮችም በቁጥር አነስተኛ የነበሩ ቢሆንም አሁን ላይ ቁጥራቸው አድጓል። የዲኖችም ቁጥር ከፍ ብሏል።
ይህ ለውጥ ታዲያ በስርዓተ ፆታ ፖሊሲው መሻሻል ምክንያት ነው የመጣው ወይስ በሌላ የሚለው ጉዳይ ግን ጥናት ይፈልጋል። ነገር ግን ከስርዓተ ፆታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለውጦች አሉ። ሆኖም ለውጦቹ በቂ ባለመሆናቸው ከዚህም በላይ ብዙ መስራትን ይጠይቃል።
ዩኒቨርሲቲዎች የፆታ እኩልነት ትንሹን ችግር ነው የሚያሳዩት። ከዚህ አንፃር ከዩኒቨርሲቲዎች ባሻገር በመላው ሀገሪቱ የፆታ እኩልነት ችግር አለ። በመሆኑም ከዩኒቨርሲቲዎች በዘለለ ከፆታ እኩልነት ጋር በተያያዘ በየትኛውም ቦታ ሄዶ መሰራት የግድ ይላል። ዩኒቨርሲቲዎችም የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ ስራቸው ነውና ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው የፆታ እኩልነት ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት ለውጥ እንዲመጣ መታገል ይጠበቅባቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/ 2015 ዓ.ም