እነተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም ዛሬ በጊዜ ተገናኝተዋል። እንደተለመደው ለመጠጥ ማድመቂያቸው የዘወትር የፖለቲካ ጭቅጭቃቸውን ማወራረጃ አድርገውታል። በእርግጥ ሦስቱም በአንድ ነገር ይስማማሉ፤ በተደጋጋሚ በፍፁም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማቀድም ሆነ መንቀሳቀስ ትልቅ ጥፋት ነው ይላሉ። ለዚህ ሃሳባቸው ፈጣሪ ዋጋቸውን አይንሳቸው። ነገር ግን በዚህ በመሠረታዊ ሃሳብ ቢስማሙም በጎን ሦስቱንም በተለያየ መንገድ የሚያጓትታቸው የየራሳቸው ሃሳብ፣ ፍላጎት እና እምነት አላቸው።
ዘውዴ በጨዋታቸው መሃል ‹‹በሌቦቹ የትህነግ ሰዎች አዲስ የታነፁና የተገነቡ ሕንፃዎችን ሳይ አዝናለሁ። አንዳንዴም ብቻዬን እንደዕብድ እስቃለሁ። ዝርፊያቸውን እያስታወስኩ ወደ ፊት ደግሞ ይኸው እንዳይደገም እሳቀቃለሁ። ለእነተሰማ አሁንም ቢሆን በመንግሥት በኩል ያሉ ስለእውነት ለሕዝብ የማይሠሩ፤ የአደርባዮችና የአስመሳዮች መሰባሰቢያ መሆን እንደማይኖርባቸው ላሳስባቸው እያሰብኩ መልሼ እንዳይቆጡ እፈራለሁ። ከተለመዱ ነውረኛ ድርጊቶች መካከል በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ‹በአቋራጭ መክበር›ም ሆነ ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› የሚባሉት ብሂሎች ትህነጎችን አሁን ላሉበት ደረጃ አድርሷቸዋል። ይህ አሁንም ፖለቲከኞቻችንን ሰቅዞ እንዳይዛቸው አደናቅፎ እንዳይደፋቸው ያሳስበኛል።››
ተሰማ በበኩሉ ‹‹ይኸውልህ እንግዲህ የትህነግ ባለሥልጣናት በ27 ዓመታት የአገዛዛ ዘመናቸው፤ የኢትዮጵያውያንን አንጡራ ሐብት ዘርፈው ያዋጣናል ብለው ያመኑበትን መንገድ በመከተል ፎቅ ሲተክሉ ኖረው ጥለውት ሔደዋል። ይሔ በእርግጥም ያስቃል።›› ብሎ እርሱም በሃሳቡ እንደሚስማማ እየገለፀ ፈገግ አለ።
ተሰማ ‹‹ደግሞ›› አለ፤ ገብረየስ ከተሰማ ቀድሞ የበኩሉን ለማለት ፈልጎ መናገር ጀመረ። ‹‹ይሔ ሊያስቅ አይገባም። የሚያስፈልገው ሰው ራሱን ወዶ ሁሉን ረስቶ ይህንን ድርጊት መፈፀም እንደማያዋጣው አስቦ ትምህርት ቢወስድበት እንደሚሻል አስብ። እነዚህ አሁንም ድረስ የትግራይን ሕዝብ መጫወቻ አድርገው እየተጠቀሙበት፤ እያጠፉት ያሉ የትግራይ ነፃ አውጪ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ አጥፊዎች አዲስ አበባ ብቻ አይደለም፤ የትህነግ ቱባ ዘራፊ ባለሥልጣኖች የትግራይ ሕዝብ ላይ ሳይቀር ዘረፋቸውን አጧጡፈው ከጎኑ እያቁለጨለጩት ሲኖሩ ነበር። በዘረፋቸው በሽራሮ፣ በሽሬና በአካባቢው፣ በአክሱም፣ በአድዋ፣ በአዲግራት፣ በውቅሮ፣ በመቀሌና አካባቢው ፎቅ ገንብተው ንግዳቸውን ሲያጧጡፉ ከራርመዋል።
