ኪነ ጥበብ የሰውን ልጅ አስተሳሰብ ይዘውራል፤ ሲፈልግ ያለማል፤ ሲፈልግ ያጠፋል። ለሰላም ይውላል፤ ለጦርነት ይውላል። በጦርነት ጊዜ አዝማሪ ለምን አስፈለገ? የውስጥ ወኔን ስለሚያነቃቃ!
በአገር ቤት በባህላዊ የሰርግ ስነ ሥርዓት ላይ ለአዝማሪ ሽልማት የሚሰጠው ለምንድነው? ወኔን ስለሚያነቃቃ፤ ‹‹የዳቦ አጣሁ!›› ብሎ ለሚለምን ከአንድ ብር በላይ ሰጥተን አናውቅም፤ መድረክ ላይ ድንቅ አጨፋፈር ወይም አተዋወን ላሳየ ሰው ግን ሃምሳ እና መቶ ብር እንሰጣለን፤ ይህ ለምን ሆነ? ኪነ ጥበብ ስሜትን ስለሚዘውር!
የትኛውም የኪነ ጥበብ ሥራ የገሃዱ ዓለም ነጸብራቅ ነው። ጥያቄው ‹‹የገሃዱ ዓለም ምንድነው?›› የሚለው ነው። የገሃዱ ዓለም ፍቅር ነው፣ ማህበራዊ ጉዳይ ነው፤ ፖለቲካ ነው። ከእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ፖለቲካ ተደጋግሞ ይነሳል፤ ምናልባትም ከአገር ምንነት ጋር በቅርብ የሚቆራኝ ስለሆነ ይሆናል። ምናልባትም በመሪነት ደረጃ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡም ፖለቲካ ይወዳል(እርግጥ ነው ፖለቲካና ኤሌክትሪክን በሩቅ የሚለው ብሂልም አለ)። ይሄ በራሱ ግን ፖለቲካ ነው። እንዲያውም የህዝቡም ፖለቲካን መውደድ እንጂ እውነት ፖለቲካ ከሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች እና ከኢኮኖሚ በላይ ለአንዲት አገር ወሳኝ ሆኖ ነው? መልስ ሊሆነን የሚችለው ሁሉም ነገሮች በፖለቲካው ውስጥ ያልፋሉ የሚለው ነው።
ወደ አገራችን ኪነ ጥበብ እንግባ። ስንገባም ኪነ ጥበብን ከፖለቲካና ሰላም ጋር አገናኝተን ነው። ኪነ ጥበብ በአገሪቱ ነባራዊ እሴቶች ላይ ስለሚሰራ ከፖለቲካ ገለልተኛ ነው የሚለው ክርክር ለዚህ ጽሑፍ አያስኬድም፤ ኪነ ጥበብ ከፖለቲካ ውጭ ነው የሚለው እምነትም በጣም የጥቂቶች ብቻ ነው።
ኪነ ጥበብ በፖለቲከኞች አለመግባባት የሚፈጠረውን ግጭት ወደ ሰላም የሚያመጣ መሆን አለበት። ምክንያቱም ከያኒዎች ‹‹ሀብታችን ሕዝብ ነው›› ሲሉ እንሰማለን። ስለዚህ ለሀብታቸው ሰላምና ደህንነት ሊሰሩ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን እንደመጡ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። በዚያው ዓመት ውስጥ የሰላም ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ጠርቶ ውይይት አካሂዶ ነበር። በዝግጅቱ ላይ ታድሜ ስለነበር እስኪ በዛሬው የሰላም ቀን የማስታውሳቸውን ላንሳ።
የሰላም ሚኒስቴር በወቅቱ በነበሩት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አማካኝነት የሰላምን ነገር ሲያሳብ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር መወያየት አለብኝ አለ። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የህዝብን ስሜት እንደሚዘውሩ አመነ። አምኖም መድረክ አዘጋጀ። የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ከሚል መድረኩ ላይ ተገኙ፤ በራሳቸው በሚኒስትሯ አወያይነት ሀሳቦች ተንሸራሸሩ። ከያኒ ከፖለቲከኛ በላይ ሃይል እንዳለው፣ ፖለቲከኛ በህዝብና በህዝብ መካከል ያጠረውን አጥር ከያኒ ማፈራረስ እንደሚችል ተናገሩ። ‹‹ከያኒ ድንበር የለውም›› አሉ የሰላም ሚኒስትሯ።
