በተቀመጠበት ትንሽዬ ክፍል ውስጥ የሰኔ ገመገም ይሰማዋል። ጥቁር ደመና ያረገዘ ነፍሰ ጡር ሰማይ በገርባባ በሩ በኩል ያላግጥበታል። ጭር ያለ ጅብማ ዓለም ዝናብን ሊወልድ ከሚያምጥ ሰኔ ጋር አብሮ ያሾፍበታል። ግንቦት አልፎ የሚመጣው ወር ለእሱ የመከራ ወር ነው። ሚያዝያ ሸሸት ሲል፣ ግንቦት ብቅ ሲል ሁሌ እንደሥጋ ነው። ሰኔን አይወደውም..መኖር የሚታክተው፣ ሰው መሆን የሚከብደው ሰኔ ላይ ነው። የምስራቅ ደጅን በጭጋግ ለጉሞ ቀዬውን በቀን ሲያደምነው ተፈጥሮ ትዛባበታለች። ጀምበርን ሰውሮ ምድርን ጽልመት ሲያለብሳት የመኖር ተስፋውን ይነጥቀዋል። እንደ ሰኔ ያላገጠበት ወር የለም። ሰኔን የሚጠላው ከወራት የተለየ ሆኖ ሳይሆን ተፈጥሮ የግፍ ሚዛኗን ወደ እሱ እንድታጋድል እድል ስለሚሰጣት ነው።
በመደዳ ከተሰሩ የቀበሌ ቤቶች ውስጥ በአንዱ ነው የሚኖረው። በአሮጌ ቆርቆሮዎች፣ በአሮጌ ሚስማሮች፣ በአሮጌ ብረቶች፣ በአሮጌ እንጨቶች፣ በአሮጌ ድንጋዮች፣ በአሮጌ ሰሌኖች፣ በአሮጌ አቡጀዴዎች በታነጸች ቤት ውስጥ። ቤቱ የሰኔን ወጀብ፣ የሰኔን ጉርምሩምታ የሚቋቋም ሀይል የላትም። በዚህም አንድ ሶስተኛው የዝናብ ውሃ እሱ ቤት ውስጥ ነው የሚገባው። በዚህም ሰኔን ይጠላዋል።
እንዲህ እንደ አሁኑ ሰኔ ሲያጉረመርም፣ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል ይከፋዋል። መግቢያ ቀዳዳ ያጣል። የጣሪያው ሽንቁሮች በክረምት ዝናብ በበጋ ብርሃን ሳያስተላልፉ ቀርተው አያውቁም። ቤቱ ውስጥ ሆኖ ድህነት በቀደደው የቤቱ ሽንቁር ፀሐይን ከነዘርማንዘሯ አይቷት ያውቃል። እንዲህ እንደ አሁኑ ሰኔ እዬዬ ሲልም ታዝቦት ያውቃል። ድህነት የቀደደው የጣሪያው ላይ ሽንቁር ለኦና ሕይወቱ ብዙ ነገሩ ነው።
አጠገቡ አብራው ለአምስት ዓመት የኖረች፣ ክረምትና በጋውን፣ ብርድና ሀሩሩን አብራው ያሳለፈች ትዋብ የተባለች ድመት አለቸው። እንደ እሱ ሰኔን ተጸይፋ ነው መሰለኝ ኩርምት ብላ ራቅ ብላ ተቀምጣለች። አንዳንዴ ድመት አትመስለውም.. ሰውነቱን በድመት የሰወረ አንድ የሆነ ሀይል አብሮት የሚኖር ነው የሚመስለው። ሁሉ ነገሯ እንደ ሰው ነው..በማሰብና በማቀድ የሚሆን። የሰሞኑ ባህሪዋ ግን ተቀይሮበታል..ምግብ መምረጥ ጀምራለች፣ እንደ በፊቱ ስታየው አይደለም ሲጠራት ተንደርድራ ጭራዋን እየቆላች መተሻሸት ትታለች። ይባስ ብሎ ጠዋትና ማታ ከስሩ የማትጠፋው አሁን ላይ ለብቻዋ መሆንን ምርጫዋ አድርጋለች። ትዋብ ከምታኮርፈው ሰማይ ቢደፋበት ይሻለዋል። ሰኔ ከነዘርማንዘሩ ቢነሳበት ይሻለዋል።
እርቧት ይሆናል ሲል አሰበ..ቢርባት አጠገቡ መጥታ በጭራዋ እየታከከች አይን አይኑን ታየዋለች እንጂ እንዲህ ተኮራምታ አትቀመጥም ሲል አሰበ። በሰኔ ጭጋግ ላይ የትዋብ ኩርፊያ ተጨምሮበት ግራ ተጋባ። አምስት ዓመት ሙሉ በአንድ ቤት አንድ አልጋ ላይ አብረው ሲያድሩ እንዲህ ሆና አታወቅም ነበር። የዛሬ ኩርፊያዋ ከየት እንደመጣ አድራሻውን አልደርስ አለበት። ሰኔ ለሀጩን ከመልቀቁ በፊት ራት ሊበላ ቅድም ከምሳ የተረፈውን ምግብ ይዞ ወደ ትዋብ ተጠጋ። አንድ ጊዜ ጎርሶ እንጀራ ጣለላት.. ትዋብ አይታ ዝም አለች።
