የጦርነት ወሬ ሽው ሲል ቅድሚያ ተጠቂዋም ተጎጂዋም ሴት እንደሆነች ሁላችንም እንስማማለን። ነገር ግን ጀብዱ ፈጻሚነቷን ለመቀበልና ለመናገር አንደበታችን ይያዛል። ስለጀግንነትና ጀብዱ ሲነሳ ሴቷ ትዘነጋለች። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ስለሌለን ነው። ግን ዞር ካልን ከየትኛውም ጦርነት ጀርባ ሴቶች አይጠፉም። ያለእነርሱ ብልሃትና ድጋፍ ወንድ ልጅ ቀድሞ መውጣት አይችልም። ያለእነርሱም ምሪት እንዲሁ መላቁ አይመጣም። ማሸነፍ ሁሉ የሚቻለው በእነርሱ ድጋፍ ብቻ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት እንችላለን። አንዱ እቴጌ ጣይቱ ናት። ምኒልክና መሰል የአገር ባለውለታዎች ብቅ ያሉት ጣይቱ በሰጠችው አመራርና እንቢ አልገዛም ባይነት ነው።
ዛሬም ቢሆን ከወንዶች በላይ ታሪክ ሰርተው የሚነሱ በርካቶች ናቸው። በተለይም ከሕወሓት ጋር በነበሩት ጦርነቶች ጠቅሰን የማንጨርሳቸው በርካታ የመከላከያ ሰራዊት ሴት ጀግኖች አሉን። ከእነዚህ መካከል ለዛሬ ቀደም ሲል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከዘገብናቸው ጥቂቶችን ልናስታውሳቸው ወደናል።
በሙያ፣ አልሞ በመተኮስ፤ ብቁ ሴት ጀነራል መኮንን በመሆን፣ ተራራና ሸንተረሩን ዱርና በረሃው ሁሉ አቋርጠው በመሄድና ተፈጥሮ ሳያግዳቸው አሸናፊ ሆነው በማሳየት አጀብ ያሰኙን ናቸው እነዚህ አባላት። ከዚያም ባሻገር ስንል ለሌሎች ሴቶች የሥነልቦናቸው ጥንካሬ ማሳያ ሆነዋል። ታሪክም አስመዝግበዋል። እርግጥ ነው ምስጢሩ አንድና አንድ ነው።
እነአርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ ሉዓላዊነትን የደፈረ ማንነትን ሊያጠፋ የተነሳ የውጭ ወራሪን ለመመከት በብዙ ነገር ተፈትነው ያልወደቁና ለአገራቸው የተዋደቁ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ሀገር መውደድን፣ ለዓላማ ጸንቶ ማሸነፍን አስተምረው ያለፉ ታላቅ ሴትም ናቸው። በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ወረራ ኢትዮጵያ ለተቀዳጀችው ድል አይተኬ ሚና ተጫውተዋልም። ምክንያቱም በጦርነቱ ወቅት መረጃ በማቀበል፣ መድኃኒት በመላክ እና መሣሪያ በመግዛት የማይተካ ሚና ነበራቸው።
ሸዋረገድ ተክሌ 12 ጊዜ ታስረው የተፈቱ፣ እስከ ሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ነገር ግን ወደ እድሜ ይፍታሽ የተቀየረላቸው አርበኛ ሆነው ለዛሬዎቹ ምሳሌ ሆነዋል። ታዲያ የዛሬዎቹስ ለምን አይሆኑም? ይሆናሉ እንጂ። ደግሞም ሆነውም አሳይተዋል። ከእነዚህ መካከል ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ አንዷ ነች። እርሷ ከሀዲውን ጁንታ ኮሎኔል ማንቁርቱን ይዛ ያስረከበች ሴት ናት። ኮሎኔሉ 20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር ሰሜን ዕዝ ካሏት የጦር ክፍሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ በዚህ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አባል የሆነችው ምክትል አስር አለቃዋ የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገ/ዮሃንስ አጃቢ ነች። ጁንታ መሆኑን ግን አታውቅም።
