“ሰከላ ዓባይን ወለደች፣
እናቴም እኔን”
ይህ በአንድ ጊዜ እንደሚሰማ አንድ የዘፈን ትራክ ዓይነት ቅርጽ ይዞ በተቀነባበረውና “ሦስት” ብሎ በተሰየመው (Truck liked album) አልበሙ ውስጥ ሙዚቀኛውና የድምጽ መሃንዲሱ ሮፍናን ኑሪ እየደጋገመ የሚያዜማት መሪ የዘፈን አዝማች ናት። በዚች መሪ የዘፈን አዝማች ስንኝ ውስጥ አርቲስቱ ንጽጽራዊ ዘይቤን በመጠቀም በሁለት ጥንድ ነገሮች መካከል ያለውን መመሳሰል ሊነግረን ይሞክራል። በሰከላና በእርሱ እናት፣ በዓባይና በእርሱ(በሮፍናን) መካከል አንዳች ዓይነት የባህሪይ አንድነት መኖሩን ይነግረናል። እናቱን ከሰከላ ጋር፤ ራሱን ደግሞ ከዓባይ ጋር ያነጻጽርልናል።
ታዲያ ሮፍናን ይህን ይበለን እንጂ እናቱ ከሰከላ፤ እርሱ ከዓባይ የሚመሳሰሉት በምን እንደሆነ ግን አይነግረንም፤ በእነዚህ አካላት መካከል ያለውን ተመሳሳይነት እኛው ራሳችን ፈልገን እንድንደርስበት ክፍት አድርጎ ትቶልናል። ወትሮም ባለቅኔ ሃሳቡን የሰም ካባ አልብሶ፣ በምሳሌ ሸፋፍኖ፣ የልቡን ፍላጎት በቅኔ ሞሽሮ ነውና ለታዳሚ የሚድረው በፈቀደችልን ልክ ሙሽራዋን ገልጦ ማየት ለእያንዳንዳችን የተሰጠ ኃላፊነት ነው። ታዲያ በሮፍናን ቅኔ ውስጥም ከሰሙ ባሻገር ሁሉም የየራሱን ወርቅ አይቶ ይሆናል፤ እኔ ያየሁትን በዚህ ጽሁፍ ላካፍላችሁ ወደድኩ። ሰከላ ከባህር ዳር ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ባህርዳር ደቡባዊ ምዕራብ 165 ኪሎ ሜትር፤ ከመዲናችን አዲስ አበባ ደግሞ 430 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ምዕራብ ጎጃም ውስጥ የምትገኝ ወረዳ ናት። ታዲያ የበርካታ ወንዞች መፍለቂያና የተለያዩ ምንጮች መገኛ ከሆነው ውኃ አዘሉና ውርጫማው የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራዎች ሥር የምትገኘው ሰከላ ወረዳ ግሽ ዓባይ የምትባል አንዲት ቲንሽ ምንጭ አለች። ይሁን እንጅ ይች ቲንሽ ምንጭ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ዓባይ ፤ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው ደግሞ ከምድር ተነስተው ገነትን ከሚያጠጡ አራት አፍላጋት መካከል ሁለተኛውና “እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል” የተባለው ታላቁ ግዮን ወንዝ መፍለቂያ ናት። የሰከላ ወረዳ ዋና ማዕከል የሆነችው የወረዳዋ ዋና ከተማ የተሰየመችውም በዚችው ምንጭ ስም ነው። እናም ሰከላ የታላቁ የዓለማችን ወንዝ ዓባይ መነሻ ስፍራ ናት። እንግዲህ ከሮፍናን እናት ጋር የተነጻጸረችው ሰከላ ከዓባይ ጋር ያላት አፍአዊ ዝምድናና “ሰከላ ዓባይን ወለደች፤ እናቴም እኔን” የሚለው የዘፋኙ ቅኔ ሰሙ ይኸው ነው። ወደወርቁ እንለፍ። በእኔ ዕይታ በዚች ቅኔያዊ መሪ የግጥም አዝማች ሊተላለፍ የተፈለገው ሚስጥራዊ መልዕክት ወይንም የቅኔው ወርቅ “መነሻህ ምንም ይሁን፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ ቦታ መድረስ ትችላህ” የሚል ነው።