ምሳሌም አነሱ። የኦሮሚያና የሶማሌ ፖለቲከኛ ድንበር ቢያበጅ፣ ቢኳረፍ፤ የኦሮሚያና የሶማሌ አርቲስት ግን ይህን ድንበር ነው ማፍረስ ያለበት። የኦሮሚያና የሶማሌ ከያኒ ከተኳረፈ ያኔ ነው ኪነ ጥበብ አድርባይ ሆነች የሚባለው።
በወቅቱ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ እሸቱ፤ ‹‹ኪነ ጥበብ ለሰላም ይጠቅማል የሚለው ቃል አገላለጽ የኪነጥበብና የሰላምን ግንኙነት የሚያሳንስ ነው›› ይላሉ። መምህር ተስፋዬ ማለት የፈለጉት፤ ኪነ ጥበብና ሰላም ፍጹማዊ አንድ ሆነው ‹‹ኪነ ጥበብ ለሰላም ይጠቅማል›› መባሉ ግን ጥብቅ ቁርኝት ያልነበራቸው ያስመስለዋል ነው። መንግስትም፣ መገናኛ ብዙኃንም ይህንን ነው የሚደጋግሙ፤ ‹‹ኪነ ጥበብ ለሰላም ፋይዳ አለው›› ቢሉም ማንም የተረዳው ግን የለም። በጣም ግልጽ የሆነውን ነገር ልክ በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር እንደ አዲስ የተገኘ ይመስል ‹‹ኪነ ጥበብ ለሰላም ይጠቅማል›› ማለት ምን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠውም ያሳያል።
መምህሩ አዝማሪዎችን ምሳሌ ያነሳሉ። የአዝማሪዎች ጨዋታ የማህበረሰቡ ነጸብራቅ ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ አዝማሪ ብዙ ነገር ነው። ኢኮኖሚ ነው፣ ፖለቲካ ነው፣ ፍቅር ነው፣ ማህበራዊ ግንኙነት ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ ይሄ ሆኖ ግን አሁን አሁን ለአዝማሪ የሚሰጠውን ዋጋ እናውቃለን፤ መሰደቢያ ሁሉ ይመስለናል። ይሄ የመንግስትም የመገናኛ ብዙኃኑም ችግር ነው፤ አልሰሩበትም። ከጥንት ጀምሮ የነበረው ታሪካዊ ዳራው አልታወቀለትም። ያ ታውቆ ቢሆን ኖሮ ኪነ ጥበብና ሰላም ድንበር የለሽ ህዝባዊ ትስስር መሆናቸው ግልጽ ይሆን ነበር።
በኪነ ጥበብ ላይ ፈላስፎች ክርክር ነበራቸው። ፕሌቶ የተባለው ፈላስፋ ኪነ ጥበብ አፍራሽ ነው ብሎ ያምን ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ዓለምን አይወክልም ነው፤ ከእውነታው ይርቃል፣ ይጋነናል ነው።
ሌላው ፈላስፋ አርስቶትል ደግሞ የፕሌቶን ሀሳብ ውድቅ ያደርጋል። ኪነ ጥበብ የስሜትና የእውነታ ውህደት እንደሆነ ያምናል። ይሄ ማለት ስሜታችን የሚጦዘው የሆነ ውስጣችን ያለውን ነገር(የነበረውን እውነታ) ሲነካው ነው ማለት ነው። ለምሳሌ ለቅሶ እንደ መዳኛ ይቆጠራል፤ ‹‹አልቅሶ ይውጣለት›› ይባላል። ለቅሶ የስሜትና የእውነታ ውህደት ነው። ይሄ እፎይታ ነው። ስለዚህ ያ ስሜት እፎይታ አስገኘ ማለት ነው። ሌላው አርስቶትል የሚለው ነገር ኪነ ጥበብ ደስታን እንደሚፈጥር ነው። ደስታ ደግሞ ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ጤንነት ነው። እንዲያውም ኪነ ጥበብ የሳይንሳዊ ግኝቶች መነሻ እንደሆነም ይታመናል።
ኪነ ጥበብ መንገድ አይሰራም፤ ሕንጻ አይሰራም፤ ይህን የሚሰሩትን ሰዎች ግን ይሰራል። ለዚህም ነው እነዚህ ሰዎች ‹‹ጥበበኞች›› የሚባሉት። ይሄ ሲሆን ኪነ ጥበብ የጋራ መግባቢያ ሆነ ማለት ነው። የአንድ አገር ሰዎች የጋራ መግባቢያ ሲኖራቸው ነው እርስ በእርስ የሚተዋወቁትና የሚግባቡት። ለዚህ ደግሞ ኪነ ጥበብ ጥሩ ማሳያ ነው። በጋራ ያግባባል፤ በጋራ ያኖራል፤ ያስተዋውቃል። ፖለቲካ ድንበር አለው፤ ሃይማኖት ድንበር አለው፤ ኪነ ጥበብ ግን ድንበር የለውም ይላሉ ባለሙያዎቹ።
