የተወደደ ይወደዳል!
በቅርቡ በብሔራዊ ቴአትር አንድ መድረክ ተዘጋጅቶ ልታደም ሄጄ ነበር። በእርግጥ በብሔራዊ ቴአትር የሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ብዙ ጊዜ ሄጃለሁ። እንዲያውም ይሄ አሁን የምነግራችሁ ገጠመኝ ያጋጠመኝ ብዙ ጊዜ በመሄዴ ነው። ከዚያ በፊት ግን መድረኩ ምን መሰላችሁ? የወግ፣ የዲስኩር እና የግጥም ሥራዎች የሚቀርቡበት ነው።
በተለይ በዲስኩር ደግሞ በጣፋጭ ንግግሮቻቸው የሚታወቁት እነ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና ዑስታዝ አቡበከር ቀድመው ተዋውቀዋል። እነዚህ ሰዎች ያሉበት ብዙ መድረክ ታድሚያለሁ፤ እዚያው ብሔራዊ ቴአትርም ታድሜያለሁ። እንደሚታወቀው እነርሱ አሉ ከተባለ አዳራሹ ይሞላል፤ ቢሆንም ግን መቆሚያ መቀመጫ የለም እስከሚባል አይደለም። የሰሞኑን መድረክ የተሸወድኩበት ምክንያት እንዲህ ነው! መድረኩ 100 ብር መግቢያ አለው። የሚጀመረው 11፡00 ነው። በክፍያ መሆኑን ሳውቅ ምን ተሸወድኩ መሰላችሁ? ክፍያ ስላለው ሰው አይበዛም፤ ስለዚህ ቦታ አይጠፋም ብዬ ተሸወድኩ።
በነፃ በሚገባባቸው መድረኮች እስከመጨረሻው ትርፍ ወንበር እንዳለ ሳስተውል ነው የቆየሁ። እናም 11፡00 ለሚጀመረው ፕሮግራም 10፡30 ደረስኩ(በኔ ቤት ቀድሜ መድረሴ ነበር!) ስደርስ ሁለቱም አቅጣጫ አሞራ ዞሮ የማይጨርሰው ሰልፍ አለ። ሌላም ነገር አለ ይሆን ብዬ ተጠራጥሬ ስጠይቅ ያው እኔው የመጣሁበት ጉዳይ ነው። ከተጀመረ በኋላም እንኳን መቀመጫ መቆሚያም አልነበረም። ያለምንም ማገነን ከኋላ ያሉ ሰዎች ምንም ማየት ስላልቻሉ ተመልሰው ወጥተዋል።
የብሔራዊ ቴአትሩን ይህን ያህል ከነገርኳችሁ አይበቃም? እንዲያው ነገር ስለማንዛዛ እንጂ ዋና ጉዳዬ እኮ ስለዚያ መድረክ አልነበረም። ቢሆንም ግን ቀጥሎ ከማወራው ጋር ስለሚገናኝ መግቢያ ቢሆነኝ ብዬ ነው(መግቢያው እንዲህ የረዘመ ዋናው እንዴት ሊሆን ነው እንዳትሉ?) ባህሪያችን ሆኖብን የተወደደ ነገር እንወዳለን። ይሄ የነገርኳችሁ ገጠመኝ እኮ ብዙ ጊዜ በነፃ ሲቀርብ የነበረ ነው። ክፍያ አለው ሲባል ግን ሰው በጣም በዛ። በዚያ ላይ ደግሞ አብዛኛው ጥንድ ጥንድ የሆነ ነው። እርስበርስ እየተገባበዙ መሆኑ ነው(አቤት ግብዣ ስንወድ!) በቃ ግብዣ ነው ከተባለ እኮ የምንወደውን ነገር ራሱ እንወደዋለን አይደል?
