ቀኑ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር:: ዕለቱ ደግሞ ሰኞ፤ የሳምንቱ የመጀመሪያ የሥራ ቀን:: ሥራ የዋለ ሁሉ ወደ ቤቱ ገብቷል፤ እንደየሥራው ባህሪ በሥራ ላይም ያለ ይኖራል::
ሰዓቱ ምሽት 3፡00 አካባቢ ነው:: የደከመው ተኝቷል፤ አብዛኛው ሰው ግን ገና ያልተኛ ይመስላል:: በድንገት የማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ አንድ አስደንጋጭ ዜና መዘዋወር ጀመረ:: ይኸውም ‹‹ሃጫሉ ተገደለ›› የሚል ነበር::
በማህበራዊ ድረ ገጾች ሀሰተኛ ዜና ማሰራጨት የተለመደ ነውና ብዙዎች ለማመን ተቸገሩ:: አንዳንዶችም ‹‹ኧረ እባካችሁ እንዲህ አይነት ቀልድ አደጋ አለው!›› እያሉ ይመክሩ ነበር:: ዳሩ ግን የመረጃዎች ፍጥነት በአንድ ጊዜ ማህበራዊ ድረ ገጾችን አጥለቀለቀው::
አሁን ነገሩ እውነት ይሆናል ተብሎ መጠርጠር ተጀመረ:: ወዲያውኑ ፈቃድ ያላቸውና መደበኞቹ መገናኛ ብዙኃን እውነት መሆኑን አረጋገጡ:: አሁን ድንጋጤ ተጀመረ! ምክንያቱም ግድያው ፍጹም አስደንጋጭ ነበር::
ከዚያን ሰዓት ጀምሮ ማህበራዊ ድረ ገጾች፣ በመንግስት እና በፖለቲከኞች የሚተዳደሩት ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ማሰራጨት ጀመሩ:: አሉባልታ እና የብሽሽቅ ስድድቦች በስፋት ተሰራጩ:: ከአርቲስቱ ግድያ በላይ ፖለቲካዊ ጭቅጭቆች አየሩን ሞሉት:: ግድያው በማን እንደተፈጸመ ግልጽ አልነበረምና የአርቲስቱ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ወገኖች ገዳዮች እነ እገሌ ናቸው የሚል የግምት መረጃዎችን ማሰራጨት ጀመሩ::
እንዲህ እንዲህ እያለ ያ አስደንጋጭ ምሽት ነጋ:: ሰዎች ወደ ሥራ ለመሄድ እያመነቱ ነው:: ምክንያቱም በማህበራዊ ድረ ገጾችና በዋናዎቹ በጽንፈኞች በሚተዳደሩት መገናኛ ብዙኃን በሚሰራጩ መረጃዎች፣ እንዲሁም ከግድያው ድንገተኛነት አንፃር የፀጥታ ሥጋቶች ነበሩ::
የተፈራው አልቀረም፤ በንጋታው ጠዋት በከተማዋ ዳር ዳር የተቃውሞ ሰልፎች መታየት ጀመሩ:: እየረፈደ ሲመጣ ወደ መሃል ከተማም መታየት ጀመሩ:: በዕለቱ ከተማዋ ጸጥ ረጭ ብላ ዋለች:: በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ደግሞ በዚሁ ግርግር ምክንያት ንጹሃን ተገደሉ፤ ንብረቶችም ወደሙ::
ከሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ እና ከግድያው በኋላ በተፈጠሩ ግርግሮች የተጠረጠሩ ፖለቲከኞ ታሰሩ:: በአጠቃላይ ያ ክስተት ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ቆየ:: ክስተቱም እነሆ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይታወሳል:: ወጣቱ ድምጻዊም በአጭር ተቀጠፈ:: አድናቂዎቹና ወዳጆቹም ዓመቱን ሙሉ አዘኑ:: እነሆ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን 2ኛ የሙት ዓመት ምክንያት አድርገን በዚህ ሳምንት እናስታውሰዋለን::
ሃጫሉ ከእናቱ ወይዘሮ ጉደቱ ሆራ እና ከአባቱ ከአቶ ሁንዴሳ ቦንሳ በ1978 ዓ.ም በአምቦ ተወለደ:: ከልጅነቱ ታሪክን መስማትና የመንገር ዝንባሌውንና ችሎታውን ጠንቅቀው ተረድተውት ስለነበር ወላጆቹ ያበረታቱት እንደነበር በተደጋጋሚ ቃለ ምልልስ ባደረገባቸው መድረኮች አስታውሷል::
የሃጫሉ የነፍስ ጥሪ ግን ወደ ሙዚቃው ሆነ:: ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለ ሙዚቃዎችን መጫወት ጀመረ:: በሙዚቃዎቹም የኦሮሞን ህዝብ ትግል የሚገልጹ መልዕክቶችን ያስተላልፋል:: በዚህም ምክንያት ገና በ17 ዓመቱ ነበር የታሰረው::
መታሰሩ ከትግሉ ሊገታው ግን አልቻለም፤ እንዲያውም ይበልጥ በሥራው እንዲገፋበትና በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና ጭቆና የበለጠ እንዲታገል እንዳደረገው በተለያዩ ጊዜያት ተናግሯል::
ሃጫሉ በአፋን ኦሮሞ ተናጋሪው ሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነለትን ‹‹ሰኚ ሞቲ›› የተሰኘውን አልበሙን አቀረበ። የዚህ የሙዚቃ ስብስብ አብዛኛዎቹ ግጥሞችና ዜማዎች ሃጫሉ በእስር ላይ እያለ የሰራቸው ነበሩ::
ሃጫሉ ተወዳጅ የሆኑ የአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ስልቶችን ከዘመናዊው ሙዚቃ ጋር በማጣመር በሚያቀርባቸው ሥራዎቹ የብዙዎችን ቀልብ ለመማረክ አስችሎታል። በአገሪቱ የሚገኙ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ሙዚቃዎቹን በተደጋጋሚ በማጫወታቸው በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ አድናቆትን ማግኘት ችሏል።