‹‹ኪነ ጥበብ ማንነትን ይገነባል›› ይላል የመምህር ተስፋዬ ጽሑፍ። ኪነ ጥበብ የጋራ ማንነትን ይፈጥራል። ማህበራዊ ማንነት ‹‹ጄኔቲካዊ›› ሳይሆን ማህበራዊ ስሪት ነው። ባህልና ኪነ ጥበብ ነው የሚቀርጸው። አገር የሚሰራው በትርክት ነው። ኃያላን የሚባሉትን አገራት የምናውቃቸው በትርክት ነው። ይህን ደግሞ የሚያደርገው ኪነ ጥበብ ነው።
በአገራችን ‹‹እንዴት እየተሰራበት ነው?›› ለሚለው፤ መምህር ተስፋዬ መንግስትንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ቀዳሚውም መንግስት ነው። ይሄ ማለት ወርዶ ድራማ ይስራ ማለት አይደለም፤ ከመንግስት የሚጠበቀው ኪነ ጥበብን ተቋማዊ ማድረግ ነው። በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ የኪነ ጥበብ ትምህርት ያስፈልጋል፤ ይህ የሚሆነው አገሩን በሙሉ አርቲስት ለማድረግ አይደለም፤ ይልቁንም ሰው እንዲሆኑ ነው። ኪነ ጥበብ ሰብዓዊነት ነውና! ሐኪሙም፣ የህግ ባለሙያውም፣ መሃንዲሱም ጥበበኛ መሆን አለባቸውና! የመንግስት ቀዳሚው ሥራው ይሄ ነው።
መንግስት በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ አልሰራም፤ ተማሪዎች አገራቸውን አያውቁም፤ ‹‹አፋር ውስጥ ያለ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የአማራ ወንድሙን አያውቅም፤ ትግራይ ውስጥ ያለው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሶማሌን አያውቅም፤ ታዲያ ላይጣሉ ነው እንዴ!›› ይላሉ መምህር ተስፋዬ። ይህ ሲሆን ነው ኪነ ጥበብ ሰላም ላይ ሚሰራው።
ወላጆች ላይም ችግር አለ ነው የሚሉት መምህሩ። ልጆቹ ከሰብዓዊነት ውጭ ሆነው እያደጉ ነው። ከሰዋዊ ነገሮች ይልቅ ቁሳዊ ነገር ነው የሚዘጋጅላቸው። አሻንጉሊት ነው የሚገዛላቸው፤ የውጭ ፊልምና ‹‹ጌም›› ነው የሚጫንላቸው። አካባቢያቸውን እንዲያውቁ አልተደረገም። ባህላቸውንና ታሪካቸውን ቢያውቁ ሰብዓዊነት ይገነባቸው ነበር። አርቲስቶች እዚህ ላይ ነበር መሥራት ያለባቸው።
ከኪነ ጥበብ ባለሙያው የሚጠበቀውንም መምህር ተስፋዬ በወቅቱ ተናግረው ነበር። የኪነ ጥበብ ሰው መሪ ነው መሆን ያለበት። መንግስት ልማት ሲል አብሮ ልማት የሚል ከሆነ፣ መንግስት ውሃ ማቆር ሲል አብሮ ውሃ ማቆር የሚል ከሆነ ኪነ ጥበብ ዋጋ አይኖረውም። ኪያኒ ማነሳሳት ነው ያለበት። ቢቢሲ የሰራው አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ በመሬት የሚሄድና በሰማይ የሚበር አውሮፕላን ‹‹እንዴት ሰራኸው?›› ተብሎ ‹‹ፊልም ላይ አይቼ›› ነው ያለው። ከያኒ እንዲህ ነው፤ ነገሮችን ፈጣሪ! ከመንደር ያለፈ ሥራ መሥራት አለበት። ዝም ብሎ ‹‹ተጋቡ ተፋቱ›› የሚል ሥራ ብቻ ነው እየተሰራ ያለው። እንኳን በምናብ ፈጥሮ ማስተማር መሬት ላይ ያለው እውነታ እንኳን አልተሰራበትም። ወሎ ውስጥ ለጥምቀት በዓል ሙስሊም ከበሮ እየመታ ይከበራል፤ ይሄን ማንም አያውቀውም፤ ከያኒ ግን ያልታየውን ማሳየት ነበር ሥራው።
ኪነ ጥበብ ከመንግስት ኃይል በላይ ነው። ግጭት ቢነሳ መንግስት ግጭቱን ማስቆም ነው የሚችለው፤ ኪነ ጥበብ ግን እንዳይነሳ ማድረግ ይችላል። መንግስት በኃይል ነው የሚያስቆመው፤ ኪነ ጥበብ ግን በአስተሳሰብ ለውጥ ነው የሚያስቆመው፤ በፍቅር ነው የሚያስቆመው። የተጋጩት ወገኖች ኃይል ፈርተው ሳይሆን ፍቅር አሸንፏቸው ነው የሚያቆሙት።
