የተወለደው በ1955 ዓ.ም ነው። እሱ ከተወለደ ከ3 ቀን በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ተገደሉ። አባቱ አቶ አጥናፉ መንገሻ የጆን ኤፍ ኬኔዲ አድናቂ ስለነበሩ ለእሱ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የልጃቸውን ስም ኬኔዲ እንዳሉት በአንድ ወቅት ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ተናግረው ነበረ። ሌሎች ደግሞ ስሙን ያወጡለት አያቱ ናቸው ይላሉ። የሆነ ሆኖ አባቱ ስማቸው አቶ አጥናፉ ይሁን እንጂ እሱ ግን የሚጠራው በአያቱ ስም ነው። ያደገውም እሳቸው ጋር አዲስ አበባ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ነው። አዲስ አበባ ያደገው ኬኔዲ የተወለደው አሁን በአፋር ክልል ውስጥ በምትገኘው አሳይታ በምትባል አካባቢ ነው።
ኬኔዲ ወደ ሙዚቃ የገባው አቶ ሳህለወርቅ በሚባሉ ሰው አማካኝነት ነው። አቶ ሳህለወርቅ አዲስ ድምፃውያን ከየስፍራው አስሰው በማግኘት የሚታወቁ የዘመኑ የሶልኩኩ ሙዚቃ ቤት ባለቤት ነበሩ። አስሰው ካገኟቸው እና ወደ ሙዚቃ ካስገቧቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ድምጽ መረዋው እና መልከ መልካሙን ኬኔዲ መንገሻን ነው። የመጀመሪያ አልበሙንም የሰሩለት እሳቸው ናቸው።
ኬኔዲ ፀባየ መልካም በመሆኑ ከሁሉም ሰው ጋር መግጠም እና ወዳጅ መሆን አይከብደውም ነበር። በዚህም የተነሳ እሱን አንድ ቦታ አቆይቶ ስራ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ቀላል አልነበረም። ታላቁ ገጣሚ ይልማ ገ/አብ በአንድ ወቅት ስለ ኬኔዲ ሲናገር ኬኔዲ ከቤት እየወጣ እየሄደ ለስራ አስቸግሯቸው እንደነበር ገልጿል። ስለዚህ መፍትሄ ብለው ያሰቡት አደገኛና ተናካሽ ውሻ ማስቀመጥን ነበር። ኬኔዲን ግን ውሻውም አላገደውም። ጭራሽ ውሻውን አላምዶ እያሻሸ እየዳበሰ ከቤት ሹልክ ብሎ መውጣት ቻለ። ይህ ስለ ኬኔዲ ባህሪ ብዙ ይነግረናል።
ኬኔዲ ደግም ሰው ነበር። በተለይም ለጎዳና ተዳዳሪ ወገኖች የነበረው ፍቅር ጽኑ እንደነበር ሌላኛው ገጣሚና የዜማ ደራሲ አበበ መለሰ ይናገራል። ነገሩን በምሳሌ ሲያስረዳም በአንድ ወቅት ዘፈን ለማስቀረፅ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ የተገኘው ኬኔዲ ቀረፃውን ጨርሶ ለዘፈኑ ይረዳ ዘንድ በሙዚቃ ቤቱ ባለቤት የተሰፋለት የሱፍ ኮቱን አውልቆ መንገድ ላይ ለተቸገረ ሰው ሰጥቶ ይሄዳል። ነገር ግን ምሽቱን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድጋሚ መቀረፅ እንዳለበት ይነገረዋል። ይሄኔ ኮቱ ከየት ይምጣ። ያለው አማራጭ የሙዚቃ ቤቱ ባለቤቱ ኮት መልበስ ነበርና ባለቤትየው የለበሰው ኮት ሰጥቶ ድጋሚ ተቀርጿል። እዚያ ዘፈን ላይ እንዲያውም ኮቱ ሰፍቶት ሲነካካ ይታይ ነበር ይላሉ አንዳንዶች።