በእነዚህ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሚታወቀው ሃጫሉ፤ ከአራት ዓመት በፊት የነበረውን ሥርዓት ለመቃወም በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የበለጠ ቀልብ ሳቢ ሆኖ መጣ:: በለውጡ ዋዜማ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በኦሮሚያ ሚዲያ ኔቶርክ (OBN) ለመላው ዓለም በሚተላለፍ የቀጥታ ሥርጭት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ፣ ዳሩ ግን የወቅቱን መንግሥት ቀልብ የገፈፈ ሥራውን አቀረበ::
ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በሥራዎቹም ሆነ በመገናኛ ብዙኋን በሚያደርጋቸው ቃለ መጠይቆች፤ ሃጫሉ ከዘፈን ባሻገር ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ነፃነት በመታገሉ ለኦሮሞ ሕዝብ ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ታጋይ ይታያል::
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ሲሆን፤ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ለብዙዎች ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ተገሏል:: እነሆ ሥራዎቹና ታሪኩ ግን ሲታወስ ይኖራል::
የደርግ ምሥረታ ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት፣ በተለይም ለግማሽ ክፍለ ዘመን የኖረውንና በኢትዮጵያ የመጨረሻ የሆነውን የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንጉሣዊ ሥርዓት ያስወገደው ወታደራዊ ደርግ የተመሰረተው በዚህ ሳምንት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ነው::
የታሪክ ባለሙያዎች ደርግ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ያስወገደበትን መንገድ ‹‹አዝጋሚው መፈንቅለ መንግሥት›› ይሉታል:: ምክንያቱም አንድ ጊዜ አይደለም ያስወገዳቸው:: የደርግ ምሥረታ ራሱ አንድ ጊዜ አይደለም:: ሰኔ 21 ቀን በይፋ የተመሰረተበት ይሁን እንጂ ወታደሮቹ ሀሳቡን ከጠነሰሱትና የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴውን ከጀመሩ ቆይተዋል::
ከታሪክ ባለሙያው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983››፣ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› መጽሐፎች እና ከተለያዩ ድረ ገጾች ባገኘናቸው መረጃዎች ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የተመሰረተውን የደርግ መንግሥት ታሪክ እንዲህ እናስታውሳለን::
ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለስርዓቱ መገለጫነት የተጠቀመው ግለሰብ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ ሲሆን ቀኑም፤ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር መምሪያ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መለዮ ለባሾች በየካቲት ወር ስለፈነዳው አብዮት ከሰኔ 19 ጀምሮ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ:: ደርግ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች) ከተመሰረተ በኋላ በዚያው ቀን ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም የደርግ ሊቀመንበር በመሆን ተመረጡ::
በ1953 ዓ.ም የተሞከረበትን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ፤ የንጉሱ ሥርዓት የተለያዩ ጥገናዎችን ሲያደርግ ቢቆይም በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ፈነዳ:: አብዮቱን የጀመረው የወታደሩ መደብ ሲሆን፤ ነገሌ እና ሲዳሞ ላይ ሰፍሮ የነበረው የምድር ጦር ሠራዊት አዛዥ መኮንኖቻቸውን ሲያግቱ ይጀምራል። ጉዳዩ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚኖሩ የሰራዊቱ ክፍሎች ድጋፍን በማግኘቱ በወታደሩ መደብ ከመዛመቱም ባሻገር ወደ ተቀረው ዜጋም በመሰራጨት አብዮቱ ተቀጣጠለ::