ሮፍናን “ሰከላ ዓባይን ወለደች” ካለ በኋላ “እናቴም እኔን” በማለት ሰከላና እናቱን ያመሳስላል። ሰከላ ያገሬው ሰው እንኳን በቅጡ የማያውቃት ምንም ትንሽ ወረዳ ብትሆን ከዓለማችን ወንዞች ሁሉ ረጅሙን፣ ከፈለቀበት ቀየ አልፎ ዓለም ሁሉ የሚያውቀውን፣ ዝነኛውንና ታላቁን ዓባይን ወልዳለች። እናም ሮፍናን “የእኔም እናት እንደዚሁ ከጎረቤቶቿ በቀር ብዙም የማትታወቅ፣ ያን ያህል ዝና የሌላት ሴት ብትሆንም “ታላቅና ዝነኛ የሆንኩትን(መሆን የምችለውን) እኔን ወልዳለች” የሚል መልዕክትን ለማስተላለፍ የፈለገ ይመስለኛል።
ይህንንም ራሱ ከሰሞኑ ስድስት የሚል ሦስተኛ አልበሙን ካሳተመ በኋላ በሸገር ኢፍ.ኤም የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ከ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጾታል። ሮፍናን ለእርሱ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የእናቱ አስተዋጽኦ እጅግ ትልቅ እንደሆነ ይናገራል። “ለእኔ ትልቅ ነገር የሚሆነኝ ከመሰላት ግን ምንም ነገር አትከለክለኝም፤ ደግሞም ትልቅ እንደምሆን እርግጠኛ ነበረች። ምንም ነገር ሞክሬ ሚያቅተኝ አይመስላትም ነበር” ይላል። ከልጅነቱ ጀምሮ የእናቱን ድምጽ እየቀረጸ የማዳመጥ ልማድ የነበረው መሆኑን የሚያስታውሰው ሙዚቀኛ ሮፍናን “…እና ዩኒቨርሳል ሪከርድስ ልናስፈርምህ እንፈልጋለን ሲለኝ መጀመሪያ ወደአዕምሮየ የመጣው ያኔ በልጂነቴ እናቴ ባወራች ቁጥር ድምጽሽን ልቅዳው ስላት እምቢ ብላኝ ቢሆንስ? የሚለው ነው። ግን እኮ ችላ አይደለም ዝም ብላ ነገር ነው የምታወራው” በማለት እናቱ እንደብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን እናቶች ዘመናዊ ዕውቀት ያልነበራቸው ሴት መሆናቸውን ይነግረናል። ይሁን እንጂ ከቲንሿ ሰከላ ፈልቆ ታላቅና በዓለም ዙሪያ ታዋቂና ዝነኛ ወንዝ መሆን እንደቻለው ዓባይ እናቱ ምንም ነገር ፈልጎ ማድረግ እንደማያቅተውና ከሁሉም በላይ እንደሆነ እንዲሰማው አድርገው ያሳደጉት ሮፍናንም ምንም እንኳን ከታዋቂና ከዝነኛ ቤተሰብ ባይወለድም አንድ ቀን ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደርስና ዝናው በዓለም ሁሉ እንደሚናኝ ዕምነቱ ነበረው። ይህንንም ነው “ሰከላ ዓበይን ወለደች፣ እናቴም እኔን” በማለት ሦስት በተባለው አልበሙ ላይ በቅኔ የነገረን።
ሮፍናን በጊዜው በዚያ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ታላቅ ሰው አለመሆኑን ባያጣውም አንድ ቀን በጊዜ ሂደት ግን ከራሱ አልፎ እናቱንና አባቱን፣ ብሎም ሃገሩን የሚያስጠራ፣ ዝናው በዓለም ሁሉ የናኘ ታላቅ ሰው መሆን እንደሚችል ውስጡ ይነግረው ነበር፣ እንደሚያሳካውም በራሱ እርግጠኛ ነበር። እነሆ “ሰው በልቡ እንዳሰበው እንዲሁ ይሆናል” ነውና ቃሉ አሁን ላይ ሮፍናን ህልሙ እውን የሚሆንበት ጊዜ ላይ የደረሰ ይመስላል። ለምን ቢሉ ድንቅ ተሰጥኦውንና ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ሕልሙና ዕምነቱን አይቶ የዓለማችን ትልቁ የሙዚቃ ኩባንያ ዩኒቨርሳል ሬከርድስ ቤቱ ድረስ መጥቶ አስፈርሞታልና!