ኮሎኔሉ በሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት ከመፈጸሙ ከሶስት ቀን በፊት ሰራዊቱ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚያገኝባቸውን መንገድ በመዝጋት ሰራዊቱን ለከፍተኛ ርሃብና ጥም ዳርጎታል። ሁሉም የሰራዊት አባል የግል ትጥቁን በአንድ ክፍል በማስቀመጥ በህብረተሰብ የድጋፍ ሥራዎች ላይ እንዲረባረብ ማድረጉንም ታስታውሳለች። በተለይም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ሁሉንም የጥበቃ ቦታዎች በትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላት እንዲሸፈኑ በማድረግ፣ የከሃዲው ቡድን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምንም አይነት ዝግጅትና ትጥቅ ባልነበረው ሰራዊታችን ላይ ከፍተኛ ተኩስ እንዲከፍትም አድርጓል። ሆኖም ታላቅ ጀግንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነትን የወረሰው ጀግናው ኃይላችን የማይታሰቡ ጀብዶችን ጭምር በመፈፀም፣ ወደ ኤርትራ ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረግ ራሱን ማዳን እንደቻለ ትናገራለች።
በዚህ ሁሉ ግፍና በደል መሃል የሻለቃዋ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገ/ዮሃንስ ራሱን መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመደበቅ በጁንታው የተሰጠውን ተልዕኮ መፈፀም እንደጀመረ በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆና ታስውሳለች።
‹‹ውትድርና በኢትዮጵያዊነት ፍቅር መታጠብና በጀግንነት ካባ መድመቅ ነው›› የምትለው እንስቷ ጀግና ፣ ራስህን ለሀገር አሳልፈህ ከሰጠህ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻውን ጀግንነትን ይወልዳል ባይ ነች። ምክንያቷም የቀድሞ አለቃዋን እንዴት ከስሯ እንዲንበረከክ እንዳደረገችው አይታበታለችና ነው። ሁኔታውን ስታስረዳ “… ሰራዊታችን በታፈነበት ጥቅምት 24 ምሽት 2 ሰዓት ላይ በከባድ መሳሪያ የታጀበ ተኩስ ወደ ካምፓችን ተተኮሰ፣ በዚህ ሰዓት ወደ መፀዳጃ ቤት ራሱን የደበቀው ከሃዲው አዛዥ ተብዬ ፣ እኔ በትግራይ ሚሊሻና ልዩ ሃይል ጥይት ከምሞት አንተን ገድዬ ራሴን አጠፋለሁ አልኩት፣ ተኩሱ በርትቷል፣ ሁሉም ራሱን ለማዳን ወደህሊናው የመጣለትን አማራጭ እየተጠቀመ ይሯሯጣል…”
“… በመጨረሻም ከተደበቀበት መፀዳጃ ቤት እንዲወጣና እኔ የምለውን ብቻ እንዲፈፅም እሽ የማይል ከሆነ ግን እንደምገድለው አስጠነቀቁኩት፥ እሱም በፍርሃት ውስጥ ሆኖ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ ወደነገርኩት ቦታ መጣ፥ ሽጉጡንና ማዕረጉን እንዲሰጠኝ አደረኩ፣ ከዛም ጫማውን እንዲያወልቅ አድርጌ በየመንገዱ ከማገኛቸው የሰራዊት አባላት ጋር በመተባበርና ሙሉ ሌሊት የእግር ጉዞ በማድረግ ኤርትራ ይዤው በመግባት ታማኝ እና ሙሉ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ አመራሮች አስረከብኩ።” በማለትም ሰራዊታችን በራሱ ወገኖች የደረሰበትን በቃላት የማይገለፅ ግፍና በደል ተሸክሞ ቂምን ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ፍቅር አስቀድሞ ለድል በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ስሜቷን አጋርታለች።