ኬኔዲ ድሬዳዋ እና ሀረርን በጣም ይወዳቸው ነበር። በዚህም የተነሳ አዲስ አበባ ነው ሲባል ብዙ ጊዜ መገኛው ድሬዳዋ እየሆነ ብዙ ሰውን ያስገርም ነበር። እዚያ ሆኖም ብዙ ስራዎችን ሰርቷል። ከፍተኛ የሆነ የሞተር ብስክሌት ፍቅር ስለነበረው አዘውትሮ ያሽከረክር እንደነበረ ወዳጅ ዘመዶቹ ይገልፃሉ።
ሌላኛው ተወዳጅ ድምጻዊ ሰለሞን ደነቀ በአንድ ወቅት አንድ ሙዚቃ ሰርቶ ዜማ እንዲይዝለት ኬኔዲን ያስሞክረዋል። ኬኔዲ ግን ሙዚቃውን ወደደው። ራሴ ነኝ ምዘፍነው አልሰጥህም ብሎ የሙጥኝ አለበት ፤ከዛ ኬኔዲ “በመላ ነው” በሚለው የመጀመሪያ አልበም ላይ አካቶ ሰራው ፤ ሙዚቃውም “ውብ እንዳንቺ” የሚለው ነበር።
ማር ወለላ ጣፋጭ አንቺ ውብ ዓለም
ቆንጆ ሸጋ ሎጋ መልከ መልካም ውብ እንዳንቺ የለም
የሕይወቱ የመጨረሻ ዓመት ላይ ኬኔዲ አበበ መለሰን ስለሞት መጫወት እፈልጋለው ፤ እስቲ ድርሰት አዘጋጅልኝ ይለዋል፤ አቤም ቆጣ ብሎ እንዴ አንተ ወጣት ምንድነው ስለ ሞት ምትዘፍነው ምን ይሰራል ብሎ መክሮት ለእርሱ ፋንታ ይሆን ዘንድ” ልሁን ደህና ደህና “የሚለውን ሙዚቃ ሰርተው በመጨረሻ አልበሙ ላይ ተካቶ ወጣ። ይህን አልበም እየሰሩ ግን ድንገት የወጋየው ንጋቱ ሕልፈት ሲሰማ አበበን ራሱ ከባድ የኀዘን ስሜት ያዘው። የተሰማውንም ስሜት በአንድ ሙዚቃ በኩል ሰርቶ ኬኔዲን አዘፈነው። በኋላም ኬኔዲ ከሞተ በኋላ አቤ ላንተም ይሁን…..
ተቸግሬ በሃሳብ ተከፍቼ
ቀረሁ ተረስቼ አስታማሚ አጥቼ
በቁሜ ስሰቃኝ ያልጠየቀኝ
ስሞት ቢያለቅስልኝ ከአፈር አያድነኝ
ኬኔዲም ይኸን አልበም በወጣበት ዓመት ሀምሌ 19 ቀን 1985 ሕይወቱ አለፈ ። ኬኔዲ መንገሻ ከ1979- 1985 በነበሩት ዓመታት “በመላ ነው” (1979) “እንዲያው የሆዴ” (1980)፣ “ቀፎኛል” (1982) “ልሁን ደህና” (1984) እና “እምባ ስንቅ አይሆነኝ” (1985) የተሰኙ አልበሞችን ሰርቷል። በ1981 ከአሰፉ ደባልቄ፣ ከራሄል ዮሐንስ እና ከተሾመ አሰገድ ጋር፣ 1982 ከየሺመቤት ዱባለ ጋር እንዲሁም በ1983 ከብርቱካን ዱባለ ጋር በሕብረት በሠራቸው ስራዎችም በርካታ ተወዳጅ ዜማዎችን ከሕዝብ ጆሮ ማድረስ ችሏል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም