ምድር በረፋዷ ጀምበር ረስርሳለች። ለጸሀይ መውጫ ደረቱን የሰጠው መኝታ ክፍሏ በረፋዷ ጀምበር ግንባር ግንባሩን እየተባለ ቆሟል። መስተዋቱ ላይ ያረፈው የጸሀይዋ ብርሀን ወደ ክፍሉ ተንጸባርቆ ጨለማ ክፍሏን በጠይም ውጋግ ሞልቶታል።
ተኝታለች..አተኛኘቷ ፍትወት ይቀሰቅሳል። አንድ እግሯን አጥፋ..አንዱን ዘርግታ በጀርበዋ ፍስስ ብላለች። የትኛውም ስዕል፣ የትኛውም ምናብ፣ የትኛውም ተፈጥሮ በዛ ጠዋት የእሷን ያክል አይማርክም። ጡቶቿ ከሌሊት ልብሶቿ ተኳርፈው ርቃናቸውን ናቸው። ጥብቆዋን ጥሰው ደረቷ ግድም ላይ አቀርቅረዋል። አተኛኘቷ አለባበሷን አዛብቶት በወናፍ የፋመ የሚመስል እሳታማ ጭኗን ገልጦታል። በዛ ጠዋት ቆሞ ላያት ቀለምና ምናብ የጸነሳት እንጂ በእውን የተኛች ነፍስ ያላት ፍጡር አትመስልም ነበር።
የምስራቅ ደጅ ብርሀናማ ፊቷ የዝምታ ወጀብ ሰፍኖበታል። በዛ ጠዋት አይኖቿ ተከድነው ሲታዩ፣ ከንፈሮቿ ተጋጥመው ሲታዩ አንዳች ስሜትን ያጋባሉ። ቆንጆ ናት..ነፍስ ድረስ ዘልቆ የሚገባ ውበት አላት። የግንቦትን አመል የወረሰ፣ እንደ ብራ ሰማይ የጠራ ገላ ታድላለች። በጸደይ ወራት እንደሚፈካ የሰማይ ርቃን ሴትነቷ እንደዛ ነው። ጥልል..ኩልል ያለ። በዚህ ሴትነት ፊት የሚቆም፣ ይሄን የሴትነት ታቦት ተሸክሞ ነጋ ጠባ ፊቷ የሚቆም አንድ የፍቅር ካህን አለ።
በጽና እጣን አድርጎ ጠዋቷን የሚቀድስ፣ አልጋዋን የሚዞር፣ ሴትነቷን የሚያጥን የፍቅር ካህን። ዳዊት በነካ እጁ፣ ጽና በጨበጠ መዳፉ፣ ሴትነቷ አትሮኖስ ፊት ቆሞ የሚቀድስ የፍቅር ገበዝ። ሱቲ በለበሰ ገላው፣ ካባ ላንቃ ባጠለቀ፣ አስኬማ በለበሰ ሰውነቱ ጠዋቷ ፊት ቆሞ የሚያረምም የፍቅር መናኝ። በዜማና ወረብ፣ በክብር ዝማሜ፣ ጸናጽል ጨብጦ፣ መቆሚያ ከፍ አድርጎ ስለፍቅሯ ማህሌት የሚቆም አበመኔት። አማኝ በሚያሳልሙ እጆቹ፣ መክፈልት በሚባርኩ ጣቶቹ፣ ነውር በሌለው አንደበቱ ፊቷ ቆሞ ተንስኦ የሚል።
አዎ በዛ ሌሊት፣ በዛ ሁናቴ እሷን የሚያይ አንድ እድለኛ ወንድ አለ…ክብሩ የሚባል። ዓለም በዛ ጠዋት በዛ ሁኔታ እሷን ቆሞ እንደማየት ምርጥ ነገር አልሰጠችውም። የህይወቴ ምርጥ የሚለው በዛ ጠዋት፣ በዛ ሁኔታ እሷን ማየት ነው። እዚህ ምድር ላይ በወፎች ዜማ ታጅቦ፣ እሷን በማለዳ መኝታዋ ላይ እንደማየት የሚባርከው የለም። አዲስ ነገሩ ናት..መሽቶ በነጋ ቁጥር ለዓለምም ለእሱም አዲስ ነገርን የሚፈጥርለት አተኛኘቷ ነው..ከልብሶቿ መሀል የተኳረፉት ጦቶቿና..እሳታማ ጭኗ። የትኛውም ሰዐሊ፣ የትኛውም ጥበበኛ እንደ እሷ ውበትና ስሜት የቀላቀለ ስዕል አይስልም።
ነፍሱን በነፍሷ ላይ ጥሎ ወደ ክፍሏ ዘው አለ..በዛ ክፍል ለእሱና ለታሪኩ የሚሆን ብዙ ደስታ አለው። ኒሻን እንደተኛች ነው..አሁንም አልተነሳችም። አብሯት ቁርስ ለመብላት፣ አብሯት ወደ አንድ ቦታ ለመሄድ እሷን መጠበቅ አለበት። እሷን መጠበቅ በምንም የማይለካው የደስታው ሰገነት ነው። እያያት ቆመ፣ በዛ ጠዋት፣ በዛ ሁኔታ እሷን ቆሞ እንደማየት ደስታ የለውም። አንዲትን ውብ ሴት፣ ከውብ አተኛኘትና ከውብ ተፈጥሮ ጋር አዘቅዝቆ ማየት ደስታው ምን ያክል እንደሆነ እሱ ብቻ ነው የሚያውቀው። ከእሷ ጋር ሁሉም ነገር አዲስ ነው። እሷ ጎን ሁሉም ነገር የተለየ ነው። አቤት ሲያፈቅራት..። ወደ አልጋው ጠጋ ብሎ ርቃን ጡቶቿን አለበሳቸው..እሳታማ ጭኗንም።