ኢትዮጵያችን ምንም እንኳን በጉያዋ ተወሽቀው ሳቋን እየቀሙ ውርደቷን የሚያፋጥኑና መበተኗን ገሃድ ለማውጣት ሌት ተቀን የሚሯሯጡ ወጪት ሰባሪዎች ቢኖሩም፣ ክብሯን የሚያስጠብቁ ከራሳቸው ሕይወት ይልቅ የሀገራችውን ክብር የሚያስቀድሙ፣ የማይታመን ጀግንነት እየፈፀሙ ኢትዮጵያችንን ከፍ ያደረጉ የበርካታ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆኗን ካስመሰከሩት መካከል ሌላኛዋ ሴት ወታደር ገነት ዮሀንስ ናት።
ገነት ገና ልጅ እያለች ነው የውትድርና ፍቅሩ ያደረባት። ለዚህም ማሳያው ሁልጊዜ ከትምህርት ቤት ስትመለስ ወታደራዊ ሰላምታ ለእናቷ በማቅረብ ነበር ወደቤት የምትገባው። ከዚያም ህልሟን እውን ለማድረግ አስረኛ ክፍል ተፈትና የውትድርናን መንገድን ምርጫዋ አደረገች። ይህ ሲሆንም 19 ዓመቷ ላይ ነበረች። ጊዜው ደግሞ በሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሆነችበት ነው።
ወጣትነትና የሀገር ፍቅር በሚያንቀለቅለው ወኔ ውስጥ ሆና ከተሰው ሰዎች ላይ ጥይት በመሰብሰብና በማከፋፈል በተሰለፈችበት ግንባር ጀብዱ የፈፀመች ጀግና ሆናለች። ከባድ ተተኳሽ በማንገብም በሸክምም ሆነ በተኩስ መከላከያውን ጭምር አስደምማለች። በተሰማራችበት አውደ ውጊያም ቢሆን መሳሪያ ለጨረሱ ጓደኞቿ መሳሪያ በማቀበል፤ በማስተባበርና በታላቅ ፅናት የታገለች አፍላ ወጣት ነች። ለዚህ ጀግንነቷም የዓለም የሴቶች ቀን በሚከበርበት ወቅት እውቅና አግኝታለች።
ሌላኛዋ ባለታሪካችን ምክትል አስር አለቃ ሂሩት አዲሱ ስትሆን፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተፋላሚውን ምሽግ ለመስበር በሚያደርገው ትንቅንቅ ላይ የቀኝ እግሯን ስትመታ ህክምናን ሳይሆን ወደፊት መጓዝን መርጣ የቆሰለ እግሯን አስራ በመፋለም አኩሪ ድል የፈጸመች ናት።
ምክትል አስር አለቃ ሂሩት፤ ምሽግ ለማስለቀቅ በሚደረግ ፍልሚያ ላይ ተራራውን ወደ ላይ እየወጣች በምትፋለምበት ወቅት ነበር እግሯ ላይ ጉዳት የደረሰው። ነገር ግን የሴትነት ድካም ብሎም ቁስለኝነት ሳያግዳት ለቆመችለት አላማ ሞትን መርጣ እግሯን በጨርቅ አስራ መፋለሟን ቀጠለች። በብዙ ጀብድም ጉዞዋን አጠናቀቀች። ለዚህ ደግሞ ጀግና በመባል እውቅና ማግኘት ችላለች።
የሴቶቻችን አኩሪ ገድል ተተርኮ የሚያልቅ አይደለምና ስንቀጥል የምናገኛት አስር አለቃ ኑሪያ አወልን ነው። እርሷም እንደሌሎቹ ጀግና ተብላ ከተሸለሙትና እውቅና ከአገኙት መካከል ነች። እንዴትና ለምን አገኘች ከተባለ አስር አለቃ ኑሪያ ሰሜን እዝ ላይ በግዳጅ ላይ እያለች ነበር ለአንድ ተልእኮ ወደ ሌላ ቦታ የተላከችው። እሷ ተመልሳ እንደመጣች ስለሆነው ነገር ምንም አይነት መረጃ አልነበራትም። በዚህም የመሳሪያ ዲፖ ላይ የጥበቃ ስራዋን መከወን ጀመረች። ነገር ግን የጠበቀችው ነገር አልነበረም የሆነው። ድንገት ከየት እንደ መጣ የማታውቀው አካል አፈናት፤ መሳሪያዋን ማስረከብ እንዳለባትም ነገራት።
እርሷ ግን ‹‹ ፈርሜ የተቀበልኩትን መሳሪያ ለማንም አልሰጥም፣ ከሞትኩም ከነመሳሪያዬ እሞታለሁ፤ ለሀገር መሞት ክብር ነው።›› በማለት ጥያቄያቸውን አልተቀበለቻቸውም። ይልቁንም እዛው በፅናት በመጠበቅ ነፃ እስኪወጣ ድረስ ታግላለች። ከነጻነት በኋላም በተለያዩ ግዳጆች ላይ ተሰልፋ በብቃት የተወጣች ጀግና ነች። በጦር ሜዳ ላይ እያለችም አዛዧ በጥይት ተመትቶ ከፊቷ ሲወድቅ እሱን ከነትጥቁ ተሸክማ ያለምንም ድካም እስከወገን ጦር ድረስ ለማድረስ በጣም ከፍተኛ ፈተናዎችን አሳልፋለች። አዛዧ ሕይወቱ ሳይተርፍ ቢቀርም በጥንካሬና ፅናቷ ግን ሁሉም የሚተማመንባት ሆናለች።
በራሷ ተነሳሽነት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሳሪያ በማጓጓዝ፤ ግዳጇን በብቃት በመወጣት፤ ስለሀገር ሲሉ የወደቁትን በመርዳት፤ ውሃ ለምና ውጊያው እንዳይቋረጥ በማጠጣት ጀብዱ የፈፀመችው ደግሞ ጀግናዋ አስር አለቃ ፀጋነሽ ያጎም አንዷ መከላከያ ካፈራቸው ጀግኖች መካከል የምትጠቀስ ናት።
ሌላኛዋ ጀግና መሰረታዊ ወታደር ወይንሸት ነገኦ ስትሆን፤ ስርቃ በሚባል ቦታ አንድ ምሽግ ውስጥ ሆኖ የሰራዊቱን እንቅስቃሴ በከባድ ተኩስ ሲያስቆም የነበረን ወታደር አነጣጥራ በመምታት ሕይወቷን ለአደጋ አጋልጣ ሌሎችን የታደገች ጀግና ነች።
ከውጊያው ባሻገር በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ሆነው ሌሎች ተግባራትን ከሚፈጽሙ መካከል ብርጋዴር ጀኔራል እርጎ ሺበሺ አንዷ ናት። መከላከያ ሰራዊትን የተቀላቀለችው በ1982 ዓ.ም ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደ ሴትም እንደ ወታደርም የአገርን ዳር ድንበር በመጠበቅ የተቻላትን ሁሉ ስታበረክት የቆየችና አሁንም እያገለገለች ያለች ናት።
ብርጋዴር ጀኔራል እርጎ ሺበሺ አባባል፤ ወታደርነት ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት ሙያ ነው። ፈተናውም ለሁለቱም ጾታ ይጠነክራል። ሆኖም ግን በሴቶች ላይ ፈተናው የበለጠ ያይላል። ሆኖም ሙያው ከፈተና ባሻገር ሕይወትን ቀላልና ዘመናዊ አድርጎ ለመምራት የሚያስችል ነው። ምክንያቱም ሙያው በሥነ ምግባር የታነጸ ያደርጋል፣ አገር ወዳድነትን ያላብሳል፣ ለአገር ክብር ዝቅ ማለትን ያስተምራል፤ ጠንክሮ መስራትንና ስኬታማ መሆንን ያረጋግጣል። ስለሆነም ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በዚህ መስክ ውስጥ ሲያልፉ እነዚህን ሁሉ በሕይወታቸው ውስጥ ያኖራሉና ወታደርነት ልዩ ነው።
በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ታሪክ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ምክትል ኮማንደር ሴት ጀነራል መኮንንና በመከላከያ ሚኒስቴር የበጀትና ፕሮግራም ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ዘውዴ ኪሮስ ሌላኛዋ መከላከያ ሠራዊት ያፈራቸው እንቁ ሴት ሲሆኑ፤ በውትድርናው ዓለም ከ30 ዓመታት በላይ ለአገራቸው ተዋድቀዋል።
እንደ እርሳቸው አገላለጽ፤ በሠራዊቱ ውስጥ ሴቶች በመሆናቸው የተለየ የሚሰጣቸው ግዳጅ የለም። ምክንያቱም ውትድርና የቡድን ሥራ ነው። ስለዚህም ሴቶች በተልዕኮ አፈፃፀምም ከወንዶች እኩል አንዳንዴም ከዛ አለፍ ብለው ይሳተፋሉ። ይህም የሚሳየው ‹‹ሴቶች አይችሉም›› ከሚባል ይልቅ ዕድሉ ከተሰጣቸው በሁሉም የሥራ መስክ ገብተው ውጤታማ ይሆናሉ የሚለውን ነው።
በመጨረሻ ልናነሳቸው የወደድናቸው ጀግነዋ ሴት ሜጀር ጄነራል ጥሩዬ አሰፌን ሲሆን፤ መከላከያ ካፈራቸው ጀግኖች መካከል ይመደባሉ። በልጅነታቸው የጀመሩት የትግል ሕይወት ዛሬ ላይ ከፍ ወዳለ ወታደራዊ ማዕረግ አድርሷቸዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሶስተኛዋና ብቸኛዋ የሴት ሜጀር ጀነራል እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። መከላከያን ሲቀላቀሉ በእድሜያቸው ትንሽ ሲሆኑ፤ እግረኛ ሆነው ሰራዊቱን አገልግለዋል። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ምዕራብ አርማጭሆ (ጎንደር) የሚባል ቦታ ላይ ነው ውጊያ የተካፈሉት። ከእግረኛ እንደወጡ የኪነት ቡድኑን ተቀላቅለው በቡድኑ ስራ ህዝባዊ ተሳትፎን መቀስቀስና ታጋዩን ማነቃቃት ጀመሩ።
