ከሰሞኑ የበርሃ ገነት በመባል በምትታወቀው ድሬዳዋ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የነጻ ንግድ ቀጠና ተቋቁሟል። በነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ አምራች ፋብሪካዎች ለምርት አገልግሎት የሚጠቀሟቸውን ግብዓቶች ያለምንም ቀረጥ፣ የኮታ ገደብ፣ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ… ወዘተ ከውጭ አገራት እንዲያስገቡ የሚፈቅድ አሰራር እንደሚኖር መረጃዎች ያመላክታሉ።
የነጻ ንግድ ቀጠናው መከፈት ዓላማዎች፤ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) መሳብ፣ የኢኮኖሚ መነቃቃትን በማምጣት የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አንድ ውጤት የሆነውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማስገኘት፣ በከፍተኛ ወጭ ተገንብተው በቂ አምራች መሳብ ያልቻሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ሥራ ማስገባት ናቸው።
የነጻ ንግድ ቀጠና ዞን አይነቶች ከአገር አገር የሚለያዩ ሲሆን፤ በዋነኛነት በሦስት መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት ነው። የመጀመሪያው የአምራች ዘርፉን ይመለከታል፤ ይህም ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርት ወይም ከተመረተ በኋላ ኤክስፖርት የሚያደርገው ነው።
ሁለተኛው በአስመጪና ላኪ ድርጅቶች ላይ የሚያተኩር ይሆናል፤ ይሄ ደግሞ ጥሬ ዕቃና አላቂ ዕቃ አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ ዕቃዎችን በማምጣት በቀጣናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀናብሩበት እንዲሁም መልሰው ወደ ውጭ አገሮች የመላክ ሥራዎች የሚያከናውኑበት ነው። እንዲሁም ሂደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥበትም ነው።
ከእነዚህ በተጨማሪም በቀጣናው የሚሰጠውን አገልግሎቶች የሚያቀላጥፉ የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የደረቅ ጭነትና የምክር አገልግሎቶች በቅንጅት ይሰጥበታል፡፡
በነፃ የንግድ ቀጣናው የአገሪቱ የጉምሩክ ሥርዓትና አጠቃላይ ሕጎች ልማቱን ለማሳለጥ በሚያስችል ሁኔታ ላልተው የሚተገበሩበት ነው፤ በዚህ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገቡ አምራቾች ከነፃ የንግድ ቀጠናው ሳይወጡ የምርት ግብአቶችን ማግኘት የሚያስችላቸውም ይሆናል። ከነፃ የንግድ ቀጠናው ውጪ የሚያመርቱ ኩባንያዎች በግብዓትነት የሚጠቀሟቸውን ያላለቁ ምርቶች ከውጭ ሲያስገቡ እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው ቀረጥና ታክስ በነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ ተግባራዊ የማይደረግ በመሆኑ የምርት ወጪ የሚቀነስ ነው።
ይህም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲገቡ ትልቅ ብርታት የሚሰጥ እንደሚሆን ይታሰባል። በመሆኑም ነፃ የንግድ ቀጣና መቋቋም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ከዚያው ጎን ለጎንም የውጭ ምንዛሬ፣ የኤክስፖርት ዕድገት፣ የኤክስፖርት ምርት ስብጥር ከማሳደግ በሻገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨሰትመንትን በመሳብ ረገድ የሚጫወተው ሚና በትልቁ የሚነሳ መሆኑ ይብራራል፡፡
የመንግሥት ገቢ በማሳደግ ረገድም የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል የሚባለው የነፃ ንግድ ቀጣና እንቅስቃሴ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የሠራተኞች ክህሎትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። በተጨማሪም የነፃ ንግድ ቀጣናው የሚመሠረትበት አካባቢን ወይም ቀጣናን በማልማትና በማሳደግ ረገድ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑም ይገለጻል፡፡
