ቤተሰባቸው በመርካቶ እና በሐረር የታወቁ ነጋዴዎች ናቸው። የሐረሩ ሚሊየነር እየተባሉ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ። በንግድ ህይወታቸው ከጨርቃጨርቅ ምርቶች ጀምሮ እስከ መስታወት እና መድሐኒት ንግድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በዘለቀ የአስመጪነት ስራ ተሳትፈዋል። አሁን ዕድሜያቸው ሰማንያዎቹ ውስጥ ቢሆንም የጥንቱንም ስራቸውን አልረሱትም። እንዲያውም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሆኖ ይሰማኛል ይላሉ።
ከዘራቸውን ይዘው ሲንቀሳቀሱ እርጅና የተጫጫናቸው ቢመስሉም ወደቢሯቸው በሚያስገቡ ከ25 በላይ ደረጃዎች በደቂቃዎች ውስጥ ተረማምደው ሲያልፉ ጥንካሬያቸው ያስገርማል። ስራቸውን ለልጆቻቸው አስተላልፈው እርሳቸው በበላይ ጠባቂነት የሚመሩት ድርጅት ቤከር አጠቃላይ ንግድ ድርጅት ይባላል።
የሐረሩ አዛውንቱ በጠዋት ነው ከቤታቸው የሚወጡት። በአዲስ አበባ በተቋቋመው ድርጅታቸው እስከ ግማሽ ቀን ድረስ የልጆቻቸውን ስራ ይመለከቱ እና ማስተካከያ የሚያስፈልገው ላይ አስተያየት ይሰጣሉ። በቀሪው ጊዜያቸው ወደቤታቸው ይመለሳሉ።
አቡበከር አህመድ ቱሬ ይባላሉ የዛሬው የሲራራ እንግዳችን። በፍቅርና ሰላም ተምሳሌትነቷ በምትታወቀው ሐረር ከተማዋ ቡዳ በር አካባቢ ነው ውልደት እና ዕድገታቸው። በሐረር ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና ስዊዲሽ ሚሽን ሉትራን ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በትምህርት ወቅት ቅዳሜና እሁድን በወንድማቸው የጨርቃጨርቅ ሱቅ በረዳትነት እየሰሩ የንግድን ጥቅም በልጅነታቸው ተረድተዋል።
ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ ወዲያውኑ በመንግስት ስራ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ከ1950 ጀምሮ ደብረብርሃን እና በቀድሞው የከፋ ጠቅላይ ግዛት ጨና በተባለች ከተማ በመምህርነት እየተዘዋወሩ መስራት ጀመሩ። በጨና ከተማ የነበረው አገርን የማገልገል ተግባር ግን በመካከሉ ከአካባቢው የወረዳ እና የቀበሌ አስተዳደሮች ጋር ግጭት ውስጥ ከተታቸው።
የአስተዳዳሪዎች ቀጠሮ ማብዛት እና የአሰራር ማጓተት ያበሳጫቸው ነበር። ከሁለት ዓመታት የመምህርነት ቆይታቸው በኋላ በወቅቱ ከፍተኛ የነበረውን አንድ መቶ ብር ወርሃዊ ክፍያቸውን ትተው ወደ ትውልድ መንደራቸው ተመለሱ። ከዚህ በኋላ በደመወዝ ተቀጥሬ መስራት የለብኝም ብለው የወሰኑት አቶ አቡበከር ድሬዳዋ ወደሚገኘው ወደ ታላቅ ወንድማቸው አቀኑ።