‹‹አርቲስት ልቡ የሸበተ ነው›› ይባላል። ሽማግሌ ነው ለማለት ነው፤ አስታራቂ ነው ማለት ነው። ጸጉራቸው የሸበተ ሽማግሌዎች ለሰላም ያላቸውን አስተዋጽኦ እናውቃለን። አርቲስት ደግሞ ዕድሜው ወጣት ቢሆን እንኳን ልቡ እንደ ሽማግሌ መሆን አለበት። ከዚያና ከዚህ ያለውን የሚያግባባ መሆን አለበት። አንድ የኪነ ጥበብ ሥራ ከብዙ መድረኮችና ስብሰባዎች በላይ ያስተምራል።
የወቅቱ የሰላም ሚኒስትር ሙፍሪያት ካሚል የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን በሰበሰቡበት መድረክ እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹እኛ ፖለቲከኞች ልንቀያየር እንችላለን፤ እናንተ ግን የማትቀያየሩ መሆን አለባችሁ!››
አዎ! ሥርዓት ይመጣል ሥርዓት ይሄዳል፤ ባለሥልጣን ይቀየራል። የጥበብ ባለሙያ ግን በሕዝቡ ውስጥ ያለውን እውነታ ይዞ መቀጠል አለበት። ፖለቲከኛ በየመንደሩ ያጠረውን አጠር ማፍረስ የሚችለው ኪነ ጥበብ ነው። ጥበብ የጋራ ቋንቋ ያለው ነው።
ሙዚቃን መውሰድ እንችላለን፤ በጎጃምኛ ሙዚቃ የሚንቀጠቀጠው ኦሮሞው ጉራጌው ትግሬው ነው፤ በትግርኛ ሙዚቃ የሚሽከረከረው አማራው፣ ኦሮሞው ሶማሌው ነው። ኪነ ጥበብ አንድ ያደርጋል። የጋራ ቋንቋ ነው ማለት ይህ ነው።
የኪነ ጥበብ ሥራ ከፖለቲከኛ በላይ ነው፤ ዘመን ተሻጋሪ ጉልበት አለው። ዛሬ ‹‹ባህላችን፣ ታሪካችን›› እያልን እንድንኮራ ያረጉን ዘመን አይሽሬ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ናቸው።
‹‹አርቲስት ድንበር የለውም›› ሲባል በአገሪቱ ውስጥ ያለ ባህልና ታሪክ ሁሉ የራሴ ነው ብሎ መሥራት አለበት ማለት ነው። ብዙሃነት ውበት መሆኑን ማወቅ አለበት። ብዝሃነት ተፈጥሮ ነው። ፈጣሪ ሁሉንም አንድ አይነት ማድረግ ቢፈልግ ኖሮ ማድረግ አቅቶት አልነበረም፤ ሁሉንም አንድ አይነት ቀለም አድርጎ መፍጠር ይችል ነበር። ይህን የፈጣሪ ውበት ማስጠበቅ የሚችለው ኪነ ጥበብ ነው፤ ከያኒ ራሱ ፈጣሪ ሆነ ማለት ነው።
ኪነ ጥበብ ይህን ሁሉ ጉልበት እያለው ዳሩ ግን ያየነው እና የሰማነው አይነት ጥፋቶች ደርሰዋል። ሰዎች በአገራቸው ‹‹አገራችሁ አይደለም›› ተብለዋል፤ በአገራቸው ባዕድ ሆነዋል፤ በአገራቸው መፈናቀል ደርሶባቸዋል።
‹‹ቅኝ ያልተገዛች አገር ነፃ አገር ›› የሚለው ስሙ ብቻ ተርፏቸዋል፤ በአገራቸው ነፃነትን ሲያጡ ‹‹ቅኝ አለመገዛት ማለት ምን ማለት ይሆን?›› ያሰኛቸዋል። ‹‹ቅኝ ገዥዎችስ ከዚህ በላይ ምን ያደርጉናል?›› ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በመስቀል አደባባይ ለድጋፍ ሰልፍ ባደረጉት ንግግር። ‹‹ድንበር የለውም›› የተባለው አርቲስት ግን ራሱም ድንበር ፈጥሮ ሲከፋፈል ታይቷል።
የአንዲት አገር ዋነኛ መለያ ሰላም ነው። ሁሉም የሚመጣው ሰላም ሲሆን ነው። ሰላም በሌለበት ስለምንም ነገር ማውራት አይቻልም፤ ስለዚህ መንግሥትም ሆነ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቀኑን ከማክበር ባለፈ ሰላም ላይ ሕዝባዊ ሥራ ሊሰሩ ይገባል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2014