ጉዳይ ኖሮን ወደ አንድ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋም ስንሄድ በቅድሚያ የሚያሳስበን ወረፋ ጥበቃ እና እንግልቱ ነው። ጊዜያችንን የሚያቃጥለው ወረፋ እንዳይገጥመን፣ እንግልት እንዳይደርስብን ብለንም መረጃ የሚያደርሰን ወይም ጉዳዩን ለማስፈጸም የሚተባበረንን ሰው ፍለጋ እስከ መማሰን እንደርሳለን።
ይህ ተግዳሮት በመንግስት አገልግሎት ሰጪዎች ተቋማት ወይም የክፍያ ቦታዎች በስፋት ያጋጥማል። በግብር ክፍያ፣ በንብረት ማዘዋወር፣ በፈቃድ እድሳትና በመሳሰሉት ቀና አሰራሮች ባለመኖራቸው ሳቢያ ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ሲቸገሩ ኖረዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሀገሮች ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ተግብረዋል፡፡ ጊዜን ለመቆጠብ፣ ከአላስላጊ ወጪ ለመዳን እንግልትን ለማስቀረት የሚያስችሉ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲከወኑ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችና የክፍያ ስርዓቶች ስራ ላይ በመዋላቸውም ጉዳዩ በፍጥነት እና ያለምንም እንግልት የሚፈጸምበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡ ፡ በአሰራር ስርዓት ችግር ሳቢያ የሚፈጥረውን እንግልት የሚቀንሱ ተገቢ ያልሆነ ወጪን የሚቆጥቡ፣ ጊዜን የሚቆጥቡ ፕላትፎርሞች፣ መተግበሪያዎችና ሲስተሞች የዘመኑ አማራጮች በመሆን ተመራጭነታቸው እየሰፋ መጥቷል።
ይህን መሰል ዲጂታል አገልግሎት በአገራችን እምብዛም ሳይታወቅ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎች ቢኖሩም፣ አሁንም ቴክኖሎጂውን ለማበልፀግ የሚሰሩ ተቋማት ብዙም አይታዩም።
በርካታ ገንዘብ ሰብሳቢ ተቋማት አሁንም ስራዎቻቸው በእጅ አሠራር/ በማንዋል/ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ደንበኞቻቸው ክፍያ ለመፈጸም በአካል እንዲቀርቡ ያደርጋሉ። ይህ አይነቱ አሰራር በሁለቱም ወገን በኩል ብዙ ችግሮችን አስከትሏል። ምክንያቱም ተገልጋዮች የግድ አገልግሎት ሰጪዎች ቢሮ ወይም አገልግሎት መስጫ ማእከል መሄድ ይናርባቸዋል፤ በእዚያም ሄደው ለፍጆታ፣ ለግብር እና ለሌሎች አገልግሎቶች ሂሳባቸውን ለመክፈል ረጅም ወረፋ ይጠብቃሉ። አንዳንድ ጊዜ የኢንተርኔት ግንኙነት ባለመኖር፣ በመብራት መቆራረጥ ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ባሉ ሌሎች ችግሮች ሳቢያ አገልግሎቱን በብቃት ማግኘት አይችሉም።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ባለቤትነት “ደራሽ” የተሰኘ ፕላትፎርም (የክፍያ ደረሰኞችን ለባንኮች ተደራሽ የሚያደርግ መድረክ) ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓል። ይሁን እንጂ ይሄም ፕላትፎርም በሚፈለገው ደረጃ አይታወቅም። ለመሆኑ ፕላትፎርሙ ምን ይዘት አለው? በምን መንገድ ይሰራል? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን የኢንሳ የተቀናጀ ፕላትፎርም ዲቪዚዮን ዳይሬክተር ከሆነው አቶ ብሩክ ገብረየስ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል። መልካም ቆይታ!
አዲስ ዘመን፦ “ደራሽ” የተሰኘው ፕላትፎርም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በልፅጎ ተግባር ላይ ውሏል። ፕላትፎርሙ በምን መንገድ ይሰራል?