ወንድማቸው በምስራቋ የንግድ ማዕከል ድሬዳዋ የህንጻ መሳሪያ ንግድ እየከወኑ ስለነበሩ ከእርሳቸው ጋር ተቀላቀሉ። ድሬዳዋ ላይ አንድ ዓመት እንደቆዩ ግን የህንጻ መሳሪያው ንግዱን ወደአዲስ አበባ ለማስፋፋት መጡ። በአዲስ አበባ መርካቶ ከወንድማቸው ጋር ሃጂ ቱሬ የሚል የህንጻ መሳሪያ እና ብረታብረት ሱቅ ከፍተው መስራት ጀመሩ። በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እቃዎችን ከውጭ አገራት ያስመጡ የነበሩት ጣልያኖች፣ ህንዶች እና አረቦች ነበሩና እርሳቸው ይህን የአስመጪነት ንግድ ሰብረው ለመግባት አስበዋል። በወቅቱ አንድ የህንጻ መሳሪያ ምርት ላይ ያዩትን የውጭ አምራች ኩባንያ አድራሻ ይይዙና ዕቃ እንዲያስመጡላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈው በፖስታ ቤት ይልካሉ። በጊዜው አንድ ደብዳቤ ተልኮ ኩባንያዎቹ ጋር የሚደርሰው በ20 ቀኑ መሆኑን ያስታውሳሉ። ኩባንያው ደግሞ ዕቃው አለኝ ወይም የለኝም የሚል ምላሽ ለላከለት ሰው ለማድረስ ሌላ 20 ቀን ይፈጃል። ደብዳቤው ለተፈለገው አካል ካልደረሰ ደግሞ ጊዜ ጠብቆ ሌላ ደብዳቤ መጻፍ ያስፈልጋል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ጥያቄያቸውም ከጊዜያቶች በኋላ በጎ ምላሽ አግኝቶ ከቻይና ቀጥሎም ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች የመጡ ምርቶችን በአሰብ በኩል ማስመጣት ጀመሩ። የመጀመሪያውን እቃ ለማስመጣት ደብዳቤ በመጻጻፍ ብቻ አንድ ዓመት መፍጀቱን ያስታወሳሉ። ይህ ሁሉ እንዲሆንና ለመጻጻፍ ስልቱ የመምህርነት ሙያቸው እንደጠቀማቸው ቢያውቁም ስራው ግን አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ይናገራሉ። አንድ ምርት ከቻይና ለማስመጣት በመርከብ ስድስት ወር ይፈጅ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የአስመጪነት ዘርፉን ለመቀላቀል ካላቸው ጉጉት የተነሳ የሚፈልጉት ምርት ላይ ያለውን አድራሻ ይዘው ደብዳቤ መጻፉን አያስተጓጉሉም ነበር። በፖስታ በመጻጻፍ ከህንጻ መሳሪያ እቃዎች ባሻገር የእህል ወፍጮ እና ብረታብረቶችን ማስመጣት ችለዋል። በወቅቱ ገበያውን ተቆጣጥረው የነበሩትን የውጭ ሀገር ዜጎች ለማሸነፍ ዋጋቸውን ቀንሰው ብዙ ገበያ ያመጡ ነበር። እንዲህ እንዲህ እያሉ ሲሰሩ ትዳር መጣና ልጆች ተወለዱ። በኋላም ከወንድማቸው ጋር ያለውን ንግድ ትተው በመርካቶ አዳራሽ ውስጥ ለብቻቸው ቢሮ ከፈቱ።
መጠነኛ እቃዎችን ለብቻቸው ማስመጣት የሚያስችል ገንዘብ በእጃቸው ገብቷል። በመሆኑም ከሮማኒያዎች ጋር በመደራደር የአምስት መቶ ሺ ብርድልብሶችንና አንሶላዎችን አስመጡ። ያስመጡትንም ምርት ለኢትዮጵያውያን የጠፈር አልጋ በሚሆን ቁመትና ወርድ ነበርና ሌሎቹ ነጋዴዎች የሚያመጡትን ረጃጅም ብድርልብስ ትቶ ገበያው ወደእርሳቸው ይጎርፍ ጀመር። ከሮማኒያዎቹ ጋር ንግዱ ስለተመቻቸላቸው ሳሙና እና ፓስታ እያስመጡ መነገድ ቀጠሉ።