ሆኖም ትህነጎች ፎቅ በፎቅ ላይ ቢደራርቡም የጠቀማቸው ነገር የለም። ሌብነትን ወደ ሕጋዊነት ቢቀይሩም መንገዱ ከዚህ በላይ ብዙ ርቀት አላስኬዳቸውም:: ከድሃ አገር የተጣበበ በጀት ላይ ብዙውን ለግል ሀብት ማከማቻ እና ለመዝናኛነት በመጠቀማቸው፤ የገዛ ወገንን እያራቆቱ ገንዘብ በመቆለል በሚገኝ ደስታ ቢሰክሩም ዘላቂ ደስታ ሊጎናፀፉ አልቻሉም። እኛ የትህነጎቹ አባል ሆነን እንደነሱ መዝረፍ ቀላል ነበር። ነገር ግን በዚያ ዘመን የተቃወምናቸው ኃላፊነት የማይሰማቸው የመንግሥት ሹማምንትና አልጠግብ ባይ ባለስልጣናት የሚሔዱበት መንገድ ስላልተመቸን ነበር።
ስልጣን ሕዝብን ማገልገያ እንጂ የተንደላቀቀ ሕይወትን መገንቢያ እንዳልሆነ ለማሳወቅ ሞከርን፤ ነገር ግን አልተሳካም። ‹ዛሬ ምንም ዓይነት ስልጣን ኖሮ እያዘዙ እና እየመዘዙ ቀናትን በደስታ ማሳለፍ ቢቻልም ብዙ መቆየት አዳጋች ነው። በእውነት ስለሃቅ ሕዝብን ማገልገልን በሚመለከት ትኩረት ካልተሰጠ በቀላሉ መውደቅ ይመጣልና ከወዲሁ ማሰብ ይሻላል።› ብንላቸውም ሰሚ ጠፋ።
ማባሪያ በሌለው ስብሰባ እያሳበቡ ከቢሮ መጥፋት፣ ተገልጋዮችን ማመናጨቅ፣ የመንግሥት በጀት መዝረፍ፣ በኔትወርክ በመቧደን ሌብነትን ማስፋፋት፣ መሬት በጠራራ ፀሐይ መውረርና ማስወረር፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ቁሳቁሶችንና ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋልና የመሳሰሉ አስነዋሪ ድርጊቶችን ማስቆም ይገባል። እያልን በተደጋጋሚ ስንናገር ቆየን ማን አድምጦን።
ከአንድ ቦታ በሌብነት ወይም በብቃት አልባነት የሚነሳን ተሿሚ ሌላ ቦታ መሾም ትክክል አይደለም። በፓርቲ ወገናዊነት ብቻ ለአገር የማያስቡ ግለሰቦችን በሕዝብ ላይ እንዲቀልዱ መፍቀድ አይገባም። የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች አይደባለቁ። የመንግሥት ተቋማት በእውነት የሕዝብ አገልጋይ ይሁኑ። ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ በነፃነትና በክብር ሥራውን ያከናውን። ሕዝብ ይገልገል አልን ጆሮ የሚሰጥ አልነበረም።
በመጨረሻ ሕዝብ ሲመረው አይቀሬው ቀን መጣ። አሁንም መማር አልቻሉም እንደለመዱት ለሕዝብ ሲሉ ስልጣንን፣ ሀብትንም ሆነ ድሎትን ለመተው ባለመውደዳቸው መልሰው ሲዘርፉት፣ ሲጨቁኑት የነበረውን ሕዝብ እያስፈጁት ነው። ይህ አያስቅም፤ ይልቁኑ ከዚህ ያለማስተዋል እና የስግብግብነት ተግባር መማር ይሻላል።›› አለ ገብረየስ። ዘውዴና ተሰማ በገብረየስ የዕለቱ ዲስኩር ተደንቀው ተያዩ።
ተሰማ ለገብረየስ ‹‹ ዛሬስ አልተቻልክም።›› አለው። ገብረየስ በበኩሉ ‹‹እኔ ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ትራሴን ከፍ አድርጌ መተኛት መቻሌ ነው። ትራስ ከፍ አድርጎ ዘላቂ ሰላማዊ እንቅልፍ የሚገኘው በንፅህና ሥራን ማከናወን ሲቻል ነው። ሀብት መቆለል ሰላማዊ እንቅልፍን አይሰጥም፤ ከሃያ ዓመት በፊት ራሴን ከትህነግ የነጠልኩት በዚህ ላይ ፅኑ እምነት ስለነበረኝና ስላለኝ ነው። ዘመኔን በትህነግ እንድሰቃይ ያደረገኝ በጊዜው ያነሳሁት ቡቃያ አይታጨድ፤ አንበሳም አይጠመድም፤ ሕዝብ ላይ የማይሆን ነገር መፈፀም ህሊናን አያሳርፍም። ዘላቂ ደስታን አይፈጥርም በማለቴ ነው።