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የብሔራዊ ጥራት መሰረተ ልማት ማረጋገጫ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ነጻ የንግድ ቀጠናን አስመልክተው እንዳሉት፤ ነጻ የንግድ ቀጠና ማለት በአገሪቱ ያሉ ወይም ደግሞ ከዚህ ቀደም ሲሰራባቸው የነበሩ የንግድ ህጎች የማይመለከተው ሆኖ ለብቻው የተለየ አሰራርና የንግድ ማዕቀፍ ተበጅቶለት በአንድ ቦታ የሚከወን የንግድ ሥርዓት ነው፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠና ዓለም አቀፍ የንግድ ህጎች የሚደግፉትና ሌሎች አገራትም ተግባራዊ እያደረጉት የሚገኝ ነው። መንግሥት በሚፈልገው ቦታ ላይ በተለይም ከትራንስፖርትና ከሎጅስቲክስ እንዲሁም ከደረቅ ወደብ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ቦታው የሚመረጥበት የራሱ መስፈርት አለው። ይህን መስፈርት መሰረት በማድረግም የራሱ አጥር ኖሮት የተከለለ ቦታ ይኖረዋል። በዛ ቦታ ላይ የሚስተናገደው ንግድ ማንኛውም በአገሪቱ ያሉ የንግድ ህጎች የማይገዙትና ቀለል ባለ ሁኔታ የሚስተናገድ የንግድ አሰራር ነው፡፡
ከሰሞኑም በድሬዳዋ ከተማ በሙከራ የተጀመረው ነጻ የንግድ ቀጠና ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ፤ ከአዋጅ ጀምሮ መመሪያና ፖሊሲ፤ እንዲሁም ራሱን የቻለና ቀጠናውን የሚቆጣጠር ተቆጣጣሪ ያለው ሆኖ የሚደራጅ ነው። ይህ በአንድ ቦታ የተከለለና የንግድ ሥርዓቱ ከተለመደው የንግድ ሥርዓት በተለየ መልኩ የሚከወነው ንግድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ነገር ግን የተለየ ዞን እንዳለ ተደርጎ የሚወሰድ የንግድ ቦታና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ነው ብለዋል፡፡
በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የተለያየ ነገር ማስቀመጥ ይቻላል የሚሉት አቶ እንዳለው፤ በአንድ አገር ውስጥ በተወሰነ ቦታ ተለይቶ የሚከወን ንግድ እንዳለ ሁሉ፤ መጠነኛ የሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎችም ይሠሩበታል ሲሉ ያብራራሉ። ለአብነትም መልሶ የማሸግና አሸጋው ከተከናወነ በኋላ የጽሁፍ መግለጫ ምርቱ ላይ ማድረግ፤ የጥራት ቁጥጥር ሥራና ሌሎችም ሥራዎች የሚከወኑበት ሲሆን በጥቅሉ አምራችነት፣ የንግድ ሥራ እና የሎጅተስቲክስ እንቅስቃሴ የሚደረግበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች የንግድ ሥራዎች የሚከወንበት እንደሆነ ያብራሩት አቶ እንዳለው፤ በነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የነጻ ንግድ ቀጠናው ተቆጣጣሪዎች፣ አስተዳደሮችና ከውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ይኖራሉ፤ ለእነዚህ አካላትም አግባብነት ያለው የሆቴል፣ የመዝናኛ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ አካለትና ሌሎች የንግድ ሥርዓቶች በአካባቢው ይኖራሉ።
ነጻ የንግድ ቀጠናው የንግድ ነክ ህጎች ተፈጻሚ የማይሆንበት ቦታ እንደመሆኑ በእጅጉ ተመራጭ የሚያደርገው ነው ያሉት አቶ እንዳለው፤ የተለያዩ ማበረታቻዎችም የሚሰጡበት እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ መንግሥት ይህን ነጻ የንግድ ቀጠና ተፈጻሚ ሲያደርግ ሁለት ነገሮችን ለማትረፍ ነው። አንደኛው አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የወጪና ገቢ ንግዱን እሴት በመጨመር ወጪ ቆጣቢና ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረግ ነው። ስለዚህ መንግሥት በነጻ የንግድ ቀጠናው ምክንያት በወጪና በገቢ ንግዱ ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።
