
አዲስ አበባ፡- ብልጽግና ፓርቲ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት በመጀመሩ ለመላ ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡
ፓርቲው ፣ የኢትዮጵያዊነታችን ዓርማ የጋራ ጥረታችን አሻራ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ ተርባይን ሃይል ላመነጨበት ለዚህ ታሪካዊ ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብሏል።
“ስለኢትዮጵያችን ብልጽግና የጋራ ራዕይ ሰንቀን በጋራ ጀመርን፣ ውጣ ውረዱን ሁሉ በጋራ ተጋፈጥን፤ ያሰብነውን ከማሳካት ማንም እንደማያስቆመን በተግባር አሳየን” ሲልም በማህበራዊ ትስስር ገጹ መልዕክቱን አጋርቷል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በአንድነት ከቆምን ማንኛውንም ፈተና አሸንፈን በድል እንደምንሻገር ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ህያው ምስክራችን ነው ሲልም ነው ፓርቲው የገለጸው።
ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፕሮጀክቱ ለዛሬው ስኬት እንዲበቃ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በሃሳብ አሻራ ማኖራቸውን የገለጸው ፓርቲው፤ እንኳን የልፋታችሁን ዋጋ ለማየት በቃችሁ ብሏል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ሀብት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነታችንና የሀገራዊ ክብራችን መገለጫ አርማ ነው፤ ልፋታችሁ ፍሬ እያፈራ ይቀጥላልም ብሏል በመግለጫው፡፡ የዛሬው ስኬትና ድል የኤሌክትሪክ ሃይል ብቻ ሳይሆን የአንድነትን ሃይል ይጨምራል ሲልም ገልጿል።
የሕዳሴን ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ አጠናቀን በህብረ ብሔራዊ አንድነት በስኬት ጎዳና እንደምንገሰግስ በዛሬው ድል አረጋግጠናል ያለው ፓርቲው ፤ ፈተናዎችን ሁሉ በጋራ እያሸነፍን እንሻገራለን ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግናም እውን እናደርጋለን ሲልም መልዕክት አስተላልፏል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014