በጥላቻ፣ በቂም በቀል፣ በመገፋፋትና በመጠፋፋት ላይ የተመሠረቱ አካሄዶች አያዋጡም። ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነትና አድሎኛነት ተወግዶ እርስ በእርስ መተሳሰብ ያስፈልጋል። ቀድሞ ይታሰብበት ብዬ ነበር። ታሞ ከመማቀቅ በቅድሚያ መጠንቀቅ ይሻላል። ችግር ከመድረሱ በፊት ጥንቃቄ ወሳኝ ነው። በማለቴ ‹በትህነግ ላይ አመፅክ ከመንጋው ተለየህ› ተብዬ ጥርስ ተነከሰብኝ ብዙ ዋጋ ከፈልኩኝ።
ሰው አጎሳቋይ፣ አድሎአዊና አግላይ ብልሹ አሠራሮች ይቁሙ፤ የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ተደራጅተው የሚዘርፉ ሌቦች አይበራከቱ፤ በኋላ ተቀምጠው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራል፤ መጀመሪያ በቀላሉ የያዙት በኋላ ሊያስቸግር ይችላል እባካችሁ ተዉ ብዬ ነበር። ይኸው አሁን እንደቀልድ የቆለሉት ድንጋይ መጥፊያቸው ሊሆን ነው። በስግብግብነታቸው ለቆለሉት ድንጋይ ሲንሰፈሰፉ የሰውን ደም እንደጎርፍ እያፈሰሱ እነርሱም የእጃቸውን ሊያገኙ ቀናቶችን ይጠብቃሉ። ይህ እንደትምህርት መወሰድ አለበት። እኔ ግን በሕይወት አለሁ እየኖርኩ ነው። ከእኔም ከእነርሱም መማር ይገባል›› አለ ገብረየስ።
ተሰማ በበኩሉ ‹‹እኔ ደግሞ የምነግርህ አለኝ። የሚያበሳጨኝ ሲዘርፉ መኖራቸው ብቻ አይደለም። አሁንም ከዘረፉ በኋላ ያንን ዘረፋ ለማስቀጠል የፈጠሩት ግብግብ አይደለም። ኢትዮጵያ ተቆጥረው የማያልቁ የሀብት ፀጋዎች ላይ ተቀምጣ፤ እነርሱ ለእነዚህ ያህል ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይተው ሁሉንም ሊያጠግቡ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ማስተዋል አለመቻላቸው እና ነፃ ልናወጣው ነው እያሉ ለነገዱበት ሕዝብ በልቶ የሚጠግብበትን ዕድል መዝጋታቸው ያንገበግበኛል።
እነርሱ ቢያንስ መላው ኢትዮጵያውያን ከድህነት የሚወጣበትን መንገዱን አመቻችተው ለማለፍ ካለመሞከራቸው ባሻገር ስለትግራይ ሕዝብ አለማሰባቸው እና አልፈው ተርፈው ይህንኑ ሕዝብ መጨቆናቸው ከነጭራሹ፤ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ዜጎቿን ለመመገብ የምትቸገር አገር መሆኗ ያናድደኛል።
መዝረፋቸው ብቻ አይደለም፤ በርካታ ሚሊዮን ሔክታሮች ያልታረሰ ለም መሬቷ ከተሠራበት ክረምት ከበጋ በማምረት አገር ሊጠግብ እንደሚችል አለማወቃቸው፤ ምን ያህል ደደብ እንደሆኑ እያስታወሰኝ፤ እነርሱ ኢትዮጵያዊ ሆነው በመፈጠራቸው አፍራለሁ።›› ብሎ ተሰማ ድራፍቱን ለመጎንጨት ብርጭቆ ሲያነሳ፤ ቀድሞም ሳቅ ሳቅ ሲለው የነበረው ዘውዴ ሳግ እያነቀው ተንከተከተ።
