የበጎ ሰው ሽልማት በ2005 ዓ.ም ነው የተጀመረው። እነሆ ዘንድሮ 10ኛ ዓመቱ ሆነ። በ10 ዓመታት ጉዞ ውስጥ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የነበሩ ተሸላሚዎችን ለማስታወስ መረጃዎችን ስናገላብጥ የኪነ ጥበብ ዘርፍ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው። ለዚህ ዘርፍ ዘንድሮ 9ኛ ዓመቱ ማለት ነው። ራሱን ችሎ ዘርፍ ባይሆንም ግን በኪነ ጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎች በመጀመሪያው ዙር ተሸልመዋል።
እግረ መንገድ ለማስታወስ ያህል፤ የበጎ ሰው ሽልማት በ2005 ዓ.ም ሲጀመር ዘርፎቹም አምስት ነበሩ። ‹‹የወጣቱን የንባብ ባህል በማሳደግ›› በሚለው ዘርፍ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ተሸላሚ ነበር። እንዳለጌታ ከበደ ደራሲ ነው፤ የንባብ ባህልን ማሳደግም ጥበብ ነው። ስለዚህ የኪነ ጥበብ ዘርፉ በተዘዋዋሪ ነበረበት ማለት ነው።
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ኪነ ጥበብ ራሱን ችሎ ዘርፍ ሆኗል። የበጎ ሰው ሽልማት ዘንድሮ 10ኛ ዓመቱ ቢሆንም ዛሬ ልናስተዋውቃችሁ የምንችለው ግን እስከ 2013 ዓ.ም ብቻ የነበሩትን ነው። የዘንድሮው አሸናፊ የፊታችን እሁድ ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ነው የሚታወቀው። ዕጩዎችን ግን እናስታውሳችሁ። ሄኖክ አየለ፣ ዓለምፀሐይ በቀለ እና አብርሃም ገዛኸኝ ናቸው።
እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የተመሰገኑ ተሸላሚዎችን እናስታውስ።
- ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ)
በ2006 ዓ.ም በተደረገው ሁለተኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ‹‹አባባ ተስፋዬ›› በመባል የሚታወቁት የተረት አባት ተስፋዬ ሳህሉ ተሸላሚ ነበሩ።
አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ ከዱ በተሰኘ ስፍራ ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ሰኔ 20 ቀን 1916 ዓ.ም ተወለዱ። በ14 ዓመታቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።የፋሽስት ጣልያን መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከረሸናቸው ሰዎች መካከል የእሳቸው እናትና አባት ይገኙበታል። በጣልያን ወረራ ወቅት በልጅነታቸው ከቤተሰቦቻቸውና ከአካባቢያቸው በቀሰሙት የሽለላ፣ ቀረርቶና መሰል ትውፊታዊ ክዋኔዎች እና በውስጣቸው በነበረው የኪነ ጥበብ ፍቅር እንዲሁም ፍላጎት አማካኝነት ወደ ሙያው ተቀላቀሉ።ገና በልጅነታቸው እናትና አባታቸውን ያጡት አባባ ተስፋዬ ለከፍተኛ የሕይወት ፈተና የተጋለጡ ቢሆንም ያጋጠማቸውን የሕይወት ፈተና ተቋቁመው በአገራችን አንቱ ለመባል በቅተዋል።
ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሀሳቡን አቅርቦ በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለ42 ዓመታት በአባትነት አገልግለዋል። ፕሮግራማቸውን ሲጀምሩ ‹‹ጤና ይስጥልኝ ልጆች! … የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምናችሁ ልጆች !›› እያሉ አቅርበዋል።
አባባ ተስፋዬ ሴት ገጸ ባህሪ ሆነው ሲጫወቱ ገፀ ቅባቸውን የሚሠሩት እራሣቸው ነበሩ።
ደቡብ ኮሪያ በተወረረችበት ወቅት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል በመሆኗ በቀረበላት ጥሪ ወቅት የክቡር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ አባል በመሆን ከ1944 እስከ 1945 በ2ኛ ቃኘው ሻለቃ ለ2ኛ ጊዜ ከሄደው ሠራዊትጋር ደግሞ ከ1946 እስከ 1947 በ4ኛ ቃኘው ሻለቃ ለሁለት ጊዜ የወታደራዊ ሳይንስ ተዋናይ በመሆን ሠራዊቱን አገልግለው ለዚሁም የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ አግኝተዋል።