የንግድ ግንኙነታቸው በአብዛኛው ከቻይና፣ ከሮማኒያ እና ሌሎች የወቅቱ ኮሚኒስት አገሮች ጋር እንደነበር የሚያስታ ውሱት አዛውንቱ አቶ አቡበከር ይህም በሌሎች ነጋዴዎች ያልተያዙ አገራትን ምርቶች እንዲያመጡና ትርፋማ እንዲሆኑ የዘየዱት ብልሃት መሆኑን ይገልጻሉ። እስከ ደርግ የስልጣን መባቻ ድረስ ደብተር፣ ብርጭቆ እና ሌሎች በርካታ ምርቶችን በደብዳቤ እየተጻጻፉ ማስመጣታቸውንም ያስታውሳሉ።
በአንድ ወቅት ያጋጠማቸው የንግድ አደጋ ግን በአስመጪነታቸው ላይ ትልቅ ኪሳራ እንዳደረሰ አይዘነጉትም። ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ኢንሹራንስ እንኳን ባልተጀመረበት ወቅት ከውጭ አገር ያዘዙት 600 ሳጥን መስታወት በመርከብ ሲጓጓዝ ባህር ውስጥ የመስጠሙ ወሬ ጆሯቸው ይደርሳል። በአደጋው ቢያዝኑም ተስፋ ቆርጠው ስራቸው መቆም እንደሌለበት የተረዱት ልበ ብርቱ ሰው ግን በንግድ ህይወት የሚያጋጥም መሆኑን አምነው ለሌላ ስራ ራሳቸወን አዘጋጁ። ሴራሚክ እና ሌሎች እቃዎችን በመነገድ የከሰሩበትን ገንዘብ በጥቂት ዓመታት ሊተኩ ችለዋል።
ደርግ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ የአስመጪነት ስራውን በመቆጣጠሩ ስራው ሁሉ ባለበት ቆመ። መንግስት ብሔራዊ ባንክ አጠገብ የእራሱ የሆነ አስመጪ ድርጅት በመክፈቱ የውጭ ዜጎችም ከስራው ወጡ። አቶ አቡበከርም ሱቃቸው ባዶ ሆኖ ገበያው ራቃቸው። መንግስት የሚያስመጣውን መስታወት እየተረከቡ ለመሸጥ ቢሞክሩም ገበያው እንደወትሮው አልሆነላቸውም። ልጆቻቸውንም በውጭ አገራት ለትምህርት ልከው አልፎአልፎ በሚገኘው ገበያ ላይ ብቻ ተወስነው ይሰሩ ነበር።
ይህን የተረዱት የንግድ ሰው ታዲያ ከአንድ ጣሊያናዊ ላይ የፊያት መኪና መለዋወጫ ሱቅ በ120ሺ ብር ገዝተው ወደሌላ ንግድ ተሰማሩ። ሰንጋ ተራ አካባቢ ከጥንቶቹ የተሽከረካሪ መለዋወጫ አቅራቢዎች መካከል የሆነው ሱቃቸውን በባለቤታቸው ስም አድርገው መጠነኛ እቃዎችን ደግሞ በመርካቶው ቢሯቸው አማካኝነት ይነግዱ ነበር።
በወቅቱ ደርግ ለተሽከርካሪዎች የሚሆን መለዋወጫ እጥረት በኢትዮጵያ መኖሩን በመረዳቱ በጥብቅ ቁጥጥር የመለዋወጫ አስመጪነትን ይፈቅዳል። በዚህ ዕድል ከጣሊያን የፔጆ እና የፊያት መኪናዎችን በመጠኑም ቢሆን ማስመጣቱን ጀመሩ። በባለቤታቸው ስም በከፈቱት የመለዋወጫ ሱቅ ለበርካታ ተሽከርካሪዎች የሚሆን መለዋወጫ በማቅረብ ድጋሚ ገበያቸው ማንሰራረት ጀመረ።
ለ18 ዓመት የመለዋወጫ ንግዱ ላይ ከሰሩ በኋላ ደርግ ከስልጣን ሲወርድ ደግሞ የአስመጪነት ስራው ለማንኛውም ሰው ክፍት ሆነ። በዚህ ወቅት የመለዋወጫ ንግዱን ጋብ አድርገው ወደመድኃኒት ንግድ ለመሰማራት ወሰኑ። በእድሜያቸው ምንም አይነት የመድኃኒት አይነት ወስደው የማያውቁት እና ስለህክምናው በቂ ዕውቀት ያልነበራቸው አቶ አቡበከር አዲሱ ንግዳቸው ግን እንደሚያዋጣ ቀድመውኑ ጥናት አድርገዋል። አንድ የፋርማሲ ባለሙያ በመቅጠር የመድሃኒት ዝርዝሩን እና ተፈላጊው እንክብል አይነት በመጀመሪያ ለዩት። ከዚያም በመንግስት የውጭ ምንዛሬ እድል ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር የመድሃኒት አስመጪነቱ ተጀመረ።
በወቅቱ ገበያው አስተማማኝነቱ ቢያጠራጥርም ቀስበቀስ ግን የሚያስመጡትን መድኃኒቶች የሚቀበሉ ፋርማሲዎች ቁጥር በእጅጉ አየለ። ከማስታገሻ መድኃኒት እስከ ውድ እና በጥብቅ የሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጡትን ያስመጣሉ። የግብርና እና የኢንዱስተሪ ኬሚካሎችንም ጨምረው 200 አይነት ምርቶችን ለንግድ ያቀርባሉ። ገበያው እየደራ ሲመጣም ውጭ አገራት የነበሩ ልጆቻቸው መጥተው ቤከር አጠቃላይ ንግድ የተሰኘው ድርጅት ውስጥ እንዲሰሩ አድርገዋል።
በአሜሪካን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ልጆቻቸው ወደኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል። አንዱ በፋርማሲስት ሌላው በጥብቅና ሌሎቹም የኮምፒውተር ባለሙያ ቢሆኑም የአባታቸውን ፈለግ በመከተል ንግዱንም እያቀላጠፉት ይገኛሉ። በየዕለቱ የእርሳቸው ምክር እና ተግሳጽ የማይለያቸው ስድስት ልጆች ንግዱን በሚገባ እየመሩት ስለመሆኑ አቶ አቡበከር አሁን ብዙ ጊዜያቸውን በስራ ላይ አያሳልፉም።
የመድኃኒት ንግዱ የሚከናወንበት ባለሶስት ወለል ህንጻ ልደታ አካባቢ የገነቡት አቶ አቡበከር አሁን የበላይ ጠባቂ ሆነው ድርጀቱን ይከታተላሉ። የመድኃኒት ንግዱ በዓመት እስከ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያስመዘገበበት ጊዜ ነበር። አሁን ደግሞ በየወሩ አርባ ሚሊዮን ብር ሽያጭ እንዳለው ይናገራሉ። አጠቃላይ ሀብታቸው ደግሞ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ደርሷል።
120 ሰራተኞችን ቀጥሮ በሚያስተዳድረው ድርጅታቸው ውስጥ እንደአባት የሚታዩት ሰው ገበያ ውስጥ አዲስ ዕቃ አምጥቶ ለማላመድ በየጊዜው ፈተና ይሆንባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ሁሉንም ግን «በጥንካሬ አልፈዋለሁ» በሚል ስሜት ውሰጥ ሆነው በበቃት እንደተሻገሩት የንግድ ህይወታቸውን ስኬት ምስክር አድረገው ይናገራሉ።
«ምንም አይነት የመድኃኒት እውቀት ሳይኖረኝ በዘርፉ ስኬታማ አስመጪ ሆኛለሁ» የሚሉት አዛውንቱ፤ ትምህርት ደግሞ የበለጠ ንግዱን እንደሚያሳድገው ይናገራሉ። እንደ አዛውንቱ ከሆነ፤ ነጋዴ ለመሆን ግን ዋናው ጉዳይ ገበያውን ማወቅ እና የሚሸጠው ወይም ለተገልጋይ የሚቀርበው ነገር አዋጭ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ነው። በተጨማሪ በመሃል የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እያለፉ በሃቅ መስራት ያስፈልጋል። እነዚህ ነገሮች ከተሟሉ ነግዶ ማትረፍ፣ ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል ያምናሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011
በጌትነት ተስፋማርያም