ቀጣዩ ተግባራቸው ከውጊያ ውጭ ሰራዊቱን የሚደግፉ የህክምና ስራዎች፣ የህትመት ውጤቶችን የማባዛትና የማሰራጨት፣ ትጥቅ ማዘጋጀት፣ የሬዲዮ መገናኛዎች ብልሽት ሲያጋጥማቸው መጠገንና ሌሎች ተግባራትን በሚያቀናጀው ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ውስጥ ጸሐፊ ሆነው ሰርተዋል። ከዛ በኋላ ደግሞ ህትመት ራሱን ችሎ ሲቋቋም የብአዴን ህትመት ክፍል ውስጥ እንዲሰሩ ሆኑ።
ሜጀር ጀነራል ጥሩዬ የሕወሓትን ጦርነት ከቀደመው ጦርነት ጋር ሲያነጻጽሩ እንዲህ ይላሉ። ‹‹ ቀደም ሲል የነበረው ዘመቻ ጠላት ተብሎ የተፈረጀውን የደርግ ሰራዊት ለማስወገድ ነበር ፤ ህዝቡም የዴሞክራሲ የእኩልነት ጥያቄን አንስቶም ስለነበር ጦርነቱም የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረጊያ ሆኖ አልፏል። አሁን ግን በትግራይ ክልል ያጋጠመን ትንኮሳና ኋላም የተሄደበት የህግ ማስከበር ዘመቻ ከዛኛው ፍጹም የተለየ ነው። ሊነጻጻር የሚችልም አይደለም። ጁንታው ቡድን ያን የሚዘገንን ክህደት የፈጸመው ባሳደጋቸውና በሚመራቸው ልጆቹ ላይ ነው።
ራዕይ እያሳየ፣ እያሰለጠነ፣ ማዕረግ እየሰጠ፣ እየኮተኮተ ያሳደገ አለቃ (አባት) ቢሆንም ከአባት በማይጠበቅ ስነ ምግባር ልጆቹን በተኙበት ጨፍጭፏል። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ጠላት እንጂ በተለያዩ መስኮች አብሮ የተሰለፈ፣ የበላ፣ የጠጣ፣ ከጎንህ የነበረ ሰው ሊሆን አይገባውም ነበር። ነገር ግን ይህንን አድርጎታል። ሆኖም ማሸነፍ እንዳልቻለ አይተነዋል። ምክንያቱም አገር ለእውነት እንጂ ለተንኮል አትንበረከክም። በአገር የመጣ አካልም ቦታ የለውም።››
ቀጥለውም ሕወሓት ጋር ያለው ስሜትም ሆነ ፍላጎት የስልጣን ጥማት ነው ይላሉ። የስልጣን ጥማት ባይሆን ኖሮ አብሯቸው ብዙ መከራን ያየ ላለፉት በርካታ ዓመታት ክልሉንና አገርን ሲጠብቅ ለነበረ ወታደር ይህንን መሰሉን ክህደት ለመፈጸም መነሳሳቱ አይኖርም ነበር ባይ ናቸው።
እንደ እርሳቸው እምነት፤ ሰራዊት ማለት በየትኛውም አገር ላይ አገር ጠባቂ፣ ለአገሩ ክብርና አንድነት የሚሰዋ፣ አካሉን የሚሰጥ፣ ደሙን የሚያፈስ ነው። ይህንን ደግሞ በሕወሓት ዘንድ ማየት አልተቻለም። ምክንያቱም እርሱ ስልጣን እንጂ ሕዝብን አላየም። ራሱን እንጂ አገሩን አላስቀደመም። ለዚህም ነው ባለመረዳት ውስጥ ሆነው ሰራዊቱን ለመግደል የሞከሩት። ይህ ደግሞ ሰራዊት የሌላት አገር አገር ሆና መቀጠል እንደማትችል ስለማያውቁ ያደረጉት ነው። አዎ ሕወሓት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ጠላት እንደሆነ መገንዘብ ያለብን ይመስላል። ምክንያቱም በዓለም ላይ ተፈጽመው የማያውቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አድርጓል። እናም ውግዘታችን ብቻ ሳይሆን ትግላችን ጭምር ሆኖ እርሱንና ተከታዮቹን ለዘላለም እንዳይኖሩ ማድረግ ላይ መረባረብ ያስፈልገናል በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015