ከተሰጣቸው ሜዳልያዎች መካከል ጥቂቶቹ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ ሜዳሊያ (ባለ አንድ ዘንባባ) ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወርቅ ሜዳልያ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ዩኒየን ሣንይቴሽን ከአሜሪካ መንግሥት ተሸልመዋል።
- ሰዓሊ ታደሰ መስፍን
የ2007 ዓ.ም ሦስተኛው ዙር ተሸላሚ ነው። ሰዓሊ ታደሰ መስፍን በ1945 ዓ.ም በወልዲያ ተወለደ። ከእረኝነቱ ጀምሮ እጅና እግሩ ላይ በእንጨት በመሞንጨር ሥዕልን የጀመረው አዳጊው ምንም እንኳን ዝንባሌው ወደ ሥዕል ማጋደሉን ከልጅነቱ ቢረዳም መደበኛ ትምህርቱን ከመከታተል ወደ ኋላ አላለም። በዚሁ መሠረት በዕቴጌ ጣይቱ ብጡል ት/ቤት መደበኛ ትምህርቱን ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ቆይታውን እንዳጠናቀቀ የ6 ዓመቱ ታዳጊ ከአጎቱ ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በስዊዲሽ ሚሽን ት/ቤት ገብቶ መደበኛ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በበዕደ ማርያም ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ግን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሚዘጋጀው መጽሔት ‹‹ኢሉስትሬሽን›› የውጭ ሽፋን የመሳሰሉትን ይሠራ ነበር።
ሰዓሊ የመሆን ጥልቅ ፍላጎትና ችሎታ ስለነበረው 1960 ዓ.ም ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ገባ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታው ታዋቂው ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ አስተምሮታል።
በደርግ ጊዜ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ዓርማን በመቅረፅ፣ ለታላቁ የሕዝብ ለሕዝብ ትዕይንት የሚሆኑ የመድረክ እና የአልባሳት ዲዛይን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የሀገራችን የመገበያያ ሳንቲሞች (25 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም) ላይ የራሱን ሙያዊ አስተዋፅዖ በማድረግ አንጋፋው አስተማሪ እና ሰዓሊ ታደሰ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ሊወጣ ችሏል።
ትግራይ ላይ ያለውን የሰማዕታት ሐውልት የመጀመሪያውን ንድፍ ያጠና እና የፈጠረ እንዲሁም በአማራ የሰማዕታት ሐውልት ሥራ ላይ የበዛ አስተዋፅኦ ያደረገባቸውም ይጠቀሳሉ።
- ደራሲ አውግቸው ተረፈ
በ2008 ዓ.ም በተደረገው አራተኛው ዙር የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ ደራሲ አውግቸው ተረፈ ናቸው። አውግቸው ተረፈ የኅሩይ ሚናስ የብዕር ስም ነው። በቀድሞው አጠራር ጎጃም ክፍለ ሀገር ቢቸና አውራጃ በ1942 ዓ.ም ተወለዱ። ዋና ትምህርታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት ነው። በስማቸው የተጻፉ ጥቂት መጻሕፍት ቢኖሩም በአንባቢያን ዘንድ ጎልተው የወጡት በአውግቸው ተረፈ ስም የተጻፉት ናቸው።
ከፈጠራ ሥራዎቻቸው መካከል፤ ‹‹ወይ አዲስ አበባ፣ እብዱ እና የፕሮፌሰሩ ልጆች›› የሚሉት ሲሆኑ ከትርጉም ሥራዎቻቸው መካከል ደግሞ፤ ‹‹ ምስኪኗ ከበርቴ፣ ያንገት ጌጡ (ከሌሎች ደራሲያን ጋር)፣ ጽኑ ፍቅር፣ ምሥጢራዊቷ ሴት፣ ጩቤው›› ሲሆኑ ከኢ ልቦለድ ሥራዎች የትውልድ ዕልቂት ይጠቀሳሉ።
ደራሲ አውግቸው ተረፈ ‹‹እብዱ›› የሚለው መጽሐፋቸው በአዕምሮ ህክምና ሰጪዎች ስለተወደደ የአማኑኤል ሆስፒታል በስማቸው ሕንፃ ሰይሟል።
- ተስፋዬ ገሠሠ
በ2009 ዓ.ም የተደረገው አምስተኛው ዙር የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ የሆነው ተስፋዬ ገሠሠ የብዙ ጥበብ ባለቤት ነው። ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና ጸሐፊ ተውኔት ነው።
ተስፋዬ ገሠሠ መስከረም 17 ቀን 1930 ዓ.ም በሐረር ጉሮ ጉቱ ተወለደ። ቴአትርን የጀመረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ነው። በዚያ እንቅስቃሴውም በስኮላርሺፕ አሜሪካ አገር ሄዷል። ከአሜሪካ ተመልሶ ቴአትርን ከባላባቶች መጫወቻ ወጥቶ እንዲያገለግል አደረገው። በከተማ ሕይወት ላይ ያተኮረውን ‹‹የሺ›› የተባለውን ቴአትርም አቀረበ። በ1966 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ቴአትር ሥራ አስኪያጅ ሆነ። ዳሩ ግን በ1967 ዓ.ም ደርግ ወደ ወህኒ ቤት አስገባው። የታሰረበት ምክንያትም ‹‹ዕቃው›› በተሰኘው ቴአትር መንግሥታዊ ሽብርን በመተቸቱ ነው። በ1968 ዓ.ም የብሔራዊ ቴአትር ሠራተኞች ባደረጉት ሰልፍ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመኅን ከብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅነት ሲነሳ ተስፋዬ ሥራ አስኪያጅ ተደረገ። ከዚያ በኋላም በሚሠራቸው ቴአትሮች እስራት አጋጥሞታል።
በቴአትር ሙያው ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የእጅ ሰዓት ተሸልሟል። በ‹‹ሐምሌት›› እና ከ20 በላይ ተውኔቶች ላይ ተጫውቷል። የተለያዩ መጻሕፍትን ጽፏል፤ ተርጉሟል። ከእነዚህም ‹‹መተከዣ›› የተሰኘው ይጠቀሳል።
- አበበ ብርሃኔ
በ2010 ዓ.ም በተደረገው ስድስተኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚው አበበ ብርሃኔ ነው። አበበ ብርሃኔ የዜማና ግጥም ደራሲ ነው። አበበ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ከታዳጊ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የኪነት ቡድን የሠራ ነው። በትምህርት ቤትም መዝሙር ይደርስ ነበር።
አበበ በ1975 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ጎንደር ከተማ ውስጥ የተቋቋመው ፋሲለደስ የኪነት ቡድን ተቀላቀለ። እዚያው ፋሲለደስ የኪነት ቡድን እያለ ለአሰፉ ደባልቄ እና ሰላማዊት ነጋ ዜማና ግጥም ደርሷል።
አበበ አዲስ አበባ በመምጣትም ከሶል ኩኩ የሙዚቃ ባለቤት ከአቶ ሣህለ ጋር በመተዋወቁ፤ በ1980 ዓ.ም የጸጋዬ እሸቱን የመጀመሪያ አልበም ‹‹ተከለከለ አሉ›› እና ‹‹ያየ አለ›› ደርሷል። አሰፉ ደባልቄን ከጎንደር በማስመጣትም ‹‹ተው ተው የእኔ አካላት›› አልበም ላይ ያሉትን ዘፈኖች በሙሉ የደረሳቸው አበበ ብርሃኔ ነው። በዚሁ ዓመትም የየሺመቤት ዱባለን እና የብርቱካን ዱባለን ሥራዎች ሠርቷል።
አበበ ብርሃኔ የበርካታ ድምጻውያን ዜማ ደራሲ ነው። ሁሉንም ከነሥራዎቻቸው መዘርዘር ባይቻልም የጥቂቶችን እንንገራችሁ።
ኬኔዲ መንገሻ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ንጋቱ ዱባለ፣ አበበ ተካ፣ ተፈራ ነጋሽ፣ ወረታው ውበት፣ ገነት ማስረሻ፣ አስናቀ ገብረየስ፣ ፍቅርአዲስ ነቃዓጥበብ፣ ሀብተሚካኤል ደምሴ፣ ማሪቱ ለገሠ፣ ይሁኔ በላይ፣ ማርታ አሻጋሪ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ውብሸት ፍስሐ፣ ጌታቸው ካሣ፣ ነፃነት መለሰ፣ ሒሩት በቀለ፣ መሀሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ማለፊያ ተካ፣ አዳነ ተካ፣ ጋሻው አዳል፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አቦነሽ አድነው፣ ፋሲል ደሞዝ፣ ደረጀ ደገፋው፣ በዕውቀቱ ሰውመሆን፣ ተመስገን ታፈሰ፣ ዳዊት ጽጌ፣ ማስተዋል እያዩ ይጠቀሳሉ።
- አቶ በዛብህ አብተው
በ2011 ዓ.ም በተደረገው 7ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ለየት ያለ ነበር። ፎቶ ግራፍ ብዙ ጊዜ እንደ ጥበብ አይታይም፤ በዚህ ዓመት ግን ፎቶ ግራፍ ማንሳት ጥበብ መሆኑን እውቅና ተሰጥቶት ባለሙያዎቹ ተመስግነዋል።
በነገራችን ላይ በዚህ በ7ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት የኛው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የካሜራ ባለሙያ የሆነው ዳኜ አበራ ዕጩ ነበር። ለካሜራ ምቹ ያልሆኑ ቅጽበቶችን በማንሳት ይታወቃል። ከምጽዋ የባህር ኃይል እስከ የተለያዩ የጦር ግንባሮች በመገኘት ታሪካዊ ፎቶዎችን አንስቷል።
የ2011 ዓ.ም የ7ኛው ዘር የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ አቶ በዛብህ አብተው ነበሩ። አቶ በዛብህ አብተው በዚህ ዓመት በሞት ቢለዩም ታሪካዊ ሥራዎቻቸው ግን ሕያው ሆነው ይኖራሉ።
አቶ በዛብህ አብተው መስከረም 17 ቀን 1919 ዓ.ም በጎንደር ክፍለ ሀገር ተወለዱ። በመብራት ኃይል መሥሪያ ቤት ተቀጥረው በማገልገል ላይ ሳሉ በመሥሪያ ቤቱ ካሉ ጀርመኖች ጋር ተዋወቁ። በዚያው ፎቶ ማንሳት ተለማምደው ሙያቸው ሆኖ ተቀጠሩ።
በተለይም በስፖርት ማዘወተሪያዎች በመገኘት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያን ሔራልድ፣ እና በወቅቱ ይታተሙ ለነበሩ የስፖርት ጋዜጦችና መጽሔቶች ፎቶ በነፃ ሁሉ ይሰጡ ነበር።
አቶ በዛብህ ኢትዮጵያ ያዘጋጀቻቸውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች (1954፣ 1960 እና 1968 ዓ.ም) ታሪካዊ ፎቶዎችን አንስተዋል።
አቶ በዛብህ ከልጆቻቸው ውስጥ አምስቱ የራሳቸውን ፈለግ ተከትለው የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሆነዋል።
አቶ በዛብህ ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ያነሷቸውን ፎቶዎች በጥንቃቄ ሰንደው በማስቀመጥ ለታሪክ አኑረዋል።
- በዕውቀቱ ሥዩም
በ2012 ዓ.ም መደረግ የነበረበት 8ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተገቢው መንገድ አልተካሄደም። ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል አስተዋፅዖ ያደረጉ ተቋማት (ለምሳሌ ጤና ሚኒስቴር) እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አስተዋፅዖ ያደረጉ ግለሰቦች ናቸው የተመሰገኑት።
ስለዚህ በቀጥታ የምንሄደው ወደ 9ኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ነው።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው 9ኛው ዘር የበጎ ሰው ሽልማት በኪነ ጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ በዕውቀቱ ሥዩም ነበር። በዕውቀቱ በአገር ውስጥ ስላልነበረ አባቱ ናቸው የተቀበሉለት። ከሽልማቱ ማግስት በማህበራዊ ገጹ በጻፈው ጽሑፍ፤ ‹‹በበጎ ሰው ሽልማት የኪነ ጥበብ ዘርፉን እኔ እወስዳለሁ፤ ‹በጎ› የሚለው እንኳን እዚያው ለአባቴ ይሁን›› በማለት በተለመደው አስቂኝ ወጎቹ አመስግኗል።
በዕውቀቱ ሥዩም የተወለደው በጎጃም ማንኩሳ ሲሆን ያደገውና የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው ደብረ ማርቆስ ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘ ሲሆን የሚታወቀው ግን በሥነ ጽሑፍ ነው። እስከ አሁን ድረስ ስምንት መጽሐፎችን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል። ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለንባብ የበቁ አጫጭር ትረካዎችም አሉት።
በዕውቀቱ ሥዩም ለተለያዩ ድምጻውያን የዘፈን ግጥሞችን ጽፏል። ኩኩ ሰብስቤ፣ ይሁኔ በላይ እና ግርማ ተፈራ ይጠቀሳሉ። በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ መድረኮች ላይ ወጎቹን ያቀርባል።
በዕውቀቱ ሥዩም በመጽሐፍ፣ በመድረኮች ላይ እና በድምጽ ትረካዎች የሚታወቅ ቢሆንም በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይም ይጽፍ ነበር። አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ አዲስ ነገር ጋዜጣ፣ አዲስ ጉዳይ መጽሔት እና ፍትሕ መጽሔት በዕውቀቱ ይጽፍባቸው የነበሩ ናቸው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 /2014