አረንጓዴ አሻራው የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት በአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከሏ ስኬታማ ውጤት መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡ የተተከሉ ችግኞች የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቋቋምና የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ለውጥ እያመጡ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ያስገኘችው ውጤት ስኬታማ ነው፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ውጤት የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተው፤ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በፍራፍሬ ችግኞች ላይ ማተኮር ይኖርብናል ብለዋል፡፡
‹‹ከልማት ስራችን የሚያስቆመን ምንም ነገር የለም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ ጥረት እያደረግን እንገኛለን ፤ የምናሳካው ነውም ብለዋል፡፡
በቀጣይ የአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለገበያ በሚውሉ ችግኞችና ጥራት ላይ በማተኮር ስንዴ ብቻ ሳይሆን ወይንና ሻይ ቅጠል የመሳሰሉ ምርቶችን በማምረት በስፋት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል
በጥቂት ሚሊዮኖች ችግኝ መትከል እንደ ድል በምትቆጥር ዓለም ላይ በአራት ክረምት 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ማሳካት እንደሚቻል አሳይተንበታል ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፃ፤ አረንጓዴ አሻራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ እድሎችን ፈጥሯል። አንደኛ በትልቁ አስበን ከተባበርን በትልቁ ማሳካት እንደምንችል ምስክር ሆኖናል፤ ሁለተኛ ለብልጽግና መሠረት የሚሆን ባህል ፈጥረናል::
ችግኝ የመትከል ባህል ሲውል ሲያድር በምግብ ራሳችንን እንድንችል፣ ግድቦቻችን ዘላቂ ዝናብ እንዲያገኙ፣ ለም አፈራችን እንዳይሸረሸር እንደሚያደርግም ገልጸዋል::
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 20 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል::
በአራተኛው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም እስካሁን ሰባት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል:: ይህም የሕዝብ ተሳትፎ ያስገኘው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል::
በአሁኑ ጊዜ ያልተተከሉ አምስት መቶ ሚሊዮን ችግኞች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ዝናብ በሚጀምርባቸው አካባቢዎች የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚተከሉም ጠቁመዋል :: በቀጣይም ችግኝ የመትከሉ ባህል ሰርፆ የዘወትር ተግባር እንዲሆን ይሰራል ብለዋል::
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ነሀሴ 9 ቀን 2014 ዓም