ቀደም ሲል በአገሪቱ የኢንዱስትሪዎች ፓርክ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አቶ እንዳለው ይናገራሉ፤ ፓርኮቹ በአብዛኛው ወደ ሥራ የገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኙት ሼዶች ወደ ሥራ የገቡት ውስን መሆናቸውን ይገልጻሉ። ነጻ የንግድ ቀጠናው በዚህ ቦታ ሲጀመርም ብዙ ነጻ ሼዶች መኖራቸው አንዲሁም በዋናነት ደግሞ በአቅራቢያው የደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጠት የሚችል ትልቅ መሰረተ ልማት በመኖሩ እንደሆነም ያብራራሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስ የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች በመኖራቸው ምክንያት ነው። አንደኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፤ ንግድን ለማስተዋወቅና ከፍተኛ ቁጥር ላላው የአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው። ሌላው የወጪ ንግዱን በከፍተኛ መጠን ይጨምራል ተብሎ ይታሰባል። በተለይም በምርቶች የእሴት ሰንሰለት ላይ ትስስርን ያመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በእሴት ሰንሰለት ትስስሩም ጥሬ ዕቃውን የሚፈልግና በከፊል ያለቀለት ምርትን በማምጣት እዚሁ በአገር ውስጥ ተጠናቅቆ የሚሄድበት ሁኔታ ይኖራል። ይህም ከተለያዩ አገራት ጋር ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የተለያዩ አይነት ምርቶችን በማምረት ኢኮኖሚ ውስጥ በአይነት ስብጥር ሊያመጣ የሚችል እንደሆነ አብራርተዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሞላ አለማየሁ፤ ነጻ የንግድ ቀጠናን ምስራቅ አፍሪካን በአብነት ወስደው ያብራራሉ። ምስራቅ አፍሪካን እንደ አንድ በማየት ከምስራቅ አፍሪካ የሚገቡና የሚወጡ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የሚወጡ ምርቶችን በአንድ ማስተሳሰር የሚችልና ለኢንፖርት ኤክስፖርት ንግዱ የተለየ አስተዳደር ያለውና የተቀላጠፈ የንግድ ሥርዓትን ማሳለጥ የሚችል እንደሆነ ያስረዳሉ።
እንደሳቸው ገለጻ፤ አንዳንድ ምርቶች ከቀረጥ፣ ከኮታና ከታሪፍ ነጻ የሆኑ ንግዶች አሉ። እነዚህን ዕድሎች ለመጠቀም ደግሞ ነጻ ንግድ ቀጠና ትስስር አስፈላጊ ነው። ከማን ጋር ምን አይነት የንግድ ስምምነት አለ የሚለው ተለይቶ ለተግባራዊነቱም የራሱ የሆነ ስትራቴጂ መንደፍ፣ ፕሮግራምና ቦታ በማዘጋጀት የሚከወን የንግድ አይነት ነው።
በኢትዮጵያ ለነጻ የንግድ ቀጠና ትስስሩ አሁን የተመረጠችው ድሬዳዋ ከተማ ምቹ እንደሆነች ዶክተር ሞላም ጠቅሰው፣ ድሬዳዋ አብዛኛው የአገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ የሚተላለፍባት ብቸኛዋ ቦታ ናት ይላሉ፤ በተለይም የወጪ ንግድ የሚካሄደው በድሬዳዋ ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉንም ንግድ በዚሁ ቦታ ላይ ማካሄድ መጨናነቅን ይፈጥራል። ኢኮኖሚው እየሰፋ ሲሄድ የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመቅረፍ ነጻ የንግድ ቀጠና ትስስርን መፍጠር ተገቢና ወሳኝ ነው ይላሉ።