አሁንም የንጉሱ መንግሥት ብዙ ጥገናዎችን እያደረገ ነው:: የዘውዱ መንግስት አብዮቱን ለማርገብ የተለያዩ ለውጦችን አድርጓል:: ለምሳሌ አክሊሉ ሃብተወልድን አንስቶ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጓል:: ለወታደሩ ልዩ ደመወዝ ጭማሪ አድርጓል፤ ሊተገበር የነበረ የትምህርት ስርዓት ማሻሻያ ለውጥ በተነሳበት ተቃውሞ ምክንያት አስቁሟል:: ሕገ መንግስት ለማሻሻል ሞክሯል። ይሄ ሁሉ ግን የወታደሩን አዝጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ማስቀረት አልቻለም::
ሰኔ 21 ቀን በአራተኛ ክፍለ ጦር የተመሰረተው ደርግ የቀድሞ ባለሥልጣናትን ማሰር ጀመረ:: ከሐምሌ 2 ቀን 1966 ዓ.ም ጀምሮ እስረኞቹ ጋዜጣና ራዲዮ እንዳያስገቡ ተከለከሉ:: ጠያቂዎች እስረኞችን የሚጎበኙት በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ጧት ብቻ ነበር:: ከሐምሌ 9 ቀን 1966 ዓ.ም በኋላ እሥረኞች ከነበሩበት የጎፋ ሠፈር ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ተዛወሩ::
እንዲህ እንዲህ እያለ የቆየው ደርግ፤ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሱን ገርስሶ መንግሥት መሆኑን በይፋ አወጀ:: አሁን ደርግ የአገሪቱ መንግሥት ሆኗል:: ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረዳቸውን፣ ህገ መንግሥቱ መሻሩን፣ ፓርላማው መዘጋቱን አወጀ::
አላግባብ የበለጸጉ፣ ፍርድ ያጎደሉ፣ በአስተዳደር የበደሉ የተባሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት ሁሉ በጦር ፍርድ ቤት የሚዳኙ መሆኑን ደርግ አዋጅ አስነገረ:: በዚሁ ዕለት የንጉሡ የልጅ ልጅ እና የባህር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ተይዘው ከእሥረኞቹ ጋር ተቀላቀሉ:: እንዲህ እንዲህ እያለ ደርግ የታሳሪዎችን ቁጥር እያበዛው መጣ:: በመጨረሻም፤ በታሪክ በጥቁር ቀለም የተጻፈውንና ደርግ እንደተወቀሰበት የሚኖረውን 60 የጦር መኮንኖችንና ባለሥልጣናትን የረሸነበት ድርጊት ተፈጸመ::
ደርግ በአራተኛ ክፍለ ጦር ተመስርቶ፣ መስከረም 2 መንግሥት መሆኑን አውጆ፤ አገር ባስተዳደረበት ዘመን በጨካኝነት የተገለጸውን ያህል፤ የአገር ዳር ድንበር በማስከበርና የውጭ ወራሪን አፈር ድሜ በማስበላት ይታወቃል:: ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ታሪካዊ አዋጆችን አውጇል:: በየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም «የገጠር መሬት አዋጅ» እና ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም «የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ» በመባል የሚታወቁት ሁለት አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው።
1966 ዓ.ም ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በመሬት ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል:: የደርግ ሥርዓት ይከተል በነበረው የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት አሸጋግሯል:: የገጠር መሬትን የሕዝብ ሀብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 የሕዝብ ሀብት በሚል ታወጀ:: አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር::
የገጠር መሬትን የሕዝብ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 31/67 አንቀጽ 5 አንድ የመሬት ተጠቃሚ በይዞታ የያዘውን መብት መሸጥ፣ መለወጥ፣ በስጦታ ማስተላለፍ፣ ማስያዝ፣ በወለድ አግድ ወይም በሌላ ሁኔታ ማስተላለፍ እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል:: እነሆ ደርግ፤ ንጉሳዊ ሥርዓቱን ከመገርሰሱ ባሻገር በእነዚህና በሌሎች አዋጆች ይታወሳል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2014