ሳህኑ ላይ ካለው ኩርማን ዳቦ ሸርፎ ወረወረላት። አይጥ እንዳየች ያህል ተወርውራ ቀለበችው..። አሁን ለምን እንዳኮረፈችው ገባው። ‹ይቺ ብጣሻም› አለ በሆዱ። የሰማችው ይመስል ተርበተበተ። ዛሬ ገና መሳደቡ ነው። አይደለም ሊሰድባት ቀርቶ ጎረቤት በክፉ አይን ሲያያት እንኳን አይወድም። ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በወንድ ልጁ በሞገስ ከተጣላው ይልቅ በእሷ ምክንያት ከሰው የተጣላው ይበልጣል።
ጫጩት ትበላለች፣ አይጥ አትይዝም ገለመሌ እያሉ በወጣች በገባች ቁጥር ከሚያሟት ሁሉ ጋር ተቀያይሟል። ዛሬ ለምን እንዳኮረፈችው ደረሰበት። ያለፉትን ሰባት ዓመታት ከጎረቤቱ ከእማማ ሽታዬ ቤት ዳቦ እየገዛ ነበር እንጀራና ዳቦ እየቀላቀለ ሲያበላት የነበረው። ከእሱ ሆድ ይልቅ ለትዋብ ሆድ ያወጣው ሚዛን ይደፋል። ከልጁ ከሞገስ ይልቅ ለእሷ የተጨነቀው ይበዛል። በዚህ ልክ ነው የሚወዳት። እሱ ቢያገኝ ብልቶ ቢያጣ ተደፍቶ ነው እሷ ግን አይደለም ጾሟን ልታድር ቀርቶ ሳንቲም አጥቶ እንጀራ የሰጣት ቀን እንዴት እንደሚያመናቅራት እሱ ነው የሚያውቀው።
ከዳቦው ደግሞ ጣለላት..መሬት ሳይደርስ አየር ላይ እያለ ቀለበችው። ደግሞ እንዲጥልላት አንዴ ወደ ሳህኑ አንዴ ደግሞ ወደ እሱ እያየች ትማጸነው ጀመር። ጭራዋን እየቆላች..አልፎ አልፎ ሚያው እያለች። ትዋብ እንደ ወዳጆቿ ብዙ መጮህ አትችልበትም..የፈለገችውን ነገር በአይኗ ነው የምትጠይቀው።
ሳይጥልላት ዝም ብሎ ያያት ጀመር። አይኖቿን ሳታዛንፍ አይኖቹ ላይ ሰክታለች..ከዳቦው እንዲጥልላት።ሳህኑ ላይ የቀረውን ሩብ ዳቦ እንዳለ ወረወረላት..መሬት ላይ እያንደባለለች ተስገበገበችበት። ዳቦውን ስትጨርስ የምትሆነውን መሆን ሲያስብ እሱ በተራው ተቀየማት። ዳቦውን ጨርሳ ቀና ስትል ባዶ ሳህን ነበር ያገኘችው። በአንድ ጊዜ ወደኩርፊያዋ ተመለሰች።
እንጀራ ወረወረላት..። አሽታ ዝም አለችው።
ትሰማው ይመስል ‹ስሚ አላት..
ትዋብ ቀና አለች..
‹እንዳንቺ ምግብ ማማረጥ ከብዶኝ አይደለም፣ የኑሮ ውድነቱ ነው ደረቅ እንጀራ እንድበላ ያደረገኝ ትኖሪ እንደሆነ አመልሽን አስተካክለሽ ኑሪ..ያለዛ› ሀሳቡን ሳይጨርስ ዝም አለ..
‹ያለዛ ምን? ያለችው መሰለው..በርቀት ብትሆንም አይኗ አይኑ ላይ ነው። ያን አሳዛኝ እይታ፣ ያን ነፍስ ድረስ ዘልቆ የሚሰማን አስተውሎት ትርጉሙን ቢያውቀው እንዴት በወደደ ነበር። አንዳንዴ ይፈራታል..ድመትነቷን አያምነውም። የሚያወራውን ሁሉ፣ የሚያደርገውን ሁሉ የምታውቅበት ይመስለዋል።
‹እዚህ ቤት ከገባን አምስት አመት ሆኖናል፣ እኔ እየከሳሁ አንቺ እያማረብሽ ነው ከእንግዲህ የምበላውን መብላት ነው የሚኖርብሽ..› ሲል ወደፊቱ ጎንበስ ብሎ ራሷን እያሻሸ ነገራት። ራሷን ሲያሻሻት ታፋው ላይ ዘላ ወጣች።
ምሽቱን ታኮ ሰኔ ተንሰቀሰቀ። ሰማይ ማንባት ጀመረ። እነዛ ክረምትን በዝናብ፣ በጋን በብርሃን የሞሸሩት የጣሪያው ላይ ቀዳዳዎች የሰኔን ጽንስ ሊቀበሉ ማህጸናቸውን ከፈቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2014