ነጻ የንግድ ቀጠና ትስስር በአብዛኛው ጎረቤት ከሆኑ አገራት ጋር የሚደረግ የንግድ ስምምነት ነው የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ሌሎች አገራትን ሆኖ ማገልገል መቻልንም የሚጨምር እንደሆነ ነው የሚናገሩት፤ ለአብነትም ወደ ሶማሊያ የሚላክ ምርት ካለ፤ ልክ እንደ ሶማሊያ ሆኖ ማገልገል የሚያስችልና ሶማሊያ ላይ ባለው ነገር ኢትዮጵያ ላይ ማካሄድ፤ ኢትዮጵያ ላይ ባለው ነገር ደግሞ ሶማሊያና ኬኒያም ማካሄድ መቻል ማለት ነው። ባጠቃላይ በመሀል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በማስወገድ የተቀላጠፈ የንግድ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠና ከተለመደው የወጪ ገቢ ንግድ ምን የተለየ ነገር አለው ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ሞላ ሲመልሱ፤ አሁን ላይ ያለው የወጪ ገቢ ንግድ ሁሉንም ያለ ልዩነት ማስተናገድ የሚችል እንደሆነ በመጥቀስ፣ ይህ ደግሞ ውጤታማነትን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል ነው የሚሉት። ነገር ግን ነጻ የንግድ ቀጠና ከማን ጋር ምን አይነት የንግድ ስምምነት አለን፤ እንዴትስ ነው የምናስተናግደው የሚለውን በትክክል ለይቶ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በፍጥነት የሚተገበርና ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል ነው ብለዋል።
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፤ ማንኛውንም ወይም ደግሞ የቀረበውን ነገር ሁሉ ያለ ልዩነት ከማስተናገድ ይልቅ በተመረጡና በተወሰኑ ነገሮች ላይ መሰረት አድርጎ ማን ነው፤ ከየት መጣ፤ ምን አይነት ስምምነት አለን፤ የሚሉ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ ከገቢ ኮታና ታክስ ጋር ምን ስምምነት አለ ብሎ ማስተናገድ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚችል ነው። የተቀላጠፈ የንግድ እንቅስቃሴን ከመፍጠሩ በተጨማሪም ደንበኛን ለይቶ በአግባቡ ማስተናገድ የሚያስችል በመሆኑ የደንበኛን ቅሬታ በመፍታት እር ካታን ይጨምራል፡፡
የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠናን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ነጻ የንግድ ቀጠናው የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። ሌሎች ሀገሮች ነጻ የንግድ ቀጠና ከፍተው የእድገታቸው አጋዥ አርገው መጠቀም ከጀመሩ ብዙ አመታትን አስቆጥረዋል፤ እኛም ነጻ የንግድ ቀጠና መክፈታችን እድገታችንን ለማሳለጥ ያስችለናል ሲሉ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና መሠረት እያጸኑ ለመሄድ መንቃት እና አዳዲስ አሰራር መጀመር አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ ነፃ ቀጣናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመጣው አለም አቀፍ የንግድ ትስስር ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣናው የአገሪቷን የወጪ እና ገቢ ንግድ ስርዓት የሚያዘምን ከመሆኑም በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በተለይ በግብርና ዘርፍ ትልቅ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። የተገኘው ውጤት የበለጠ እንዲያድግ ነጻ የንግድ ቀጠናው ወሳኝ እንደሆነና ከድሬዳዋ በተጨማሪ በሌሎች የአገሪቱ የንግድ ኮሪደሮችም ነጻ የንግድ ቀጠናው አዋጭነት እየታየ እንደሚስፋፋ ነው ያመላከቱት።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፓሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለነጻ ንግድ ቀጠናው የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች የማሟላቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፤ የሕግ እና የአሰራር ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 /2014