ከእንቅልፏ ስትነቃ ክብሩን አጠገቧ አገኘችው። ይሄ የምንግዜም እጣ ፈንታዋ ነው። ክብሩን አጠገቧ ሳታገኘው ከእንቅልፏ ነቅታ አታውቅም። እሱን አጠገቧ ስታገኘው ጠባቂ መላዕክቷ እንጂ ባሏ ብቻ አይመስላትም። የክብሩ ሚስት ስለሆነች ራሷን ከሴቶች ሁሉ ትለያለች። ከሁሉም በኋላ ነፍስ አምሳያዋን ካላገኘች ዋጋዋ ምንድነው? ስትል ከእንቅልፍ በነቃ አእምሮዋ ራሷን ትጠይቃለች። የሴት ነፍስ የአባት ነፍስ ብርቋ ነው። የሴት ነፍስ ሁሉን አግኝታ በክብርና በማዕረግ ለመኖር የአባት አይነት ነፍስ ትሻለች።
ከአባቷ ቀጥሎ እንደ አባቷ የሆነላት ወንድ ክብሩ ብቻ ነው። ሴት በባሏ ነፍስ ውስጥ የአባቷን አይነት ነፍስ ስታገኝ ያኔ ሙሉ ትሆናለች። ካጣች ደግሞ ጎደሎ። ሴቶች የሚጎሉት የአባትነት መንፈስ በሌላቸው ጎደሎ ወንዶች እንደሆኑ ታውቃለች። ሚስቶች ዝቅ የሚሉት በባሎቻቸው አናሳ ነፍስ እንደሆነ ይሄንንም ታውቃለች። ክብሩ የአባቷን ነፍስ ተጋርቶ የሚኖር ሰው ነው። ሳታገባ በፊትና አባቷ በሞት ሳይለያት በፊት እንዲህ እንደ አሁኑ መኝታዋ ራስጌ ቆሞ እስክትነቃ የሚጠብቃት እሱ ነበር።
ከዛም በእናቷ ግልምጫ መንቃት ጀመረች። ማታ የባጥ የቆጡን ስትከውን ታመሽና ጠዋት በእናቷ ግልምጫ መንቃት ልማዷ ሆነ። ይሄ አጋጣሚ በህይወት የሌለ አባቷን እንድትናፍቅ ቢያደርጋትም እናቷን ግን ለመቀየም አልቻለችም። ዛሬም ነገም የእናት ነፍስ እግዚአብሄራዊ ነፍስ እንደሆነች ታውቃለች..በምህረትና በመቻል የተሞላች።
‹ይብላኝ ለሚያገባሽ እኔስ እናትሽ ነኝ እችለዋለው› ይሏታል እናቷ..ከንቅልፏ ከቀሰቀሷት በኋላ። ከእናቷ ወቀሳ የአባቷ ዝምታ ሚዛን ደፍቶ በሁሉ ነገሩ ሙሉ የሆነው ክብሩ ላይ ጣላት። ክብሩ ለምን ተኝተሽ አረፈድሽ ሳይሆን ለምን ቶሎ ነቃሽ..ትንሽ አተኚም ነበር ብሎ የሚቆጣት ወንድ ነው። እሷ ተኝታ እሱ ቁርስ መስራትና መልፋትን የሚወድ ባሏ ነው። ይሄ ወንድ የአባቷ የዝምታ ተማጽኖ ከመሆን ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ለማንም ባልተነፈሰችው ዝምታዋ እንዲህ ታስባለች። በክብሩ በኩል እግዚአብሄርን ደግማና ደጋግማ ታመሰግነዋለች።
በጠዋት መነሳት አትወድም…በህይወቷ ሞክራ ያቃታት በጠዋት መነሳት ነው። አቤት የጠዋት እንቅልፍ ስትወድ…ጽድቅ ሰርታ ገነት ብትገባ እንኳን የጠዋትን ያክል የሚመቻት አይመስላትም። ብቸኛ ደስታዋ ጠዋትን ተኝቶ ማሳለፍ ነው። እንደ ስሟ ናት..። ኒሻን የሚለውን ስሟን አያቷ ነው ያወጡላት። ከስሟ መጉደል አትሻም። ለየት ማለት ትወዳለች ለወንድ ልጅ ብቻ አይደለም፣ ለሰው ልጅ ብቻ አይደለም ለዓለምም ሽልማት እንደሆነች ነው የምታስበው።
ክብሩ አጎንብሶ ግንባሯን ሳማት። የመጀመሪያ ሳቋን ሳቀችለት። የመጀመሪያ ነገሯ ሁል ጊዜ የእሱ ነው። ከእሱ አትርፋ ለሌላ የምትሰጠው ሴትነት የላትም። ነፍሷን ነፍሱ ውስጥ አሳርፋ ከአልጋዋ ላይ ብድግ አለች። ሁለቱም ሳያውቁት እየሳቁ ነበር።
ወደ ሻወር ቤት ስታመራ..
ያዘጋጀላትን ቁርስ ለማቀራረብ ወደ ሳሎን አመራ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2014