አቶ ብሩክ፦ “ደራሽ” ማለት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ባለቤት የሆነበት በአገር ውስጥ የለማ ፕላትፎርም ነው። ፕላትፎርሙ የክፍያ አማራጭ ሳይሆን ለክፍያ አገልግሎት የሚሆን ደረሰኝ በዲጂታል አማራጭ ማቅረብ “bill aggregations” ነው። ይህ ማለት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለክፍያ የሚጠቀሙበትንደረሰኝ በደራሽ አማካኝነት እንዲቀርብ ይደረጋል። ባንኮች ደግሞ የቀረበውን ደረሰኝ “Bill Presentment” ተጠቅመው ያለምንም መጉላላት ከዚያ ላይ በመውሰድ ክፍያ እንዲፈፅሙ ይቀርባል። ይህ ፕላትፎርም የሞባይል አፕሊኬሽን (መተግበሪያ)፣ ዌብሳይትና ሲስተምን “Application Programming Interface” አካትቶ የሚሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የደራሽ ፕላትፎርም ስራ ላይ ከዋለ ምን ያህል ጊዜ ሆነው? ደህንነቱስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
አቶ ብሩክ፦ የተቀናጀ የደራሽ ፕላትፎርም አገልግሎት ላይ መዋል ከጀመረ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። በኢንሳ ባለቤትነት ይሁን እንጂ በአገር ውስጥ ከሚገኝ ተቋም ጋር በትብብር የለማ ነው። የሚያስተዳድረውና በባለቤትነት የያዘውም ኢንሳ ነው። ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገ ነው። የፍቃድና አላስፈላጊ ወጪ እንዳይኖርበትም ተደርጓል።
በኦላይን አማራጭ ደራሽን የመሰሉ ፕላትፎርሞች ለአገልግሎት ሲቀርቡ ብዙ አይነት አደጋን ሊያስከትሉ የሚችሉ አካላት ያጋጥማሉ። ይህን መሰል አገልግሎት በበይነ መረብ እስካቀረብክ ድረስ ተጋላጭነትህም ሰፊ ነው የሚሆነው። በተለይ ከፋይናንስ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያለው ከሆነ ለጥቃት የመዳረግ ሁኔታው ከፍተኛ ነው።
ይህን መሰል ፕሮግራሞችን ለማጥቃት ፍላጎት ያላቸው አካላትም በስፋት በዓለማችን ላይ አሉ። ይህን ጥቃት ለመከላከል ፕላትፎርሙን ዲዛይን ከማድረግ ጀምሮ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ታስቦ ነው የሚሰራው። ስለዚህ ከስሪቱ ጀምሮ ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው ደራሽ የተሰራው። በተለይ የባንክ መረጃን (አካውንትን) እንዳይዝ ተደርጎ የተሰራ ነው።
በተለይ የግብር ክፍያን በተመለከተ ባንኮች ራሳቸው በደራሽ ፕላትፎርም መረጃ ሲያስተላልፉ ገንዘብ አይልኩም። ይህ አይነት አሰራር መኖሩ ለጥቃት በቀላሉ ተጋላጭ እንዳይሆን አድርጎታል። ከዚህ ውጪ ዓለም ላይ ያሉ የጥቃት መከላከያ ስርዓቶች በሙሉ ተተግብረውበታል። ይህ ደግሞ የበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን አስችሎታል።
ይህን መሰል ፕላትፎርም በአገር አቀፍ ደረጃ ባንኮች ላይ ያለውን መሰረተ ልማት የተገበሩ አገራት ጥቂት ናቸው። በየጊዜው የሳይበር ጥቃት ትራፊኩን በመከታተል ጥቃት እንዳይደርስ ይሰራል። ይህን መከታተል ካልተቻለ ሰርገው የሚገቡ ጥቃት አድራሾች ተጠቃሚዎች በአግባቡ እንዳይገለገሉ አገልግሎቱን የማቆራረጥ ስራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ይህ እንዳይሆን ጥቃቱን የሚከታተልና የሚከላከል ቡድን ለደራሽ በልዩ ሁኔታ ተዋቅሮ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የተቀናጀ የደራሽ ፕላትፎርም እስካሁን ድረስ ከሳይበር ደህንነት አንፃር ያጋጠመው ጉዳት ይኖር ይሆን?
አቶ ብሩክ፦ በየቀኑ በጣም ብዙ ሙከራዎች አሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ፕላትፎርሙ ላይ አደጋ ያደረሱ እስካሁን አልተመዘገቡም። ከአሰራር ጉድለትና ከግንዛቤ ጉድለት አንፃር አገልግሎቱ የተቀቆራረጠበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል። ይሄ ራሱ እንደ ደህንነት ስጋት ችግር ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጂ የውጪ ጥቃት ግን እስካሁን ድረስ አላጋጠመንም። በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙከራዎች ግን አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ደረሰኞችን ለባንኮች በማቅረብና የክፍያ ስርዓት በማቅለል የሚሰሩ ሌሎች ፕላትፎርሞች በአገር ውስጥ አሉ? እንደ ደራሽ ያሉ ዲጂታል ፕላትፎርሞች ከሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶች በምን ይለያሉ?