ዩኒቨርሳል ሪከርድስ በስድሳ ሦስት የዓለም ሃገራት ትልልቅ ቅርንጫፎች ያሉት፣ የዓለምን የሙዚቃ ገበያ 98 በመቶ የተቆጣጣረ የዓለማችን ትልቁ የሙዚቃ ካምፓኒ ነው። ከሙዚቃ ንጉሡ ማይክል ጃክሰን እስከ የሙዚቃ አብዮተኛው የሬጌ ፈጣሪው ቦብ ማርሌ፣ ከማዶና እስከ ሪሃና፣ ከካንትሪ ሙዚቃ ፈርጦቹ ኬኔ ሮጀርስ እስከ ሊዮኔል ሪቸ፣ ከራፕ ንጉሱ ቱፓክ ሻኩር እስከ ኢሚኔም፣ ከካቲ ፔሪ እስከ ቢዮንሴ፣ ትልልቆቹ የዓለማችን ዝነኛ ድምጻውያን በዩኒቨርሳል ሪኮርድስ በኩል አልፈው ወደዝና ማማ የመጡ ናቸው። ከሞሮኳዊው ሻሃታ ሃሰን እስከ ደቡብ ኮሪያዊው ሱፐር ጁኒየር…ከኢንዶንዥያ እስከ አልባኒያ፣ ከደቡብ አሜሪካ እስከ ካሪቢያን እስያ…በሰባቱም አህጉራት በየሃገሩ የሚገኙ ዝነኛ አቀንቃኞችና አርቲስቶች ዝናቻው ከሃራቸው አልፎ በዓለም ዙሪያ እንዲናኝና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ያስቻላቸው ግዙፉ ዓለም አቀፋዊ የሙዚቃ ኩባንያ ዩኒቨርሳል ሪከርድስ ነው።
እናም ለአንድ አርቲስት ከዩኒቨርሳል ሪከርድስ ጋር መሥራት ማለት ከትውልድ ሃገሩ ተሻግሮ በመላው ዓለም የሚታወቅበትን ዕድል ማግኘት ማለት ነው። የሮፍናንም ህልም ይኸው ነው፤ የሙዚቃ ስራው በሃገሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚደመጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ዝነኛና ታላቅ አርቲስት መሆን። በሸገር ኤፍ.ኤም የቅዳሜ ጫዋታ ፕሮግራም ላይ ራሱ ሮፍናንም እንዳለው ይህን ዕድል ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። የሙዚቃውን ንጉስ ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን ጨምሮ የሃገራችን ትልልቅ ዝነኛ ድምጻውያን ያላገኙት ወርቃማ ዕድል ነውና። በዓለም አቀፍ ደረጃ መደመጥ የሚችል ሙዚቀኛና ድምጻዊ አጥተን፤ ሙዚቃችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመደመጥ አቅም ስላለው ሳይሆን እንደዛ እንዲሆን የሚያስችል ሥራ ባለመሠራቱ የተነሳ በእርግጥም ለአንድ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ይህን እንደ ትልቅ ዕድል የሚቆጠር ብቻ ሳይሆን ትልቅ ድልም ነው። እምነቷ ተራራን የሚያንቀሳቅሰው ያች ምስኪን እናቱ ምንም ነገር ማድረግ እንደማያቅተውና ከሁሉም በላይ እንደሆነ እየነገረች ያሳደገችውና ከትንሽም ሆነ ከትልቅ፣ ሰው ከየትም ይወለድ ራሱን ለትልቅ ነገር ካጨና ትልቅ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብሎ ካመነ “እንደእምነቱ ይሆንለታል” ብሎ የተነሳው ብላቴናው ሮፍናን ግን አንድ ቀን ይህን ያሰበው እንደሚሳካ ቀድሞ ገብቶታል። ይህንንም “ሰከላ ዓባይን ወለደች፣ እናቴም እኔን” በማለት በሙዚቃው ተናግሮ ነበር። “አንተ መሆን የምትፈልገውን ነገር ከልብህ ወደኸው ጽኑ ፍላጎት ኖሮህ በተግባር መጣር በምትጀምርበት ጊዜ ፍላጎትህ እንዲሳካ መላው ዓለም ከአንተ ጋር አንድ ላይ ያሴራል” እንዲል የምንጊዜም ምርጥ ሽያጭ መጽሐፍ የ“ዘ አልኬሚስት” ደራሲው ፓውሎ ኩዊንልሆ ከልብ ካመኑና በርትተው ከጣሩ ሁሉ ይቻላልና እነሆ ለታላላቆች ያልተቻለው ለሮፍናን ተችሏል።
ከአፍሪካም ይሁን ከአሜሪካ፣ ቋንቋው ዓለም አቀፍም ይሁን ሃገርኛ፣ እንግሊዝኛም ይሁን አማርኛ ከልብ ካመኑና ከጣሩ ሁሉ ይቻላልና ስንት ታላላቅ የሃገራችን ድምጻውያን ያልቻሉትን በዓለም አቀፍ መድረክ የመሥራትና የመታወቅ እድል ሮፍናን ሊያገኘው ችሏል።
ባገኘው ትልቅ ዕድል እጅግ መደሰቱንም ገልጿል። እንዲህ ሲል፡- “ዩኒቨርሳል ሪከርድስ የዓለማችን ትልቁ የሙዚቃ ኩባንያ ነው፤ ይህን ዕድል ማግኘቴ ለእኔ ትልቅ እድል ነው። ጎፋ ተወልዶ ቄራ ላደገ፣ በሕዝብ ትምህርት ቤት ለተማረ፣ ለአንድ ኢትዮጵያዊ አርቲስት እዚህ ደረጃ መድረስ ቀላል አይደለም። አንድ አሜሪካዊ ይህንን ዕድል ለማግኘት ብዙ መከራውን ነው የሚያየው፤ ይህንን በሚያክል ትልቅ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ካምፓኒ እውቅና አግኝቼ አብሬ እንድሠራ ዕድል ማግኘቴ ለእኔ እጅግ ትልቅ ዕድል ነው። እንዲህ ዓይነቱን ዕድል ማግኘት መመረጥ ነው፤ በዚህም ኩራት ይሰማኛል”።
የሮፍናን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ወደትልቅ ደረጃ መምጣትና ከትውልድ ሃገሩ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ዝነኛ ሊያደርገው የሚያስችልውን ሥራ መሥራት የሚችልበትን ዕድል ማግኘት ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሃገሩ ኢትዮጵያም ትልቅ እንድምታ ያለው መሆኑንም አርቲስቱ ተስፋውን አመላክቷል። “ሙዚቃችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥቶ እንዲሰማና ዕውቅና እንዲያገኝ፣ ትልቅ ገቢ ምንጭ እንዲሆን በር የሚከፍት በመሆኑ ለእኔ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለሃገራችንም ትልቅ ዕድል ነው ብዬ አስባለሁ። አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ ሙዚቃዎችን ትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ሲዘፈኑ ለመስማት፤ የወላይታ፣ የጋምቤላ…የሃገራችን ሙዚቃዎች ከእኛ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ መድረኮች ላይ ለመስማት ምናልባት እኔ በር ሆኜ ይሆን ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል” ብሏል። የሃገር ታሪክ ዜጎቿ የሚሠሩት ታሪክ ነውና በእርግጥም የሮፍናን ወደዓለም አቀፍ መድረክ የመምጣት ታሪክ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪም የራሱን አሻራ የሚያስቀምጥ ነውና አስተዋፅኦው በቀላል ሚታይ አይደለም። እናም በአርቲስቱ ሕልም ውስጥ የእኛም የሁላችንም ሕልም አለና ሕልሙ እንዲሳካ ከልብ እንመኛለን።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 /2014