በግብዣ ነበር እኛን የአዲስ አበባን ቆሻሻ ማስጠረግ! አንድ ነገር በነፃ ከሆነ ፍላጎታችን ይቀንሳል። እንኳን በነፃ ዋጋው ዝቅተኛ የሆነ እና ከፍተኛ የሆነ ራሱ ይለያያል። አገልግሎቱ አንድ ዓይነት ቢሆን ራሱ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው ደስ የሚለን። ለምሳሌ የልብስ ምርጫችንን ልብ በሉ። የሚታየው ጥንካሬው መሆኑ ቀርቷል።
በቃ ዋጋውና እነማን ለብሰውታል የሚለው ነው ሚታይ! የምግብ ምርጫችንንም ልብ በሉ! በነገራችን ላይ እነዚህ ኮንቴነር ውስጥ ያሉ በተለምዶ ‹‹ማዘር ቤቶች›› የሚባሉ ምግብ ቤቶች በጣም ነው የሚጣፍጡ! ፍርፍርና ሽሮ። ኢንተርናሽናል ሆቴል ውስጥ ከምጋበዝ እነዚህ ቤቶች ውስጥ ከፍዬ ብበላ ይሻለኛል። አሁን እኔ ታዋቂ ወይም ሀብታም ብሆን ብላችሁ አስቡት፤ እነዚህ ቤቶች ገብቼ ብበላ ሰው ምን ይለኝ ነበር? አያችሁ አይደል ልማዳችንን? ደግነቱ ፈጣሪ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በተፈጥሮ የሚገኙ አደረገልን እንጂ እንደ እኛ የተወደደ ነገር መውደድ ቢሆን ኖሮ ድሃ አልቆ ነበር።
እስኪ አስቡት! ውሃ በኢንተርናሽናል ሆቴል ውስጥ ብቻ የሚገኝ ቢሆን፣ አየር የሚገዛ ቢሆን ምን ይበጀን ነበር? የተወደደ ነገር እንወዳለን። እንዲያውም አሁን አሁን ሳስበው ደራሲዎች የመጽሐፍን ዋጋ ከፍተኛ ያደረጉት ለብሩ ሳይሆን በብዛት እንዲሸጥላቸው ይመስለኛል። ግደላችሁም እውነትነት አለው። እስኪ እንገምት! አንድ ጥልቅ የፖለቲካ ትንታኔ ወይም የአገሪቱን ጓዳ ጎድጓዳ ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ታተመ እንበል። ይሄ መጽሐፍ ‹‹በነፃ የሚታደል›› የሚል በደማቁ ቢጻፍበት የሚወስደው ያለ ይመስላችኋል? ከዚያ ይልቅ በአንድ ጀንበር የተጻፈ መጽሐፍ ከፍተኛ ዋጋ ቢጫንበት በርብርብ ይገዛል።
እኔ እኮ ግን ያልገባኝ ነገር! እዚህ ጋ ‹‹አጣን! ተቸገርን! ኑሮ ተወደደ!›› የሚል ሮሮ አለ። እዚህ ጋ ደግሞ በአነስተኛ ዋጋ ለዚያውም ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ እያለ ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ለቁርጠት የሚዳረግ ሰው አለ። ሰውነትን ከብድርም ሆነ ከፀሐይ የሚከላከል፣ ጥንካሬ ያለው ልብስ በአነስተና ዋጋ መግዛት እየተቻለ ቁራጭ ልብስ በከፍተኛ ዋጋ ገዝተው ፀሐይና ብርድ የሚፈራረቅባቸው አሉ። ይሄ ሁሉ የሆነው እንግዲህ የተወደደ ነገር ስለምንወድ ነው።
በነገራችን ላይ የተወደደ ነገር መውደዳችን በዋጋ ላይ ብቻ አይደለም። እስኪ ነገሩን ወደ ሰውም እናምጣው። ታዋቂ የሆነ ሰው እንወዳለን። አንድ ታዋቂ ያልሆነ ሰው የቱንም ያህል ምርጥ ንግግር ቢያደርግ፣ የቱንም ያህል ማራኪ ጽሑፍ ቢጽፍ፤ አንድ ታዋቂ የሆነ ሰው የተናገረው ወይም የጻፈው ትርኪ ምርኪ ነገር የበለጠ በሰዎች ዘንድ ይዳረሳል። ጥቅስ ተብለው በየግድግዳው የተለጠፉ፣ በየንግግሩና በየጽሑፉ የመግቢያ ማጣፈጫ የተደረጉ ‹‹የእገሌ አባባል›› ተብለው የሚጠቀሱ ሃሳቦችን ልብ ብዬ አስተውላለሁ። አንዳንዶቹ የጎረቤታችን ሽምግሌዎች ሲናገሩት የምሰማው ነው። አንዳንዶቹም ማንም ሰው ሊላቸው የሚችል ቀላል ትርጉም ያላቸው ይሆኑብኛል። የተናገራቸው ሰው የአገር መሪ ከሆነ (በተለይም የኃያላን አገር)፣ ታዋቂ ከሆነ ሃሳቡ የተለየ ትርጉም የሰጠ ይመስለናል። ያንኑ አባባል አንድ ተራ ግለሰብ ሲለው ብንሰማ ግን ከምንም አንቆጥረውም።
ፌስቡክ ላይ እንኳን ያለውን ነገር ልብ በሉ! ብዙ ተከታይ ያለው ሰው ምንም ተራ ነገር ይጻፍ ብዙ ወዳጅና ተጋሪ አለው። በእርግጥ ፌስቡክ ላይ ብዙ ተከታይ የሚኖረው ሰው መጀመሪያ በሌላ ነገር ታዋቂ ከሆነ ነው። ለምሳሌ በቴሌቪዥን ታዋቂ ከሆነ፣ ወይም በፖለቲካም ይሁን በሌላ ነገር ሰው ካወቀው ነው ብዙ ተከታይ የሚኖረው። ይሄ እንግዲህ የሚያሳየን ሃሳብ ዓይተን እንደማናደንቅ ነው።
የምናደንቀው ሌላ ሰው ሲያደንቀው ስላየን ነው። ምናልባት በዚህ ልማዳችን ይሆን ፖለቲካችንም የመንጋ ጋጋት የበዛበት? በነገራችን ላይ የተወደደ ነገር የሚበረታታባቸው ብዙ ልማዶች አሉን። እስኪ አሁን ደግሞ የጠላ ቤት አመራረጥን ልንገራችሁ (አይ የገጠር ልጅ ነገር!) ሰዎች የጠላን ጥራት የሚለኩት በጠላ ቤቱ ውስጥ ባሉት ሰዎች ብዛት ነው።
በጠላ ቤቱ ውስጥ ብዙ ሰው ካለ ጠላው ጥሩ ነው ማለት ነው፤ ትንሽ ከሆኑ ግን አይረባም ማለት ነው። ገጠርን ምሳሌ ያደረኩት አዲስ አበባ ለዚህ ምሳሌ ስለማይመች ነው፤ ምክንያቱም እንኳን ምግብ ቤትና መጠጥ ቤት መንገድ እንኳን ስትሄድ በወረፋ ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የተጨናነቀ ቦታ ቢታይ የጥራት ምልክት ሳይሆን የሕዝብ ብዛት ችግር ነው። በዚያ ላይ ደግሞ የሚጠጣውም ሆነ የሚበላው ነገር ተመሳሳይ ስለሆነ ሙያ የሚለካበት አይደለም።
ለምሳሌ ጃምቦና ቢራ የትም ቢገቡ አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህ የወረፋ ሱስ ካልሆነ በስተቀር ሰው የበዛበት ቦታ መሄድ አይጠበቅብንም ማለት ነው። ለነገሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሰልፍ ሱስ አለበት። ግደላችሁም ማሳያ አለኝ። የ10 ደቂቃ መንገድ ለመሄድ 30 እና 40 ደቂቃ የሚሰለፍ ሕዝብ እኮ ነው ያለው! በታክሲ ሰልፍ ላይ አማራጭ እንኳን አይጠቀምም። ለምሳሌ ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ መሄድ የሚፈልግ ሰው መተባበር ሕንፃ ጋ ይሰለፋል።
የካ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት ምንም ሰልፍ የለም። ሌላው ልዩነት ደግሞ ልብ በሉ። መተባበር ሕንፃ ጋ ያሉ ታክሲዎች በአራት ኪሎ አንሄድም እያሉ ጭቅጭቅ ነው፤ ከክፍለ ከተማው ፊት ለፊት የሚነሱት ግን የግድ በአራት ኪሎ ነው የሚሄዱት። ሰው ግን ይሄን አማራጭ አይጠቀምም። በሁለት ወይም ሦስት ደቂቃ የሚደርሰውን ግማሽ ሰዓት ቆሞ ይሰለፋል። እንዲህ ነን እንግዲህ! የግድ ሰው የበዛበት ብቻ ነው ሚታየን። እባካችሁ ሰዎች የተወደደ ነገር ብቻ አንውደድ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ዋለልኝ አየለ