አቶ ብሩክ፦ በመጀመሪያ ፕላትፎርም ምንድነው የሚለውን ነገር መረዳት ያስፈልጋል። ፕላትፎርምና ሲስተም የተለያዩ ናቸው። ሲስተም በአንድ ጎን ብቻ አቅራቢ ኖሮት ተጠቃሚዎችን ብቻ የሚያካትት ሲሆን ነው። ድረ ገፅ፣ ፖርታሎች፣ መተግበሪያዎችና ሌሎች አማራጮችም ሊሆኑ ይችላሉ።
ፕላትፎርም ስንል ግን ብዛት ያላቸው ተሳታፊዎችን የሚያካትት ነው። ለምሳሌ ፌስቡክን ፕላትፎርም ያስባለው እዚያ ውስጥ የተለያዩ ወገኖች በጋራ ተሳትፎ ማድረጋቸው ነው። እነዚህን አካላት ማገናኘት ሲቻልና ደንበኞች በዚያ ውስጥ ሲገለገሉ ፕላትፎርም ይሆናል። የዩቱብ፣ አሊባባ፣ አማዞን ፕላትፎርም የሚያስብላቸው በውስጣቸው አንዱ አቅራቢ ሌላኛው ደግሞ ተጠቃሚ ስለሚሆንና ተሳታፊዎቹ ብዛት ያላቸው “multisided” አሊያም “two-sided” የሚያገናኙ ስለሆኑ ጭምር ነው።
ከዚህ አንፃር አገልግሎት ሰጪና ባንኮችን በነፃነት፣ በቀላሉ ገብተው ሊሳተፉበት የሚችሉበት አሊያም ደግሞ ለረጅም ጊዜ የሰራ አስተማማኝ የሆነ ፕላትፎርም አገር ውስጥ አለ ብዬ አላስብም። ወደዚህ ለመድረስና መሰል የዲጂታል አማራጮችን ለማቅረብ እየሞከሩ ያሉና የተለያዩ መነሻዎች ግን አሉ። ጅማሮዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፦ ፕላትፎርምና የኢኮኖሚ ስርዓቱ በምን መልኩ መስተጋብር አላቸው ብለህ ታምናለህ። ከዚህ አኳያ የደራሽ ሚና ምንድነው?
አቶ ብሩክ፦ በአሁኑ ወቅት የአገራት ኢኮኖሚ ወደ ፕላትፎርም ኩባንያዎች ዞሯል። ለምሳሌ የፌስቡኮችን ፕላትፎርምን ማየት ብንችል አመታዊ ትርፋቸው ከአንድ አገር ሃብትና በጀት ጋር የሚስተካከል እየሆነ ነው። የእነ ጎግል እና ሌሎች ፕላትፎርሞችም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው። አለምን እየመራው ያለው ይህ ኢኮኖሚ መርህ በመሆኑም መንግስታት በዚህ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ።
ኢንሳም ይህንን በመረዳት ደራሽ ፕላትፎርምን አበልጽጎ ለተጠቃሚዎች ማስተዋወቅ ላይ እየሰራ ይገኛል። አንደኛው ስራው በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያለውን የአሰራር ስርዓት በዲጂታል አማራጭ እንዲቀል የማድረግ ስራን መስራት ነው። በሁለተኛ ደረጃ በአብዛኛው የገንዘብና የመረጃ ዝውውር የሚደረገው ይህን በመሰለው ፕላትፎርም ስለሆነ ይህንን በባለቤትነት መቆጣጠር፣ ማስተዳደር እንዲሁም ደህንነታቸውን መጠበቅ ከተቻለ በቀጣይ ዜጎች ወደ እነዚህ አገግልግሎትና ቴክኖሎጂ ባለቤትነት እንዲሄዱ ፈር ቀዳጅ የመሆን ስራ መከወን ነው። ከዚህ አንፃር ኢንሳ ኢኮኖሚውንም ሆነ የደህንነቱን ጉዳይ በማቀናጀት ፈር ቀዳጅ ለመሆን እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ደራሽን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከማሻሻልና አዳዲስ የአገልግሎት አማራጮች እንዲኖሩት ከማዘመን አንፃርስ ምን ሰርታችኋል?
አቶ ብሩክ፦ አሁን የመጀመሪያው የተደራሽነት ስራ ላይ እየሰራን ነው። ያለውን ፕላትፎርም በአግባቡ እንዲጠቀሙበት የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው። ወደ ማሻሻል የመግባቱን ስራ ተጠቃሚዎች ያላቸው የመሰረተ ልማት አቅም ይወስነዋል። በተጠቃሚዎች ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት ነው የማሻሻል ስራ የሚካሄደው። አሁን እያደረግን ያለነው ባንኮች በቅርንጫፍም በኢንተርኔትም አገልግሎት ሰጪዎች አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ነው። ከዚያ ውጪ ግን የሞባይል መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ተዘጋጅቶ በሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛል። በቅርቡም የውሃ፣ የመብራትና ሌሎች የክፍያ ደረሰኞችን ወዳጅ ዘመዶች ለቤተሰቦቻቸው ከውጪ ሆነው ካሉበት ስፍራ መክፈል እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ተጀምረዋል።
አዲስ ዘመን፦ በደራሽ ፕላትፎርም ተጠቃሚ የሆኑ ምን ያህል ደንበኞች አሏችሁ? በዚህ ዲጂታል ስርዓት ለመጠቀም ያላቸው ተነሳሽነትስ ምን ይመስላል?
አቶ ብሩክ፦ አሁን ባለው ሁኔታ 16 ባንኮች ተሳስረዋል። ተጨማሪ አራት ባንኮችም በዚህ ወር ወደ አገልግሎት እየገቡ ነው።
በአገልግሎቱ እንዲጠቀሙ የማድረጉ ስራ ትልቅ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። በመሆኑም የማለማመድ፣ ማሳመንና አገልግሎታቸውን በዚህ አግባብ እንዲሰጡ ማስቻል ራሱን የቻለ ስራ የሚፈልግ ነው። ያንን በመስራት ላይ እንገኛለን። ከአንዱ ወደ ሌላኛው ባንክ የሚደረግ የደረሰኝ ክፍያን የብሄራዊ ባንክ ህግና አሰራር ቢፈቅድም ባንኮች ገንዘብ ከራሳቸው እንዳይወጣ ስለሚፈልጉ ፍቃደኛ አለመሆን ይታይባቸዋል። አሁን ግን በተለይ የግብር ክፍያ ከየትኛውም ባንክ ወደ ንግድ ባንክ መክፈል እንዲቻል ተደርጓል። ሌሎችም የትራፊክ፣ የውሃና መሰል የክፍያ ስርዓቶች በዚህ ፕላትፎርም እንዲከፈሉ ማድረግና ማሻሻል ተችሏል።
አዲስ ዘመን፦ በተቀናጀ የደራሽ ፕላትፎርም እስካሁን ድረስ ምን ያህል የደረሰኝ አቅርቦትና የገንዘብ ክፍያ ተደርጓል?
አቶ ብሩክ፦ በመጀመሪያው ዓመት ላይ በግብር ከፋዩ ነበር የጀመርነው። 10 ከፍተኛ የመንግስት ግብር ከፋዮችን ሃላፊነት ተወስዶ ከንግድ ባንክ እንዲከፍሉ ለማድረግ ተሞክሮ ነበር። ይህን ያደረግነውም በስንት ጥረት አመኔታ ለማሳደር ተብሎ ነው። ወደ ስርዓቱ ለማስገባት አንድ አመት ያህል ፈጅቷል። ሆኖም በቀጣይ በተሰራው ስራ ወደ 5 እና 6 ሺህ ለማስገባት ተችሏል። በዚያ ወቅት ከ5 እስከ 10 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈፅሟል።
ከዚያ በኋላ ባለው ከሰኔ ጀምሮ ተጨማሪ 6 ባንኮች ተካተውና አገልግሎት ሰጪዎችም ወደ 50 ተጠግተው በሲቢኢ ብርና በሌሎች አማራጮች ወደ 70 ቢሊዮን ብር የደረሰኝ ክፍያዎች ተከፍለዋል። ይህ ማለት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከነበረው ሁለት እጥፍ በአንድ ዓመት ውስጥ መጥቷል። አጠቃላይ ሲስተሙ ላይ ክፍያ የፈፀሙና የሚጠቀሙ ወደ 450 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች አሉ። ከዚህ ውጪ 65 የሚደርሱ አገልግሎት ሰጪዎች በደራሽ የተቀናጀ ፕላትፎርም ለደንበኞቻቸው በዲጂታል አማራጮች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። ይህን በወር ሲሲሰላ እስከ 70 ሺ ተጠቃሚዎች ይደርሳሉ።
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
አቶ ብሩክ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014