ተሰማ በስጨት ብሎ ‹‹ሳቁን ተወውና እኔን ግራ የሚገባኝ አሁን የእነርሱ መጠቀሚያ ሆኖ የሚማገደው ወጣት ጉዳይ ነው።›› ሲል ዘውዴ ከተንከተከተበት ሳቅ እየታገለ በመላቀቅ ቀና ብሎ ‹‹በእውር የጠቃቀሱ በደንቆሮ ይንሾካሾኩ፤ ነውና ሰው አንድ ነገር ከተሰወረበት መቀለጃ ሊሆን ይችላል። በበጋም ሆነ በክረምት በሚከናወን የእርሻ ግብርና ጤፍ፣ ስንዴ፣ ምስር፣ አተር፣ ገብስ፣ በቆሎና ሌሎች አዝርዕቶች በስፋት ሊመረት እየቻለ ኢትዮጵያ የምግብ ተመፅዋች እንዳትሆን ትህነግ አለመሥራቱ ቢያበግንም፤ እነተሰማም ሥጋ፣ ዶሮ፣ ዓሣ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ዓይብና የመሳሰሉትን በገፍ ማምረት ስለሚቻል ኢትዮጵያ በሚያሳዝን ሁኔታ ምንም እንደሌላት እንቁላል ከውጪ እንዳታስገባ ከወዲሁ ሀብትን አውቆ በሚገባው ልክ የሥራ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ላይ መሥራት አለባቸው፤ ያለበለዚያ እነርሱም መሳቂያ ይሆናሉ። ›› አለ።
‹‹ከኢትዮጵያ ምድር ስግብግብነት ሥሩ መነቀል አለበት። ስንል የምናወራው ስለትህነግ ብቻ ሳይሆን ስለእያንዳንዳችንም ጭምር ነው። ሰውን ለመጥቀም ሕዝብን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት እያስመሰሉ ሕዝብ እየጨቆኑና እየዘረፉ በእግር ጫፍ መቆም አያዋጣም። ተረጋግቶ ሠርቶና አሠርቶ ውጤት ከማምጣት ይልቅ፤ ሁልጊዜ ቸኩሎ ለመሔድ ተዘጋጅቶ ሕዝብን እና ነገን ሳያስቡ መንቀዥቀዥ ደስታን አያስገኝም። በተፈጥሮ ሀብት የተንበሸበሸችውን ኢትዮጵያን ተጠቅሞ አገር ከማሳደግ ይልቅ በማይመለከት ነገር ተደርቦ ሰው መጣላት፣ በማይመለከት ነገር ተደርቦ ሰውን በብሔሩ መጥላት፣ በማይመለከት ነገር ተደርቦ ሰው ማጥቃት፣ በማይመለከት ነገር ተደርቦ ብሔር ማጥቃት ሥራ ማጣት ብቻ ሳይሆን እንደትህነጎች ሁሉ የአገር ጠላት፤ የሕዝብ እና የትውልድ ባላንጣ ሆኖ መቅረትን ያመጣል።›› ሲል ገብረየስ ተናገረ።
ዘውዴ በበኩሉ ‹‹በእርግጥ በራስ መንገድ መጓዝ ለህሊና መታመን ሰዎች ሲጣሉ ወይም አንዱ ለሌላው ሰው እና ብሔር ጥላቻ ሲያድርበት በተቻለ መጠን ለማስታረቅ መሞከር እና ችግሩን ለመፍታት አማራጭ ከመፈለግ ይልቅ ተደርቦ መጣላት ወይም ለአንዱ አባሪ ሌላው በሃሰት መስካሪ መሆን አያዋጣም። እውነት ላይ ተሞርኩዞ የስግብግብነት ባህሪን ቀንሶ፤ ሕዝብን አስቦ ለሕዝብ ብቻ ከተሠራ በፈረስ የፈለጉት በእግር ይገኛል። ሀብት ብቻ አይደለም፤ የዓለም ሕዝብ የሚመኘውን ለሰዎች በጎ በማድረግ ታሪክ በመመዝገብ ስም ከመቃብር በላይ ይውላል።
በዘረፋና ሀብት በመቆለል በጥቂቶች ለመወደድ መድሎ በመፈፀም፤ ብዙ ጥረት ከማድረግ እና ደስታን ከመፈለግ ይልቅ፤ ተግቶ ለሕዝብ በመስራት በቀላሉ ጊዜያዊ ሳይሆን ቀጣይነት ያለውን ተወዳጅነትን ማትረፍ ይቻላል። በፍቃዴ ከተሰጠችው በቅሎዬ ይልቅ ያለ መንገድ የሔደችው ዶሮዬ እንደሚባለው ሕዝብ በፍቃዱ ከሰጠው ይልቅ ያለትክክለኛ መንገድ የተወሰደበት እንደሚቆረቁረው ተረድቶ የሕዝብን ሀብት ለሕዝብ መተው ያስፈልጋል።›› አለ።
ገብረየስም ‹‹አሁን ያልገባችሁ ነገር የትግራይ ሕዝብ በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንደሚባለው መሆኑን ነው። በራሱ አገር በገዛ ንብረቱ በገዛ ልጆቹ እንደልቡ ማዘዝም ሆነ መጠቀም አልቻለም። ሕዝቡ ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረገ ሲሆን፤ ጊዜውን እየገፋ ያለው በሃሳብና በሰቀቀን ነው። ሕዝቡ በስግብግብ ትህነጎች ምክንያት ሰላም አግኝቶ ከድህነት አዘቅት ውስጥ መውጣት አልቻለም። የትግራይ ሕዝብ በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊ መንገድ የአገሩ ባለቤት መሆን አልቻለም።… ቀጠለ ምሬት የተቀላቀለበትን ንግግር።
ድሮም ቢሆን የትህነግ ሹማምንትም ሆኑ ፖለቲከኞች በመንግሥትነት ዘመናቸው የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ ብቻ እንደሆነ አልተረዱም ነበር። በነፃ አውጭነት ስም ፀረ ሕዝብ ድርጊቶችን ሲፈፅሙና በስሙ ሲነግዱ አልፈው ተርፈው ሲዘርፉ ኖረዋል። ሕዝብን ማማለል የሚቻለው ለመብቱ፣ ለነፃነቱ፣ ለኑሮውና ለአገሩ ህልውና የሚበጅ ፕሮግራም ይዞ በመቅረብ፣ በሥልጣን ዘመንም ይህንን በመተግበር መሆኑን ባለመረዳታቸው የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅምና ደኅንነት ሲጎዱ ኖረው አሁንም ከስልጣን ተገፍተው ከመጉዳት ወደ ኋላ አላሉም።
ስለዚህ ካለፈ የውድቀትና የጥፋት ታሪክ ሳይማሩ በቀላሉ በአቋራጭ መክበርን አስቦ ለማጭበርበር ከመሞከር ይልቅ ተዓማኒነት ለማግኘት ለሕዝብ መስራት ይሻላል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች የሚቀምሱት አጥተው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እየተለመነላቸው፣ በርካታ ሚሊዮኖች በሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት ኑሯቸው ተመሰቃቅሎና ግራ ተጋብተው በእነሱ ላይ ያልተገባ ትርፍ በማጋበስ ሀብት መሰብሰብ እና ስልጣን ላይ ተቆናጦ ብዙ ዘመን ለመኖር መሞከር አያዛልቅም። በትክክልም ትህነግ የአማራን ወይም የአፋርን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የትግራይን እና የመላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨቋኝ ነው። ዛሬም አሁንም ዘረፋውን ለማስቀጠል ከውጭ ጠላት ጋር አብሮ ኢትዮጵያን እየወጋ ነው። እየዘረፈ ለመሞት ወስኗልና ቀድመን እንቅበረው።›› ብሎ ገብረየስ ንግግሩን ሲያጠናቅቅ ዘውዴ እና ተሰማ ተነስተው አጨበጨቡ።
ፌኔት
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም