ከአመታት በፊት መንግስት የሴቶችን መብት አስከብራለሁ እያለ ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት የሁላችንም መነጋገሪያ የነበረና እንደ ህዝብም እንደ ሀገርም አንገት ያስደፋን ጉዳይ ተከስቶ ነበር። አንድ ወጣት አፈቅራታለሁ በሚላት ልጅ ላይ አሲድ በመድፋት ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባት ተጎጂዋን ቤተሰቦቿንና መላውን ህዝብ አሳዝኖ ቆይቷል።
ወጣቱ ለፍርድ ቀርቦ ተገቢ ነው የተባለለት የቅጣት ውሳኔ ተላልፎለትም በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል። ጉዳት ደርሶባት የነበረችው ካሚላት መህዲ ከአስራ አራት አመት በኋላ ገና ያልጨረሰቻቸውን ህክምና በመከታተል ላይ ባለችበት ሀገር ሆና በሰይፉ የኢ.ቢ.ኤስ ፕሮግራም ላይ በመቅረብ በደል ያደረሰባት ወንጀለኛ ገና ከመፈታቱ በርካታ ሴቶችን አጭበርብሮ መያዙንና በቴሌቪዥን መስኮት መታየቱ እንዳሳዘናት ስትናገር ሰምተናል።
የአዋጁን በጆሮ እንዲሉ ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት ለህዝብ ይፋ የተደረገ በመሆኑ ለሀሳቤ መንደርደሪያ አንዲሆን እንጂ እንዲህ አይነት ጉዳዮች በርካታ መሆናቸውን ሁላችንም የምንረዳ ይመስለኛል። በሀገራችን ያሉ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን አርመውና አስተካክለው ወንጀል ጠል አድርጎ ከማውጣት ይልቅ የተሻሻሉ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ ማሰልጠኛ እያደረጓቸው ነው የሚል ስጋት እንዲያድርብኝ አድርጎኛል።
ከሚላት መህዲ ላይ አሲዲ በመድፋትና ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የፍርድ ውሳኔ አግኝቶ ከአስር አመት በላይ በእስር ቆይቶ የወጣው ወንጀለኛ በቅርቡ በርካታ ሴቶችን በማጭበርበር ወንጀል እየተጠየቀ ይገኛል። የቀድሞው ወንጀለኛ የአሁኑ ተጠርጣሪ በፖሊስ እንደተገለጸው ለሁለተኛ ግዜ ወንጀል መስራት የጀመረው በእስር ቤት እያለ መሆኑንና የህግ አስከባሪ አካላትን ጨምሮ በርካታ አባሪዎች ያሉት መሆኑ ደግሞ የሚያስገርምና እንዴት የሚል ጥያቄንም የሚያጭር ነው።
ይህንን ያነሳሁት የቅርብ ግዜ ስለሆነ ይፋ በመውጣቱ እንደማሳያ ለማድረግ እንጂ ወደ ማረሚያ ቤት እንደ ዘመድ ጠያቂ በተደጋጋሚ የሚመላለሱ ከቀላል አስከ ከባድ ወንጀለኞች እንዳሉ ያደባባይ ሚስጥር ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እስር ቤቶችን ሰብአዊ መብቶች የማይጣስባቸው ፤ በርካታ ስልጠናዎችና ትምህርቶች የሚሰጥባቸው ለማድረግ ተግቶ እየሰራ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየተነገረ ይገኛል። ከሀገር ውስጥ ሰብአዊ መብት ተሟጋች እስከ አለም አቀፍ ያሉት በየደረሱበት የሚነግሩንም በእስር ቤቶች በታራሚዎች ላይ የሚደርስ ከፍተኛ ሰቆቃ መኖሩን ነው።
እንደ አንድ ጤነኛ አእምሮ እንዳለው ግለሰብ ሁሉም ነገር በህግና በስርአት መመራት እንዳለበት በጽኑ አምናለሁ። ይህ ማለት በወንጀል የተጠረጠሩ አልያም ወንጀለኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦች በሰዎች ፈቃድ ሳይሆን በህግ በተደነገገው መሰረት ብቻ መሆን አለበት። ይህም ሆኖ ግን ማረሚያ ቤቶች የተቋቋሙለትን አላማ ፍርድ ቤቶች የተመሰረቱበትን አላማ ሊስት አይገባም።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ የምንሰማቸው ዜናዎች የሚነግሩን ግን በተለይ ወጣቶች ወደማረሚያ ቤቶች ጎራ ብለው ከወጡ ከወንጀል ሲርቁ ሳይሆን ይልቁንም በተደጋጋሚ ወንጀሎች ላይ በንቃትና በትጋት ሲሳተፉ ነው። ለዚህ የሚዳርጋቸው ደግሞ እንደየሰው ምልከታ የተለያየ ቢሆንም በማረሚያ ቤቶች የሚያሳልፉት ግዜ በቅጣት መልክ አለመሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።
በወንጀለኛ መቅጫም ሆነ በፍትሃ ብሄር ህጉ የተቀመጡት ህጎች መንፈሳቸው ወንጀለኞች ተመልሰው ወንጀል እንዳይሰሩና ሌሎችም ከወንጀል ድርጊቶች እንዲቆጠቡና ህግ እንዳይጥሱ ማድረግ ነው። ይህንን መነሻ አድርገን የተጠናከረ መረጃ ባይኖረንም በተደጋጋሚ ወንጀል የሚሰሩ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ግን ቅጣቱ አስተማሪ እንዳልሆነ አመላካች ነው።
በአካል ተገኝተን ባናየውም በአንዳንድ ሀገራት የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ከሲኦል የከፉ በመሆናቸው ብዙዎች ከእስር ለማምለጥ የማይከፍሉት መስዋእትነት የለም። በተወሰኑ ሀገራት ደግሞ በህጋዊ መንገድ ወንጀለኞች በትልልቅ የሀገር ፕሮጀክቶች ላይ ጨምሮ በጉልበት ስራ እንዲሳተፉ ስለሚደረግ ታራሚዎች ተመልሰው ወደ ወንጀል የመግባታቸው ሁኔታ እጅግ ጠባብ ነው።
በአሜሪካ የተወሰኑ ግዛቶች ስራ ለመቀጠር ከወንጀል ሪከርድ ነጻ መሆን የሚታይባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው ደግሞ ወንጀለኞች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ማህበረሰቡ ህግን በመጣስ ወንጀል በመስራትና በእስር ቤቶች ላይ የሚኖረው እይታ ጠንካራና አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል።
በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየን ግን ይህንን አይደለም። እዚህ ላይ ጥናት ባላካሂድም ያለኝን ግላዊ ምልከታ እንደሚከተለው ልሰነዝር እወዳለሁ። ብዙዎች ወንጀል ከሰሩ በኋላ በእስር ቤት ከሚያሳልፉት ግዜ በላይ የሚያስፈራቸው በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸው መገለልና መገፋት ነው። ለዚህም ይመስለኛል አንዳንድ ታራሚ ወጣቶች በእስር ከሚያሳልፉት ግዜ በላይ ማህበራዊ ተጽእኖዎችን በመፍራት አካባቢያቸውን ይለቁ ወይንም ሰፈር መዋል ያቆሙ ይሆናል እንጂ ከቀደመ መጥፎ ምግባራቸው የመታቀቡ ነገር እምብዛም የማይስተዋለው። በማረሚያ ቤት በተፈጠረ ጓደኝነት ተደጋጋሚ ወንጀሎችን የሚሰሩ መኖራቸውም በተለያዩ ግዜያት በሚቀርቡ የፖሊስ ፕሮግራሞች ለመመልከት በቅተናል።
አንዳንድ ግዜ ከታራሚዎችም ሆነ ንግግሮች በማህበረሰቡ ዘንድ ተዘውትረው የሚነሱት ምን ይሆናል መንግስት ቀልቦ አስተምሮ ይለቀዋል የሚሉና ወንጀለኞች ራሳቸው አልሟሟ ታስሮ መውጣት ብርቅ አይደለም ይሉት ፈሊጥ ለዚህ አመላካች ይመስሉኛል። ከአእምሮና ከስነ ልቦና ጋር የተያያዘውን ነገር ለባለሙያዎችና ለታራሚዎች እንተወውና በአይናችን እንደምናየው ግን አብዛኛው ወንጀለኛ ከእስር ሲወጣ አምሮበትና በአካላዊ ሁኔታው ተስተካክሎ ነው።
በእስር የቆዩ ወንጀለኞች በድጋሚ በወንጀል ስራ ተሳትፈው መገኘታቸው ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብና መንግስት የሚያስተላልፈው ጥሩ ያልሆነ መልእክትም አለ። የወንጀል ተጠቂ የሆኑ ግለሰቦችና ማህበረሰቡ እንዲህ አይነት ነገሮችን በተደጋጋሚ ሲመለከቱ በሀገሪቱ የህግ ስርአትና የህግ አስከባሪ አካላት ላይ የሚኖራቸው እይታ የተዛባ ከመሆኑ ባሻገር እምነት ወደማጣቱ ይሄዳሉ። ይህም ወንጀል ሲፈጸም ለህግ አለማሳወቅ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ፈቃደኛ አለመሆንና አንዳንድ ግዜም ከወንጀለኞች ጋር መደራደር በመጀመር ወንጀል እንዲስፋፋ የሚያደርግ ይሆናል።
በተጨማሪ በማህበረሰቡ ውስጥ ወንጀል እየሰሩ በሰላም በደስታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መብዛት የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች የእነሱን አርአያ እንዲከተሉ በር የሚከፍት በመሆኑ ልጆች በወጣትነታቸው በወንጀል ውስጥ ለመግባት የሚኖራቸውን እድል ሰፊ ያደርገዋል። በመንግስትም በኩል ቢሆን የህግ አስከባሪ አካላት ካለ ህብረተሰብ ተሳትፎ ህግ የማስከበር ስርአቱ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል ባጡት ታማኝነት ልክ የስራቸውም ውጤታማነት እየከሸፈ የሚመጣ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ሀገር ሊያበጣብጡን ሊያፈርሱን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ረብጣ ብር ይዘው ላሰፈሰፉት አሸባሪዎች አማራጭ መንገድ መክፈትም ይሆናል።
በመሆኑም መንግስት በአንድ ወገን አስፈላጊውን የህግ ማእቀፍ በማዘጋጀት። በሌላ በኩል ታራሚዎች በማረሚያ ቤቶች የሚኖራቸው ቆይታ ከወንጀል እንዲርቁ አስገዳጅ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ሊሆን ይገባል ፤ በትክክልም ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት የሚያገኙበት እና የሚማሩበት ሊሆን እንደሚገባ አጠናክሮ ሊሰራ ይገባል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም